ወታደራዊ ሕግ ለመደንገግ በመሞከር ምርመራ እየተደረገባቸው የሚገኙት የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንት ዩን ሱክ ዮል ከሀገር እንዳይወጡ ዕገዳ ተጣለባቸው። የደቡብ ኮሪያ አመራሮች ፕሬዚዳንቱ ከሀገሪቱ እንዳይወጡ የጉዞ ዕቀባ መጣላቸውን አስታውቀዋል።ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ክስ ሊመሠርትባቸው ከጫፍ ደርሶ ነበር። ሆኖም ግን የገዢው ፓርቲ (ፒፒፒ) አባላት የሆኑ የሀገሪቱ ምክር ቤት አባላት ፕሬዚዳንቱ እንዲከሰሱ የተሰጠውን ድምጽ አግደዋል።
ፕሬዚዳንቱ የሥልጣን ዘመናቸውን ለማገድ እና በውጭ እንዲሁም በሀገር ውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ ላለመግባት መስማማታቸውን ተከትሎ ነው እንዳይከሰሱ የተወሰነው። ተቃዋሚ ፓርቲው ‘ዴሞክራቲክ ፓርቲ’ ግን ክስ ሳይመሠረት መቅረቱን አልተቀበለውም።የፓርቲው መሪ ፓርክ ቻን-ዴ “ይህ ሕገ ወጥ፣ ሕገ መንግሥቱን የሚጻረር እና ሁለተኛ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ለአጭር ጊዜ የቆየው ወታደራዊ ሕግ መደንገጉን ተከትሎ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለተቃውሞ አደባባይ ወጥተዋል።ፕሬዚዳንቱ ከሥልጣን እንዲወገዱ እና እንዲከሰሱ ጠይቀዋል። ፕሬዚዳንቱ ባይከሰሱም ከወታደራዊ ሕጉ መደንገግ ጋር በተያያዘ ተሳትፎ ያላቸው ቁልፍ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት እርምጃ ተወስዶባቸዋል።
ወታደራዊ ሕግ እንዲደነገግ ለፕሬዚዳንቱ ሃሳብ ያቀረቡት የቀድሞው መከላከያ ሚኒስትር ኪም ዮንግ-ሁን ትናንት በቁጥጥር ሥር ውለዋል። ያለፈው ሳምንት ረቡዕ ሥልጣናቸውን ለቀው “ኃላፊነት እወስዳለሁ” ብለው ነበር። የመከላከያው ስለላ ክፍል ኮማንደር ይዎ ኢን-ሁንግ እና ኤታማዦር ሹሙ ፓርክ አን-ሱ ላይ የጉዞ ማዕቀብ ተጥሏል።
ሥልጣናቸውን ለቀው “የሕዝቡ እና የፕሬዚዳንቱን ፍላጎት ባለማስጠበቄ ኃላፊነት እወስዳለሁ” ያሉት የቀድሞው የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ሊ ሳንግ-ሚንም የጉዞ ዕቀባ ተጥሎባቸዋል። የገዢው ፓርቲ ፒፒፒ መሪ ሀን ዶንግ-ሁን፣ ፕሬዚዳንቱ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገቡ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ሀን ደክ-ሱ ኃላፊነት እንደሚረከቡ ተናግረዋል።
“ፕሬዚዳንቱ ሥልጣን ሳይለቅ በፊት ዲፕሎማሲን ጨምሮ በማንኛውም ጉዳይ ጣልቃ አይገባም” ብለዋል። የተቃዋሚ ፓርቲው ‘ዴሞክራቲክ ፓርቲ’ መሪ ፓርክ ቻን-ዴ ግን “ሁለተኛ መፈንቅለ መንግሥት” ሲሉ ነው ክስተቱን የገለጹት። የፓርቲው ተወካይ ኪም ሚን-ሱክም የገዢው ፓርቲ መሪ ውሳኔ ለማሳለፍ “ሥልጣን የለውም” ሲሉ ተችተዋል።
“ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የገዢው ፓርቲ ማንም ሥልጣን ሳይሰጣቸው የፕሬዚዳንቱን ኃላፊነት መረከባቸው ሕገ መንግሥቱን ይጻረራል” ብለዋል።ፕሬዚዳንቱ ለሀገሪቱ ብሔራዊ መከላከያ ትዕዛዝ የማስተላለፍ ሥልጣናቸው ባለበት እንደሚቆይ ተገልጿል። ይህ ማለት ከሰሜን ኮሪያ ትንኮሳ ቢኖር የመጨረሻውን ውሳኔ የሚሰጡት ፕሬዚዳንቱ ይሆናሉ ማለት ነው። በሚዮንግጂ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ሺን ዩል ለኮሪያ ሄራልድ እንዳሉት፣ ፕሬዚዳንቱ “ሃሳባቸውን ከለወጡ ወደ መሪነት መመለስ” ይችላሉ።
“ማንም ሊያስቆማቸው አይችልም” ሲሉ አስረድተዋል።ፕሬዚዳንቱ ወታደራዊ ሕግ በመደንገጋቸውና ሕዝቡ ላይ በፈጠረው “ጭንቀትና ውጣ ውረድ” በይፋ ዜጎችን ይቅርታ ጠይቀው በድጋሚ ወታደራዊ ሕግ እንደማይደነግጉ አስታውቀዋል።ተቃዋሚዎች ግን ፕሬዚዳንቱ እንዲከሰሱ ግፊት ማድረግ እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።”ለመጪው የገና በዓል እና ለአዲስ ዓመት ስጦታችን ሀገራችንን ወደነበረችበት መመለስ ነው። የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ፕሬዚዳንቱ የደቡብ ኮሪያን ምጣኔ ሀብት በማዳከሙ ሥልጣን ሊለቅ ይገባል” ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
ወታደራዊ ሕግ (ማርሻል ሎው) የሲቪል ባለሥልጣናት ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን እንደማይችሉ በሚቆጠርበት ጊዜ ወታደራዊ ባለሥልጣናት እንዲመሩ የሚደረግበት ጊዜያዊ አገዛዝ ነው። አንዲት ሀገር በወታደራዊ ሕግ ስር በምትሆንበት ወቅት የሲቪል መብቶች መታደግ እንዲሁም ወታደራዊ ሕጉ ሊራዘም የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠራል። በደቡብ ኮሪያ ለመጨረሻ ጊዜ ወታደራዊ ሕግ የታወጀው በአውሮፓውያኑ 1979 ሲሆን፤ ወቅቱም ሀገሪቱን ለበርካታ ዘመናት የገዙት አምባገነኑ ፖርከ ቹንግ ሂ በመፈንቅለ መንግሥት መገደላቸውን ተከትሎ ነው።
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 1 ቀን 2017 ዓ.ም