ለቤተሰቡ ስድስተኛ ወንድ ልጅ ናቸው:: አባታቸው ሴት ልጅ እየጠበቁ እያሉ ነው እሳቸው ይህችን ምድር የተቀላቀሉት:: ይህም ለአባታቸው ጥሩ ዜና አልነበረም:: ሁኔታው እናትና ጨቅላውን ከቤት አስከመውጣት አደረሳቸው::
እናታቸው እቅፍ እንዳሉ ከወላጅ አባታቸው ቤት የተባረሩትና አጎታቸው ዘንድ ለማደግ የተገደዱት የዕለቱ እንግዳችን አቶ ወላንሳ ኤንጋሞ ይባላሉ:: በወቅቱ ያጡትን ፍቅር፣ እንክብካቤና ድጋፍ ለማግኘት እንዲሁም በራሳቸው ለመቆም በብዙ ተንገዳግደዋል:: በብዙ መንገዳገዳቸውም ብርቱና ጠንካራ እንዲሆኑ አግዟቸዋል:: ለዚህም ነው ‹‹ትናንት መገፋቴ ዛሬ ለደረስኩበት ደረጃ መሠረት ጥሎልኝ አልፏል›› በማለት ትናንትናቸውን “በኩራት የሚናገሩት::
ከልጅነት እስከ ዕውቀት በብዙ ትግልና ውጣ ውረድ ያለፉት አቶ ወላንሳ፤ በሲዳማ ክልል ሸበዲኖ ወረዳ ሆርሶ ቀበሌ ነው የተወለዱት:: ከወላጅ እቅፍ ወጥተው በማደጋቸው ትምህርት ቤት ለመሄድ አልታደሉም:: ‹‹ከትምህርት ያጣሁትን ዕውቀት በሕይወት ውጣ ውረድ አግኝቼያለሁ›› የሚሉት አቶ ወላንሳ፤ ሥራ ሳይንቁ የሚሠሩ ጠንካራ ሠራተኛ መሆናቸውን ያስረዳሉ::
የዕድሜ እኩዮቻቸው ወደ ትምህርት ቤተ ሲሄዱ እርሳቸው ገንዘብ ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ያነፈንፉ ነበር:: ገና በለጋ ዕድሜያቸው ጀምረው በሥራ የተጉት አቶ ወላንሳ፤ ከወጣትነት ዕድሜያቸው ጀምረው አሁንም ድረስ ኑሯቸውን በሲዳማ ሰሜናዊ ዞን ሃዋሳ ዙሪያ ወረዳ ዶሬ ባፈኖ ከተማ አድርገዋል:: ኑሮን ለማሸነፍ የተለያዩ ሥራዎችን ሠርተዋል፤ ፍላጎታቸው ዕለት ዕለት እያደገ ሲመጣ ፍጥነት ጨምረው ከላይ ታች ብለዋል:: በወቅቱም በሃዋሳ ከተማ ዙሪያ በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውረው ሠርተዋል::
የመጀመሪያውን የንግድ ሥራቸውንም በሃዋሳ ዙሪያ ሸመና ከተማ በማድረግ የንግድ ሥራን ተቀላቅለዋል:: የንግድ ሥራን ‹‹ሀ›› ብለው ሲጀምሩ ቡና በትከሻቸው ተሸክመው ረጅም ርቀት በመጓዝ ነው:: ቡና ከሸበዲኖ ወረዳ እየገዙ በትከሻቸውና በእህያ ጭነው ከተማ ወስደው ይሸጡ እንደነበር ያስታውሳሉ::
ከቡና ቀጥለው በቆሎ ነግደዋል:: ቡና አላዋጣ ሲል በቆሎ፤ በቆሎም ደከም ሲል ወደ ቡና መለስ ቀለስ እያሉ በትከሻቸው፣ በአህያና ከፍ ሲል በመኪና ጭምር ከቦታ ቦታ አዘዋውረው ነግደዋል::
አቶ ወላንሳ፤ የቡና ንግድን በጨው ቁምጣ እየሰፉ በትከሻቸው ተሸክመው ብዙ ኪሎ ሜትሮችን በእግራቸው ተጉዘዋል:: ይሁንና የቡና ንግድን ከመጀመራቸው አስቀድሞ ሳንቡሳ ከመሸጥ ጀምረው ትናንሽ የሚባሉ ማንኛውንም ሥራ ሳይንቁ ሠርተዋል:: ሳንቡሳ ከመጥበስ ጀምሮ ጨው፣ ሸንኮራና ቦሎቄ ሲሸከሙና በችርቻሮ ሲሸጡ እንደነበር አስታውሰው፤ ከልጅነት እስከ ዕውቀት በብዙ ልፋትና ትጋት በሥራ እንዳደጉና በሀቅ ሠርተው ዛሬ ላይ እንደደረሱ ይናገራሉ::
