መርከቦች በስዊዝ ቦይ በኩል ለማለፍ የሚወስድባቸውን ጊዜ እስከ 15 ቀናት ማሳጠር ይችላል ተብሏል፡፡ ፕሮጀክቱ በአገልግሎቱ የግብጹን ስዊዝ ቦይ ይቀናቀናል የተባለ ግዙፍ መንገድ ፕሮጀክት ወደ ተግባር ለመግባት የእቅድ ስራው በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።
17 ቢሊዮን ዶላር ያወጣል የተባለው ሜጋ ፕሮጀክት ከ1198 ኪሎ ሜትር በላይ እርዝማኔ እንደሚኖረው ተነግሮለታል። ምዕራብ እስያ እና አውሮፓን በማገናኘት ያልተቆራረጠ የምርት ዝውውር ያሳልጣል የተባለ ሲሆን፤ ሁለቱ አህጉሮች ምርት ለመለዋወጥ በስዊዝ ቦይ ላይ ያላቸውን ጥገኝነት እንደሚቀንስ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
የመንገድ ግንባታው መነሻውን ከቱርክ ሰሜናዊው ድንበር አድርጎ እስከ ደቡባዊ የፋርስ ባህረ ሰላጤ ድረስ ይዘረጋል። የመንገድ ፣ የባቡር ሀዲድ ፣ የወደብ እና የከተማ መንገዶችን ከሀገር አቋራጭ መንገዶች ጋር ማገናኘትን ያቀፈው ይህ ሜጋ ፕሮጀክት በእስያ እና በአውሮፓ መካከል ያለውን የጉዞ ጊዜ ለመቀነስ ያለመ ነው፡፡
በሁለቱ አህጉራት መካከል ለሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ወሳኝ የንግድ መስመር ለሆነው የግብጹ ስዊዝ ቦይ ተፎካካሪ የመሆን እድሉም ከፍተኛ መሆኑ ተመላክቷል። ቱርክ ላይ የንግድ ኮሪደር ከዘረጋ በኋላ የኢራቅን ዓለም አቀፍ ተሰሚነት እንዲሁም የሀገር ውስጥ ኢኮኖሚዋን እና መሠረተ ልማትን ያጠናክራል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ ሺዓ አልሱዳኒ ፕሮጀክቱ በዘላቂነት ከነዳጅ ጥገኝነት የተላቀቀ ኢኮኖሚን ለመገንባት የማዕዘን ድንጋይ ነው ያሉ ሲሆን፤ ኢራቅንና አካባቢውን የሚጠቅም ለቀጣናዊ ትስስር እና ለኢኮኖሚ ውህደት የሚኖረውም ድርሻ ከፍተኛ ስለመሆኑ አንስተዋል::
የኢራቁ “የግራንድ ፎው ፖርት” በዚህ መንገድ የሚተላለፉ ምርቶችን ጭነው የሚመጡ መርከቦችን ለማስተናገድ ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡ እንደ ሀገሪቱ የትራንስፖርት ሚኒስትር መረጃ ከሆነ ይህ ወደብ እስከ 19 ነጥብ 5 ሜትር ጥልቀት ያላቸው ትላልቅ የንግድ መርከቦችን ማስተናገድ ይችላል። ከግብጹ ስዊዝ ካናል ጋር ሲነፃፀርም በጉዞ ጊዜ ከ12 እስከ 15 ቀናት መቆጠብ እንደሚችልም ተሰምቷል፡፡
ሚኒስትሩ ራዛቅ ሙሂቢስ አልሳዳዊ “በዚህ ፕሮጀክት ኢራቅ እና ቱርክ የጂኦፖለቲካዊ ጠቀሜታ ያገኛሉ፤ ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ከፖለቲካ የጸዳ ኢኮኖሚ ላይ ያተኮረ ብቻ ይሆናል” ብለዋል፡፡ በሶስት አመት ለማጠናቀቅ እቅድ የተያዘለት ሜጋ ፕሮጀክት በበርካታ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሀገራት ድጋፍ ያገኘ ሲሆን፤ አረብ ኤሚሬትስ እና የኳታር መንግሥታት ባለፈው ክረምት በፕሮጀክቱ የጋራ ልማት ዙሪያ ስምምነት መፈረማቸው አል ዐይን ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 2 ቀን 2017 ዓ.ም