የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን ያጎለበተው ቀን

የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ላለፉት 18 ዓመታት በደማቅ ሥነሥርዓት ሲከበር ቆይቶ ዘንድሮ ላይ ደርሰዋል፡፡ ዘንድሮ ለ19ኛ ጊዜ ዛሬ በደቡብ ሕዝቦች ክልሏ አርባምንጭ ከተማ በደማቅ ሥነሥርዓት እየተከበረ ነው፡፡ አርባ ምንጭ ለበዓሉ ስታደርግ የቆየችውን ዝግጅት አጠናቃ፣ እንግዶቿንም ስትቀበል ሰንብታለች፡፡ በከተማዋ ሰሞኑን በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር የቆየው ይህ በዓል እነሆ ዛሬ ከማለዳ አንስቶ በዓሉም በደማቅ ሥነሥርዓት እየተከበረ ይገኛል፡፡

ይህ በዓል በሀገር አቀፍ ደረጃ ከኅዳር 29 ቀን 1998 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች በደማቅ ዝግጅት እየተከበረ ይገኛል። ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነታቸው እንዲከበር፣ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ፣ በቋንቋቸው እንዲማሩ እንዲዳኙና እንዲሠሩ እንዲሁም የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው እንዲወስኑ ያስቻላቸው የኢፌዴሪ ሕገመንግሥት የፀደቀበት ኅዳር 29 ቀን የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በሚል እንዲከበር ከተወሰነ ጀምሮ ቀኑን በተለያዩ ክልሎች በሚካሄዱ ዝግጅቶች በመሳተፍ በድምቀት እያከበሩት ይገኛሉ፡፡

በእነዚህ ዓመታት ሁሉ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባሕላዊ ልብሶቻቸውን ለብሰው፣ ማንነታቸውን የሚገልጹ ቁሳቁስን ይዘው እያዜሙ እየጨፈሩ ቱባ ባሕሎቻቸውን አስተዋውቀዋል፤ ከሌሎች ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር ያላቸው ትስስር ይበልጥ እንዲጎለብት አድርገዋል፤ ራሳቸውን፣ ክልላቸውን ሀገራቸውን ለማልማት ቃል ኪዳን ገብተዋል፡፡

የቀኑ መከበር ለድንቅ የሀገሪቱ ባሕሎች መጠበቅ፣ ማደግና መተዋወቅ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ጠቀሜታ እንዳለው የባሕልና ቱሪዘም ዘርፍ ባለሙያዎች እና የታሪከ አጥኚዎች ያስረዳሉ። በኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል በሀገር አቀፍ ደረጃ ኅዳር 29 ቀን 1998 ጀምሮ በየዓመቱ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ ይገኛል። የሀገራችንን ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቱባ ባሕሎች በሚገባ እንዲተዋወቁ፣ የሀገር ውስጥ እንዲሁም የውጭ አገር ቱሪስቶችን እንዲሳቡ አስተዋፅዖ ማበርከቱን የባሕልና ቱሪዝም ዘርፍ ባለሙያዎች እና የታሪከ አጥኚዎች ይናገራሉ።

ቀኑ መከበር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እሴቶች፣ ባሕሎች ወጎች እና የማንነት መገለጫዎች በስፋት እንዲተዋወቁ ተደርገዋል። ለድንቅ የሀገሪቱ ባሕሎች መጠበቅ፣ ማደግና ለሀገር ምጣኔ ሀብት እድገት አስተዋፅዖ በማድረግም የበኩሉን ሚና ተጫውቷል ሲሉ ባለሙያዎቹና አጥኚዎቹ ያስረዳሉ።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ የባሕል ታሪክ እና ቅርስ ጥናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ለማ እንዳስታወቁት፤ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል በየዓመቱ በጋራ መከበሩ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ይበልጥ እንዲጠናከር አድርጓል፤ በዓሉ ለሕዝቦች አንድነት መጠናከር እና ለአካታችነት ጉልህ አስተዋፅዖ አበርክቷል።

ኢትዮጵያ ከ75 በላይ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአንድነት የሚኖሩባት ሀገር ናት። እነዚህ ሁሉ የበርካታ ቱባ ባሕሎች ባለቤቶች ናቸው። ባሕሎቹ ለባሕልና ቱሪዝም መጠናከር ማደግ የጎላ አስተዋፅዖ አላቸው።

