“ግብርናችን ከእጅ ወደአፍ መባሉ ቀርቶ ወደኮሜርሻል እየተሻገረ ነው” – ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የግብርና ሚኒስትር“ግብርናችን ከእጅ ወደአፍ መባሉ ቀርቶ ወደኮሜርሻል እየተሻገረ ነው” – ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የግብርና ሚኒስትር

ኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት እያስመዘገበች ከምትገኝበት ዘርፍ አንዱ ግብርና ነው። በዘርፉ ወሳኝ የሆኑ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በመተግበሯና የአሠራር ለውጥ በማድረጓ በዓይን የሚታይ ለውጥ መመዝገብ ተችሏል። በተለይም የተካሔደው የስንዴ አብዮትን ጨምሮ ሜካናይዜሽኑ፣ የልማት ትሩፋቱና አረንጓዴ ዐሻራው በዋነኝነት ዘርፉን ወደፊት ያራመዱ ትልልቅ ተግባራት ናቸው።

አዲስ ዘመንም፣ በግብርና ዘርፍ የተሠሩ ሥራዎችን፣ በተለይም መንግሥት ለዘርፉ ስኬታማነት የወሰዳቸው ርምጃዎችና የተገኘውን ውጤት እንዲሁም ወደፊት ስለታቀደው ሥራ አስመልክቶ ከኢፌዴሪ ግብርና ሚንስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አጠናቅሮ አቅርቧል።

አዲስ ዘመን፡- ግብርናው ከለውጡ በኋላ ያሳየው እምርታ እንዴት ይገለጻል?

ግርማ (ዶ/ር)፡- የግብርና ሴክተር ባለፉት ሥርዓቶች ትኩረት ሳይሰጠው የቀረበት ጊዜ ብዙም የለም። ግብርና መር ኢኮኖሚ፣ ግብርና መር ኢንዱስትሪያላይዜሽን በሚል የትኩረት አቅጣጫ መሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል። ዋናው ነገር ግን የተቀረጸለትስ ፖሊሲ ምን ይመስላል? ምን ኢኒሼቲቮች ነበሩት ? በተጨባጭ ምን ተሠራ? የሚለው ነው።

ከዚህ አንጻር ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተገኘው ለውጥ ምንድን ነው? የሚለው ሲታይ ከዚህ ቀደም በግብርናችን አሠራር ምርት ይመረት የነበረው በተበጣጠሰ ማሳ ላይ ነበር፤ ከ90 በመቶ በላይ ግብርናችን በተበጣጠሰ ማሳ የሚሠራ ስለነበር። ይህም በመሆኑ የትም መድረስ አልተቻለም። ግብርናው የሚዘምነው በጣም ሰፋፊ በሆነ ማሳ በባለሀብቱ ሲሠራ ነው ብለው የሚያምኑ ሰዎች አሉ።

ይህን አሠራር ማዘመን የሚቻለው እንዴት ነው? የሚለው ሲጤን በተበጣጠሰ ማሳ የሚያመርተውን አርሶ አደር ሕይወት ማየት ተገቢ ነው ፤ ተጨባጭ እውነታው የሚያሳየን ባለፉት ዓመታት የአርሶ አደሩ ሕይወት ከእጅ ወደአፍ መሆኑን ነው። አርሶ አደሩ የሚያመርተው በልቶ ለማደር እንጂ ለኢንዱስትሪ ግብዓት አሊያም ለወጪ ገበያ ዓላማ አድርጎ ሲሠራ አይስተዋልም። ምናልባት ከቤተሰቡ የምግብ ፍጆታ እልፍ የሚል ምርት ካለው አቅራቢያው ወደሚገኘው ገበያ ወስዶ ሊሸጥ ይችላል። በቃ የተለመደው ይኸው ነበር።

ከዚህ የተለመደ ዓይነት አሠራር ወጥቶና ገበያን፣ ኢንዱስትሪንና ተኪ ምርትን ትኩረት አድርጎ እንዲሠራ ማድረግ ምርታማነት እንዲጨምር እንደ ማድረግ የሚወሰድ ነው። የእኛ ሀገር ግብርና መለወጥ የሚችለው ደግሞ በተበጣጠሰ መሬት ላይ የሚያመርተው አርሶ አደር የአመራረት ስልቱን መለወጥ ሲችል ነው። ስለዚህ አሠራሩ መለወጥ አለበት።

መለወጥ አለበት ሲባል መለወጥ ያለበት ነገር በበሬ ትከሻ እየተጎተተ የሚሠራው ግብርና የቱንም ያህል እናዘምነዋለን ብንል ሊዘመን አይችልም። በዓለም ላይ ያለው ተሞክሮ የሚያሳየው ግብርና የዘመነው ሜካናይዝድ በመደረጉ ነው። ስለዚህ በፖሊሲ ተደግፎና ትኩረት ተሰጥቶት መፈታት ያለበት አንዱ ነገር ግብርናን ሜካናይዝድ ማድረግ ነው።

ይህን እውን ለማድረግ ባለፉት አምስት ዓመታት የተወሰደው የፖሊሲ ርምጃ ነው። ማናቸውም የሜካናይዜሽንና የመስኖ እቃዎች ከቀረጥ ነፃ ወደ ሀገር እንዲገቡ ተደርጓል። ውሳኔው በእኔ እይታ ግብርናን ለማዘመንና ወደፊት ለማሻገር ከተወሰዱ ርምጃዎች አንዱና ትልቁ ነው ተብሎ የሚወሰድ ነው። ምክንያቱም ከ500 በላይ የሜካናይዜሽን እቃዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ መንግሥት ፈቅዷልናል።

አዲስ ዘመን፡- ይህ የመንግሥት ውሳኔ ለግብርናው ሴክተር ያመጣው ነገር ምንድን ነው?

ግርማ (ዶ/ር)፡- ይህ ምን አምጥቷል ከተባለ አንድ አመላካች ነገር ብቻ ማንሳት ይቻላል። ለምሳሌ በመኸር የምናርሰው ወደ 20 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ነው። ይህ የመኸሩ፣ የመስኖው እንዲሁም የበልጉንም አንድ ላይ ስንደምር አንድ ላይ ወደ 30 ሚሊዮን ሔክታር መሬት እንደሚሆን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንም ከዚህ በፊት ለፓርላማ ሲገልጹ እንደነበር ይታወሳል።

መኸሩን ብቻ ነጥለን ብናወጣው የባለፈውን መኸር 20 ነጥብ አራት ሚሊዮን ሔክታር መሬት አካባቢ ማድረስ ችለናል። ከዚህ ውስጥ ወደ አምስት ሚሊዮን ሔክታር መሬት በሜካናይዜሽን የታረሰ ነው። ይህ ማለት በሜካናይዜሽን የታረሰው መሬት ወደ 25 በመቶ አካባቢ ደርሷል ማለት ነው። ይህ ትልቅ እድገት የመጣው ማሽነሪዎች ወደሀገር ውስጥ ከቀረጥ ነፃ ሆነው እንዲገቡ በመደረጉና አርሶ አደሩ፣ ወጣቱ፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ ማሽነሪ እንዲያገኙ በመመቻቸቱና መግዛት የማይችለውም ጭምር ማሸነሪ መከራየት የሚያስችለው ሥርዓት በመበጀቱ ነው። በዚህም ለግብርናው መዘመን መሠረት መጣል ተችሏል።

ይህ የበለጠ እንዲሳካ ማድረግ የተቻለው፣ አርሶ አደሮች የሚያመርቱት አነስተኛ ማሳዎችን በመጠቀም ነው። አርሶ አደሮቹ የሚያመርቱት በአንድ አግሮኢኮሎጂ ውስጥ ነው፣ የሚጠቀሙትም አፈር አንድ ዓይነት ነው። የአየር ንብረቱም ተመሳሳይ ነው፤ ይሁንና አርሶ አደሮቹን የሚለያቸው የማሳቸው ድንበር ብቻ ነው።

ይህ የኩታ ገጠም እርሻን ተግባራዊ ለማድረግ የተሻለ አጋጣሚ የፈጠረ ነው። ለምሳሌ ለበቆሎ ምርት ምቹ የአየር ንብረትም ሆነ መሬት ላይ ያለ አርሶ አደር፤ አንደኛው ጤፍ፣ ሌላኛው ስንዴ ከሚዘራ ሁሉም በአንድ ሆነው በተመሳሳይ የዘር ዓይነትና በተመሳሳይ ግብዓት እንዲሁም በተመሳሳይ ጊዜ በቆሎውን ቢዘሩ ምርታማነታቸው ከፍተኛ ይሆናል።

የስንዴ፣ የበቆሎ፣ የቦሎቄ ኩታ ገጠም ስንል አርሶ አደሩ ለዚያ ምቹ የሆነውን እድል በመጠቀም አቅሙን አሟጥጦ እንዲጠቀም ነው። እኛ አርሶ አደሩን ስንፈርጅ ግንባር ቀደም፣ መካከለኛ እንዲሁም አነስተኛ በሚል ነው። በኩታ ገጠም እሳቤ እነዚህ በተለያየ ምድብ የተፈረጁ አርሶ አደሮች ወደ አንድ የማምረት አቅም እንዲሳቡ ለማድረግ ነው። ይህ የራሱ እድል ያለው በመሆኑ መሬቱን ሰብሰብ ለማድረግ ረድቶናል።

