ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ ለምን እንፈራለን?

በብዙዎች ላይ የሚስተዋል ልማድ እየሆነ ነው። ‹‹አሞኛል!›› ብለው ተኝተው ‹‹ሐኪም ቤት ሂድ/ሂጂ›› ሲባሉ ‹‹ቆይ እስኪ›› እያሉ በራሱ ጊዜ እስከሚለቅቃቸው መጠበቅ። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሁለት ይመስለኛል። በአሁኑ ጊዜ ‹‹ዋናው ምክንያት የትኛው ነው?›› የሚለው ግን እንደየሰው ወይም ግለሰቦች ልማድና ግለሰባዊ ባህሪ ይወሰናል።

እንደ እኔ ግን አንደኛው ምክንያት፤ ለረጅም ዘመን ከኖረው ልማድ አለመላቀቅ ነው። በተለይም በገጠሩ ክፍል ህክምና ከመሄድ ይልቅ በራሱ ጊዜ እስከሚለቅቃቸው መጠበቅ ለዘመናት የኖረ ልማድ ነው። በጣም የከፋ ካልሆነ በስተቀር ‹‹እስኪ ሐኪም ላማክር›› ብሎ የመሄድ ልማድ የለም። ከዚህ ይልቅ ባህላዊ በሆነው መንገድ ሕመሙን ለማከምና ለመዳን ይሞከራል።

ሁለተኛው ምክንያት ግን፣ በህክምና ተቋማቱ ውስጥ ያለው መጉላላት ነው። ሰዎች ይሄን ጉዳይ ለማስረዳት ሲሞክሩም የታመመ ሰው ለማሳከም፤ ‹‹ጤነኛ ሆኖ የሄደ ሰው ታሞ ይመለሳል›› እያሉ ብሶታቸውን ሲገልጹ ይደመጣል። ይሄ ማለት ደግሞ ቀለል ያለ ህመም የታመመ ሰው ቢሄድ፤ ምናልባትም በተቋማቱ ከሚያገኘው አገልግሎትና መስተንግዶ አኳያ ችግሩ ተባብሶበት ሊመለስ ይችላል ማለት ነው።

ያም ሆኖ ግን እነዚህ ምክንያቶች የስንፍና መገለጫዎች ከመሆን የዘለሉ አይደሉም። ምክንያቱም ምንም እንኳን የሕክምና ተቋሞቻችን አስፈላጊውን አገልግሎት ሁሉ በቅልጥፍና ይሰጣሉ ባይባልም፤ ይህን በመፍራትና ምክንያት በመደርደር ለህክምና አለመሄድ በራሱ ራስን መጉዳት ነው። ከባሰብን በኋላ ወደዛው መሄዳችን ላይቀር፤ መዘግየቱ ነገርየውን ከሕክምናው አቅም በላይ ማድረግ፤ የመፈወስ እድልንም ማመናመን ነው።

የሕክምና ባለሙያዎችም በተደጋጋሚ የሚያስደምጡት ‹‹ህመም እስከሚጠነክርባችሁ ድረስ አትቆዩ›› የሚለው መልዕክትም ለዚሁ ነው። ይሄውም ህመሙ ገና ሲጀማምር ካልታየ ከሀገራችን የሕክምና አቅም በላይ ሊሆን ይችላል፤ ይሄ ሲሆን ደግሞ የገንዘብም የሕይወትም ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል ማለት ነው።

በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን አንድ የምንታዘበው ነገር አለ። የምርም የሕክምና ተቋማት ውስጥ ያለው መጉላላት የሚያማርር እና ገና ሲያስቡት የሚያደክም ነው። የተማሩ የሚባሉት ሳይቀር ህመሙ በራሱ ጊዜ ይሻለኝ ይሆናል ብለው የሚዘናጉት የሕክምና ተቋማቱ በተለይም በመንግሥት በሚባሉት (ሁሉም ባይባልም) ውስጥ ያለውን ውጣ ውረድ በመፍራት ነው።

ይሄ ለመሆኑ በርካታ ምክንያቶች ሊኖሩት ይችላሉ። ለምሳሌ፣ የመንግሥት የሕክምና ተቋማት ሀገራዊና ሕዝባዊ ኃላፊነት ስላለባቸው በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው። በዚህም ምክንያት ብዙ ዜጋ ያስተናግዳሉ። አሰልቺ ወረፋ እና ውስብስብ ውጣ ውረድ ይኖራቸው ዘንድ ሁኔታው ያስገድዳል። ምክንያቱም ከመላው ሀገሪቱ ‹‹ሪፈር›› ተብሎ የሚመጣውን ሁሉ የሚያስተናግዱ ናቸው።

