አሲዳማ አፈርን በኖራ አክሞ ምርታማነትን ማሳደግ ያስቻለው ተሞክሮ

የኢትዮጵያን የግብርና ምርታማነትና ምርታማነትን ከሚፈታተኑ ችግሮች አንዱ የአፈር አሲዳማነት መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ አሁን በሀገሪቱ ከሚታረሰው መሬት ወደ ሰባት ሚሊዮን ሄክታሩ ወይም 43 ከመቶው የሚሆነው በአፈር አሲዳማነት የተጠቃ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ሶስት ሚሊዮን ሄክታሩ ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ በአሲዳማነት የተጠቃ መሆኑ ይገለጻል፡፡ ይህ ችግር እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ ትኩረት ሳይሰጠው በመቆየቱም በምርታማነት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ ሲፈጥር መቆየቱን የግብርና ባለሙያዎች ያመለክታሉ፡፡

በዚህ አሲዳማነት ከተጠቃው መሬት ሰባት ሚሊዮን ሄክታር የሚሆነውን ብቻ በኖራ የማከም ስራ ቢሰራ ምርትና ምርታማነትን በሃምሳ በመቶ ማሳደግ እንደሚቻልም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ኖራን ብቻ በመጠቀም ምርታማነትን ከ10 ኩንታል በሄክታር ወደ 40 እና 50 ኩንታል ማሳደግ እንደሚቻልም ይጠቅሳሉ፡፡

ግብርናው በምግብ ራስን ከመቻል አልፎ በኢኮኖሚ እድገቱ ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ሀገራዊ የግብርና ማሻሻያ መርሃ ግብሮች ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም መካከል ኩታ ገጠም እርሻ ፣ የበጋ ስንዴ፣ የከተማ ግብርና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡

በአሲድ የተጠቃ መሬትን በኖራ እያከሙ የምርታማነት ደረጃን ማሳደጉም ትኩረት የተሰጠው ሌላው ጉዳይ ነው፤ በዚህም ምርት አልሰጥ ብለው የቆየ መሬት ምርታማ እየሆነ መምጣቱንና አስገራሚ ለውጦች የተመዘገቡ መሆኑን መመልከት ተችሏል፡፡

በአሲድ የተጠቁ መሬቶችን በኖራ እያከሙ ምርታማነትን የማሳደግ ሥራ ከሚሰራባቸው ክልሎች አንዱ የኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ነው፡፡ በዘንድሮው የመኸር ወቅት በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ሸዋ ዞን፤ ወልመራ ወረዳ፤ ሀሮ ቦኪ ቀበሌ ልዩ ስሙ ተሴ በረንዳ በሚባል መንደር በኖራ በታከመ 853 ሄክታር መሬት ላይ የተዘራ የገብስ ሰብል የምርታማነት ደረጃ ከእጥፍ በላይ ማደግ ችሏል፡፡

በክልሉ አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱራህማን የተመራ ቡድንም በቅርቡ በሥፍራው ተገኝቶ የመስክ ምልክታ ባደረገበት ወቅት የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ዲዳ ጉደታ እንደገለፁት፤ በኦሮሚያ ክልል በአፈር አሲዳማነት የተጠቃ መሬት ከሚገኝባቸው አካባቢዎች አንዱ የምእራብ ሸዋ ዞን ነው፡፡ በዘንድሮው የመኽር ወቅት 108 ሺህ 886 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች የተሸፈነ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ በአሲዳማነት የተጎዳና ለረዥም ጊዜ የሚፈለገውን ምርት መስጠት ያልቻለ መሬት ይገኝበታል፡፡

የዞኑ አስተዳዳሪ እንዳሉት፤ የክልሉ መንግሥት አሲዳማ አፈርን በኖራ የማከም ንቅናቄ ውስጥ መግባቱን ተከትሎ ለዚሁ አገልግሎት የሚውል የኖራ ፋብሪካ በዞኑ እንዲገነባ ተደርጓል፡፡ በዚሁ መሰረት በአፈር አሲዳማነት የተጎዳ መሬትን በኖራ በማከም የምርታማነት መጠኑ እንዲጨምር ማድረግ ተችሏል፡፡

በ2016/17 የመኸር ወቅት በአሲዳማነት የተጠቃ ከ40 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በኖራ አክሞ የተለያዩ አዝርዕቶችን በመዝራት የዞኑን ምርታማነት ማሳደግ መቻሉን አቶ ዳዲ አስታውቀዋል፡፡ የአፈር አሲዳማነቱን በኖራ በማከመም አበረታች ውጤት እየተገኘ ስለመሆኑ ያመላክታሉ፡፡

የወልመራ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የእርሻና መሬት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ተሾመም በዘንድሮው የመኸር ወቅት ከሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል ጋር በመተባበርና በኦሮሚያ ግብርና ቢሮና በዞኑ ድጋፍ በአሲድ የተጠቃ መሬትን በኖራ በማከም ምርታማነትን ማሳደግ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