በአሁኑ ወቅት ትንሹ ኩታ ገጠም የሚባለው የመሬት መጠን አስር ሔክታር ነው። እንደሚገመተው የአንድ አርሶ አደር ማሳ ደግሞ በአማካይ አንድ ሔክታርና ከዚያም በታች ነው። በዚህ አርሶ አደሮችን በመሰባሰብ ቢያንስ አስር ሔክታር አንድ ላይ ማምጣት ይቻላል የሚል እሳቤ አለ።

ትልልቅ ኩታ ገጠም የምንላቸው ግን ባለፈው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከቢልጌት ጋር መቂ አካባቢ ተዘዋውረው የጎበኙት የስንዴ ኩታ ገጠም ነው፣ አርሶ አደሮቹ እንደተናገሩት ሃያ ሺ ሔክታር መሬት ነው። በዚያው ኩታ ገጠም ውስጥ ወደ ሁለት ሺ የሚሆኑ አርሶ አደሮች ተካትተውበታል።

ይህ መሬት ከሌላ ቦታ የመጣ ሳይሆን ድሮም የነበረ ነው። የተቀየረ ነገር ቢኖር አመለካከት ነው፤ ኩታ ገጠም ሲሆን ሜካናይዝድ ለማድረግ፣ ወጥ ግብዓት ለመጠቀምና ለሌላም ሥራ ምቹ ይፈጥራል። በዚህም ምክንያት ወደኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ ተገብቷል። ኩታ ገጠም በተለይ ለሜካናይዜሽን ከፍተኛ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። አንድ ትራክተር የተበጣጠሰ መሬትን ለማረስ የሚወስደው ጊዜ ብዙ ነው፤ ምክንያቱም የአንዱን አርሶ አደር መሬት ለማረስ በመጣ ጊዜ ሌላኛው አርሶ አደር ዝግጁ የማይሆንበት ጊዜ ይኖራል ይህ ብቻ በራሱ የጊዜ፣ የምልልስ፣ የነዳጅ ብክነት ይፈጠራል።

ከዚህ ባለፈ ወደምርት ስብሰባ ሲገባም እንደሚታወቀው ማሽኖቹ በጣም ውድ እንደመ ሆናቸው አንድ አርሶ አደር በግል ለመግዛት ሆነ ለመከራየት ይከብደዋል፤ ነገር ግን ሁለት ሺ ሔክታር አንድ ቦታ ላይ የተሰበሰበ ማሳ ካለ በአንድ ጊዜ ሰርቶ እንዲሔድ ያደርገዋል።

ዘንድሮ መኸር ላይ ካረስነው ወደ 11 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሔክታር መሬት በኩታ ገጠም የታረሰ ነው። ከ20 ነጥብ አራት ሚሊዮን ሔክታር መሬት ውስጥ ማለት ነው። በትራክተር የታረሰው መሬት ደግሞ አስቀድሜ እንደጠቀስኩት አምስት ሚሊዮን ሔክታር ነው። ስለዚህ ብዙ መሬት በኩታ ገጠም እየታረሰ መሆኑ መልካም ነገር ነው። ነገር ግን ለዚህ ለተሰበሰበ መሬት ብዙ ማሽነሪ አርሶ አደሩ ዘንድ ማድረስ የግድ የሚል ነው።

በሚቀጥሉት ዓመታት መሥራት ያለብን ነገር ቢኖር ብዙ ማሽነሪዎችን ማስገባት ላይ ነው። ማሽነሪዎችን ሀገር ውስጥም ጭምር ገጣጥመን ብዙ ማሽነሪዎችን ለግብርናው ሴክተር ማቅረብ የሚጠበቅብን ይሆናል። የግብርናው መዘመን በዚህ ደረጃ እየመጣ ነው ማለት ይቻላል። ምክንያቱም መሬት በኩታ ገጠም እየታረሰ ነው፤ አርሶ አደሩም በሜካናይዜሽን እየተጠቀመ ነው። ለውጡን ከዚህ አንጻር ማየት ይቻላል።

ሌላው መጥቀስ የምፈልገው ነገር ትራክተሮችንና ማሽነሪዎችን ከቀረጥ ነፃ ማስገባት ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊት አብዛኞቹ ባንኮቻችን ለእንደዚህ ዓይነት ሥራ ብዙም እድል አለመስጠታቸውን ነው። ባለፉት ዓመታት ወደባንክ ሄደን አርሶ አደሩ ትራክተር እንዲገዛ ብድር ስጡን ማለት በጣም ከባድ ነበር።

መንግሥት የወሰደው ርምጃ ቢኖር የፖሊሲ ለውጥ ማድረግን ነው። ሥራውን ለማበረታታት የፋይናንስ ተቋማቱ ለዚህ የሚሆን ብድር ማቅረብ ጀምረዋል። በርግጥ በእኛ እይታ ይህ በቂ ነው ብለን አናምንም። ምክንያቱም ብዙ ፋይናንስ ወደገጠር መሔድ አለበት ብለን ስለምናምን ነው። በአሁኑ ወቅት ከዚህ በፊት ታይተው በማይታወቁ አካባቢዎች ጭምር ትራክተሮች እየታዩ ነው። በቂ ግን አይደለም። ነገር ግን ግብርናችን መዘመን ጀምሯል ማለት ይቻላል። ግብርናችን ከበሬ ጫንቃ መውረድ ጀምሯል።

ሌላው ግብርናን ከማዘመን አንጻር ወሳኙ ጉዳይ ግብዓት ማቅረብ ነው። እነዚህ ግብዓት የምንላቸው ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር፣ ኖራ፣ አግሮ ኬሚካልና መሰል ግብዓት ማቅረብ ማለት ነው። ባለፉት ዓመታት ክልል ላይ ስሠራ የነበረኝ ልምድ እንደሚያመለክተው አርሶ አደሩ ግብዓት የመጠቀም ልምዱ ዝቅተኝ መሆኑን ነው። አንዳንድ አካባቢ መሬታችን ለም በመሆኑ እንዲያውም ማዳበሪያ አያስፈልግም፤ ሌላ አካባቢ ደግሞ ማዳበሪያ መሬቱን ሊጎዳ ስለሚችል ባንጠቀም ይሻላል ይሉ ነበር ።

ብዙ ቦታ ማዳበሪያም ምርጥ ዘርም በመጋዘን ውስጥ እያለ አገልግሎት ላይ ሳይውሉ የሚወገድበት ጊዜ ነበር። ባለፉት ዓመታት መሬትን አንድ ላይ በማምጣት በኩታ ገጠም እንዲታረስ በተሠራው ሥራ አርሶ አደሩ ግብዓት እንዲጠቀም፣ ለገበያ እንዲያቀርብ እንዲሁም ምርቱን አንዲያድግ በተደረገው ጥረት የአርሶ አደሩ የግብዓት ፍላጎት እኛ ከምናቀርበው በላይ ሆኗል።

ከዚህ በፊት የምናቀርባትም ግብዓት ትንሽ ከመሆኗ በላይ እሷም መጋዘን የምታድር ናት። አሁን ግን እንኳን መጋዘን ውስጥ ማደር ይቅርና የአርሶ አደሩን ፍላጎት ማርካት አልተቻለም። እኔ ይህንን ፍላጎት እንደሥጋት አልቆጥረውም። እንዲያውም አርሶ አደሩ ‹‹ግብዓት አሟላልኝ›› ሲለኝ፣ ያለብኝ ማቅረብ ነው እንጂ አርሶ አደሩ ግብዓት አጠረኝ በማለቱ ተግዳሮት ነው ልል አልችልም።

ባለፉት ዓመታት የመጣውን ለውጥ ስናይ ኢትዮጵያ ስትጠቀም የነበረው ማዳበሪያ ቢበዛ አስርና አስራ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል አካባቢ ነበር፣ በዓመት ስናቀርብ የነበረው እሱኑ ብቻ ነበር። አምና በ2016/17 የምርት ዘመን ገዝተን ያቀረብነው 20 ሚሊዮን ኩንታል ነው። ይህ ከባለፈው ከለውጥ ዓመታት አንጻር ጀማሮ ሲታይ አንደኛ መጠኑን በእጥፍ አሳድገናል። የመግዛትም ተደራሽ የማድረግም አቅማችንን ከፍ አድርገናል። ወደ ክልሎች ከደረሰ በኋላ ወደ አርሶ አደሩ አካባቢ የመድረሱ ጉዳይ ተግዳሮት የነበረበት ቢሆንም መጠኑ ግን አሁንም ጨምሯል።

ሁለተኛው መንግሥት የወሰደው የፖሊሲ ርምጃ በተለይ ደግሞ በዓለም ተከስቶ የነበረው የዩክሬንና ራሽያ ጦርነት ጋር ተያይዞ እንዲሁም ቀደም ሲል ተከስቶ ከነበረው ኮቪድ ጋር ተያይዞ የማዳበሪያ ዋጋ ጨምሮ እንደነበር የሚታወስ ነው። በዚያን ወቅት አርሶ አደሩ እንዳይጎዳ መንግሥት ለመጀመሪያ ጊዜ ማዳበሪያ የደጎመው ባለፉት ሶስት ዓመታት ነው። ከዚያ ቀደም የማዳበሪያ ድጎማ የሚባል ነገር አልነበረም። ባለፉት ሶስት ዓመታት ብቻ መንግሥት ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ ለማዳበሪያ ድጎማ አድርጓል።

ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ስንዴ ከውጭ ስታስገባ ለሸማቾች የምታቀርበው ያስገባችውን ስንዴ ድጎማ አድርጋ ነበር። ይህ ማለት ድጎማ የሚደረገው በሌላ ሀገር ስንዴ ላይ ማለት ነው። አሁን በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው ከፍተኛ ለውጥ ነው። በአሁኑ ወቅት ከሌላ ሀገር ምርት ገዝተንና ደጉመን ማቅረብ ሳይሆን ምርታማነትንና ግብዓት ደጉመን ምርት ሀገር ውስጥ እንዲመረት ማድረግ ላይ ነን።