በአህያ የተጀመረው የበቆሎ ንግድ ቀስ በቀስ በመኪና አለፍ ሲልም የግላቸው አይሱዙ በመግዛት እራሳቸው ሹፌር በመሆን በቆሎ ከቦታ ቦታ ኦሮሚያ ክልል ድረስ ተጓጉዘው ነግደዋል:: ችግርን ተቸግረው፤ ርሃብን ተርበው፤ ያደጉና መከራን ማሸነፍ የቻሉ ናቸው::
ከሲዳማ ክልል ባለፈ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ቡና እንዲሁም በቆሎ ሲነግዱ የኖሩት አቶ ወላንሳ በዚህ ሁኔታ የተጀመረው ንግድ አዋጭ እየሆነ የመጣላቸው ሲሆን፤ ‹‹ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል›› እንደሚባለው አንድ ሁለት እያሉ የንግድ ሥራቸውን አስፋፉ::
ከቡና እና በቆሎ ንግዳቸው ጎን ለጎን በሆቴል ኢንቨስትመንት በመሰማራት በሃዋሳ ዙሪያ ወረዳ ዶዮ ጨሌ ከተማ አነስተኛ ሆቴል ከፈቱ:: የሆቴል ሥራቸውን አጠናክረው በመቀጠል በ2007 ዓ.ም በሃዋሳ ከተማ ሌላ ሆቴል ጨመሩ::
የሆቴል ገበያው ቀዝቀዝ ሲል ቀድመው ወደሚያውቁት ቦታ ሃዋሳ ዙሪያ ወረዳ ዶሬ ከተማ እንዲሁም ሸመና ከተማ ላይ በስማቸው የተሰየሙትን ወላንሳ ሆቴሎች ከፍተው ቤተሰባቸውን መምራት ችለዋል:: በአካባቢው ታዋቂ ከሆኑት ወላንሳ ሆቴሎች በተጨማሪ በሃዋሳ ከተማ የህንጻ መሣሪያ አቅራቢም ናቸው::
በሕይወት መውጣትና መውረድ ውስጥ ያጋጠማቸውን ፈተና ሁሉ ተጋፍጠው ማለፍ የቻሉ ናቸው:: መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ሲሉ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ሥራ ሳይመርጡ በመሥራት በሥራ አድገዋል:: በዚህም ኑሯቸውን አሻሽለዋል:: ከራሳቸው አልፈው ልጆቻቸውን ጨምሮ ለሌሎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ለአካባቢው ማህበረሰብ አርዓያ ሆነዋል::
በአሁኑ ወቅትም ልጆቻቸው የሚሠሩበት የህንጻ መሣሪያን ሳይጨምር በሁለቱ ወላንሳ ሆቴሎች ብቻ 60 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል:: አቶ ወላንሳ፤ በሥራ የሚያምኑ ጠንካራ ሠራተኛ ሲሆኑ፤ ከጠንካራ ሠራተኝነታቸው ባሻገር በአካባቢያቸው አንቱ ከተባሉ የሀገር ሽማግሌዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው::
እርሳቸው እንዳሉት፤ በደረሱበት ቦታ ሁሉ አንድ ዐሻራ አስቀምጠው መውጣት ያስደስታቸዋል:: በተለይም ኃይማኖታዊ አስተምሮን በመከተል ሰዎች ህብረት እንዲፈጥሩና አንድ ሆነው ጊዜ፣ ጉልበትና አቅማቸውን ሁሉ በመልካም ሥራ ላይ እንዲያውሉ የማስተባበር ሥራ በመስራታቸው ውጤታማ ሆነዋል::
