ጥሮ ግሮ ማደርን ባሕል ያደረጉ፣ እድሜ ያልገደባቸው ጠንካራ እናት ናቸው። አርብቶ አደርነት እንኳን እንደሳቸው ከተማ ተወልዶ ላደገ ሰው ይቅርና እድገቱን ገጠር ላደረገም ትልቅ ጥረት እና ልፋትን ይጠይቃል። እሳቸው ግን የከተማን ሰው ሥራ አይችልም ያለው ማነው ብለው የተነሱ ቆራጥ ናቸው። ሁሉንም በልኩ በጥበብና በብርታት ይዘው ውጤታማ መሆን ችለዋል።
ከተሜነታቸውም የከብት ሳር ከማጨድ አንስቶ ሌሎች ተያያዥ ሥራዎችን ለመከወን አላገዳቸውም:: ምክንያቱም ሥራውን የጀመሩት ዓላማ ይዘው ነው:: የሥራቸው ትልቁ ዓላማ በሞት የተለያቸውን የአብራካቸውን ክፋይ ማስታወስ ነው:: አለፍ ሲልም አንገት አስደፊ ከሆነው ድህነት ማምለጫ መፍትሔው ሥራ መሆኑን በመገንዘባቸው ነው::
በአርአያነታቸው የመረጥናቸው ብርቱ ሴት ወይዘሮ ወይንሸት ጥላሁን ይባላሉ:: ወይዘሮዋ የሚኖሩት እንጦጦ አካባቢ ሲሆን፤ ባለትዳርና የአራት ልጆች እናት ናቸው:: የ65 ዓመት እድሜ ባለፀጋ የሆኑት ወይዘሮ ትውልድና እድገታቸው አዲስ አበባ ከተማ ቀጨኔ መድኃኒዓለም አካባቢ እንደነበር አጫውተውናል።
ትምህርት የማግኘት አማራጭ ከገጠር ይልቅ በከተማ አካባቢ የተሻለ እንደሆነ ቢታመንም፤ እሳቸው ግን ከደሃ ቤተሰብ በመወለዳቸው እና በወቅቱ ማህበረሰቡ ለሴት ልጅ ትምህርት ካለው አመለካከት የተነሳ መደበኛ ትምህርት የማግኘት እድል አልገጠማቸውም::
“የተማርኩት መሠረተ ትምህርት ብቻ ነው:: ቤተሰቦቼ እኔን ለማስተማር አቅም ከማጣታቸው ሌላ ቀደም ሲል ሴት ልጅ ትምህርት እንድትማር ያለው አመለካከት እስከዚህም ነው:: ከዚህ የተነሳ ከልጅነት እስከ እውቀት እድሜዬን በልፋት ነው ያሳለፍኩት::” ይላሉ::
የተለያዩ ሥራዎች በመሥራት እራሳቸውን ሲያስተዳድሩ ነበር ከባለቤታቸው ጋር ተገናኝተው ትዳር የመሠረቱት:: በትዳራቸው አራት ልጆችን ያፈሩ ሲሆን፤ አንደኛው ልጃቸው ወታደር ቤት ግዳጅ ላይ እያለ ነው የተሰዋው::
ወይዘሮ ወይንሸት ወደ ከተማ ግብርና ከመግባታቸው በፊት ከሚያረቧቸው ጥቂት በጎች ውጭ፤ በባለቤታቸው ደሞዝ ነበር የሚተዳደሩት:: አጋጣሚ ሆኖ ልጃቸው በግዳጅ ላይ ስለሞተ በተሰጣቸው የካሳ ክፍያ ላም ገዝተው ወደ ከብት ርባታ ሥራ ገቡ::
“አጋጣሚ ልጄ ወደ ውትድርና ገብቶ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ግዳጅ ላይ ስለሞተ ዳረጎት ተሰጠኝና ገንዘቡን ሳላጠፋ፤ አንድም የልጄ ማስታወሻ እንዲሆነኝ በማለት ሥራ ፈጠርኩበት::” ሲሉ ይናገራሉ::
የካሳ ክፍያውን የተቀበሉት ልጃቸው ከሞተ ከሶስት ዓመት በኋላ እንደነበር በመግለጽ፤ ታናናሽ ልጆች ስለነበሯቸው እነሱን እያሳደጉ፤ አንድ የሀበሻ ላም በአራት ሺህ ብር ገዝተው ነው ሥራውን የጀመሩት:: ያች ላም እየወለደች ወደ ለውጥ መንገድ እንዲገቡ ምክንያት ሆነች::
