ለመንግሥት የሰላም ጥሪ ምላሽ በመስጠት የሰላም አሸናፊ እንሁን!

መንግሥት በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪን ቢያቀርብም በሀገር ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች መሳሪያ አንስተው ወደ ጫካ የገቡ አካላት በሚፈለገው ልክ ለሰላም ጥሪው ተገቢውን ምላሽ እየሰጡ ባይሆንም፤ ሰሞኑን በትጥቅ ትግል ውስጥ ይገኝ የነበረው በጃል ሰኚ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ለቀረበለት የሰላም ጥሪ ምላሽ በመስጠት መሳሪያ እየፈታ ወደ ተሀድሶ ማሰልጠኛ ጣቢያዎች እየገባ ይገኛል። ክስተቱ የመላውን ሕዝብ ይሁንታም አግኝቷል።

በርግጥ ሰላማዊ ትግል ምንጊዜም በሕዝብ የሚደገፍ የትግል ስትራቴጂ ነው። ጦርነት ሕዝብን ለመከራ እና ለተመሰቃቀል ሕይወት ከመዳረግ፣ የዜጎችን ሕይወት በተለይም አምራቹን ኃይል ከመቅጠፍ፣ ቁሳዊ ውድመት ከመፍጠር ፣ የሀገርን ኢኮኖሚ ከመጉዳት እና የፖለቲካ አለመረጋጋትን ከማስከተል፣ ሀገርን በውጪ ጠላት አደጋ ውስጥ እንድትወድቅ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር ያለፈ ፋይዳ የለውም።

ጦርነት ሕዝብን ለመከራ እና ለተመሰቃቀል ሕይወት መዳረጉ ሲነሳ፤ በዋነኛነት በቅርቡ በሀገራችን የሰሜኑ ክፍል ተቀስቅሶ ብዙ ዋጋ ያስከፈለንን ጦርነት ማየት ተገቢ ነው። ልዩነቶችን በሰከነ መንፈስ በንግግር መፍታት ስንችል ወንድም በወንድሙ ላይ ጠመንጃ አንስቶ እና ቃታ ስቦ እንደ ሀገር ያልተገባ ዋጋ ለመክፈል የተገደድንበት ሁንታ ተከስቷል።

በጦርነቱ ወላድ እናቶች ሆስፒታል መሔድ ሳይችሉ ቀርተዋል፤ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆች እና ወጣቶች ከትምህርታቸው ተስተጓጉለዋል፤ ነጋዴም ሆነ መላው አገልግሎት ሰጪ ከሥራ ውጪ ሆኖ በድባቴ ውስጥ ረጅም ጊዜያትን ለማሳለፍ ተገድዷል። ይህ ብቻ አይደለም፤ ብዙ ልጆች ያለወላጅ ፣ ብዙ ወላጆች ያለጧሪ ቀርተዋል።

ከዚህ ጦርነት ብዙ መማር የሚጠበቅብን ቢሆንም፤ እንዳለመታደል ሆኖ የሕዝብ ጥቅም የሚረጋገጠው በጦርነት ሳይሆን ሰላማዊ በሆነ መንገድ መሆኑን የዘነጉ ወገኖቻችን አሁንም ጫካ አሉ። አሁንም ዜጎች ከጦርነት ጋር ለተያያዙ ችግሮች ተጋላጭ እንደሆኑ ናቸው።

በሰሜኑ አካባቢ የነበረው ጦርነት በመጨረሻም በሰላም ስምምነት ማጠናቀቅ ቢችልም፤ አሁንም በዛው በሰሜኑ የሀገራችን አካባቢ/በአማራ ክልል ፍላጎትን በኃይል ለመጫን የሚደረግ በጠመንጃ የተደገፈ ያልተገባ ጥረት ሀገር እና ሕዝብን ብዙ ዋጋ እያስከፈለ ነው። በዚህም ከሁለም በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች አስቸጋሪ ለሆነ የኑሮ ውጣውረድ ተዳርገዋል።

ችግሩ ሀገር ሊቀይር የሚችልን የወጣት ኃይል ከማሳጣት ባለፈ፤ ከፍያለ የሀገር ሀብት እና ንብረት እንዲወድም እያደረገ ነው። በመነጋገር ሊፈታ የሚችል ሃሳብና ጥያቄን አግባብ ባለው/ ዘመኑን በሚዋጅ ንግግር መፍታት እየተቻለ እንደ ሀገር ዛሬም ያልተገባ ዋጋ እንድንከፍል እያስገደደን ነው።