ይህም ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ ከሚሠሯቸው በጎ ሥራዎች መካከል ተጠቃሽ ሲሆን፤ በትውልድ አካባቢያቸው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲገነባ ምክንያት ሆኗቸዋል:: ትምህርት ቤቱ እንዲገነባ ጥቂት የአካባቢውን ማህበረሰብ አባላት በማስተባበር በኃላፊነት ይሠራሉ:: ለዚህም አደናቆሬ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲገነባ ያደረጉት አስተዋጽኦ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም::
በአሁኑ ወቅትም ትምህርት ቤቱ 600 የሚደርሱ ተማሪዎችን የሚማሩበት ሲሆን፤ ትምህርት ቤቱ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች የቀለም ትምህርት የሚሰጥበት ነው፤ ህጻናት የነገ ሀገር ተረካቢ እንደመሆናቸው ከቀለም ትምህርት በተጨማሪ በሥነምግባር ታንጸው እንዲያድጉ ጽኑ ፍላጎት አላቸው:: ልጆች በጥሩ ሥነምግባር ካደጉ የምንሰራት ሀገር ሰላማዊ እንደምትሆን ያምናሉ::
ለዚህም ነው ቀን ከሌት ከመደበኛ ሥራቸው በተጨማሪ በማህበራዊ ጉዳዮች የነቃ ተሳትፎ የሚያደርጉት:: በተለይም የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተስማምተው በጋራ በሚኖሩባት ሲዳማ ክልል ውስጥ ሰላም እንዲፈጠር ሰዎች በጋራ ተስማምተውና ተግባብተው እንዲኖሩ ብዙ ሠርተዋል:: ላለፉት 30 ዓመታት አካባቢ የሻመና ከተማ ቀበሌ ሊቀመንበር ሆነው ያገለገሉበት ወቅት አንድ ማሳያ እንደሆነ ይጠቅሳሉ::
በአሁኑ ወቅትም የሲዳማ ብሔራዊ ክልልዊ መንግሥት እንዲሁም በሃዋሳ ዙሪያ ወረዳ የምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ወላንሳ፤ ከግል ሥራቸው በተጨማሪ ማህበረሰቡ የጣለባቸውን ኃላፊነት በመወጣት በርካታ ሥራዎችን እየሠሩ ይገኛሉ:: የማህበረሰቡን የመልማት ጥያቄ ለመመለስ በተለይም ሌብነትን በመጸየፍ ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በጋራ በመሆን ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው እየሠሩ ይገኛሉ:: ለማህበረሰቡ ጠቃሚ ናቸው በተባሉ ማንኛቸውም የልማት ሥራዎች ገንዘባቸውን፣ ዕውቀታቸውን፣ ጊዜና ጉልበታቸውን ሳይሰስቱ እየሰጡ እንደያሚሠሩ የገለጹት አቶ ወላንሳ፤ በቅርቡም ክልሉ በማህበረሰብ ተሳትፎ አስገንብቶ ካስመረቃቸው የፖሊስ ጽህፈት ቤቶችና አገልግሎት ሰጪ የጸጥታ ማዕከላት መካከል ግንባር ቀደም ተሳታፊ ነበሩ::
የክልሉ ጸጥታና ሰላም ቢሮ በሰላምና ጸጥታ ዙሪያ እየሠራ ባለው ሥራ ከፍተኛ ተሳትፎ ያላቸው አቶ ወላንሳ፤ በዚህ ሥራ ላይ አሻራቸውን ካኖሩ የማህበረሰብ አካላት መካከል አንደኛው በመሆን ከክልሉ መንግሥት ዕውቅናን አግኝተዋል:: ለማዕከሉ ግንባታ በግላቸው 100 ሺህ ብር በማዋጣት ማህበረሰቡን በማሳተፍ ሌት ተቀን ሳይሉ ሥራቸውን ወደጎን በመተው ማዕከሉን ለመገንባት ከተሰጣቸው 90 ቀናት አስቀድመው በ54 ቀናት ውስጥ ማጠናቀቅ ችለዋል::