ከዛ ቀጥለው ዝርያዋ የተሻሻለ ጥጃ ገዝተው አሳደጉና ጥጃዋ ስታድግ አምስት ሴት ላሞች ወለደች:: መጀመሪያ የገዟትን ላም ሸጠው ዝርያቸው የተሻሻሉ ላሞችን ማርባት ጀመሩ:: ወደ ሥራ ገብተው መሥራት ከጀመሩ አሁን 20 ዓመት ሆኗቸዋል:: በእነዚህ ዓመታት ግን ሥራቸው አልጋ ባልጋ ሆኖላቸው አይደለም ሲሰሩ የቆዩት::
ሌሎች አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንዳሉ ሆነው ብዙ ጊዚያት የሚያረቧቸው ላሞች እየሞቱባቸው ልባቸው ቢሰበርም፤ እንደምንም ተጣጥረው ሌሎች ላሞችን በመግዛት ላሞቻቸውን ያሳጣቸውን ሞት መልሰው ይበቀሉታል::
“በቀደም የሚታለቡ ሁለት ከብቶች ምን እንደነካቸው አላውቅም በተከታታይ ነበር የሞቱብኝ:: እነዛ ሲሞቱብኝ በእልህ ሶስት ጥጃዎች ገዛሁ:: ከዛ በኋላ እንግዲህ እስካሁን የሞተብኝ የለም:: ነገር ግን በየጊዜው ላሞች የሚሞቱበት ሁኔታ ይገጥመኛል::” ይላሉ::
ወይዘሮ ወይንሸት ሁለት ጥጆችን ጨምሮ ዘጠኝ የፈረንጅ ላሞች ያሏቸው ሲሆን፤ ወንድ ጥጃ ካልሆነ ብዙ ጊዜ ከብት የመሸጥ ልምድ የላቸውም:: ወንድ ጥጃ ሲሆን ከመኖ አቅርቦት አንጻር ስለሚቸገሩ ገና በተወለዱ በጥቂት ጊዚያት ውስጥ ገበያ አውጥተው እንደሚሸጡ ይናገራሉ::
“እኔ ላሞችን ሸጬ አላውቅም ከወንዶች በስተቀር፤ ለዛም ነው በርከት ሊሉ የቻሉት:: አሁን ግን መኗቸውም እየተወደደ ስለሆነ መሸጤ አይቀርም:: ጊዜው ለመሥራት ትንሽ ያስቸግራል፤ በመኖ አቅርቦት መንግሥት ቢያግዘን ጥሩ ነው::” ሲሉ ይገልጻሉ::
“ጥናት ተሰርቶ የከብቶች መኖ በመንግሥት በኩል የሚቀርብበት መንገድ ቢመቻች መልካም ነው:: አሁን ከግለሰብ ስንገዛ በጣም ነው የሚወደድብን እስከ 60 ሺህ ብር የማይበቃበት ጊዜ አለ:: ይህም የሚገኘው ገቢ ለላሞች መኖ ብቻ እንዲውል እያደረገሁ ነው::” ይላሉ::
አሁን ላይ ሁለት ላሞች የሚታለቡ ሲሆን፤ ሌሎቹ ነፍሰ ጡር ናቸው:: እነዚህ ላሞች በቀን እስከ አስር ሊትር ድረስ ይታለባሉ:: ዝርያቸው የተሻሻለ ላሞች ቢሆንም፤ አንደኛ የሚባሉ አይደለም በማለት ይገልጻሉ::
“ወደ ተለያዩ ቦታዎች ሄጄ እንዳየሁት እና ከወሰድኩት ከሥልጠና እንደተገነዘብኩት ከሆነ ላሞቹ ደረጃ አላቸው:: እኔ የማረባቸው አንደኛ የፈረንጅ ላሞች አይመስሉኝም:: ምክንያቱም እስከ 20 ሊትር ድረስ የሚታለቡ ላሞች እንዳሉም እንሰማለን:: እና የእነዚህ ደረጃ ትንሽ የሚያንስ ይመስለኛል::” ይላሉ::
“በሥልጠናው ተነግሮኝ ከፍተኛ የወተት ምርት የሚያስገኙ ላሞችን ዝርያ ለያዙ ዶክተሮች ደውለን እንዲመጡ ስንነግራቸው እንደሚመጡ ቢገልጹልንም አይመጡም:: አንዳንዴ ደግሞ ወረዳችን አይደለም የሚሉበትም ጊዜ አለ::” ሲሉ ይናገራሉ::