በዚህም ከሳምንት ሳምንት፣ ከዕለት ዕለት (7/24) በዚያ ሁሉ ወከባ ውስጥ መሥራት የሕክምና ተቋሙን ሠራተኞች ነጭናጫ እና ቁጡ ሊያደርጋቸው ይችላል። በአንጻራዊነት የግል የጤና ተቋማት ፈጣን አገልግሎት አላቸው ቢባልም፤ የሚያስከፍሉት የገንዘብ መጠን ግን የሀገራቸውን ሕዝብ ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ አይደለም።

ያም ሆኖ ግን አንድ በግልጽ መነገር ያለበት ችግር አለ። ለቦታው የማይመጥኑ፣ የተሰጣቸው የሥራ ድርሻ ከአቅማቸው በላይ የሆነባቸው፤ ለሥራ ዕድል ሲሉ ብቻ የማይገባቸውን የሥራ መደብ ይዘው ደንበኛ የሚያጉላሉ ሠራተኞች መኖራቸው አንዱ ምክንያት ነው። በተመሳሳይ ዘርፉ ከሚፈልገው ለውጥና ቴክኖሎጂ ጋር የተራራቁ ሠራተኞችና ባለሙያዎችም አሉ። እነዚህና መሰል ጉዳዮች ደግሞ በዘርፉ አገልግሎት ላይ የሚኖራቸው ጫና ከፍ ያለ እንደመሆኑ፤ የጤና ዘርፉ አስተዳደሮች ጉዳዩን በልኩ ተገንዝበው ሊፈቱ፤ ተገቢው ሰው በተገቢው ቦታ እንዲሰራ ሊያደርጉ ይገባል።

አንድ በራሴው ያጋጠመኝን ገጠመኝ ለማሳያነት ልጠቀም። ከሳምንታት በፊት አንድ ጓደኛዬ ድንገተኛ ህመም ታሞ በአንድ ታዋቂ የሀገራችን ሆስፒታል ገባን። ይህ ጓደኛዬ በሐኪሞች ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት ህክምናውን አገኘ። በዚህ አጋጣሚ በሐኪሞች የሕክምና ብቻ ሳይሆን የስነ ልቦናም ጥበብ ተደንቄያለሁ። ከፈጣሪ ቀጥሎ የሰው ልጅ መተማመኛ የሆኑትን የሐኪሞችን ውለታ ራሱን በቻለ ጽሑፍ እመለስበታለሁ።

ወደማሳያዬ ስመለስ፣ ሕክምናውን ጨርሰን ለመውጣት የሚሞሉ ቅጾች አሉ። ከምንሄድባቸው መስኮቶች አንደኛው ላይ ለረጅም ሰዓት አቆዩን። ጉዳዩ ማህተም መምታት እና ሲስተም ላይ ስም ማስተላለፍ ነው። እኔና ሌላ ጓደኛችን ጉዳዩን የሚከውኑት ሴት እስከሚጨርሱ ድረስ መስኮት ላይ ቆመናል። ከእኛ ቀጥሎ ወረፋ የያዘ አንድ ጎልማሳ ሰውዬ በተደጋጋሚ ‹‹ጉድ!›› እያለ ይገረማል። ሰውዬውን ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ውጭ ሀገር ቆይቶ የመጣ ይመስላል። ‹‹እንዴት ማህተም ማድረግና ስም ማስተላለፍ ይሄን ያህል ያቆያል?›› እያለ እየደጋገመ ይገረማል። እኔና ጓደኛዬ የሀገራችንን ሁኔታ ስለምናውቅ ብዙም ሳንገረም ታግሰን ቆመናል።

ሴትዮዋ አንድ ጊዜ ወደ ወረቀቱ፣ አንድ ጊዜ ወደ ኮምፒውተሩ እያዩ ለረጅም ደቂቃዎች ቆዩበት። ያላሟላነው የጎደለ ነገር ይኖር ይሆናል ብለን ብንጠብቅም የሚነግሩን የጎደለ ነገር የለም። እሳቸው ግን እንደ አንዳንድ ተቋማት ወይ ‹‹ሲስተም የለም›› አላሉን ለደቂቃዎች አቆዩን።