ባለፉት 18 ዓመታት በተከበሩት የብሔር ብሔረሰቦች በዓላት አማካይነት በየክልሎቹ የሚገኙ ባሕሎችና ራሳቸው ክልሎቹም ከመላ ዓለም ሀገራት በመጡ ቱሪስቶች እንዲሁም በሀገር ውስጥ ጎብኚዎች መጎብኘታቸውን አቶ ወንድሙ ጠቅሰዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱ የአያሌ ቱባ ባሕሎች እና የተፈጥሮ ሀብቶች መገኛ የሆነው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል መሆኑን ጠቅሰዋል።

እንደ አቶ ወንድሙ ገለጻ፤ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል 13 ብሔር ብሔረሰቦች ይገኛሉ። ዘጠኙ የኦሞቲከ ቋንቋ ተናጋሪ ናቸው። እነዚህም የዳውሮ፣ የኮንታ ፣ የካፋ ፣ የማኦ ፣ የፃራ፣ የቤንች፣ የሸኮ ፣ የሸካ እና የዲዚ ብሔረሰቦች ናቸው።

እሳቸው እንዳሉት፤ አራቱ ብሔረሰቦች ደግሞ የናይሎ ሰሐራን ቋንቋ ተናጋሪዎች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ እነዚህም አርብቶ አደሮች እና ከፊል አርብቶ አደሮች ናቸው፡፡ ብሔረሰቦቹም የሜኒክ፣ የዝልማሙ፣ የሱሪ፣ የማጃንግ ብሔረሰቦች ናቸው። የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል እነዚህ 13 ብሔረሰቦች በአብሮነት፣ በአንድነት እና በአካታችነት የመሠረቱት ክልል ነው። በክልሉ በወረዳ፣ በዞን እና በክልል ደረጃ በዓሉ ይከበራል።

የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በአርባ ምንጭ ከተማ ዛሬ ከመከበሩ አስቀድሞ በእያንዳንዱ ክልል ብሔር ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን ባሳተፈ መልኩ ለሳምንት ያህል ሲከበር ቆይቷል። በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልልም ይሄው ተደርጓል፤ በዚህም የአገር አንድነትን፣ የሕዝቦች ፍቅርን፣ ሠላምን፣ መተሳሰርንና ቅንጅትን፣ ለማጠናከር በሚያስችል መልኩ ተከብሯል፡፡

እንደ አቶ ወንድሙ ገለጻ፤ በክልሉ 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በዓል የተከበረው የክልሉን 13 ብሔረሰቦች ባሕላዊ ጨዋታዎችን በመጫወትና ልዩ ልዩ ትርዒቶችን በማሳየት ነው፡፡ በዚህም የተለያዩ ባሕላዊ አልባሳት፣ የወግ እና የባሕል እቃዎች፣ የመገልገያ ቁሳቁስን ጨምሮ በርካታ እሴቶች ቀርበዋል። ብሔረሰቦቹ ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች እና ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ያላቸውን አብሮነት በሚያሳዩና በሚያጠናክሩ መልኩ ሲከበር ሰንብቷል፡፡

በዓሉ ዛሬ በአርባ ምንጭ ከተማ ሲከበርም የመላ ሀገሪቱ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባሕላዊ አልባሳት፣ ባሕላዊ አመጋገቦች፣ ባሕላዊ ጭፈራዎች፣ የወግ እና የባሕል እቃዎችን ጨምሮ የሀገራችን ኅብረ ብሔራዊ ቱባ ባሕሎች መገለጫዎች ለእይታ ይቀርቡበታል። እነዚህ ባሕላዊ እሴቶችም የአብሮነት፣ የአካታችነት እና የአንድነት መገለጫዎች ስለሆኑ የሕዝቡን የቆየ በጋራ የመኖር ባሕል ለማሳየት ያስችላሉ።

ከቱሪዝም አኳያም ፋይዳ እንዳለው አቶ ወንድሙ ይገልጻሉ፡፡ በቅድሚያ የውጭ ጎብኚዎች እዚህ መጥተው የሚጎበኙበትን ዕድል እየፈጠረ ነው፤ ከጎብኚዎቹ የውጭ ምንዛሪ የሚገኝበትን ሁኔታ ያሰፋል፤ በሁለተኛነት ደግሞ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ከአንዱ አካባቢ ወደ ሌላው አካባቢ በመሄድ የባሕል ልውውጥ የሚያደርጉበት ነው።

