አዳማ:- ጨፌ ኦሮሚያ የቀረበለትን የ25 አዲስ የቢሮ ኃላፊዎችና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ሹመት ጨምሮ የተለያዩ ሰነዶችን በማጽደቅ የሦስት ቀናት ጉባኤውን አጠናቀቀ።
በአዳማ ከተማ ገልማአባገዳ አምስተኛ የጨፌ ኦሮሚያ አራተኛ የሥራ ዘመን 10ኛ ጉባኤውን ሲያካሂድ የቆየው ጨፌ ኦሮሚያ ትናንት ሲያጠናቅቅ ሹመታቸው ከጸደቀላቸው 25 የስራ ሃላፊዎች መካከል 13ቱ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ሲሆኑ 12ቱ ደግሞ አዲስ የተለያዩ የቢሮ ኃላፊዎች ናቸው። ተሿሚዎቹም በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቃለ መሐላ ፈጽመዋል። ሴት ተሿሚዎች ሁለት ብቻ ናቸው።
በቀረበው ሹመት ላይም ከጨፌው አባላት ሴቶች ከወንዶች እኩል እንዲሆኑና 50 በመቶ ድርሻ እንዲኖራቸው በመንግሥት በኩል መነገሩን በማስታወስ፣ በእያንዳንዱ ሹመት ውስጥ አንዳንድ ሴት ብቻ መሆናቸው ከምን የመነጨ እንደሆነ ጥያቄ አዘል አስተያየት አቅርበዋል።
የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሹመትን በተመለከተ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ደሳ ቡልቻ ለቀረበው አስተያየት በሰጡት ምላሽ መስፈርቱን የሚያሟሉ ባለመኖራቸው ማቅረብ አልተቻለም።በቀጣይ በጀት አመት የሴቶችን አቅም ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎችን ለማከናወን መታቀዱን በሪፖርታቸው ማቅረባቸውን አመልክተዋል።
ጨፌው ባለ 88 ገጽ የጨፌ አባላት ሥነምግባርና አደረጃጀት ደንብ ሰነድ እና ለክልሉ ዋና ኦዲተር ባለሙያዎች የቀረበውን የጥቅማጥቅም ማሻሻያ ላይ ተወያይቶ አጽድቋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10/2011