ላሞቹ ጽንስ ሊይዙባት የሚችሉት 24 ሰዓት ያለች ቢሆንም በቀኑ እኩሌታ ነው ዘረመሉ የሚሰጣቸው:: ሰዓቱ ከዛ ካለፈ ወይም ካነሰ ዋጋ የለውም:: ወይዘሮ ወይንሸት ምንም እንኳን ትምህርት ባይማሩም፤ ረጅም ዓመት በሥራው ላይ ከመቆየታቸው የተነሳ ላሞቻቸው በየትኛው ሰዓት ዝርያውን መወጋት እንዳለባቸው በራሳቸው ቆጥረው ነው የሚደርሱት::
ወደ ሥራው ከመግባታቸው በፊት ምንም ዓይነት እውቀቱ እንዳልነበራቸው የሚገልጹት ወይዘሮዋ፤ ወደ ሥራው ስገባ ምንም እውቀት አልነበረኝም:: ነገር ግን ሰዎችን እየጠየኩ እና ወደ ሥራው ከገባሁ በኋላ ደግሞ አንዳንዴ በሚሰጠን ሥልጠና ነው እዚህ ልደርስ የቻልኩት ይላሉ::
“እኛ ላሞቹን የምናልባቸው በቀን ሶስት ጊዜ ነው:: በሚሰጠን ሥልጠና ሶስት ጊዜ ማለብ አይፈቀድም ይሉናል:: ግን ላሞቹ ስለለመዱ ካልታለቡ ይረብሹናል:: ስለዚህ የግድ ሶስቴ መታለብ አለባቸው::” ሲሉ ይናገራሉ::
ወይዘሮ ወይንሸት ከከብቶቹ የሚያገኙትን ወተት ሸጠው ነው የላሞቹን መኖ የሚገዙትም ሆነ፤ ቤተሰቡን የሚያስተዳድሩት:: ወተቱን የሚያስረክቡት ለካፌዎች ሲሆን፤ አንድ ሊትር በ70 ብር ነው የሚሸጡት::
የሚያገኙትን ወተት በራሳቸው ሱቅ ለማቅረብ አስበው ቢንቀሳቀሱ ከቤት ኪራይ ውድነት የተነሳ አልቻሉም:: የሱቁ ጉዳይ ባይሳካላቸውም የገበያ ግንባር አላጡም:: በጾም ወቅት ካልሆነ የገበያ ችግር የሌለባቸው ሲሆን፤ ለካፌዎች ወስዶ ከማስረከብ በተጨማሪ፤ የሰፈር ሰውም የሳቸውን ወተት ፈልጎ ነው የሚገዛላቸው::
“ከሚወጣው ወጪ አንጻር ወተቱ የሚሸጥበት ዋጋ አትራፊ አይደለም:: ከብቶች ዘጠኝ እንደመሆናቸው እና የሚታለቡት ሁለቱ ብቻ በመሆናቸው ወጪው አይመጣጠንም:: ያው ልጆቼ ጥሩ ቦታ ላይ ስላሉ እነሱም ይረዱኛል:: እነሱ የሚሰጡኝን ገንዘብ ጨምሬ መኖ እገዛላቸዋለሁ::” ይላሉ::
አሁን ካሏቸው ዘጠኝ ከብቶች አምስቱ የሚታለቡ ሲሆኑ፤ የተቀሩት ጥጃ እና ጊደር ናቸው:: ከሚታለቡ ላሞች ለጊዜው ወተት እየሰጡ ያሉት ሁለቱ ሲሆኑ፤ ሁለቱ ነፍሰጡር መሆናቸውን ያስረዳሉ::
ለጥጆቹ ወተት የሚሰጠው ታልቦ በእቃ ነው። “ጥጆቹ ይጥቡ ከተባለ መመለስ ከባድ ነው:: የሚመልሳቸው ሰው የለም:: ከዚህ በፊት እያስጠባሁ ለማለብ ሞክሬ ነበር ግን ትግል ነው:: ላሞቹ እንዳያዩ ገና እንደወለዱ ነው በጨርቅ ሸፍኜ የማነሳቸው::” በማለት ይናገራሉ::
“በዚህ ሥራ የሚረዱኝ ልጆቼ እና ባለቤቴ ናቸው:: ልጆቼ ሥራ ይዘው ትዳር መስርተው ስለወጡ ነው እንጂ በጣም ጎበዝ ናቸው:: እነሱ ስለሚረዱኝ ሠራተኛ እንኳን አልፈልግም ነበር:: አሁን ላይ አቅሜም እየደከመ ስለሆነ ሠራተኛ ለመቅጥር አስባለሁ:: አሁን የሚረዱኝ ባለቤቴ እና አንድ ልጄ ከእኔ ጋር ስለሆነች እሷ ናት::” ይላሉ::
