የ26 ዓመቱ ግለሰብ ባለፈው ሳምንት ዩናይትድ ሄልዝኬር የተባለው ኩባንያ ኃላፊን ገድሎ በማምለጥ የወንጀል ክስ ቀርቦበታል። ሉዊጂ ማንጂዮኒ ከኒውዮርክ ከተማ 450 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው አልቱና ከተማ ማክዶናልድስ የተባለ ምግብ መሸጫ እየተመገበ ሳለ ነው አንድ ሰው ጠቁሞ ያስያዘው።
ሉዊጂ በቁጥጥር ሥር ሲውል በ3ዲ ማሺን የተሠራ ሽጉጥ እና በእጅ የተፃፈ ለተጠረጠረበት ወንጀል “መነሻ ሊሆን ይችላል” የተባለ ፅሑፍ መያዙን ፖሊስ አስታውቋል። ወጣቱ ፔንሲልቬኒያ የሚገኘው ፍርድ ቤት ቀርቦ አምስት ክሶች የቀረቡበት ሲሆን፤ በዋስ እንዲለቀቅ ጠይቆ ውድቅ ተደርጎበታል። ከሰዓታት በኋላ ደግሞ የኒውዮርክ መርማሪዎች ሉዊጂ ማንጂዮኒን በግድያ እና የጦር መሣሪያ በመያዝ እንዲሁ በሌሎች ሶስት ወንጀሎች ከሰውታል።
የዩናይትድ ሄልዝኬር ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት የ50 ዓመቱ ብራያን ቶምፕሰን ባለፈው ረቡዕ ጠዋት ነው ኒው ዮርክ በሚገኘው ሒልተን ሆቴል አቅራቢያ እየተራመዱ ሳለ ጀርባቸው ላይ በጥይት ተመትተው የተገደሉት።ቶምፕሰን በሥፍራው የተገኙት ግዙፉ የጤና ኢንሹራንስ የሆነው ኩባንያቸው ከኢንቨስተሮች ጋር ለሚያደርገው ስብሰባ ነበር።ፖሊስ እንደሚለው ኃላፊው በተጠና መንገድ ነው የተገደሉት።
ተጠርጣሪው ግድያውን ፈፅሞ ካመለጠ በኋላ የኒው ዮርክ ከተማ ፖሊስ በቴክኖሎጂ በታገዘ መንገድ በድሮን እንዲሁም በፖሊስ ውሻዎች እና በጠላቂዎች አማካይነት ፍለጋ ሲያደርግ ነበር። ሉዊጂ ማንጂዮኒ ፔንሲልቬኒያ እስር ቤት የሚገኝ ሲሆን ያልተመዘገበ የጦር መሣሪያ በመያዝ፣ በማታለል እና ለፖሊስ ሐሰተኛ መታወቂያ በማሳየት ተከሷል።
ሰኞ ዕለት ፍርድ ቤት ሲቀርብ እጁና እግሩ በካቴና ተጠፍሮ ነበር። ጂንስ ሱሪ እና ጥቁር ሰማያዊ ቲሸርት አድርጎ ፍርድ ቤት የቀረበው ተጠርጣሪው ረጋ ያለ ሲሆን አልፎ አልፎ ማን እንደተገኘ ለማየት ዞር እያለ ሲቃኝ ተስተውሏል። ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር ሲውል ቦርሳው ውስጥ 10 ሺህ ዶላር በጥሬ ገንዘብ ይዞ እንደነበር ከዚህም ውስጥ ሁለት ሺህ የሚሆነው የሌላ ሀገር ገንዘብ እንደሆነ ፖሊስ ቢናገርም ተጠርጣሪው ይህን አልቀበልም ብሏል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 2 ቀን 2017 ዓ.ም