የጣሊያን ፖሊስ በወንጀለኛ ቡድን ላይ ከሚያደርገው ምርመራ ጋር በተያያዘ 24 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ያዋለ ሲሆን፣ ከታሰሩት መካከል አንዲት መነኩሴ እንደሚገኙበት ተገለጸ። በሰሜን ጣሊያን ከሚደረገው የወንጀለኛ ቡድን (ማፊያ) ምርመራ ጋር በተያያዘ የታሰሩት መነኩሴ አና ዶኔሊ ይባላሉ።
ንዴራንጌህታ የተባለው የማፊያ ቡድን አባላት ሲታሰሩ ለቡድኑ አባላት መልዕክት የሚያስተላልፉት እኚህ መነኩሴ እንደሆኑ ፖሊስ ያምናል። ከዚሁ ዘመቻ ጋር በተያያዘ ፖሊስ ሁለት ፖለቲከኞችንም አስሯል። በተጨማሪም በሎምባርዲ፣ በቬኒቶ እና ካላብራ ከተሞች ከአንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ዩሮ በላይ የሚያወጣ ሃብት ንብረት በቁጥጥር ሥር አውሏል።
ማፊያ የተባለው የወንጀለኛ ቡድኑ በአውሮፓ አደገኛ ከሚባሉ ቡድኖች አንደኛው ሲሆን፣ ፖሊስ ለአራት ዓመታት ምርመራ ሲያደርግ ቆይቷል። ምርመራውን ያካሄዱት የፖሊስ ባልደረቦች ባወጡት መግለጫ እንዳሉት፣ መነኩሴዋ እስር ቤት በነፃነት የመግባት እና የመውጣት መብታቸውን ተጠቅመው በወንጀለኛ ቡድኑ አባላት መካከል መረጃ ሲያቀባብሉ ነበር።
“ማንም እሷን አይጠረጥርም። በሃይማኖት ምክንያት ወደ እስር ቤቱ በነፃነት መግባት እና መውጣት ትችል ነበር” ሲል መርማሪ ቡድኑ አስታውቋል። ከምርመራው በኋላ የታሰሩ ፖለቲከኞችን ማንነት እንዲሁም ከወንጀል ቡድኑ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል የተመረመሩትን ማንነት ይፋ አላደረገም። ፖሊስ አሁንም በሰሜን ጣሊያን ፍተሻ እያደረገ ይገኛል።
በአነፍናፊ ውሾች በመታገዝ መሣሪያ፣ አደንዛዥ ዕፅ እና ገንዘብ እየተፈለገ ነው። የወንጀል ቡድኑ ቁርጥራጭ ብረት በመሸጥ ስም ሕገ ወጥ ገንዘብን ወደ ሕጋዊ መስመር ያስገባ እንደነበር ፖሊስ አስታውቋል። የወንጀል ቡድኑ መነሻ ካላብሪያ ከተማ ስትሆን ከአውሮፓ ባሻገር በዓለም አደገኛ ከሚባሉ ቡድኖች መካከል አንደኛው ነው።
ያለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት ላይ በጣሊያን ታሪክ ትልቁ በተባለ በማፊያ የወንጀለኛ ቡድን አባላት ላይ በተካሄደ የፍርድ ሂደት ላይ 200 ሰዎች ከሁለት ሺህ 200 ዓመታት በላይ እስር ተፈርዶባቸዋል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም