በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት ጥራት ወሳኝ ጉዳይ ነው። ለዚህም ዓለም የደረሰባቸውን የጥራት መስፈርቶች እና የጥራት መለኪያ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ ማድረግ፣ ወቅቱ የሚጠይቀውን የተቀባዩም ሆነ የላኪውን ሀገር የጥራት ደረጃ ማሟላት ያስፈልጋል።
በዚህ ሂደትም የምርቶችና አገልግሎቶች የጥራት ደረጃ ብቻ አይደለም መፈተሽ ያለበት፤ የጥራት መለኪያ ላቦራቶሪዎችና መሳሪያዎች በየጊዜው በትክክል ስለመሥራታቸው መፈተሽ እንዳለባቸውም የዘርፉ ባለሙያዎች ምክረ ሃሳባቸውን ይሰጣሉ።
ኢትዮጵያም በቅርቡ ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ መሳሪያዎችን ያሟላ የጥራት መንደር አስመርቃለች። ሀገሪቱ መንደሩ በተመረቀበት ማግስት ባሳለፍነው ሳምንት “የጥራት መስፈርቶችን ከማሟላት ወደ ላቀ የአፈፃፀም ብቃት!” በሚል መሪ ቃል የዓለም የጥራት ቀንንም አክብራለች።
የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መዓዛ አበራ እንደገለፁት፤ የዘንድሮው የዓለም የጥራት ቀን መሪ ቃል ፅንሰ-ሃሳብ በዓለም ዙሪያ ላሉ አምራቾች እና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች የደረጃ መሥፈርቶችን ከማሟላት አልፈው ወደ ላቀ የአፈጻጸም ብቃት የመሻገርን አስፈላጊነት ማስገንዘብ ነው።
በኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ውስጥ ዘጠኝ የተደራጁ የፍተሻ ላቦራቶሪዎች አሉ። በእነኚህ ላቦራቶሪዎች የግብርና ምርቶችና ግብዓቶች፣ ምግቦች፣ መጠጦች፣ ማዕድናት፣ ኬሚካሎች፣ ኤሌክትሮኒክስ እቃዎች፣ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች፣ ጨርቃጨርቆችን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶች በእነዚህ የፍተሻ ላቦራቶሪዎች ጥራታቸው እንዲረጋገጥ ይደረጋል።
ይህ ሥራ የሀገር ውስጥ ገበያውንም ይሁን ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ጥራት ከማረጋገጥ አኳያ ወሳኝነት አለው። በዚህ ዘመን ጥራት ሳይረጋገጥ ምርቶችን ለዓለም ገበያ ማቅረብ አይቻልም። የህብረተሰቡን ጤንነትና ደህንነት ለማስጠበቅም የምርቶችን ጥራት ማረጋገጥ ያስፈልጋል። መንግሥትም ለዚህ ሁሉ ትኩረት ሰጥቶ እነዚህን የፍተሻ ላቦራቶሪዎች በማደራጀት የጥራት መንደር ውስጥ ተገንብቷል። በዚህም ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ጥራት የማረጋገጥ ሥራ ይሠራል። ይህም በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን የጎላ ድርሻ አለው።
ድርጅቱ ከውጭ ሀገር የሚገቡ ምርቶችን ናሙና ከሌሎች ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቶች ጋር በመውሰድ ባሉት ላቦራቶሪዎቹ የፍተሻ ሥራ ይሠራል። በመቀጠልም ምርቶቹ ወደተለያዩ አካባቢዎች ይሰራጫሉ። በዚህም ሂደት ገለልተኛ የሆነ የሶስተኛ ወገን አገልግሎት እንደሚሰጥ ጠቁመው፣ የምርቶችን ጥራት ከመቆጣጠር አንፃር ከመንግሥት ሥልጣን የተሰጣቸው መሥሪያ ቤቶች እንዳሉም አመልክተዋል።
ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡት ምርቶች የኢትዮጵያን ደረጃዎች መስፈርት ማሟላታቸውን በማረጋገጥ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ እንደሚደረግ ገልጸው፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችም ጥራት በእነዚህ ላቦራቶሪዎች እንደሚረጋገጥ አስታውቀዋል። ምርቶች በሚላክባቸው ሀገራት ደረጃዎችንም መስፈርቶች ማሟላታቸው በላቦራቶሪ ተፈትሾ የማረጋገጥ ሥራ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ኢንጂነር መአዛ እንዳመላከቱት ኢትዮጵያም የምርት ጥራትን ለማስጠበቅና ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችላትን ከአፍሪካ ቀዳሚ የጥራት ማዕከል የሚያደርጋትን የጥራት መሠረተ ልማት ገንብታለች። የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅትም ምርቶች ከሀገር ውስጥ አልፈው በዓለም አቀፉ ገበያ ተወዳዳሪ እና ተመራጭ እንዲሆኑ ለማድረግ አገልግሎት የመስጠት አቅሙን እያሳደገ ይገኛል።
በተስማሚነት ምዘና የአሠራር ሥርዓት ውስጥ ማለፍ ውጤቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማምጣት ለሚደረገው ጥረት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወትም አስታውቀዋል። አምራቾችና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በመጠቀም ጥራት ያለው ምርትና አገልግሎት እንዲያቀርቡ ጥሪ አድርገዋል።
ድርጅቶቹ መሠረታዊ የጥራት ደረጃን ከማሟላት አልፈው ወደ ላቀ የአፈፃፀም ብቃት ለመሸጋገር በሚያደርጉት ጥረት የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ተቀናጅቶ ለመሥራት ከምንጊዜውም በላይ ያለውን ቁርጠኝነትም አረጋግጠዋል። በምርትና አገልግሎቶች ጥራት ላይ ተግባራዊ የሚሆኑ ውሳኔዎች ለተሻለ ነገ ያላቸው አስተዋጽኦ የላቀ ነው ሲሉም አስታውቀዋል፡፡ አምራቾችና የድርጅቶች ባለቤቶችም በጥራት ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ እና ምርጥ ተሞክሮዎችን ለማስፋት የሚደረገው ንቅናቄ አካል በመሆን የጥራት አምባሳደር እንዲሆኑ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እንዳለው መኮንን እንዳስታወቁት፤ መንግሥት ለጥራት መንደሩ ግንባታ ከስምንት ነጥብ ሁለት ቢሊየን ብር በላይ ወጪ አድርጓል። ይህም መንግሥት ለወጪና ገቢ ምርቱ ጥራት መጠበቅ የሰጠውን ትኩረትና በዘርፉ ለውጥ እንዲመጣ ያለውን ከፍተኛ ቁርጠኝነት እና ተነሳሽነት ያመላክታል።
ጥራት በጣም መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፣ የወጪም ሆኑ የገቢ ምርቶች የላኪውን እንዲሁም የተቀባዩን ሀገር የጥራት ደረጃዎች መስፈርት በማሟላት ተወዳዳሪነትን አስጠብቀው ማለፍ አለባቸው።
አቶ እንዳለው እንዳብራሩት፤ ላኪ ሀገራት ደረጃ እንዳላቸው ሁሉ ተቀባይ ሀገራትም የሚፈልጉት መስፈርት አላቸው። ምርትና አገልግሎትን ለመላክም ሆነ ለመቀበል ያንን ደረጃ ማሟላት ያስፈልጋል። ደረጃው መኖሩ ብቻ በቂ አይደለም። በደረጃው መሠረት መረጋገጥ አለበት። ልክ ሰዎች ወደ ውጭ ሀገር ሲሄዱ ቪዛ እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ በኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት በወጣ ደረጃ መሠረት ድርጅቱ በትክክል ምርቱ የተቀመጠለትን መሥፈርት አሟልቷል? የገዢውን ፍላጎትስ አሟልቷል? በተቀባይ ሀገር የተቀመጠለትን መስፈርትስ አሟልቷል? ብሎ ማረጋገጫ ማህተም ሲያሳርፍበት ያ ምርት ያለማንም ጠያቂ የታለመለት የገበያ መዳረሻ ገብቶ መሸጥ ይችላል ማለት ነው ሲሉ አብራርተዋል።
እነዚህ ተቋማት አምስቱም እርስበርሳቸው የሚናበቡ፣ የሚተሳሰሩ፣ የሚደጋገፉ ዓይነት ተቋማት ናቸው ሲሉ አስታውቀው፣ አንደኛው የቴክኖሎጂ ባለሥልጣን ለየት ያለ ነው ብለዋል። ተጠሪነቱም ለኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ ይህ ተቋም አጠቃላይ ቴክኖሎጂዎች ላይ ቁጥጥር የሚያደርግ ሲሆን፣ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ጨምሮ ቀደም ሲል የጨረራ ባለሥልጣን ይባል ነበር፤ አሁን ያለንበትን ዘመን አጠቃላይ ቴክኖሎጂ የምንጠቀምበት፣ የምንፈጥርበት ወቅት ነው። ቴክኖሎጂ ላይ ጥቅም እንዳለ ሁሉ ጉዳትም ያለ በመሆኑ ቴክኖሎጂን በሚመለከት የሚሠራ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት አንዱ ነው።
አራቱ የጥራት መሠረተ ልማት ተቋማት እርስበርሳቸው የሚደጋገፉ የሚናበቡ ናቸው። የኢትዮጵያ የሥነ ልክ ኢንስቲትዩት የሚባለው በተስማሚነት ምዘና ውስጥ ያሉ መሳሪያዎችን ብቻ ሳይሆን በኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉ ማንኛቸውንም በላቦራቶሪ ውስጥ ያሉ መሳሪያዎችን ትክክለኛነት ማረጋገጥ፣ በትክክል ጥራትን እየለኩ ነው ወይ የሚለውን መፈተሽ ላይ ይሠራል። በህክምና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ የምንጠቀምባቸው ማንኛቸውም መለኪያ የሚባሉ በላቦራቶሪ ውስጥ ያሉ መሳሪያዎች፣ ዶክተሮች በቀጥታ በእጃቸው ይዘው የሚሰሩባቸው መሳሪያዎች፣ የሙቀት እንዲሁም የክብደት መለኪያዎች፣ በላቦራቶሪ ናሙና ተወስደው ፍተሻ የሚደረግባቸው በዚያ ውጤት ላይ ተመስርቶ ደግሞ ዶክተር ይወስንባቸዋል። እነዚህ መሳሪያዎች ሁሉ ትክክለኛነታቸው የሚረጋገጠው በዚህ ተቋም ባለው አቅም ነው።
በእነዚህ ተቋማት ደግሞ ሰርተፊኬት የሚሰጠው አካል፣ የኢንስፔክሽን ሥራ የሚሠራ፣ ካሊብሬሽን የሚሠራውም አካል ብቃት በሰው ኃይልም በአደረጃጀትም ባለው የመሳሪያ አሠራር ተፈትሾ እውቅና ወይንም ምስክርነት የሚሰጠው የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ነው።
አራቱ ተቋማት ተናበው የሚሠሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል። አቅማቸውም ከምንጊዜውም በላይ በልዩ ሁኔታ ተገንብቷል። ህንፃ መገንባት አንድ ነገር ሲሆን፣ በመሳሪያ ደረጃ ያለው አቅርቦት ሀገሪቱን ከአፍሪካ ቀዳሚ ያደርጋታል። ከሁለት ነጥብ አንድ ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪም ዘመናዊ የፍተሻ መሳሪያ ተሟልቶላቸዋል።
እንደ አቶ እንዳለው ማብራሪያ፤ ለኢንዱስትሪ ገብዓት የሚሆኑ እና በቀጥታ ጥቅም ላይ የሚውሉ የግብርና ምርቶች በበርካታ ሀገራት ዘንድ ተፈላጊነት አላቸው። የሀገሮች የግብርና ምርቶችን የመጠቀም ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል፡፡ ለዚህም ሲባል መስፈርቶችን የማጥበቅ ሁኔታዎች ያስፈልጋሉ። እዚህ የተፈጠረው አቅም ያንን መስፈርት ለማሟላት ያስችላል። የግብርና ምርቶች በተቀባይ ሀገራት የተቀመጡ መስፈርቶችን እንዲያሟሉ ትልቅ አቅም ተገንብቷል።
በተመሳሳይ በጨርቃ ጨርቅ፣ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ በኤሌክትሪክ፣ በኤሌክትሮ ሜካኒካል፣ በባዮኬሚካል፣ ወዘተ አቅሙ በሚፈለገው ዓይነት ተሟልቷል። ከዚህ በፊት የማንፈትሻቸው እስከ ዶፒንግ ድረስ ያሉትን ሁሉ መፈተሽ የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል፤ ምግብ ነው ወይስ ጀኔቲካል ማሻሻያዎች ያሉበት ወይስ ኦርጋኒክ ነው የሚለውን ለማወቅ የሚያስችሉ መሳሪያዎች ተገጥመውለታል።
በጤናው ቱሪዝም ላይ መንግሥት በልዩ ሁኔታ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ወደ አምስት በሚሆኑ ሆስፒታሎች የጨረራ አገልግሎት የካንሰር ህክምና እንደሚሰጥ ጠቅሰው፣ አሁን በትክክል የሚሰጠው የጨረር ህክምና መሳሪያ በየጊዜው ስለመሥራቱ ካሊብሬት ይደረጋል ወይ የሚለውን ለማወቅ የሚያስችል አቅምም ተገንብቷል ብለዋል። በግብርናው፣ በማዕድኑ፣ በኢንዱስትሪው ዘርፎች፣ ሁሉንም ዘርፍ ሊደግፍ በሚችል መልኩ ሀገራዊ ተቋማት ያሉበትና ትልቅ አቅም የተገነባበት ነው ሲሉም አብራርተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው እንዳስታወቁት፤ ተወዳዳሪ ለመሆን እና የዓለም ገበያን ሰብሮ ለመግባት የሚያስችለው ዋጋ ወይም ጥራት ነው። በመሆኑም በዋጋ ተወዳዳሪ ለመሆን የተሻለ ቴክኖሎጂ አምርቶ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እና ተጠቃሚው በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት እንዲችል ማድረግ ይገባል።
ጥራት ካለ ግን በየትኛውም የገበያ መዳረሻ /አንዳንድ ሀገራት ታሪፋቸውን 80 እና 100 በመቶ ማሳደጋቸውን ቢገልፁ እንኳ/ ለመግባት የሚከለክል ነገር አይኖርም። የተሻለ ጥራት ይዞ መቅረብ ትልቁ የሚባለውን ዋጋ በውድድር ማግኘት ያስችላል።
ጥራት ከምንጊዜውም በላይ መወዳደሪያ መስፈርት መሆኑን በማመን፣ ለሀገር ውስጥ አምራቾችም ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችም ጥራት ወሳኝ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አስገንዝበዋል። የመወዳደሪያው መስፈርት ጥራት መሆኑን አውቆ ለመሥራት መንግሥትም በከፍተኛ ቁርጠኝነት ኢንቨስት አድርጎ ሲሰራ ተቋማትም አቅማቸውን በመገንባት ለሌሎች ምሳሌ በሚሆን መልኩ በዓለም አቀፍ ገበያውም ተወዳዳሪ በመሆን የሀገራችንን ኢኮኖሚ ማሳደግ እንዲችሉ ያግዛል ብለዋል።
አቶ እንዳለ የሀገሪቱ ወጪና ገቢ ምርት ያልተመጣጠነ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለምሳሌ ዘንድሮ እስከ አምስት ቢሊየን ዶላር የውጪ ምንዛሪ እናገኛለን ብንልም እስከ 18 ቢሊየን ደግሞ ከውጭ እናስገባለን ሲሉ በመግለጽ ልዩነቱን አመልክተዋል፡፡
የወጪና ገቢ ሚዛኑን ለማስተካከል የግድ ወደ ምርቶችንና አገልግሎቶችን ወደ ውጭ መላክ ያስፈልጋል ያሉት አቶ እንዳለው፣ ወደ ውጭ ለመላክ ደግሞ ኢትዮጵያ በቅርቡ ወደ ሥራ ያስገባችው ዓይነት የጥራት መሠረተ ልማት ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል።
ከተቋማት የሚቀርቡ የጥራት ማረጋገጥ ቅሬታዎችን በተመለከተ ሲያብራሩም የተስማሚነት ምዘና አካላት የሚያወጧቸው የምዘና ውጤቶች ከሌሎች ሀገራት ላቦራቶሪዎች ጋር እንደሚመሳከርም ተናግረዋል፡፡ ‹‹አንድ ናሙና ለብዙ ላቦራቶሪዎች ተሰጥቶ ይፈተሻል። ለምሳሌ ጀርመን ወይም ፈረንሳይና ከመሳሰሉት ሀገሮች ላቦራቶሪ የመጣው ውጤት ታይቶ በተቀመጠው ደረጃ ውስጥ ከሆነ የሀገሪቷ ብቃትም ተመስክሯል ማለት ነው ብለዋል። ደንበኛው መሳሪያዎቹ ላይ የፍተሻ አሠራሩን፣ ናሙናውን እያየ ፍተሻ ላይ ምስክር የሚሆንበት እና የቅሬታ ማቅረቢያ አሠራር ሥርዓት መኖሩንም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዛሬ ዘጠኝ ዓመት አካባቢ በግቢው ውስጥ ቀድሞ የጥራትና ደረጃዎች ባለሥልጣን የሚባለው ተቋም በነበረበት ወቅት ግቢውን በተደጋጋሚ መጎብኘታቸውን በቅርቡ መግለጻቸውን አቶ አንዳለው አስታውሰው፣ ግቢው እርጅና የተጫናቸው ላቦራቶሪዎች፣ ዘመኑን የሚመጥኑ አዳዲስ መሳሪያዎችን ማስተናገድ የማይችሉ ህንጻዎች የነበሩበት መሆኑን ማስታወሳቸውን ተናግረዋል። ወቅቱን የሚዋጅ የሚቀጥሉትን 50 እና 100 ዓመታት ታሳቢ ያደረገ፣ ኢትዮጵያን የሚመጥን ተቋም መገንባት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት በተከናወነ ተግባር መንደሩ መመስረቱን መናገራቸውን አመልክተዋል፡፡
በዚህ ታላቅ ሀገራዊ ሥራም ህንፃዎች ተገንብተዋል፣ መሳሪያዎች ተደራጅተዋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰው፣ በቀጣይም የአነስተኛና መካከለኛ ማምረቻ ኢንዱስትሪዎችን በሚገባ በመደገፍ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረግ ላይ እንደሚሰራ አመላክተዋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 2 ቀን 2017 ዓ.ም