ከመላው ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰብ በዓል ለማክበር ወደ አርባምንጭ ከተማ የሚጓዙ ልዑካን ቡድኖች በወላይታ ሶዶ እንዲሁም በአርባምንጭ ከተማም በተመሳሳይ ከፍተኛ አቀባበል እንደተደረገላቸው አመላክተዋል። በበዓሉ ወቅት የተለያዩ ባሕላዊ አልባሳት፣ ባሕላዊ ምግቦች እና መጠጦች፣ የወግ እና የባሕል እቃዎች ለሽያጭ የሚቀርቡበት፣ የሚጎበኙበት፣ እና በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ አገር ጎብኚዎች ወደ አካባቢው የሚገቡበት መሆኑንም ተናግረው፣ ለቱሪዝም ዘርፉም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ብለዋል። በዓሉ በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች እና ከተሞች እየተከበረ እዚህ መድረሱ የሕዝቦችን አንድነት፣ አካታችነት እና ትስስር እያጠናከረ መምጣቱንም ያመለክታል ይላሉ።

ከምንም በላይ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በሀገር ደረጃ ሠላም፣ ፍቅር፣ አንድነት እና አብሮነት እንዲጠናከር ለማድረግ በጋራ ወጥተው አንድ መሆናቸውን የሚገልፁበት ሁነት ነው ሲሉም ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ ብዝኃ-ባሕል ያላት ሀገር መሆኗን የሚያሳይ ነው ይላሉ። ብዝኃነት በኢትዮጵያ ውስጥ ውበት እና የአንድነት እና የአብሮነት መገለጫ መሆኑን እንደሚያሳይ አመልክተው፣ በዓሉ በደማቅ ሁኔታ በየጊዜው እየተከበረ እንዲቀጥል መደረግ እንዳለበትም ጠቁመዋል።

አቶ ወንድሙ ብሔሮችና ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከዚህ በዓል በተጨማሪ ባሕሎቻቸውን የሚያስተዋውቁባቸው፣ ማንነታቸውን የሚገልጹ ባቸው እንደ ዘመን መለወጫ ያሉ ሌሎች የተለያዩ በዓላት እንዳሏቸውም ጠቅሰዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ የሲዳማ፣ የዳውሮ፣ የከፋ፣ የቤንች፣ የሸካ ብሔረሰቦች የራሳቸውን የዘመን መለወጫ በዓላት ያከብራሉ፤ በየክልሉ ያሉ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችም እንዲሁ የራሳቸውን ባሕል፣ ወግ የሚያንፀባርቁባቸው በዓላት እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡

የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚከበሩ መሆናቸው ደግሞ እነዚህን ባሕሎች የበለጠ ለማስተዋወቅ ሰፊ ዕድል ይፈጥራል ይላሉ፡፡ የብሔሮችና ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተወካዮች የማያቋቸውን ባሕሎች እንዲያዩ፣ እርስበርስ እንዲተዋወቁ፣ ባሕላቸውን ቋንቋቸውን ማንነታቸውን እንዲያስተዋውቁ በማገዝ በኩል ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለው አመላክተዋል፡፡

አቶ ጌታቸው ገብረፃዲቅ የከምባታ ብሔረሰብ አባል ናቸው፤ በከምባታ ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ባለሙያ ሆነው ሠርተዋል፤ በአርባ ምንጭ ከተማ የሚከበረው 19ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ባለፉት 18 ዓመታት ሲከበር እንደታየው ሁሉ የኢትዮጵያን ኅብረብሔራዊነት በሚገባ ለማሳየት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ይላሉ፡፡ የተለያዩ የአለባበስ፣ የውዝዋዜ፣ የአመጋገብ፣ ወዘተ ባሕሎች ባለፀጋ በሆነችው ኢትዮጵያ ይህ የአደባባይ በዓል የባሕል ትውውቅ ለማድረግ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ በዓሉም እንደ ሀገር እና እንደየብሔረሰቡ በልዩነት ውስጥ ያለውን ውበት ለማየት ያግዛል ሲሉ አስታውቀዋል።

በመስሕብ ደረጃ በተለይ በአዲሱ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብቻ ገና በርካታ የቱሪስት መስሕቦች እንዳሉ ጠቅሰው፣ ከእነዚህም መካከል በዞኑ ሕዝብና አስተዳደር እንዲለማ የተደረገውን ከዱራሜ ከተማ ቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘውን የአምበርቾ 777 ተራራን በአብነት ጠቅሰዋል፡፡