ይህ በእኔ እይታ አርሶ አደሩን ብቻ ሳይሆን ጠቅላላ ምርትና ምርታማነትን መደጎም ነው። ይህ የተደረገው ሸማቹም ተጠቃሚ እንዲሆን ነው። ይህ ትልቅ የፖሊሲ ለውጥ ነው። ስንዴ ላይ ያመጣነው ለውጥ የዚህ አካል ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። ሩዝንም ለመተካት የሔድነው ርቀት የዚህ አካል ነው። ማሽነሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ማድረግ፣ ግብዓት ላይ ድጎማ ማድረግና ተደራሽ እንዲሆኑ ማድረግ በግብርናው ላይ ትልቅ ለውጥ እንዲመጣ ያደረገ ከፍተኛ ለውጥ ነው።

ሶስተኛው ከትልልቅ ፖሊሲዎች አንጻር በለውጥ ዓመታት የመጡና ከዚህ በፊት ያልነበሩ ግብርና ውስጥ ያለው አቅም በጣም ብዙና ሰፊ ነው። ነገር ግን ሁሉንም በአንድ ጊዜ መሥራት ስለማይቻል የተለየ ትኩረት ሰጥተን የምንሠራቸው ጉዳዮች ተለይተው እነሱን አድምተን መሥራት አለብን ተብለው በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን የተጀመሩ ኢኒሼቲቮች እንደ አንድ መነሻ መውሰድ ይቻላል።

ኢትዮጵያ ለስንዴ የተሻለ አግሮኢኮሎጂ አላት፤ ነገር ግን ስንዴን ገዝተን እየበላን ነው። ቢያንስ ይህን ነገር በትጋት ሰርተን ማስቆም አለብን የሚለው ብሔራዊ የስንዴ ኢንሼቲቭ፣ የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ፣ የአረንጓዴ ዐሻራ ኢንሼቲቭ የሚባሉት ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ በመሪዎች ደረጃ አልነበራትም።

ከእነዚህ ኢንሼቲቮች የተነሳ ባለፉት ለሃምሳ ዓመታት ከውጭ እያስገባን የነበረው ስንዴ በአምስት ዓመታት ውስጥ መተካት ችለናል። ይህ ትልቅ የታሪክ እጥፋት ነው። አንደኛ የሥራ ባሕላችንን ቀይሮታል፤ ከዚህ በፊት ክረምት ብቻ እንሠራ የነበረውን ሥራ በጋውንም ጭምር እንድንሠራ አድርጎናል። ከዚህ የተነሳ ግብርናው በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ድርሻ ከፍ ብሏል።

ለምሳሌ በ2016 የፕላንና ልማት ሚኒስቴር እንዳለው፤ ግብርናው ስድስት ነጥብ ዘጠኝ በመቶ አድጓል። የግብርና ሀገራዊ ምርቱን በኢኮኖሚው ውስጥ ሲሰላ ማለት ነው። ግብርና ባለፉት ጥቂት ዓመታት ይህን ያህል አድጎ አያውቅም። በ2004 ላይ አምስት ነጥብ አራት ነበር። ከዚያም ስድስት ነጥብ አንድ እያለ መጥቶ አምና ግን ያስመዘገበው ከፍተኛ ነጥብ ነው ማለት ይቻላል። እነዚህ የፖሊሲ ርምጃዎች ምርትና ምርታማነትን እያሳደጉ ነው።

በአጠቃላይ ባለፉት አምስት ዓመታት መንግሥት ግብርናው ሴክተር ላይ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ያስቻሉ የፖሊሲ ርምጃዎችን ወስዷል። ኢኒሼቲቮች ቀርጾ ተግባራዊ አድርጓል። ለግብርናው ሴክተር ወሳኝ በሆኑ ግብዓቶች ላይ መንግሥት ድጎማ ጭምር አድርጎ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ አድርጓል። በጥቅሉ ያለፉት አምስት ዓመታት በዘርፉ ትልቅ መሠረት የተጣለበት ነው ማለት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- ለውጪ ገቢ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶች አሁናዊ አፈጻጸማቸው ምን ይመስላል?

ግርማ (ዶ/ር)፡- ግብርና ፋይዳው ለምግብ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ገበያ ተጠቃሚ መሆንን የሚያካትት ነው። ለምሳሌ የሀገራችንን የዘርፉን የ2016 አፈጻጸም ስናይ የግብርና ምርቶች ከጠቅላላ የወጪ ምርት 75 በመቶ ይይዛሉ። በዚሁ ልክ የግብርና ምርትና ምርታማነት ሲያድግ በውጪ ንግድ ላይ የሚኖረን ተሳትፎም ይጨምራል።

አርሶ አደሮቻችን የሚያመርቱት በልተው ለማደር ብቻ አይደለም። ኢንዱስትሪ እና የውጪ ገበያን ታሳቢ አድርገው ትርፍ ምርት እንዲያመርቱ ጭምር ነው። ከዚህ አኳያ በውጪ ምርት ላይ ያለውን እንመልከት። ከወጪ ምርትም ቡናን ነጥለን ብንወስደው ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ነች፤ ነገር ግን የቡና ምርታማነታችን በሚገባው ልክ አላደገም ነበር። ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ በዓመት የምናመርተው የቡና ምርት መጠኑ በእጥፍ ጨምሯል።

ባለፈው ከአምስት ዓመት ከነበረው በእጥፍ ጨምሮ ዘንድሮ ወደ አንድ ሚሊዮን ቶን ወይም ወደ አስር ሚሊዮን ኩንታል ቡና ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል። ይህም በዓለም ቡና ከሚያምርቱ ሀገራት ኢትዮጵያን ቁጥር ሶስት ላይ ያስቀምጣታል። ከብራዚልና ቬትናም ቀጥሎ ማለት ነው። ይህ ማለት ኢትዮጵያ የምታመርተው የቡና ምርት በአካባቢም ደረጃ ይሆን በምርታማነት ደረጃ መጨመሩ የሚያሳይ ነው።

ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ወደ ስምንት ነጥብ አምስት ቢሊዮን የቡና ችግኞች ኢትዮጵያ ውስጥ ተተክለዋል። ይህ ከአረንጓዴ ዐሻራ በተጨማሪ ማለት ነው፤ ይህ የሚያሳየው የወጪ ምርት በሆነው የቡና ልማት ላይ ኢትዮጵያ ኢንቨስት እያደረገች መሆኑን ነው። ያረጁ ቡናዎችን ጎንድላለች። በአዲስም ተክታለች። በጥራቱ ላይ ሰርታለች። በዚህም የቡና ምርት ጨምሯል። ምርቱ ብቻ ሳይሆን የቡና ጥራቱም ጨምሯል።

በዚህም ኢትዮጵያ ከወጪ ንግድ (ኤክስፖርት) የምታገኘው ቡና ከአምስት ዓመት በፊት ከነበረበት ወደ እጥፍ ጨምሮ በ2016 ዓ.ም አንድ ነጥብ 43 ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች። በቅርቡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን እንዳሉት፣ በ2017 ዓ.ም ሁለት ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሎ ይገመታል። ይህ ዶላር የተገኘው ከቡና ምርት ብቻ ነው። ይህ አሀዝ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ በዓመት የምታገኘው የወጪ ምርት ገቢዋ ነበር። በተመሳሳይ በጥራጥሬና በቅባት እህሎች፣ በአበባና በሆርቲካልቸር፣ እንዲሁም በእንስሳቱ ዘርፍ በምርት በኩል እድገት አለ፤ ይህ ምርት ደግሞ ወደ ውጪ ንግድ የሚሔደው ሀገር ውስጥ ያለውን ፍጆታ ጭምር ሸፍኖ ነው።

በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያ በቅርቡ በማክሮ ኢኮኖሚው የወሰደችው ሪፎርም የወጪ ምርቶችን የሚያበረታታ ነው። ከዚህ ቀደም በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ውጪ ይወጣ የነበረውን የእንስሳት ሀብት፣ ቡና፣ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ወደ መደበኛው ገበያ እንዲመጣ አድርጓል። ከዚህም የተነሳ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የኢኮኖሚ ሪፎርም ከተደረገ በኋላ ከፍተኛ ለውጥ መምጣት ተችሏል።

ለምሳሌ ባለፉት አራት ወራት ብቻ ከግብርና ምርቶች ከአንድ ቢሊዮን በላይ ዶላር ተገኝቷል። ይህ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር የ20 እና 25 በመቶ ጭማሪ አለው። ይህን ያመጣው ምርቱ መመረቱ ብቻ ሳይሆን የተወሰደው የፖሊሲ ርምጃ የወጪ ምርቶችን የሚያበረታታ በመሆኑ ነው። ምርቱ አለ፤ ያ ምርት ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ እየወጣ ነው። የውጭ ምንዛሬን እያሰገኘ ነው።

የግብርና ወጪ ምርቶችን ስናጤን በእኔ እይታ የምርት ጭማሪ አለ፤ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ደግሞ ለወጪ ምርቶች ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው። የግብርና ድርሻ ከዚህ በፊትም ትልቅ ነበር፤ አሁንም ትልቅ ሆኖ የሚቀጥል ይሆናል። የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የማዕድን ዘርፉን በማነቃቃቱ፣ ወርቅ እየመጣ ነው። ይህ ደግሞ የግብርናን ጫና ይጋራል ብዬ አስባለሁ።

አዲስ ዘመን፡- የግብርናውን ሴክተር በቴክኖሎጂ በመደገፍ ለማዘመን እየተደረገ ያለው ጥረት እንዴት ይገለጻል?

