ለወሎ ተርሸሪ ሆስፒታል ግንባታ የተሰበሰበው 23 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ባንክ አለመግባቱ ተገለጸ

 – ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ አላግባብ ወጪ መደረጉ ተጠቆመ

– ቦርዱ በሌለው ስልጣን አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ትኬቶችን የጠፉ በሚል መሠረዙም ተመለከተ

አዲስ አበባ፡- ለወሎ ተርሸሪ ኬር የሕክምናና ማስተማሪያ ሆስፒታል ግንባታ የተሰበሰበው 23 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ወደ ባንክ አለመግባቱን ዋናው ኦዲተር አስታወቀ። የግንባታ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ ከ2010 እስከ 2016 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ድረስ ሕጋዊ እውቅና ሳይኖረው ያለ አግባብ ዘጠኝ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር በሥራ ማስኬጃ ስም ማውጣቱን አመለከተ፡፡

ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ2015/16 በጀት ዓመት በወሎ ተርሸሪ ኬር የሕክምናና ማስተማሪያ ሆስፒታል ግንባታ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ከህብረተሰቡ የተሰበሰበው ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ለማረጋገጥ ትናንት በክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ምክክር አካሂዷል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ለሆስፒታሉ ግንባታ ከሕዝብ የተሰበሰበው ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ ስላለመዋሉ፣ ጽህፈት ቤቱ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ሀብቱን ኦዲት አስደርጎ ለዩኒቨርሲቲው ለምን እንዳላስረከበ፣ ጽህፈት ቤቱ የሚያከናውናቸው ተግባራት ሕጋዊነት፣ የግንባታ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ ለምን በድጋሚ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅትነት መመዝገብ እንዳልቻለና ሌሎችንም ጥያቄዎች አቅርቧል፡፡

የወሎ ተርሸሪ ኬር የሕክምናና ማስተማሪያ ሆስፒታል ግንባታ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት እንዲሁም ሥራ አመራር ቦርድ አመራሮች በሰጡት ምላሽ፤ የሆስፒታሉን ግንባታ እውን ለማድረግ በበጎ ፈቃደኝነት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡

ለግንባታው ከአማራ ክልል አልፎ በመላው ኢትዮጵያ ብሎም በተለያዩ ሀገራት በሚገኙ ኤምባሲዎች ጭምር የብር ኩፖኖችንና የቶምቦላ ትኬቶችን ለመሸጥ ጥረት ተደርጓል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከሕዝቡ የተሰበሰበ 93 ሚሊዮን ብር በባንክ ይገኛል፡፡ከዚህ ውስጥ የተወሰኑ ትኬቶችን መሰብሰብ እንዳልተቻለ ይሁን እንጂ ከአሠራር ውጪ የተከናወነ ምንም ሥራ አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡

ጽህፈት ቤቱ ለወሎ ዩኒቨርሲቲ አስረክቦ እንዲወጣ በመወሰኑ በድጋሚ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅትነት መመዝገብ እንዳልፈለጉ አስታውቀዋል፤ ዩኒቨርሲቲው እስካሁን ድረስ ስራውን ሊረከብ አልቻለም፡፡ አሁንም በተቻለ ፍጥነት ያለውን ሀብት አስረክቦ ለመውጣት  ጽህፈት ቤቱ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የወሎ ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ፤ የጽህፈት ቤቱ ሀብት በአግባቡ ኦዲት ተደርጎና አስፈላጊውን ሕግ ተከትሎ ከተከናወነ የሆስፒታሉን ግንባታ ተረክቦ ግንባታ ለማከናወን ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ እንዳሉት፤ የሆስፒታሉን ግንባታ ሂደት የሚመራ የቦርድ አመራር ተሰይሟል፡፡ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤትም ተቋቁሟል፡፡ ከሕዝብ የተሰበሰበው ገንዘብ የታለመውን ፕሮጀክት ለመገንባት የሚያስችል እንዳልሆነ በመታመኑ ከ2010 ጀምሮ ለወሎ ሆስፒታል እንዲያስረክብ የቦርዱ የበላይ ጠባቂ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