ጦርነቱን በአካል ሲያዩ የነበሩ፣ የከባድ መሳሪያ የተኩስ ድምፅ ሲረብሻቸው የቆዩ ልጆች፣ ወላጆቻቸው እንደቀልድ ወጥተው በጦርነቱ ቀልጠው የቀሩባቸው ሕፃናት ብቻ ሳይሆኑ መሃል ከተማ ላይ ቁጭ ብሎ ዜናውን ሲመለከት እና ሲሰማ የነበረ ኢትዮጵያዊም በጦርነቱ ሕሊናው ቆስሏል።

ጦርነት ማንንም በምንም መልኩ አልጠቀመም። ከጠቀመ ምናልባት የኢትዮጵያ ጠላት የሆኑ ኃይሎችን ብቻ ነው። በተለያዩ አካባቢዎች መሳሪያ ይዘው ጫካ የገቡ ወገኖቻችን አሁንም ልብ ሊሉት የሚገባው ነገር፤ በጦርነት ማንም አሸናፊ እና ተጠቃሚ መሆን እንደማይችል ነው።

በሰሜኑ ጦርነት በትሪሊዮን ብር የሚቆጠር የሀገር ሀብት ወድሟል። ከመንግሥት ተቋማት በተጨማሪ የንግድ ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች እና የግል ተቋማት ወድመዋል። ለጦርነቱ የሚውል መሳሪያን ለመግዛት የወጣው ወጪም በሀገር ላይ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት ሳይታለም የተፈታ ነው።

ምንም እንኳ በዛ ጦርነት ከፍተኛ ቁሳዊ ውድመት ቢደርስብንም አሁንም ከዛ ጦርነት መማር አልቻልንም። ዛሬም ስለጦርነት የሚያዜሙ ኃይሎች አሉ፤ ጠመንጃ አንስተው በገዛ ወገናቸው ላይ ቃታ እየሳቡ ከፍ ያለ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት እያደረሱ ነጻ አውጪ ነን የሚሉ አሉ።

እነዚህ ኃይሎች በጃልሰኚ ነጋሳ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ለመንግሥት የሰላም ጥሪ ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ወደ ሰላም የመጣበትን መንገድ በመከተል፤ በቅንነት በሀገር ጥላ ስር ተነጋግሮ ችግሮችን ለመፍታት እራሳቸውን ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል።

በጃልሰኚ ነጋሳ የሚመራው ኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ወደ ሰላም መምጣቱ ከሁሉም በላይ ተጠቃሚ ያደረገው፤ በጦርነት በእጅጉ የተጎዳውን የኦሮሞ ሕዝብ ነው። ክስተቱ ከዚህም ባለፈ እንደ ሀገር ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ትልቅ አቅም ፤ተጨባጭ ተሞክሮ ነው።

በተቃራኒው መሳሪያ ይዞ ጫካ በመግባትም ሆነ ጦር በመማዘዝ በምንም መልኩ ማንም ለዘለቄታው የሚያሸንፍበት ዕድል አይሰጠውም። የዛሬ አሸናፊ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር አሸናፊነቱን አጽንቶ ማስቀጠል፤ የዓለም ተሞክሮም የሚያሳየው ይሄንኑ ነው።

ድርድር እና ሰላማዊ ንግግር ሁሉንም አሸናፊ ያደርጋል፤ ኪሣራ የለውም። ሰላም ከውድመት ይልቅ ዕድገት፤ ከመበታተን ይልቅ አንድነትን ያመጣል። አንድነት እና ዕድገት ሕዝብን ከጉስቁልና በማውጣት ወደ ተመቻቸ ኑሮ ይመራል። ሀገር በጠላቶቿ መጫወቻ ከመሆን እና ለትንኮሳ ከመጋለጥ ይልቅ ተከብራ እና ተፈርታ ትኖራለች።

እርግጥ ነው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት ወደ ተሀድሶ ማዕከላት እየገቡ የመሆናቸው ዜና የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሕዝቡም አጥብቆ የሚሻው ነው። ይህን አዲስ የፖለቲካ ባህል በሀገሪቱ ጠመንጃ አንስታችሁ ጫካ ለገባችሁ ኃይሎች ትክክለኛ አዋጭ ተሞክሮ ነው። ከሰላም እንጂ ከጦርነት ማንም ስለማያተርፍ ለመንግሥት የሰላም ጥሪ ምላሽ በመስጠት የሰላም አሸናፊዎች ሁኑ፤ ለሰላም እጃችሁን ዘርጉ።

ፌኔት ኤሊያስ/

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You