በአምበርቾ ተራራ ላይ 777 ደረጃዎች በሰው ጉልበት መሠራታቸውንና ተራራውን የቱሪስት መስሕብ ማድረግ መቻሉን ተናግረው፣ ይህ በመሆኑ በርካታ ቱሪስቶችን መሳብ እያቻለ መሆኑን አስታውቀዋል። ስፍራው መጎብኘት ከጀመረ ሦስት ዓመት እንደሆነውም ገልጸዋል።

በሌሎች መዳረሻዎች ላይ መሥራት ከተቻለ በርካታ ቱሪስቶች መሳብ እንደሚቻል ገልጸዋል። አርባምንጭ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ከምባታም ሀድያም ሲዳማም በተመሣሣይ ከፍተኛ አቅም ያላቸው ዞኖች ክልሎችና ብሔር ብሔረሰቦች ናቸው።

የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የከምባታ ብሔረሰብ እነዚህን ባሕሎቹን አውጥቶ እንዲያሳይ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ ቱባ ባሕሉን ለማስተዋወቅ እና አሁን ላለው ትውልድ ለማስተላለፍ እንደሚያግዝ ጠቅሰው፣ ባለፉት 18 ዓመታት የተከበረው ይህ በዓል ለከምባታ ማኅበረሰብ አኗኗር፣ ወግ፣ ባሕሉን እና የቱሪዝም መስሕቦቹን ለማሳደግ፣ ለማስቀጠል እና ለጎብኚዎች ለማስተዋወቅ ትልቅ አስተዋፅዖ ማበርከቱን ገልጸዋል።

በከምባታ ብሔረሰብ ዘንድ በጦርነት እና በሠላሙ ጊዜ የሚለበሱ የባሕል ልብሶች እንዳሉም ጠቅሰው፣ እነዚህን አልባሳት ጨምሮ በርካታ የባሕል ቁሳቁስ በ19ኛው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ዝግጅት ላይም እንደሚቀርቡ ተናግረዋል፡፡ በአጠቃላይ የማይዳሰሱና የሚዳሰሱ ባሕላዊ ቅርሶችን በመያዝ በዓሉን ለማክበር በቂ ዝግጅት መደረጉንም ያስታወቁት።

ይህም ከግሎባላይዜሽን ጫና የተነሳ በአዲሱ ትውልድ ላይ ሊደርስበት የሚችውን የባሕል ብረዛ ለመከላከልና ቱባ ባሕሉን እንዲጠብቅ የሚያስችሉ ዝግጅቶች የተደረጉበት መሆኑንም ገልጸዋል። በዝግጅቱ ቱባ ባሕሉን በሚገባ ያላወቁ እንዲያውቁ ለማድረግ ይሠራል። በእድሜ ጠና ያሉ አባቶች፣ እናቶች ለአዲሱ ትውልድ የማስተዋወቅ፣ የአንገት አጨፋፈሩን፣ የእግሬ አጣጣሉን፣ አለባበሱን ቱባ ባሕሉን ሳይለቅ እንደወረደ እንዲጫወቱ ለማድረግ ዝግጀት መደረጉም አስታውቀዋል፡፡ በዓሉ ባሕልን ለትውልድ ለማውረስ ለሚከናወኑ ተግባሮች ባለው ትልቅ ሚና መሠረትም ዝግጅት ተደርጓል ይላሉ።

በዞኑ በርካታ ለቱሪስት መዳረሻነት ሊያገለግሉ የሚችሉ ባሕላዊ፣ ተፈጥሯዊ ሀብቶች እንዳሉ ጠቅሰው፣ እነዚህ ቱባ ባሕሎች በአርባ ምንጭ ከተማ በተዘጋጀው 19ኛ ዓመት የብሔሮች ብሔረሰቦች በዓል ላይ ለማቅረብ ዝግጅት ተደርጎ በዓሉ ከሚከበርባት አርባ ምንጭ ከተማ መገባቱን ተናግረዋል፡፡ አቶ ጌታቸው ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ጠብቀን ኢትዮጵያን ለማበልፀግ በርትተን እንሥራ ሲሉም ለመላው ኢትዮጵያውያን መልዕክት አስተላልፈዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን እሁድ ኅዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You