ግርማ (ዶ/ር)፡- ቴክኖሎጂ ስንል አንዱ ሜካናይዜሽን ነው። ሜካናይዜሽን በተጠቀምን ቁጥር የድኅረ ምርት ብክነትንም ጭምር ማስቀረት ያስችላል። የተዘራው ምርት ከማሳ የምግብ ሳህናችን ላይ የሚደርሰው ከሃያ እስከ ሰላሳ በመቶ የሚሆነው ምርት ባክኖ ነው። ይህ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በታዳጊ ሀገሮችም ጭምር የሚከሰት ነው። የድኅረ ምርት ቴክኖሎጂዎችን ስንጠቀም አጭደን ወዲያኑ በማሽን ወቅተን ምርቱን እንድንወስድ የሚያደርግ በመሆኑ የሚባክነውን ምርት ያስቀርልናል። ይህን አሠራር አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል።

ሌላው የተሻሻሉና ምርታማ የሆኑ ምርጥ ዘሮችን ለአርሶ አደሩ ማቅረብ ነው። ምርጥ ዘርን መጠቀም ብቻ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከ30 እስከ 50 በመቶ ምርታማነት ላይ በጎ ተጽዕኖ አለው። ስለዚህ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ከማቅረብ አንጻር ትልቅ ሥራ እየሠራን እንገኛለን። አርሶ አደሩ ከማዳበሪያ ቀጥሎ እየጠየቀን ያለው አንዱ ምርጥ ዘር ነው።

ባለፉት ዓመታት በአማካይ ስናቀርብ የነበረው ምርጥ ዘር በዓመት ወደ አንድ ሚሊዮን ኩንታል አካባቢ ነው። ይህ የሁሉም የተሻሻሉ ዝርያዎች ተደምረው ማለት ነው። የሶስት ዓመት የተሻሻሉ የዘር አቅርቦት ፍኖተ ካርታ አዘጋጅተናል። በዚያ ላይ ይህን ቁጥር በእጥፍ ማሳደግ አለብን ብለን ከዚህ ዓመት ጀምሮ ወደ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል የተሻሻሉ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ አቅደን በመሥራት ላይ ነን። ቢያንስ በያዝነው ዓመት 2017 ዓ.ም በጀት ዓመት ወደ ሁለት ሚሊዮን ኩንታሉን እናሳካል ብለን እናስባለን።

ትኩረት የምናደርገው ከምግብ እህልም፤ ከወጪ ምርትም አንጻር ወሳኝ የሆኑ ምግቦች ላይ ነው። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ አምስት ያህሉ ማለትም፤ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ማሽላና ጤፍ ብቻ የኢትዮጵን የምግብ እህል ምርትን ከ85 በመቶ በላይ ይሸፍናሉ። በእነዚህ አምስት ሰብሎች ላይ የተሻሻለ ዝርያዎችን ብናቀርብ ምርታማነታችን በዚያው ልክ ይጨምራል።

ከዚህ በኋላ የሚቀረን መሬት ማስፋፋት ሳይሆን ምርታማነትን መጨመር ነው። ለምሳሌ ስንዴ የዓለም አቀፍ አማካይ ምርት የሚያሳየው በሔክታር ወደ 36 ኩንታል ነው። ኢትዮጵያም በአማካይ ወደዚያው እየተቃረበች ነው። ይህ ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ 80 ኩንታል በሄክታር የሚያመርቱ መኖራቸው እንዳለ ሆኖ ከአንድ ሔክታር 60 ኩንታል የሚያመርቱ አሉ። የምንወስደው ግን ሀገራዊ የሆነ አማካይ ውጤቱን ነው።

ሌላው ትልቁ ኢንቨስትመንት ነው ብዬ የማስበው ግብርና ሚኒስቴር አምስት አውሮፕላኖችን መግዛቱን ነው። እነዚህ አውሮፕላኖች የአንበጣ መንጋን፣ የግሪሳ ወፍንና መሰል ነገሮችን ከመከላከል አኳያ ወሳኝ ናቸው። በተለይ ድንበር ዘለል የሆኑ ተባዮችን ለመከላከል የሚያስችል አቅም ፈጥረዋል። በአንድ ወቅት በጣም ከፍተኛ የአንበጣ መንጋ ባጋጠምን ጊዜ ከደቡብ አፍሪካ ጭምር አውሮፕላኖችን በኪራይ  ስናስመጣ እንደነበር የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያን የሚያክል ትልቅ ሀገር አብዛኛው ኢኮኖሚያችን ግብርና ላይ ሆኖ ያንን ሁሉ ወጪ አውጥተን ደቡብ አፍሪካ ድረስ መሔድ የለብንም በሚል አውሮፕላኖችን ለመግዛት ችለናል። የተገዙትም ዘመናዊ የሆኑ አምስት አውሮፕላኖች ናቸው። አውሮፕላኖቹ ከእኛ ተርፈው ለንግድ አገልግሎት መዋል እንዲችሉ ተደርገዋል። በመሆኑም በቅርቡ የምርጥ ዘር ድርጅቶች የኬሚካል ርጭት ሲያካሔዱባቸው ነበር። ሌሎችንም ተዛማጅ ሥራዎችን እየሠሩ ነው።

በአሁን ወቅት ደግሞ የአየር ንብረቱ እንደሚ ያመላክተው ከፍተኛ ተባይ የሚፈጥርበት ነውና ኢትዮጵያም ለዚያ ራሷን አዘጋጅታለች ማለት ነው። በአጭሩ የራሷን አቅም ፈጥራለች። ይህ አንዱ ቴክኖሎጂ ነው። ስለዚህ ከሜካናይዜሽን፣ ከግብዓት፣ ከምርጥ ዘር አቅርቦት አጠቃላይ ከሰብል ጥበቃ አንጻር ታይቶ ግብርናውን ለማዘመን የሚያግዙ የቴክኖሎጂ አቅርቦቶች እየተሠሩ ነው። ይህ ግን በቂ አይደለም፤ እያደገ መሔድ አለበት። ጅምሩ ግን መልካም የሚባል ነው።

አዲስ ዘመን፡- የግል ባለሀብቱን በግብርና ሜካናይዜሽን ላይ ለማሳተፍ ምን እየተሠራ ነው? የሚሰጡስ ማበረታቻዎች ይኖሩ ይሆን?

ግርማ (ዶ/ር)፡- የግብርና ሴክተር ውስጥ ያለው የግሉ ሴክተር ተሳትፎ በብዙ መንገድ ሊገለጽ ይችላል። አንዱ ባለሀብቱ ራሱ መሬት ወስዶ ሊያርስ መቻሉ ነው። እስካሁን ባለው ሁኔታ ወደ አንድ ሚሊዮን ሔክታር ሊጠጋ የሚችል መሬት ወስደው ሰፋፊና መካከለኛ እርሻ ላይ የተሳተፉ ባለሀብቶች አሉ። በአበባ እና ሆርቲካልቸር የሚሠሩት እንዳሉ ሆነው አብዛኛዎች ያሉት ቆላማ በሆኑ አካባቢዎች እንደጋምቤላና ቤኒሻንጉል አካባቢ ነው።

ይሁንና ተሳትፏቸው ከዚህ በበለጠ መጨመር አለበት እንላለን። ምርጥ ዘር በማባዛትና በማቅረብ እየተሳተፉ ያሉ ባለሀብቶች አሉ። ብዙ የበቆሎ ምርጥ ዘሮች የሚያባዙት በባለሀብቶች ነው። ይህ ድርሻቸው የበለጠ እያደገ እንዲሄድ እንፈልጋለን።

አብዛኞቹ የሜካናይዜሽን መሳሪያዎች ከውጭ ተገዝተው እየገቡ ያሉት በግሉ ሴክተር ነው። እንዲያውም ሁሌም ከውጭ እየገዙ ማቅረብ አይቻልምና በሀገር ውስጥ መገጣጠሚያዎች እንዲኖሩ አጥብቀን እየሠራን እንገኛለን። ከዚህ አንጻር በቅርብ ከፋኦ ጋር በመሆን በግብርና ሴክተሩ ውስጥ ትኩረት የሚሰጣቸው የኢንቨስትመንት መስኮች ምንድን ናቸው? የሚለውን ሁሉ ለይተናል።

ለምሳሌ ሜካናይዜሽን ላይ ብዙ ማሽነሪዎች ያስፈልጉናል። ከዚህ ጋር ተያይዞ መንግሥት ከታክስ ነፃ እንዲሆን አድርጓል። ይህን እድል ባለሀብቱ ተጠቅሞ ማሽነሪዎቹን ማምጣት ቢችል ለራሱም ተጠቃሚ መሆን ይችላል የሚል እምነት አለን። ሁለተኛው የግብርና ግብዓት ማዳበሪያን ጨምሮ ሌሎችንም የግብርና ግብዓቶች የግሉ ሴክተር እንዲያስገባ ከማድረግ አንጻር ትኩረት ተሰጥቶታል። በርግጥ ለማዳበሪያ የሚሆን ግብዓት በሀገራችን ያለ ከመሆኑ አንጻር ወደማምረት መገባት አለበት የሚል አቅጣጫም አለ።