የቆየነውን ያህል ቆይተን፤ ቀጣይ የት መሄድ እንዳለብን ሳይነግሩን ከእርሳቸው ጋር መጨረሳችንን ብቻ ነግረውን ብጣሽ ወረቀታችንን ሰጡን። የት ነው መሄድ ያለብን ብሎ ለመጠየቅ የሚያስችል ገጸ ሁኔታ ስለሌላቸው በዙሪያችን ያሉትን ሰዎች ጠይቀን ቀጥሎ መሄድ ያለብን መስኮት ቁጥር ሄድን። የተጠቆምንበት መስኮት ቁጥር ላይ ያለችዋ ልጅ የታማሚውን ስም ጠየቀችን፤ ተናገርን። በአንዲት ቃል ብቻ ‹‹አልተላለፈም!›› ብላን ከመስኮቱ አጠገብ ካለው ወንበር ተነስታ ወደ ክፍሉ መሐል ወለል ሄደች። ‹‹ምንድነው የጎደለው? የት ነው መሄድ ያለብን?›› ብለን ለመጠየቅ ራቀችን።

አብራኝ የነበረችውን የታማሚውን ጓደኛ ዝም ብዬ በድፍረት ‹‹ይሄ ነገር እዚያች ሴትዮ ጋ ይመስለኛል ችግሩ›› አልኳት። እየተሳሳቅን ልጅቷን ወደ መስኮቱ እስከምትጠጋ ጠበቅናት። ሌሎች ባለጉዳዮችን ልታናግር ስትመጣ ምን እንደሚጎለውና የት መሄድ እንዳለብን ጠየቅናት። በተሰላቸ ድምጸት ‹‹እዚህ መምጣት ያለባችሁ ስም አስተላልፋችሁ ነው›› በማለት ቀደም ሲል የቆየንበትን መስኮት ቁጥር (የሴትዮዋን) ጠቆመችን። ይህችኛዋ ልጅ አይፈረድባትም፤ ምክንያቱም እዚያ መሄዳችንን አታውቅም።

በድጋሚ ሴትዮዋ ጋ ሄድን። እንደገና ወረፋ ያዝን፤ ወረፋው ሲደርሰን እንዳልተላለፈ ነገርናቸው። ወረቀቱን ተቀብለው እንደገና ደግሞ ከኮምፒውተሩ ጋር ተፋጠው ቆዩ። ወረቀቱን በድጋሚ ሰጡን። አሁን ጉዳዩ አለቀ! ‹‹ተመስገን›› ብለን ወጣን።

እንግዲህ ልብ በሉ! ያ ሁሉ የሐኪሞች ድካም፣ ያ ሁሉ ነፍስ የማዳን ውለታ፣ ያ ሁሉ የሐኪሞች ቀልጣፋ አሰራር፣ ያ ሁሉ የነርሶች ትህትና… በእንዲህ አይነት ጥቃቅን ችግሮች መጉላላትና ትርምስ ይፈጠራል ማለት ነው። በእንዲህ አይነት ጥቃቅን ችግሮች ተገልጋዩ ሌላ የአዕምሮ ውጥረትና ጭንቀት ውስጥ ይገባል ማለት ነው። ከበር ጥበቃ እስከ አልጋ ክፍል ያሉት ሰንሰለቶች ሰውን የሚያሳብዱ ይሆናሉ ማለት ነው። ከአልጋ ክፍል በታች ባሉ የአሰራር ውጣ ውረዶች መሰላቸትና ተስፋ መቁረጥ፤ እናቶች ‹‹እሪ!›› ብለው ሲጮሁ፣ አካል ጉዳተኞች ምርኩዛቸውን ወርውረው ሲፈጠፈጡ በዓይኔ አይቻለሁ። ከታች ባለው አሰራር ተቋሙንም፣ ሀገራቸውንም ሲራገሙ ሰምቻለሁ።

እነዚያ ሰውን ከሞት አፋፍ የመለሱ ሐኪሞች፣ እነዚያ እንቅልፍ ሳይተኙ ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው ሌላውን ለማዳን የሚታትሩ ነርሶች… በጥቃቅን አሰራሮች፣ በአስተዳደራዊ ችግሮች ምክንያት ሙያቸው ሲረገም መስማት ለማንም ሰው ይረብሻል። ሰዎች ወደ ሕክምና ተቋም ለመሄድ የሚፈሩት በእነዚህ ምክንያቶች ጭምር ስለሆነ፤ የጤና ተቋማት የሕክምና ተቋማቱን አሰራሮችና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ልብ ሊሉም፣ ፈትሸው ሊያርሙም ይገባል!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You