ሙስና በሀገራችን ስር የሰደደ ፣ አጠቃላይ በሆነው የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መስተጋብሮች ላይ ፈተና ሆኖ የተጋረጠ የከፋ ችግር ነው። ችግሩ ትናንት ላይ ብቻ ሳይሆን ዛሬም ሀገርን ከፍያለ ዋጋ እያስከፈለ የሚገኝ፤ ለጀመርነው ለውጥም ትልቅ ተግዳሮት የሆነ ነው።
የሙስና ችግር በኢትዮጵያ ከኑሮ ውድነትና ሥራ አጥነት ቀጥሎ የሀገር ደህንነት ስጋት ስለመሆኑ በመንግሥት ይፋ ከሆነ ውሎ አድሯል። በአንድ በወቅት መንግሥት ቀይ መስመር ብሎ የሰየመውን የሌብነት ተግባር ሙሰኞች ቀይ ምንጣፍ በማድረግ ሲረማመዱበት እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መናገራቸው፤ ችግሩን ለመግታትም ብሔራዊ ፀረ ሙስና ኮሚቴ መቋቋሙም ይታወሳል።
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ ሙስና የማኅበረሰቡን የሞራል፣ የሕግና ፍትህ እሴቶች የሚያፈርስ ፣ ነባር የግብረገብ እሴቶችን የሚያደበዝዝ ፣ አጠቃላይ ለሆነው የማኅበረሰብ ህልውና አደጋ እንደሆነ ይታመናል፡፡ የተጋነነ ምቾት፣ የስግብግብነትና ራስ ወዳድነት መንፈስ የተጠናወተው እኩይ ምግባር መላበስ ነው። በጥቂቶች ብዙኃኑን የሚበክል አጥፊ ድርጊት ነው። ኢ-ፍትሐዊነት፣ የግል ጥቅም አሳዳጅነት፣ ነውረኝነት፣ አድልዎ እና የሞራል ዝቅጠት እንዲለመዱ የሚያደርግ ነው።
በመንግሥት ተቋማት እንደሚዘወተር በብዛት ቢገለጽም ከአነስተኛ ሀገር በቀል እስከ ድንበር ተሻጋሪ ኩባንያዎች እንዲሁም መንግሥታዊ ባልሆኑና በግል ድርጅቶችም የሚስተዋል የከፋ ችግር ነው። ድህነትን የሚያባብስ ፣ ሰብዓዊ መብትና ክብርን የሚጋፋ፣ ዕድገትን የሚጎትት ፣ በሀገር ውስጥ እና በሀገራት መካከል ግጭት የሚቀሰቅስ ፤ የመንግሥትን ቅቡልነት እና ዴሞክራሲን የሚፈታተን ነው ።
ጠንክሮ መሥራትን የሚኮንን፣ ሳይሰሩ መብላትን የሚያጀግን፣ የአጋርነትን ሞራል የሚሰብር፣ ሀገርን ለውጫዊ ደህንነት ስጋት አደጋ የሚጥል፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን የሚያቀጭጭ፣ ውስጣዊ ሰላምንና መረጋጋትን የሚፈትን፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና አጠቃላይ ዘላቂ ልማትን የሚገታ ነው። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ሙስና ይዞት ሊመጣ የሚችለው መዘዝ የከፋ እንደሚሆን ይታመናል።
የሙስና ችግር ቀደም ባለው ሥርዓት ምን ያህል ሀገር እና ሕዝብን መጠነ ሰፊ ዋጋ እንዳስከፈሉ የሚታወስ ነው። የመንግሥት ባለስልጣናት በተናጠል እና በተደራጀ መንገድ የሀገርን ሀብት ከመቀራመት ባለፈ፤ ሀብትን ከሀገር በማስወጣት ወንጀሎች በስፋት ሲሳተፉ መቆየታቸውም የአደባባይ ምስጢር ነው። ችግሩ በለውጡ ማግስትም ለሀገር ህልውና ተጨባጭ አደጋ በመሆን ሀገርን እና ሕዝብን ብዙ ያልተገባ ዋጋ አስከፍሏል።
ችግሩ ዛሬም ቢሆን፤ በታችኛው መዋቅርና በመካከለኛ ደረጃ ባሉ ተቋማት ሠራተኞች ላይ የሚስተዋል ነው ፤ በተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎት ፍለጋ የሚሄዱ ዜጎች ከሙስና ጋር በተያያዘ በሚያጋጥሟቸው እንግልቶች ዙሪያ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሲጮኹ መስማት የተለመደ ነው። አገልግሎቶችን ለማግኘት ተጨማሪ ክፍያ የሚጠየቁበት ሁኔታም እንዳለ በስፋት ሲነሳ ይስተዋላል።
ችግሩን ለመቅረፍ መንግሥት በየወቅቱ የተለያዩ ርምጃዎችን እየወሰደ ቢሆንም፤ ከችግሩ ስፋት እና ጥልቀት ከዚያም ባለፈ ወንጀሉ ዕለት ተዕለት እየተወሳሰበ መምጣቱ የመከላከል ሥራውን ፈትኖታል። በተለይም ቀደም ባለው ጊዜ በሙስና ዙሪያ የነበረው የተዛባ አተያይ አሁን ላይ ችግሩ እንዲገነግን ፣ ሕዝቡም ከሙስና ጋር እንዲላመድ እና ችግሩን አቅሎ እንዲያይ አድርጎታል።
እንደ ሀገር ሁለንተናዊ ብልፅግናን እውን ለማድረግ ከፍ ባለ መነቃቃት ውስጥ ባለችው ሀገራችን ሙስና ትልቁ የለውጡ ፈተና መሆኑ የማይቀር ነው። የመከላከሉን ሥራ ለመንግሥት ብቻ ትቶ ፤ መንግሥት እንዳደረገ ያድርገው የሚባል አይደለም፡፡ ከዚህ ይልቅ የሁሉንም ዜጋ ንቁ ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው።
ችግሩን ለዘለቄታው ለመከላከል ፣ በተለይም ሀገር ተረካቢው ትውልድ ሙስናን የሚጠየፍ ሆኖ እንዲወጣ ብዙ መሥራት እና መድከም ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ወላጆች ፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ፣ የፖለቲካ ተዋናዮች … ወዘተ ትልቁን ኃላፊነት ወስደው ሊንቀሳቀሱ ይገባል።
ችግሩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የመንግሥት እና የሕዝብ ተቋማትም የሙስናን አስከፊነት ማኅበረሰቡ እንዲገነዘብ ከማስቻል ጀምሮ የአሠራር ህጋዊነት እና ተጠያቂነትን ማስፈን፤ በቴክኖሎጂ የታገዙ የአሠራር ሥርዓቶችን በመዘርጋት ሙስናን ለመከላከል የተጀመሩ ሥራዎችን በኃላፊነት መንፈስ በቁርጠኝነት ማስቀጠል ይኖርባቸዋል!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ኅዳር 28 ቀን 2017 ዓ.ም