በእንስሳት ዘርፉ ከመኖ ጋር በተያያዘም መኖ ከማምረት አንጻር የባለሀብቱ ድርሻ እንዲኖር እየሠራን ነው። ግብርናው እያደገና እየዘመነ ሲሄድ፤ ቀጥሎ የሚመጣው እሴት መጨመር ነው። ወደ አራት ኢንዱስትሪያል ፓርኮች ማለትም የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርኮች አሉ። ፓርኩ ውስጥ የገቡም ሆነ ከፓርኩ ወጪ የሚሰሩ የግብርና ምርቶች እንደ አቮካዶ፣ ቡና እንዲሁም የእንስሳት ምርቶች ላይ እሴት ጨምረው የመሄድን ሥራ ይጠይቃሉ።

አሁንም ቢሆን በግብርናው ዘርፍ ያለው የግል ባለሀብቱ ተሳትፎ በቂ ነው አንልም። ምክንያቱም ያለው ጅምር ሥራ ነው። የግሉ ባለሀብት ከዚህ በላይ ወደዘርፉ መጥቶ ኢንቨስት ማድረግ አለበት። ባለሀብቱ ከተማ ውስጥ ቀለል ባለ መልኩ ከሚሠራው አንጻር ሲታይ፤ አንዳንዴ ወደ ገጠር ወጣ ብሎ መሥራቱ ላይ ፈተና ያለበት ስለሚመስለው የሚፈራው ነገር ይኖራል።

ለዚህ ደግሞ ማበረታቻዎችን ይጠይቃል። ለምሳሌ እንደ ልማት ዓይነት ባንኮች ለግብርና የሚሰጡት ብድር ከወለድ ምጣኔም ጭምር በተሻለ የመስጠትና የማበረታታት አቅጣጫዎች አሉ። ስለዚህ የግሉ ሴክተር ጅምር ሥራዎች አሉ። በተለይ እሴት ጭመራ ላይ፣ ግብርናን በሚያዘምኑ ቴክኖሎጂዎች ማቅረብ ላይ እና የግብርና ግብዓትን በማቅረብ ላይ በስፋት መሥራት አለብን ብለን እናስባለን።

አምና የወጣ “የኮንትራት እርሻ” የምንለው አዋጅ፤ ግብርና ለግሉ ተሳትፎ ትልቅ ውጤት ያመጣል ብለን እናምናለን። ባለሀብቶች የራሳቸው እርሻ ሊኖራቸው ይችላል። ከአርሶ አደሩ ዘንድ በመሔድ “ይህን ምርት አምርትልኝ፤ ካመረትክ እኔ እገዛሃለሁ” ብለው ሲፈልጉ ለዱቄት ፋብሪካቸው፤ ሲፈልጉ ደግሞ ለተለያየ ኢንዱስትሪያቸው በኩታ ገጠም ከተደራጁ ከተወሰኑ አርሶ አደሮች ጋር የአምራች አስመራች ውል መግባት ማለት ነው።

አንዳንድ በአደጉ ሀገሮች የኮንትራት እርሻ ማለት የግሉ ዘርፍ ጥራት ያለው ምርት ለማግኘት ባለሙያ ጭምር ይቀጥራሉ፤ ለአምራቹ ግብዓት ይሰጣሉ። ላደረጉት ሁሉ ደግሞ ምርቱን ሲረካከቡ የሚተሳሰቡ ይሆናል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው በቢራ ገብስ ላይ የተሠራው ሥራ ነው፤ የቢራ ኢንዱስትሪዎች የብቅል ኢንዱስትሪዎች የተሻለ የቢራ ገብስ ለማግኘት የተሻለ ዝርያዎችን ለማግኘት ከውጭ ጭምር አምጥተው አርሶ አደሩን አላምደዋል።

ውል ፈርመው የቢራ ገብሱን ሲያመርቱ አርሶ አደሩ አንደኛ የገበያ ጉዳይ አያሰጋውም። ባለሀብቱም ጥራት ያለው ምርትን ሊያገኝ ይችላል። ስለዚህም ይህን ተግባራዊ የሚያደርግ አዋጅ ወጥቷል። መመሪያውንም አጽድቀናል።

በመሰረቱ በእኔ እምነት አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ራሱ የግል ባለሀብት ነው። ስለሆነም እነርሱን ማገዝና ወደ እሴት ጭመራ እንዲገቡ ማበረታታት ይጠበቃል። እንደ ኦሮሚያ ዓይነት ክልሎች ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ሥራ ጀምረዋል። ለምሳሌ ሞዴል ተብለው እውቅና የተሰጣቸው አርሶ አደሮች በቀጣይ መሆን የሚጠበቅባቸው ባለሀብት ነው። እነርሱን ወደ ኢንቨስትመንቱ ማሻገር ይጠበቃል። ከዚህ አንጻር ሥራዎች እየተሠሩ ነው።

አዲስ ዘመን፡- የኅብረት ሥራ ማኅበራት ለግብርናው አቅም እንዲሆኑ እየተሠራ ያለው ምንድን ነው?

ግርማ (ዶ/ር)፡- እንደ እኛ ባለ ሀገር የገጠር ሽግግር ኢኮኖሚ ለሚለው እሳቤችን የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ ሚናቸው ጉልህ ነው። እንደ ሕንድ ሌላው ቀርቶ እንደፖላንድ ዓይነት ሀገሮች ከዚህ ጋር ተያይዞ ያላቸውን ሁኔታ ሄጄ ለማየት ሞክሬያለሁ። ለገጠሩ መለወጥና መዘመን የኅብረት ሥራ ማኅበራት ድርሻቸው ትልቅ ነው። ያሉት ትንንሽ የአርሶ አደር አቅሞች አንድ ላይ ተደምረው ትራክተር መግዛት፣ ፋብሪካ ማቋቋምና ሌሎች ኢኮኖሚው ላይ ትልቅ ዋጋ ማምጣት የሚያስችል ነው። ከዚህ አንጻር የእኛ ማኅበራትን ስናጤን ከ100 ሺ በላይ የኅብረት ሥራ ማኅበራት በሀገራችን አሉ። አባላቶቻቸው ደግሞ ከ20 ሚሊዮን በላይ ናቸው። ይህ ከቁጥር አንጻር ሲታይ ትልቅ ነው። ነገር ግን አቅማቸው ሲታይ በጣም አነስተኛ ነው።

ይህንን አቅም ለመጠቀም ከኅበረት ሥራ ማኅበር ኮሚሽን ጋር እየሠራን ያለነው ማኅበራትን የመደራጀት፣ አቅማቸውን የማሳደግ የሪፎርም ሥራ አለ። አነስተኛ አቅም ያላቸውን አንድ ላይ በማዋሃድ ትልቅ አቅም እንዲኖራቸው፤ አስተዳደራቸው በሙያተኞች እንዲመሩ ማድረግ የሚያስችል ሥራ እየሠራን ነው።

ትልልቅ ኢንዱስትሪ ያላቸው ማኅበራት አሉ። ኦሮሚያ አካባቢ የአሰላ ብቅል ፋብሪካ፣ የዱቄት ፋብሪካም ያላቸው ብዙ ማኅበራት አሉ፤ ይህ የሚፈልገው ነገር ቢኖር ሙያተኛን ነው። ተቋማቱ ለአርሶ አደሩ ግብዓት ብቻ ማቅረብ ሳይሆን ለምሳሌ የእኛ ማዳበሪያ በአብዛኛው አርሶ አደር ዘንድ የሚደርሰው በማኅበራቱ በኩል ነው። ማዳበሪያ እንደሚያደርሱ ሲመለሱ ምርቱን ምን ያህል መሰብሰብ ይችላሉ ቢባል ያላቸው የገንዘብ አቅም አነስተኛ ነው።

ማዳበሪያ ተገዝቶ የሚሄደው በማን ነው ሲባል ክልሎች በጀታቸውን አስይዘውና ተበድረው ነው፤ አርሶ አደሩ ጋር ደርሶ ከተሸጠ በኋላ የሚመለስ ነው። ምርቱን ለመግዛት ካፒታል ያስፈልጋል። ከነጋዴ ጋር ተወዳድረው መግዛት አለባቸው። ብዙዎቹ የካፒታል አቅማቸው አነስተኛ ነው።

ይህንን ችግር ለመፍታት ከኮሚሽኑ ጋር የግብርና ትራንስፎርሜን ኢንስቲትዩትን ጨምረን አንድ “Quick Win” ለፈጣን ድል በሚል የማኅበራቱ አሁን ያለባቸውን አስተዳደራዊ ማነቆዎች፤ ከአቅም፣ ከአደረጃጀት እና ከማሰበሳሰብ አንጻር በመለየት የሪፎርም ሥራ ጀምረናል።

በዚህም አንዳንድ ክልሎች ከፍተኛ ለውጥ አሳይተዋል። ይህንን ታሳቢ በማድረግ እኛና የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት በጋራ በመሆን ማኅበራትን ከየት አንስተን ወደየት መውሰድ አለብን? በዓለም ያለው ተሞክሮስ ምንድን ነው? የሚል ፍኖተ ካርታ እያዘጋጀን ነው።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ያለውና አሁን በደረስንበት ደረጃ በገጠር ልማቱ ውስጥ ሊኖራቸው የሚገቡ ነገሮች ምንድን ናቸው? የሚለውን ሊያሳይ በሚችል መልኩ ማቋቋሚያ አዋጆቻቸውን ጭምር የመከለስ ሥራ እየሠራን ነው። ስለዚህ እንደ ግብርና ሚኒስቴር በተለይ ግብርናው ሲሻገር ወደ ገጠር መዋቅራዊ ሽግግር ሲያመጣ ለዚህ ወሳኝ ሂደት አንዱ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ናቸው ብለን እናስባለን። ይህን የማዘመንና ሪፎርም የማድረግ ሥራን ከኮሚሽኑ ጋር እየሠራን ነው።

አዲስ ዘመን፡- የግብርና ምርቶችን በቀጥታ ወደተጠቃሚው ለማድረስ እየተሠራ ያለው ሥራስ እንዴት ይገለጻል?