በ853 ሄክታር መሬት ላይ የተደራጁ 173 አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም እርሻ መሬታቸውን በኖራ አክመው በገብስ ዘር መሸፈናቸውን አቶ ደሳለኝ ጠቅሰው፣ ውጤቱም አስደሳች መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የአካባቢው መሬት በአሲዳማነት በመጠቃቱ ምክንያት ምርት የመስጠት አቅሙ ተዳክሞ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ደሳለኝ፤ መንግሥት በግብርናው ዘርፍ ባደረጋቸው ማሻሻያዎች ምርታማነት እየጨመረ እንደሚገኝና የአካባቢው አርሶ አደሮችም መሬታቸውን በኖራ የማከሙን ቴክኖሎጂ እየተጠቀሙ ውጤት ማስመዝገብ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

በአሲድ የተጠቁ መሬቶች ከዚህ በፊት ማዳበሪያ ቢደረግላቸውም የሚሰጡት ምርት አነስተኛ ነበር ያሉት አቶ ደሳለኝ፤ በኖራ እያከሙ መዝራት ከተጀመረ ከአስር ዓመታት ወዲህ ግን አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል፡፡

ከወረዳው በቅርበት የሚገኘው የጉደር ኖራ ፋብሪካም መሬቱን ለማከም የሚያስፈልገውን የኖራ ግብዓት ከማምረት አንጻር ለግብርናው ምርታማነት አስተዋጽኦው ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ መሬቱን በማከሙ ሂደትም ቢያንስ አንድ ሺ 700 ጆንያ/ቁምጣ ጆንያ/ ኖራ በ853 ሄክታር መሬት ላይ በመጠቀም ውጤት ማምጣት መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

አርሶ አደሮች በዚህ ልክ በክላስተር ተደራጅተው መሬታቸውን በኖራ በማከምና የግብርና ፓኬጆችን በሙሉ በመጠቀም ያገኙት ውጤት በቀጣይም የባለሙያዎችን ምክር እንዲሰሙና ለተሻለ ውጤት እንዲተጉ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል ፡፡

በወልመራ ወረዳ በተጎበኘው የገብስ አዝመራ፤ አርሶ አደሮች በኖራ በታከመው መሬት ላይ ኩታ ገጠም እርሻንና ምርጥ-ዘርን በመጠቀም፣ በመስመር በመዝራትና የግብርና ፓኬጆችን ሙሉ ለሙሉ በመጠቀም በሄክታር 70 ኩንታል የሚገመት ምርት ማግኘት መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡

የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ዲዳ ጉደታ በአምቦ ከተማ አካባቢ አርሶ አደሩ የሚያመርተውን የገብስ ምርት ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት እንዲሆን በማሰብ ግዙፍ የቢራ ፋብሪካ ግንባታ እየተጠናቀቀ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ በኖራ በሚታከመው መሬት ላይ የሚመረተው የቢራ ገብስ ምርታማነት እንዲጨምርም አርሶ አደሩ በክላስተር የማረስ ልምዱን አዳብሮና አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ ኢንዱስትሪዎችን በመመገብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጥበት እድል ተፈጥሮለታል ብለዋል፡፡

ማምረት ብቻ ሳይሆን የደረሱ ሰብሎችን በሰዓቱ ሰብስቦ ወደ ጎተራ ማስገባትም የግብርናውን ዘርፍ ውጤታማ የሚያደርግ ሌላው ሥራ ነው ያሉት የዞኑ አስተዳዳሪ፤ እስከ አሁንም ከደረሱ ሰብሎች ውስጥ 40 በመቶ የሚሆነው ሰብል መሰብሰቡን ይገልጻሉ፡፡ የደረሱ ሰብሎችን በማሽኖች የመሰብሰብ ልምድ እንዳልነበር ገልጸው፤ በአሁኑ ሰዓት እንደ ገብስና ስንዴ የመሳሳሉት የደረሱ ሰብሎች በማሽኖች እንዲሰበሰቡ እየተደረገ ነው ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

በምዕራብ ሸዋ ዞን ወልመራ ወረዳ የሀሮ ቦኪ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር መልካ ጆቴ እንደሚሉት፤ ከ10 ዓመት በፊት የአካባቢው አርሶ አደሮች ስለአሲዳማ መሬቶች ምንነት አያውቁም ነበር፡፡ የወረዳው ግብርና ቢሮ በሚመራው ፕሮግራም አማካኝነት የግብርና ባለሙያዎች ለአካባቢው አርሶ አደሮች ተገቢውን ግንዛቤ በማስጨበጥ ስለአሲዳማ መሬቶችና በኖራ እየታከሙ ምርታማ ስለሚሆኑበት ሁኔታ አስተምረዋል፡፡ በተሰጠው ስልጠና መሰረትም መሬቱ በኖራ የተጠቃ ስለመሆኑ አስቀድሞ ይመረመራል፤ አሲዳማነቱ ከተረጋገጠ በኋላ በኖራ የማከሙ ስራ ይከናወናል ፡፡