“ይህን ሥራ በመሥራቴ ባንክ ያስቀመጥኩት ገንዘብ ወይም ያፈራሁት ትልቅ ሀብት ባይኖረኝም፤ ቤቴን ለማሳደስ ችያለሁ:: ሌላው ቤቴ ውስጥ የሚያስፈልጉኝን ነገሮች እንድሸፍን ከማድረግም ያለፈ ለማህበራዊ ወጪ የሚያስፈልጉኝን ወጪዎች እንድሸፍን ረድቶኛል:: ልጆቼንም የማስቸግር ሰው አይደለሁም ግን የእናትነት ጉዳይ ስላለ ግዴታ ነው::” በማለት ይገልጻሉ::
ሁሉም ነገር ትእግስት ያስፈልገዋል የሚሉት ወይዘሮዋ፤ ከብቶችን ማብላቱም ማጠጣቱም ትእግስት ይጠይቃል:: ምክንያቱም ወንፊት ላይ እህል ሲቀመጥ ነው ወደታች የሚወርደው:: ልክ እንደዛው ላሞቹም በሥርዓት ካልበሉ ካልጠጡ ደግሞ ምንም ዓይነት ጥቅም ማግኘት ከባድ ነው ይላሉ::
ወይዘሮ ወይንሸት እስካሁን በሰሯቸው ሥራዎች የተለያዩ እውቅናዎችን እና ሽልማቶችም አግኝተዋል:: ለልምድ ልውውጥ የተለያዩ አካባቢዎች ሄዶ የማየት እድሉም ገጥሟቸዋል::
“እውነት ለመናገር በዚህ ሥራ ዓለም ነው ያየሁበት፤ እናም ልጄ እየጦረኝ ነው የምለው:: በከተማ ግብርና ውጤት በማምጣት ታጭቼ ዋንጫ፣ ሜዳሊያ ከመሸለም በተጨማሪ የብር፣ የልብስ ሽልማት ተሸልሜያለሁ:: እሱ ብቻ ሳይሆን አዳማ እና ሌሎች አካባቢዎች ሄጄ በዘርፉ የሚሠሩ ሥራዎችን ጎብኝቼለሁ:: ከወረዳም ሰዎች በየጊዜው እየመጡ ጎብኝተው ሃሳብ ይሰጡኛል::” ይላሉ::
“ላሞቹ የሚያድሩበትን ቦታ እንዳስፋፋ የፈቀዱልኝም የወረዳ ሰዎች ናቸው:: በፊት ከብቶቹ በሚያድሩበት ቦታ ላይ ከላይ ቆጥ ሰርቼ ነው ሳር ሳስቀምጥ የነበረው:: መጥተው ጎብኝተው የከብቶቹን መጎዳት ሲመለከቱ፤ አስፋፍቼ እንድሠራ ፈቀዱልኝ:: አሁን ለሁለቱም የተለያየ ቦታ ለማዘጋጀት ችያለሁ::” ሲሉ ይናገራሉ::
ከተማ ስለተወለዱ ብቻ መንቀባረር የለም የሚሉት ወይዘሮዋ፤ ከችግር ለመውጣት የማልፈነቅለው ድንጋይ የለም:: ከብቶች ሳይኖሩኝ በፊት ልጆቼን ለማስተማር በተወሰነም ቢሆን እንዲረዳኝ በጎች አረባ ነበር:: እነዚህን ሥራዎች ሲጀምሩ ምንም እውቀቱ እንዳልነበራቸው ይገልጻሉ::
“ የመጀመሪያዋን ከብት ስገዛ ማለብ እንኳን ባለመቻሌ ባለቤቴ ነበር የሚያልበው:: ከዛም ልጆቼን ከብት ማለብ አስተማራቸው:: እኔም ቀስ በቀስ እየለመድኩ መጣሁ:: አሁን እድሜ እየገፋ እየደከምኩ መጣሁ እንጂ ከተሠራ ለውጥ የማይመጣበት ምንም ምክንያት የለም::” ይላሉ::
ወተት የማለቡንም ሆነ የመናጡን ሥራ የሚሠሩት በባሕላዊ መንገድ ነው:: ዘመናዊ መናጫ እና ማለቢያ ለመግዛት ገንዘብ እንደሚያስፈልጋቸው ለወረዳ አስረድተው ከባንክ ጋር እንደሚያስተሳስሯቸው ቃል የተገባላቸው ቢሆንም የመዘግየት ነገር እንዳለ ጠቁመዋል::
በመጨረሻም በጉለሌ ክፍል ከተማ ወረዳ አንድ ስለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን የሚያቀርቡት ወይዘሮ ወይንሸት፤ በተጨማሪም ባለቤታቸውን እና ልጃቸውን አመስግነዋል::
አመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 1 ቀን 2017 ዓ.ም