ግርማ (ዶ/ር)፡- ምርት ማምረት ብቻውን በቂ አይደለም። የግብርና መርህ ሲጤን ከማምረት በላይ ነው ወደማለት መጥተናል። ቀደም ሲል የእኛ ኃላፊነት በቃ ማምረትና ምርትና ምርታማነቱን ማሳደግ ነው፤ ሌላው የሌላኛው ኃላፊነት ነው የሚል ዓይነት እሳቤ ነበረን።

አሁን በጀመርነው የሥርዓተ ምግብ ፍኖተ ካርታ በላይ ኢትዮጵያ ዲዛይን ካደረገችው ውስጥ ትልቁ እሳቤ የመጣው “ከማሳ እስከ ጉርሻ” ያለውን ሂደት ሁሉ መሠራት አለበት። ይህን ካልተቆጣጠርን የሆነ ቦታ ላይ ትርፍ ምርት አለ፤ ትርፍ ምርቱ ግን ገበያ አልደረሰም። ገበያ ያልደረሰው ስላልተመረተ ብቻ አይደለም፤ በመንገድ እጦት፣ ወይም በአንድ ችግር ምክንያት ኢትዮጵያ የተመረተውን ምርት አልተጠቀመችም። ስለዚህ ያንን ትርፍ ምርት ከሸማች፣ ከኢንዱስትሪ፣ ከወጪ ምርት ጋር የማገናኘት ሥራዎች በጣም በስፋትና በቀጣይነት ለመሥራት ከሚገቡን ጉዳዮች አንዱ ነው።

ምርትና ምርታማነትን ከመጨመር አንጻር ብዙ ርቀት ሄደናል ብለን እናምናለን። ነገር ግን የተመረተውን ምርት ቀጥሎ ላለው ጊዜ የመያዝ፣ የማጠራቀም እና ተጠቃሚው ዘንድ የማድረሱ ሥራ በሁለት ተቋማት የሚሠራ ነው። አንዱ በተለይ ግብይቱን በተመለከተ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ማኅበራትንና የኮንትራት እርሻን ጨምሮ አርሶ አደሮቻችን ገበያን ታሳቢ አድርገው እንዲያመርቱ ከማድረግ አንጻር የእኛ ድርሻ ይሆናል።

የእኛ የግብይት ሥርዓት እስካሁን መዘመን የሚቀረው ነው ተብሎ በመንግሥት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ይገኛል። ከዚያ አንጻር የተመረተው ምርት ምንም እሴት ሳይጨመርበት አራትና አምስት እጆች ስለነኩት ብቻ መጥቶ ሸማቹ ዘንድ ሲደርስ ዋጋው ሊጨምር ይችላል።

ዋጋውን የጨመረው አርሶ አደሩ አይደለም። በመሐል ያሉ ተዋናይ ናቸው። ስለዚህ ይህን ችግር ለመቀነስ እንደ ግብርና ሚኒስቴር ያለው የመፍትሔ አቅጣጫ ሸማቹንና አምራቹን ማገናኘት ነው። እንዲህ ሲባል አንድ አዲስ አበባ ውስጥ ያለ ሸማች ማኅበር በኩታ ገጠም ከሚያመርቱት ጋር ወይም ደግሞ ከኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር በመገናኘት ምርቱን ማምጣት ይችላል። ይህን የሚከለክል አሠራር የለም። ነገር ግን በስፋት አልሔድንበትም።

አዲስ አበባ ውስጥ አሁን የገበያ ማዕከላት እየተገነቡ ነው። በመሆኑም ምርቶችን በቀጥታ ከአርሶ አደሩ አሊያም ከማኅበራቱ ለማምጣት የረጅም ጊዜ ስምምነት ጭምር መፍጠር ይችላሉ። አስቀድሜ በጠቀስኩት የሥርዓተ ምግብ ፍኖተ ካርታችን ላይ ከግብርና ሚኒስቴር ጀምሮ ወደ 15 ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አንድ ላይ ተጣምረው “ከማሳ እስከ ጉርሻ” ባለው ሰንሰለት ላይ እንደ ኢትዮጵያ መሥራት ካልተቻለ ማምረቷ ብቻ በቂ አይሆንም።

የምግብ ሉዓላዊነት የሚለው ጽንሰ ሃሳቡ ራሱ ምግብ ማምረት ብቻ አይደለም። በርግጥ አንዱ ማምረት ነው። የምግብ መገኘትን እና ለዜጎች በቂ የሆነ ምግብ ለምሳሌ ኢትዮጵያውያን ካላቸው የሕዝብ ብዛት አንጻር የምግብ አቅርቦት እንዲኖር ማድረግ ነው። ማምረት የማይቻል ከሆነ ደግሞ በመግዛት የምግብ አቅርቦቱን ሙሉ ማድረግ ማለት ነው።

የምግብ ሉዓላዊነት ሲባል ሌላው ቀርቶ ዜጎች የሚመገቡትን በምርጫቸው እንዲሆን ማድረግ ጭምር ነው፤ ይህ ደግሞ ለአንድ ሰሞን አሊያም ለአምስትና አስር ዓመት ብቻ ሳይሆን ለሁልጊዜ ማለት ነው። መሬት የማያርሱ በርካታ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገሮች አሉ። እነዚህ ሀገራት ለሕዝባቸው ምግብ ገዝተው እንደየፍላጎታቸው የሚያቀርቡ ናቸው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ምግብን ከማምረትና ከማቅረብ አንጻር ባለፉት ዓመታት ሰፊ ርቀት መሄድ ችለናል። ነገር ግን የተመረተው ምርት ተደራሽ እንዲሆን የማድረግ ሁለተኛው ክፍል ነው። እንዲህ ሲባል አንዱ ወደ ገበያ እንዲቀርብ ማድረግ ነው። አንድ ሰው የእርሻ ማሳ ላይኖረው ይችላል፤ የተመረተውን ገዝቶ ለመብላት በገበያ ምግቡ መኖር አለበት። ሳያርሱ ገዝተው መጠቀም የሚችሉ ሰዎችም በምግብ ራሳቸውን ችለዋል ማለት ነው።

ሌላው የዜጎች የመግዛት አቅም ወሳኝ ነው፤ ምግቡ ገበያ ላይ ቀርቦ ገዝቶ የመብላት አቅም አነስተኛ ይሆናል። እንዲያ ሲሆን የዜጎችን የመግዛት አቅም እንዲጨምር ማድረግ አንዱ ነው፣ መንግሥት ድጎማ አድርጎ ያንን ክፍተታቸውን እንዲሞላ የማድረግ ሁኔታም አለ።

ስለዚህ ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነቷን ከማስከበር አንጻር ምግብ ማምረት አንድ ጉዳይ ነው። ትርፍ በሚመረትበት ቦታ ላይ የማከማቸት ነገር ላይ በመሥራት ችግር በሚፈጠርበት ጊዜ ውጪ ሳንሔድ በራስ አቅም ከተከማቸው ምግብ እገዛችንን ለሚፈልጉ ዜጎች ማድረስ ያስፈልጋል።

የምግብ ሉዓላዊነት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ ከማምረት በላይ ነው። ምርት በሚመረትበት ጊዜ ትርፍ ሲኖር ማከማቸት ወሳኝ ነው። በአሁኑ ወቅት እኛ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ላይ ነን። ነገር ግን ምርት የመያዝ አቅማችን አነስተኛ ነው። በባንክ ውስጥ መጠባበቂያ ዶላር ያስፈልጋል እንደሚባለው ሁሉ ኢትዮጵያ የምግብ መጠባበቂያ ያስፈልጋታል።

አዲስ ዘመን፡- ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ግብርና ያለው ትስስር ምን ይመስላል? ፈጠራዎችን ከመጠቀም አኳያ ምን ያህል ርቀት እየተኬደ ነው?