መሬታችን ከ30 አመታት በፊት ጀምሮ ምርታማ አልነበረም ያሉት አርሶ አደር መልካ፤ እህል ተዘርቶ ሸማማ የሚባል ነገር እንደሚያበቅልና እሱም ቢሆን በደንብ ተመችቶት እንደማያድግ ገልጸዋል፡፡ በወቅቱ ከሚዘራው ነጭ-ገብስ ከሄክታር ከአምስት እና ስድስት ጆንያ በላይ እንደማይገኝ ጠቅሰው፤ የልማት ሠራተኞች ምስጋና ይግባቸውና በዘንድሮው ዓመት ከወረዳው ግብርና ቢሮ ጋር በመነጋገር መሬቱን አስመርምረን አስፈላጊውን የኖራ መጠን በመጠቀም ይህን የመሰለ ምርት ማግኘት ችለናል ብለዋል፡፡ ‹‹መሬት እንደሰው ይታመማል፤ ታመመ ብለንም አንተወውም፤ የሚያስፈልገውን ህክምና አድርገንለት ምርታማ እንዲሆን እናስችለዋለን እንጂ››ይላሉ፡፡

በኖራ ታክሞ የተዘራው ገብስ አዝመራ ባለፉት ዓመታት ከነበረው ጋር ሲነጻፀር እጅግ በጣም አስደሳች ነው ያሉት አቶ መልካ ፤ አርሶ አደሩ እንደከዚህ ቀደሙ በፈለገው መንገድ መጓዝ ሳይኖርበት የዘርፉ ሙያተኞች የሚሰጡትን ምክር ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል፡፡ በዚህ ቴክኖሎጂ ከዚህ በኋላ በየዓመቱ ጤፍም ይሁን ሌሎች ሰብሎችን የማምረት ተስፋ እንደተገኘም ተናግረዋል፡፡

በጉብኝት መርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱራህማን በበኩላቸው፤ መንግሥት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ቀርጾ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ግብርናው ከምግብ ፍጆታ ያለፈ ምርት በማምረት ለገበያ ማቅረብ እንዲችልም ከተለምዷዊ አሠራር ተላቆ በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የእርሻ መሬቶች ሁሉ ጾማቸውን እንዳያድሩ እና በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉም እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ ምርታማነትን ለማሳደግ ያሉትን አቅሞች በሙሉ መጠቀም እንዲቻልም አቅጣጫ ተይዞ ሰፊ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ሸዋ ዞን ተግባራዊ የተደረገው መሬትን በኖራ እያከሙ ምርታማነትን የማሳደጉና የበጋ ስንዴን በከርሰ ምድር ውሃ የማልማቱ ሥራ መንግሥት በግብርናው ዘርፍ እየወሰደ ያለውን ርምጃ ያመለክታል፡፡ በርትቶ መሥራት ከተቻለ ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችል ትልቅ ሀብትና አቅም እንዳለም የታየበት አጋጣሚ ብዙ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በወልመራ ወረዳ የታየው የቢራ ገብስ ምርታማነትም ለእዚህ አንዱ ማሳያ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

ለቢራ ፋበሪካዎች ግብዓት የሚሆን የቢራ ገብስ ከውጭ ይመጣ እንደነበር ያስታወሱት ወይዘሮ ሰዓዳ፤ በአሲድ የተጠቃውን መሬታችንን በመኖራ በማከምና የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የተገኘው ውጤት ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት መሆን የሚችል ምርት ማምረት እንደምንችል ያየንበት ነው ብለዋል፡፡

በከፍተኛ ደረጃ በአሲድ የተጠቃውን እና ምርት ለመስጠት ይቸገር የነበረውን መሬት በኖራ በማከም ከሚገመተው በላይ ምርታማነትን ማሳደግ መቻሉ ለአርሶ አደሩ ተስፋ የሰጠ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ምርት አይሠጥም ብለን ችላ ያልነው መሬት ላይ ትኩረት ሰጥተን አማራጮችን ሁሉ ተጠቅምን የምንሰራ ከሆነ ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚቻል አይተናል ሲሉ ተናግረዋል ፡፡

እሳቸው እንዳብራሩት፤ የግብርና ባለሙያዎች ቁርጠኛ ሆነው ከአርሶ አደሩ ጎን ከቆሙ አግሮ ኢኮሎጂውን በጠበቀ መንገድ ያለውን መሬት በአግባቡ በመጠቀም ከተሰራበት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አልፎ ለገበያ የሚተርፍ ምርት ማምረት ይቻላል፡፡ አርሶ አደሩ የመንግሥትን የልማት አቅጣጫዎች ከተከተለና የባለሙያዎችን ምክር ተቀብሎ ጥቅም ላይ ካዋለ አትራፊ እንጂ ተጎጂ እንደማይሆን በኖራ የታከመው አሲዳማ መሬት ምስክር ነው ፡፡

በቀጣይም ምርታማነትን ለማሳደግ መንግሥት የሚነድፋቸውን የሥራ አቅጣጫዎች አርሶ አደሩ በግብርና ባለሙያዎች እየታገዘ እንዲተግበራቸው ወይዘሮ ሰዓዳ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You