ጽህፈት ቤቱ ለግንባታ የሚያስፈልገውን ገንዘብ በአይነት፣ በብር፣ በቶምቦላ ሎተሪና በሌሎችም መንገዶች ገቢ ለማሰባሰብ ጥረት አድርጓል፡፡ የሕዘብ ጥያቄ የተሰበሰበው ገንዘብ ምን ላይ ዋለ የሚል በመሆኑ ትኩረት ተደርጎ ኦዲት የተሠራው ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ መዋሉንና በአግባቡ ወደ ባንክ ገቢ መደረጉ ላይ ነው፤ ከኩፖን ቲኬት ሽያጭ የተገኘ 16 ሚሊዮን 43ሺህ 63 ብር እንዲሁም ከቶምቦላ ትኬት ሽያጭ የተገኘ 7 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በድምሩ 23 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ወደ ባንክ አልገባም ብለዋል፡፡

የሆስፒታሉ ግንባታ ቦርድ የመሠረዝ ስልጣን ሳይኖረው አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ትኬቶች የጠፉ በሚል ሰርዟል ብለዋል፡፡ በተለይ ባንክ ያልገባው ገንዘብ ለማን እንደተሰጠ ስለሚታወቅ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ ከሚመለከታቸው አካላት አሰባስቦ ወደ ባንክ ማስገባት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

ፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ ያለውን ሀብትና ንብረት ኦዲት አድርጎ ያስረክብ ሲባል እስከ 2010 በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባስልጣን ሕጋዊ እውቅና ነበረው፡፡ ከ2010 በኋላ አስረክቦ እንዲወጣ ስለተወሰነ ሕልውና ስለሌለው ምንም አይነት ወጪዎች መውጣት እንዳልነበረባቸው ጠቅሰው፤ ሆኖም ከ2010 እስከ 2016 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ድረስ 9 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር የሥራ ማስኬጃ ተብሎ ወጪ ሆኗል፡፡ አሁንም እየወጣ ሊሆን ስለሚችል መቆም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የሥራ አመራር ቦርዱ ጽህፈት ቤቱ ተዘግቶ ለወሎ ዩኒቨርሲቲ የማስረከቡ ሥራ እንዲከናወን መሥራት እንዳለበት አመላክተው፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣንም ያለውን ሀብት ኦዲት አድርጎ የሀብት ርክክብ ተደርጎ ጽህፈት ቤቱ እንዲዘጋ ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል፡፡

የወሎ ዩኒቨርሲቲም የተሰጠው የሕዝብ አደራ ተቀብሎ የሆስፒታሉን ግንባታ አከናውኖ ለሕዝብ ጥቅም እንዲውል ማድረግ እንደሚገባው ጠቁመው፤ መንግሥትም ለግንባታው የሚውል የበጀት ድጋፍ ቢያደርግ የሚል አስተያየት አቅርበዋል፡፡

የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ አራሬ ሞሲሳ በሰጡት የማጠቃለያ አስተያየት፤ ጉዳዩ የሕዝብ ጥያቄ በመሆኑ ተገቢ መልስ እንደሚያስፈልገው፤ በሂደቱ ለተፈጠሩ ክፍተቶች ተጠያቁ መሆን ያለባቸው አካላት ተጠያቂ መሆን እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል፡፡

እስካሁን ባንክ ያልገቡ ብሮች በማን እጅ እንዳለና ለምን ባንክ ገቢ እንዳልተደረገ፣ ጽህፈት ቤቱ ሀብቱን አስረክቦ እንዲወጣ ከተወሰነ በኋላ እየወጣ ያለው ወጪ፣ ቦርዱም ባልተሰጠው ስልጣን ላይ ያደረገው የእዳ ስረዛ እና ሌሎችም የአሠርራር ጥሰቶች መታረም እና ተጠያቂ መሆን ያለበት አካል ተጠያቂ መደረግ እንደሚኖርበትም አሳስበዋል፡፡

በቀጣይነት ዋና ኢዲተር፣ የወሎ ዩኒቨርሲቲ፣ ቋሚ ኮሚቴው፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊዎች እንዲሁም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተገኙበት ውይይት ተካሂዶ ውሳኔ ማግኘት እንዳለበት አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

ፋንታነሽ ክንዴ

 አዲስ ዘመን ታህሳስ 1/2017 ዓ.ም

Recommended For You