ግርማ (ዶ/ር)፡- ግብርና ቴክኖሎጂ ያስፈልገዋል፤ የሚያስፈልጉት ቴክኖሎጂዎች ብዙ ከመሆናቸው አንጻር፤ ቴክኖሎጂውን የግብርና ምርምር ተቋማት ወይም ደግሞ ዩኒቨርሲቲዎች አሊያም ደግሞ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት እንዲሁም የግል ወርክሾፖች ሊያመነጩት ይችላሉ።

ይህ ከሳይንስና ከፈጠራ አንጻር ሁሉም ነገር እኛ ዘንድ ላይሠራ ይችላል። እኛ ዘንድ ያለው የግብርና ምርምር ተቋም ነው። እነርሱ የሚሠሩት አብዛኛው ምርጥ ዘሮችን ማውጣት ነው፣ ለሜካናይዜሽን አኳያ የሚሠራው ውስን ነው። በሌላ በኩል ግብርና ምርምር ላይ ቴክኖሎጂ የሚያፈልቁ ዩኒቨርሲቲዎች አሉ። ስለዚህ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ሆነ በምርምር ማዕከላት የሚሠሩ የግብርና ምርምሮች ማቀናጀት ወሳኝ ነው። ለዚህም የሚሆኑ ፕላትፎርሞች አሉ። ግን መጠናከር ይኖርባቸዋል።

ባለፈው በሳይንስ ሙዚየም የግብርና ቴክኖሎጂዎች እንዲቀርቡ በተደረገ ጊዜ ወጣቶች በጣም የሚያስገርሙ ፈጠራዎችን አቅርበዋል። ቴክኖሎጂን የማባዛት ፋይናንስ ደግሞ አስፈላጊ ነው። ስታርትአፕ ያልነው ቴክኖሎጂን የማባዛት አቅም ይጠይቃል። ክብር ጠቅላይ ሚኒስትራችን በባለፈው የስታርትአፕ ይፋዊ መርሃ ግብር ላይ ወጣቶች ፈጠራቸውን ሕዝብ ዘንድ የሚያደርሱበት እና የሚበረታታበት እንዲሁም ፋይናንስ የሚያገኙበትን ሁኔታ እንፈጥራለን ማለታቸው የሚታወስ ነው፡

ስለዚህ ሥራው በጥቅሉ በሁለት መልኩ ሊሠራ ይችላል። ለምሳሌ ግብርናን ሊያስተባብራቸው የሚችላቸውን ከምርምር ተቋማት ጋር አቀናጅተን የምንሠራው ነገር ሲኖር፤ በሌላኛው በኩል ደግሞ ቴክኖሎጂን የሚያፈልቁ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ከሥራ እና ክህሎት እንዲሁም ከሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስቴሮች ጋር መቀናጀት የሚያስፈልግና እነዚህ ስታርአፖች ግብርና ሴክተርንም ጭምር ተደራሽ እንዲያደርጉ ተባብረን መሥራት ይጠበቅብናል።

አዲስ ዘመን፡- ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች ያለው የግብርና ሥራ ምን ይመስላል?

ግርማ (ዶ/ር)፡- ይህ በጣም ወሳኝ ጥያቄ ነው። በእነዚህ ጥቂት ዓመታት ትምህርት የወሰድንባቸው ነገሮች አሉ። ግጭት አለ በሚባሉ አካባቢዎች እየተሠራ ያለው የግብርና ሥራ እኛ ከጠበቅነው በላይ ሆኖ ተገኝቷል። እኛ እንደ ግብርና ሚኒስቴር የምናደርገው እንደዚህ ግጭት ያሉባቸው አካባቢዎች ላይ ግብዓትን ማድረስ ነው። አምና አማራ ክልል ተደራሽ ያደረግነው ግብዓት አማራ ክልል እስካሁን ግጭቶች ባልነበሩባቸው ጊዜያት ከሚደርሰው የበለጠ ማዳበሪያ አድርሰናል። ይህም ማለት ወደ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ አርሶ አደሩ ዘንድ ደርሷል ማለት ነው። ይህ ከዚህ በፊት በአማራ ክልል በየትኛውም ጊዜ ተደርጎ አይታወቅም። ማዳበሪያው ሲደርስ የነበረው በእጀባ ጭምር ነው። ምክንያቱም አርሶ አደሩ ካላረሰና ካልዘራ፤ እንደ አርሶ አደር ቀጥሎም እንደ ሀገር መውደቅ ይመጣል።

በቅርቡ ወደ ሰሜን ሸዋ አካባቢ ከጠቅላይ ሚኒስትራችን ጋር አቅንተን በነበረበት ወቅት ለማመን የሚከብድ ምርት ለማየት ችለናል። የእኛ ድርሻ አርሶ አደሩ ዘንድ ግብዓት ማድረስ ነው። የጸጥታ አካላትን ጭምር አስተባብረን እንደ ግብርና ሚኒስቴር ግብዓት በማድረስ በኩል ትልቅ ሥራ ሠርተናል ብዬ መናገር እችላለሁ። ግጭት አልፎ አልፎ በሚከሰትባቸው ኦሮሚያም አማራም ትግራይንም ጨምሮ ያሉ አካባቢዎች ግብዓት ተደራሽ በማድረግ ላይ ትልቅ ሥራ ተሠርቷል።

አዲስ ዘመን፡- በትግራይ ክልል የምርጥ ዘር እጥረት እንደነበር ይነገራል፤ ለዚህ ችግር መፍትሔ ለመስጠት የተደረገ ጥረት አለ?

ግርማ (ዶ/ር)፡- ትግራይ የፕሪቶሪያው ስምምነት ልክ እንደተፈረመ፤ በግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን መጋዘን ውስጥ ያለውን ማዳበሪያ መጀመሪያ መጫን የጀመርነው እኛ ነን። ወደ 700 ሺ ኩንታል ማዳበሪያ በ2015 ለትግራይ አቅርበናል። እንደዚያ ሲባል ለሌሎች ክልሎች አስቀድሞ ማዳበሪያ ተገዝቷል። ለእነሱ ተገዝቶ እስኪቀርብ ድረስ ጊዜው እንዳያልፍ እና አርሶ አደሩ ወደ ሥራ እንዲገባ ወደ ትግራይ ክልል የላክነው ወዲያው ነው። አምና በ2016 በጀት ዓመት የደረሰው ወደ 800 ሺ ኩንታል ማዳበሪያ ነው፤ አምና የማዳበሪያ እጥረት አልነበረም።

ምርጥ ዘርን በተመለከተ ግን ሁሉም ዘንድ እጥረት አለ። ለእሱም መፍትሔ ብለን በትግራይ ክልል ያደረግነው ነገር፤ እዚያው ዘርን በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ ማባዛትን ነው። የመንግሥት ኢንተርፕራይዝም ሆነ የግሉ ሴክተር ላይኖር ይችላል፤ ዘሩን ግን አርሶ አደሩ ማባዛት ይችላል። ከአምና ጀምሮ ይህን በስፋት እየሠሩ ነው። የዚህ ችግር በቀጣዩ ዓመት የበለጠ ይቃለላል ብዬ አስባለሁ።

ትግራይ ክልልን ጨምሮ የአምና በልግ፤ የእቅዳችንን መቶ በመቶ መሥራት ችለናል። የዘንድሮን መኸር ማረስ ያቀዱትን ያህል መሬት የሸፈኑበትና በጣም የተሻለ የሚባል የሰብል ቁመና ያለበት ጊዜ ነው።

ወደምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ ያለው የግብዓት ተደራሽነት ከየትኛው የኦሮሚያ አካባቢ ተመጣጣኝ የሆነ ግብዓት እንዲቀርብ አድርገናል። ስለዚህ በእኔ እይታ እነዚህን አካባቢዎች በግብዓት ተደራሽ ለማድረግ በጣም ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል። አርሶ አደሩ ደግሞ ግብዓቱን ሲያገኝ እንደማንኛውም ሌላ አካባቢ ሥራውን የሠራበት ሁኔታ አለ። አሁን ያንን ምርት የመሰብሰብ ሥራዎች ላይ ተጨማሪ ድጋፍ እየተደረገ፣ የጸጥታ አካላት ጭምር እያገዙ ምርት የመሰብሰብ ሥራ እየተሠራ ነው።

በግጭት አካባቢዎች ምክንያት ያልተሠራ የግብርና ሥራ ጥቂት ነው። እንደ መደበኛው ጊዜ ተደራሽ ለማድረግ መቶ በመቶ እንኳ ባይቻል ተሠርቷል የሚል አተያይ አለኝ። በዚህ ሰሞን ራያ አካባቢ ግሪሳ ላይ ርጭት እያደረግን ነው።

በነገራችን ላይ አማራ ክልል ማዳበሪያ ሲዘረፍ ነበር። በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ማዳበሪያ መንገድ ላይ ተዘርፏል። ይሁንና እሱ ድርጊት ማዳበሪያን ከማድረስ አላገደንም። ምክንያቱም ግብዓቱ አርሶ አደሩ ዘንድ የግድ መድረስ ስላለበት ያንን አድርገናል። በጸጥታ ኃይሎች ሳይቀር ታጅቦ ጭምር መድረስ ስለነበረበት አድርሰናል። ያም በመሆኑ ዘንድሮ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢ የምንጠብቀው ምርት ከፍተኛ ነው።

አዲስ ዘመን፡- በሌማት ትሩፋት እየተሠራ ያለው ሥራ የተጠበቀውን ያህል ነው ማለት ይቻላል? በከተማ ግብርና የተሠራው ሥራስ የሚገለጸው እንዴት ነው?

