ዜና ትንታኔ
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ለሚኖር ወዳጅነት እና የጋራ ተጠቃሚነት ከፍተኛ ትኩረት እየሰጠ ነው። ይህ ስትራቴጂካዊ የፖሊሲ አካሄድ የፖለቲካ ዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚ አጋርነት፣ የጸጥታ ትብብር፣ የባህል ልውውጦች እና የአካባቢ ዘላቂ ግንኙነትን ጨምሮ የሁለትዮሽ እና ክልላዊ ትብብርን በተለያዩ መስኮች ማሳደግ ቅድሚያ የሚሰጥ ነው።
ኢትዮጵያ አካባቢያዊ ቀጣናዊ መረጋጋትን፣ የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረጉ የልማት ስራዎችን መስራት ፣ በተለይም ሰላምን በማስፈን ሀብቶችን ለጋራ ጥቅም ለመጠቀምና ለማልማት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት በተደጋጋሚ አስታውቃለች። ለጉዳዩ ያላትን ቁርጠኝነትም በተጨባጭ አሳይታለች።
ለዚህም በማሳያነት የሚገለፀው የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን እያካሄደች ነው። በተለይም በኃይል አቅርቦት፣ በባቡር መስመር ግንባታ እና በንጹህ ውሃ አቅርቦት ዙሪያ ተጠቃሽ የሆኑ ሥራዎችን አከናውናለች፤ ለሱዳን፣ ለደቡብ ሱዳን፣ ለኬንያ እና ለጅቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል እያቀረበች ነው። ለጅቡቲ ንጹሕ የመጠጥ ውሃ እያቀረበች ትገኛለች።
ከሰላም አኳያም የሶማሌን ሰላም ለማረጋገጥ የከፈለችው መስዋእትነት እንዲሁም፤ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳናውያን የውስጥ ችግራቸውን በሰላም እንዲፈቱ ሰፊ ጥረቶችን አድርጋለች፡፡ ሀገሪቱ የሰላም አስከባሪም አሰማርታለች።
በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአውሮፓና የአሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተንታኝ ዳርእስከዳር ታዬ(ዶ/ር) እንደሚናገሩት፤ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ማለትም ከምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት ጠንካራ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ አንደኛው ጎረቤት መሆናቸው በራሱ የግንኙነት አድማሱ በጣም ሰፊ እንዲሆን ያስገድዳል፡፡ እንደሩቅ ሀገሮች ለምሳሌ ኢትዮጵያ እና ኤሜሬት በጂኦግራፊ የተቀራረቡ አይደሉም፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ከኤሜሬት ጋር ያላት ግንኙነት የተነጠለ ነው፡፡
የኢትዮጵያ እና የምሥራቅ አፍሪካ ግንኙነት ግን ከሩቅ ሀገሮች ከፍ ያለ ነው፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት፣ የማንነት ተመሳሳይነት ፣ ንግድ እና ድንበርን በጋራ ማስተዳደር አለ፡፡ የጋራ የድንበር ኮሚሽን አለ፡፡ ይህ በራሱ በግድም ሆነ በውድ የሚያስተሳስር ነው። ይህን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ኢትዮጵያ ደግሞ በልዩ ሁኔታ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ለጎረቤት ሀገራት ልዩ ትኩረት ሰጥታለች፡፡
በውጭ ጉዳይ ፖሊሲው በግልፅ እንደተቀመጠው ሁሉ፤ ኢትዮጵያ ምሥራቅ አፍሪካን በተለያየ መንገድ በማስተሳሰር በኩል ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች ነው፡፡ ይህም ወደ ፊት ሀገሪቱን ስኬታማ እንደሚያደርጋት ይታመናል፡፡
በዋናነት እስከ አሁን በቀጣናው ሰላም ለማስፈን የከፈለችው ዋጋ ትልቅ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በሀይል እና በመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ እያደረገችው ያለው ተሳትፎ የሚበረታታ ነው። አሁን ላይም አካባቢውን በልማት እና በንግድ ለማስተሳሰር የጀመረችው ስራ ተስፋ ሰጪ እንደሆነም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይልን በስፋት ለማመንጨት መሥራት ከጀመረች አስር ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ኤሌክትሪክ የማምረት አቅሟ በመጨመሩ ለኬንያ፣ ለሱዳን፣ ለጅቡቲ ማቅረብ ጀምራለች፡፡ ይህ ከፖለቲካ ነፃ በሆኑ በሰላም ጉዳይ ላይ ብቻ ሳይሆን፤ የልማት ሥራዎች የሚሠራበት ዕድል በኢትዮጵያ አማካኝነት እየሰፋ መምጣቱን የሚያመላክት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል የማምረት አቅም እየጨመረ ሲሄድ ተቀራርቦ የመነጋገር አቅም እየጨመረ ይሄዳል፡፡ አሁን ላይ ከሱዳን ጋር ኢትዮጵያ ትልቅ ግብይት እያካሔደች ነው፡፡ ነዳጅን ጨምሮ ሽንኩርት ሳይቀር ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ እየገባ ነው፡፡ ከደቡብ ሱዳን ጋርም አሁን በመንገድ ለመተሳሰር ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ይህም የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ያላቸውን ውስን ሀብት በጋራ የሚጠቀሙበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው ለማለት እንደሚያስደፍር አመልክተዋል፡፡