ግርማ (ዶ/ር)፡– የሌማት ትሩፋት ከተጀመረ ሁለት ዓመት በማስቆጠር ላይ ይገኛል። ወደሥራ የገባነው የአራት ዓመት እቅድ በማስቀመጥ ነበር። በባለፈው ሀዋሳ ላይ የሁለት ዓመት አጠቃላይ ሥራዎችን በገመገምንበት ወቅት ያስተዋልነው ነገር ቢኖር የአራቱን ዓመት እቅድ በሁለቱ ዓመት መድረሳችንን ነው። ግባችን ላይ ስለደረስንም ተጨማሪ ግቦችን አስቀምጠን ወደ ሥራ የገባንበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

በአጠቃላይ ከሌማት ትሩፋት አንጻር ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ይፋ ካደረጓቸው ኢንሼቲቮች ውስጥ በፍጥነት ሁሉም ቤት የደረሰ ኢንሼቲቭ የሌማት ትሩፋት ነው ብዬ አስባለሁ። አምስቱ የተመረጡ ማለትም፤ የዶሮ፣ የወተት፣ የንብ፣ የዓሳ ሥራዎች በቀላሉ አርብቶ አደሩና አርሶ አደሩ ከተማውም ሊሠራው የሚችል ነው። በእያንዳንዱ ቤት ውስጥ የገባ ኢንሼቲቭ ነው።

ለምሳሌ በዶሮ እርባታ ስንጀምር ከሁለት ዓመት በፊት የአንድ ቀን ጫጩት ስናካፍል የነበረው በዓመት 26 ሚሊዮን ነበር። በ2015 ላይ ወደ 41 ሚሊዮን ደረስን። አምና በ2016 ላይ ደግሞ ያደረግነው ሥርጭት ወደ 80 ሚሊዮን የተጠጋ ነው። ዘንድሮ ለማሰራጨት የያዝነው እቅድ ወደ 150 ሚሊዮን የአንድ ቀን ጫጩት ነው።

ኢትዮጵያ፣ ቢሻን ጉራቻ ላይ “ቅድመ ውላጅ ፕሮጀክት” የሚባለውን አቋቁማለች። ዘንድሮ ወደሥራ ይገባል። የመጀመሪያዎቹ መጥተዋል። በዚያ ጫጩት እናመርታለን። ማዕከሉ በሙሉ አቅሙን ማምረት የሚችለው ወደ አራተኛ ሩብ ዓመት ላይ ነው። ሙሉ አቅሙ ላይ ሲደርስ 110 ሚሊዮን የአንድ ቀን ጫጩት ያመርታል። ከዚህ በፊት ካሉት ጋር ተደምሮ 150 ሚሊዮን መድረስ እንችላለን ያልነው ለዚህ ነው።

እንስሳትን ከማዳቀል አንጻር ከዚህ ቀደም የተሻለ ወተት የሚሰጡና በቀን ብዙ የሚታለቡ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚደርሱ እናዳቅል ነበር ፤ ይህ እንደ ሀገር ሲታይ በጣም ትንሽ ነው። አምና ይህን አሀዝ ሁለት ሚሊዮን በላይ አድርሰናል። ዘንድሮ ወደ ሶስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን አካባቢ እንስሳት ማዳቀል ሥራ ለመሥራት እቅድ አለን።

በንብና በሌሎችም ሁኔታዎች ላይ ግቦቹ ከተጠበቀው በላይ መሔድ ችለዋል። ይህንን ከከተማው ጋር ስናስተሳስርና የሌማት ትሩፋት በብዛት በከተማ ውስጥም የሚታዩ ናቸው። ድሮ ወደ ገጠር እየተቃረብን በሄድን ቁጥር የእንቁላል ዋጋ እየረከሰ ይመጣ ነበር። አሁን እሱ በተቃራኒው ሆኗል። ይህ ማለት በከተማ በአግባቡ እየተመረተ ነው ማለት ነው።

የወተትም ምርት እንዲሁ ነው። የመንግሥት ሠራተኛውን ጨምሮ ብዙዎች በከተማ ውስጥ በማምረት ላይ ይገኛሉ። በጡረታ የተሰናበቱ የመንግሥት ሠራተኞች ይህ ሥራ ቀደም ሲል ገብቶን ቢሆን ኖሮ በሚል አሁን ከእርባታው ላይ እያገኙ ያለውን ገቢ ሲያጤኑ የሚቆጩ ሆነዋል። በተለይ የከተማ ግብርናን በጣም ከቀየረው ነገር አንዱ በሌማት ትሩፋት ላይ የተሠራው ሥራ ነው።

የከተማ ግብርና ከዚያ በላይ ነው። የሌማት ትሩፋት አንዱ ነው። የከተማ ግብርና ፍራፍሬ፣ አትክልት የከተማ ሰዎች ባላቸው አነስተኛ ቦታ ላይ ብዙ ምርትን የማምረት ሁኔታ በስፋት የተጀመረበት ሁኔታ ነው። ድሮ ከተሜው ሸማች ነበር፤ አሁን አምራችም ጭምር ሆኗል።

በአትክልትና ፍራፍሬ አካባቢ የለየናቸው ሁለት ነገሮች አሉ። ምርጥ ዘር ላይ ዋጋው የመወደድ ነገር አለ፤ እኛ በአብዛኛው የምርምር ውጤት የምናወጣው በአዝርዕትና ሰብል ላይ ነው። አሁን ግን በአትክልትና ፍራፍሬ ግብዓትን የማቅረብ ሰፊ ሥራ እንደሚጠበቅ አስተውለናል።

ከሌማት ትሩፋት ሥራ አንጻር ትልቅ ነገር እየጠየቀን ያለው የመኖ አቅርቦት ነው። በተለይ ታስረው በአንድ ቦታ የሚቀለቡ እንስሳት የተቀነባበረ መኖ ይፈልጋሉ። ይህን ችግሮች ለዘለቄታው ለመፍታት ትንንሽ የመኖ ፋብሪካዎችን በየአካባቢው ማብዛት እንደሚያስፈልግ ተምኖበት፤ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በመሆን እንቅስቃሴ ጀምረናል።

አመራረቱን በተመለከተ ገጠር ላይ ያደራጀናቸው ልክ በሰብል ላይ ኩታ ገጠም እንዳልነው በሌማት ትሩፋት የወተት መንደር፣ የእንቁላል መንደር የማር መንደር እያልን ነው። እንደዚያ የማድረጋችን ምስጢር ወደ ገበያ ለማቅረብ አመቺ እንዲሆን ነው።

ለምሳሌ እንደ ግብርና ሚኒስቴር አምና ያደረግነው ነገር ቢኖር ከወተት አንጻር ወደ ሰባት የወተት ማመላለሻ ቦቴዎችን ለክልል መስጠታችን ነው። ትርፍ የወተት ምርት ያለባቸው አካባቢዎች ላይ ተሰብስቦ ወደ ወተት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች እንዲሄድ በማድረግ ወተቱ ተፈጥሯዊ ይዘቱን እንደጠበቀ ወደ ተጠቃሚው ዘንድ እንዲደርስ አድርገናል። በዚህም የሌማት ትሩፋት ከተቀመጠለት ግብ አንጻር ሲታይ በጣም የተሳካ ሥራ እየተሠራበት ያለ ኢንሼቲቭ ነው ማለት ይቻላል።

አሁን ግብርናችን ከእጅ ወደ አፍ መባሉ ቀርቶ ወደ ኮሜርሻል እየተሻገረ ነው። ይህ ደግሞ የሚታየው በስንዴ፣ በሩዝ እንዲሁም በቢራ ገብስ ላይ ያመጣነው ለውጥና ወጪ ምርቶቻችንንም በመጨመር ያሳካናቸው ነገሮች ማሳያ ናቸው ማለት ይቻላል። ግን አሁን መድረስ በሚገባን ግብ ላይ አልደረስንም። ግብርናችንን በሙሉ ሜካናይዝ አላደረግንም። አሁንም ግብርናችን ገና ዝናብ ላይ ጥገኛ ነው።

የመስኖ አውታሮቻችንን ማዘመን እና በብዛት መገንባት አለብን። ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ግብርናን መፍጠር አለብን። የምግብ ሉዓላዊነታችንን ከማስከበር አንጻር አሁንም የሠራናቸው ሥራዎች እንዳሉ ሆነው ቀሪ የቤት ሥራዎች አሉና ይህን አጠናክረን መሥራት አለብን።

ነገር ግን እስካሁን የመጣው ለውጥ ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ያለው ባለሙያው፣ አርሶ አደሩ፣ አርብቶ አደሩ ሁሉ ድርሻ አለው። እነርሱን እያመሰገንን በቀጣይ የሚጠበቅብን የተጀመረውን ሥራ ማስፋት ነው። ያልደረስንባቸው ቦታዎች ላይ መድረስ ነው። ምርታማ የሆኑ አካባቢዎች እንዳሉ ሁሉ ገና ጅምር ላይ ያሉ አካባቢዎችም አሉ። የተገኙ መልካም ውጤቶቻችንን በመላው ሀገሪቱ ለማድረስ የሚያስችሉ ሥራዎችን እየሠራን ነው።

ሁሉም ክልሎች ተመሳሳይ አቅምና ጸጋ የላቸውም። የተለያዩ ጸጋ ያላቸው እንደመሆኑ የክልሎች የግብርና ሽግግር ፎረም ፍኖተ ካርታ እየሠራን ነው። ቤኒሻንጉል ጉምዝ ምን ላይ ቢሠራ ነው አዋጭ የሚሆነው? ምክንያቱም የእሱ አቅም የኢትዮጵያ አቅም ነው። ደቡብ ምዕራብ ላይ ምን የተለየ አቅም አለ? የሚለውን ለይተን እሱ ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሠራ ማድረግ ነው። ጋምቤላም ሆነ ሌላው ክልል የግድ ስንዴ ላይ መሥራት አይጠበቅበትም፤ የሚጠበቀው እንዳለው አቅምና ጸጋ በመጠቀም ምርታማነትን ማሳደግ ነው።

ሁሉም አቅሞች ግን የኢትዮጵያ አቅሞች ናቸው ብለን የግብርና ሽግግር ፍኖተ ካርታ ለየክልሎቻችን እየሠራን ነው። አሁን ለአምስት ክልሎች አዘጋጅተናል። የሌሎችንም በሂደት እየሠራን ነው። እሱ ደግሞ በሁሉም አካባቢ ያሉ አቅሞችን እና ጸጋዎችን አንድ ላይ ደምረን ለኢትዮጵያ ብልፅግና አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ እናደርጋለን ብለን እየሠራን እንገኛለን። ይህ ደግሞ ይሳካል የሚል እምነት አለኝ።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ ከልብ ላመሰግንዎ እወዳለሁ።

ግርማ (ዶ/ር)፡– እኔም አመሰግናለሁ።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You