ለምሳሌ የኬንያ ኢንቨስትመንት ወደ ኢትዮጵያ እየመጣ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም ሳፋሪኮምን አንስተዋል፡፡ በቀጣይ በስፋት በባንክ እና በሌሎችም የንግድ ዘርፎች ኢትዮጵያ ውስጥ ለመሥራት ከፍተኛ ተነሳሽነት ማሳየታቸውንም ተናግረዋል፡፡
ዳርእስከዳር(ዶ/ር) እንዳብራሩት፤ ትስስር በሀገራቱ መካከል ከፍተኛ ግጭት እንዳይፈጠር ያስችላል፡፡ በምሳሌነትም ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ሁለቱም ተጠቃሚ በመሆናቸው እርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ የመግባት ዕድላቸው ዝቅተኛ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ምንም ቢፈጠር ጦርነት ውስጥ ይገባሉ ብሎ ለመገመት አዳጋች ነው፡፡ ሁለቱም ጥቅማቸውን ላለማጣት ችግርን በውይይት ለመፍታት ጥረት ያደርጋሉ፡፡
ከኬንያ ጋርም በተመሳሳይ መልኩ ጦርነት የመፈጠር ዕድሉ ዝቅተኛ ነው፡፡ ባለፉት ጊዜያት ከሱዳን ጋር ብዙ ነገሮች ተፈጥረው ነበር፡፡ ነገር ግን ወደ ጦርነት አልተገባም፡፡ ምክንያቱም ሱዳን እና ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ እርስ በእርስ ተሳስረዋል፡፡
በተጨማሪ የናይል ተፋሰስ ሀገራት ስምምነት ኮሚሽንን ለመመስረት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሩዋንዳ ፣ ዑጋንዳ እና ደቡብ ሱዳን ተቀላቅለዋል። በቅርቡም ኮሚሽኑ ወደ ሥራ እንደሚገባ ይጠበቃል፡፡ይህ ቀጣናውን የማስተሳሰር የኢትዮጵያ ዕቅድ ቀስ በቀስ ፤ ሀገሪቱን እና ቀጣናውን ሊጠቅም በሚችል መልኩ እየሰፋ ይሄዳል፡፡ በቀጣናውም ለኢትዮጵያ ትልቁ ስኬት ይሆናል ብለዋል፡፡
ስራው ከተፅዕኖ እና ከጫና ነፃ እንዳልሆነ የሚናገሩት ዳርእስከዳር (ዶ/ር)፤ አሁን ላይ የተለያዩ አካላት በቀጣናው ፍላጎት እያሳዩ ነው፤ ትኩረትም እየሳበ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ለብቻ መሥራት የሚቻልበት ሁኔታ እየተመናመነ መጥቷል። ይህም በሁሉም መስክ በጋራ መስራትን አስገዳጅ ያደርገዋል። ይህንን ታሳቢ ባደረገ መንገድም ሀገራችን እየተንቀሳቀሰች እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
አላስፈላጊ ጫናዎች ሲኖሩ ራሷን እያገለለችም ቢሆን፤ ሁኔታዎችን ተቋቁማ ሚናዋን ለመወጣት ጥረት በማድረግ ላይ ናት፡፡ ሶማሊያም ላይ የተከሰተው የዚህ እውነታ መገለጫ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ቀደም ሲልም ከምሥራቅ አፍሪካ ጀምሮ ነፃ ያልወጡ ሀገሮች ነፃ እንዲወጡ አፍሪካ ውስጥ ሰላም እንዲሠፍን መረጋጋት እንዲኖር ለምሳሌ በሶማሊያ እና በሱዳን ከፍተኛ ሚና ስትጫወት የቆየች ሀገር ናት፡፡
ቀድሞም ሆነ አሁን ኢትዮጵያ ምሥራቅ አፍሪካን በማስተሳሰር በኩል ያላት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይ የሕዝብ ለሕዝብ፣ የባህል እና የእምነት የመሳሰሉት ትስስር አላት፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ እና የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት እጣ ፈንታ በእጅጉ የተሳሰረ ነው፡፡
በተለይ አሁን በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ውስጥ ጎረቤት ሀገሮች ማለትም የአፍሪካ ቀንድ ወይም ከምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ጋር ያለን ግንኙነት በወታደራዊ፣ በማህበራዊ እና ፖለቲካዊ መስክ እጅግ በጣም መተሳሰር እንደሚያስፈልግ ተቀምጧል፡፡ በዚህ ላይ ኢትዮጵያ በትጋት ሠርታለች፤ ወደ ፊትም ትሠራለች ብለዋል፡፡
ከምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነቷን በማጠናከር እና በማስፋት የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) እንዲመሠረት እና እንዲጠናከር እንዲሁም ወደ ፊት በቀጣይነት ብዙ ሥራዎች እንዲሠሩ ኢትዮጵያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገች ሀገር መሆኗን ጠቁመው፤ ወደፊትም በዚህ መልኩ ትቀጥላለች ብለዋል፡፡
እንደ ምሁራኑ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ተቀራርቦ ልማትን ለማከናወን እና ለምሥራቅ አፍሪካ ውህደት የበኩሏን አስተዋፅኦ ለማበርከት፣ አዎንታዊ የእድገት ውጤቶችን እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እየሠራች ነው፡፡ በቀጣይም ትሠራለች።
በተለይ በቀጣይ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ጎረቤት ሀገራት ከተጨማሪ የኃይል ሀብቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ በተጨማሪ ከጎረቤቶቿ ጋር በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያላት ግንኙነት ሰፊና ጠንካራ እየሆነ ይቀጥላል፤ በቀጣናው ሀገራት መካከል መተባበር ፣ የጋራ ልማትን ማረጋገጥ እና ዘላቂ ሰላም መምጣቱ አዳጋች አይሆንም ብለዋል።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 1 ቀን 2017 ዓ.ም