‹‹ሀገርን እየጎዳ ያለው ሃሳብ ማጣት እንጂ ገንዘብ ማጣት አይደለም›› የሚሉት አቶ ወላንሳ፤ ሰላም ከሌለ ማንም ሰው በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት አይችልም:: ንበረታችንን የሚጠብቁ ፖሊሶች ውጭ እያደሩ እኛ ቤታችን ማደር የለብንም:: በማለት የጸጥታ አካላት ለሥራ ምቹ በሆነ ቦታ ላይ ሆነው መሥራት እንዳለባቸው ይናገራሉ::
ይህ ምቹ የፖሊስ ጽ/ቤት 1200 ካሬ መሬት ስፋት ባለው ቦታ ደረጃውን በጠበቀ መንገድ የተገነባ ሲሆን፤ ግንባታውም በጥሬ ገንዘብ ብቻ ሰባት ሚሊዮን ብር ወጪ የጠየቀ ነው:: አጠቃላይ ማዕከሉ በ35 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ መሆኑን ተናግረዋል:: ማዕከሉ ደረጃውን የጠበቀና የደህንነት አጥር ያለው ሲሆን፤ አጠቃላይ ማህበረሰቡ ለዚህ ሥራ ከፍተኛ ተነሳሽነት የነበረው እንደሆነ ያመለክታሉ::
ትናንትን አሸንፈው ዛሬ በሆቴል ኢንቨስትመንትና በኮንስትራክሽን ግብዓቶች ንግድ የተሠማሩት አቶ ወላንሳ፤ በቀጣይም የተለያዩ ዕቅዶች እንዳላቸው ይጠቅሳሉ:: መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት በሰጠው ለየሌማት ትሩፋት በመሳተፍ ለሆቴል ግብዓት የሚሆኑ እንደ እንቁላል፣ ወተትና ስጋ የመሳሰሉትን በራሳቸው የማምረት ዕቅድ አላቸው:: በሆቴል ኢንቨስትመንት እንደመሰማራታቸውም በተጓዳኝ ለሆቴሎች ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን ማቅረብ ከቻሉ ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችላቸው ይሆናል:: ከዚህ ባለፈም ጉልህ አበርክቶ ያለው ነው:: ለዚህም መንግሥት ማስፋፋፊያ እንዲሰጠኝ ጥያቄ እያቀረብኩ ሲሆን በቀጣይ ይህንኑ ተግባራዊ አደርጋለሁ ይላሉ::
ከዚህ በተጨማሪም በአይነቱ ለየት ያለ ሁለገብ ህንጻ በሃዋሳ ከተማ የመገንባት ዕቅድ አላቸው:: ህንጻው ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችል ነው:: ለዚህም አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ የክልሉ መንግሥት የግንባታ ቦታ እንዲፈቅድላቸው ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፤ ጥያቄቸው መልስ ሲያገኝ በቀጥታ ወደ ግንባታ የሚገቡ ይሆናል:: በሃዋሳ ከተማ የሚገነቡት ህንጻ የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጥ እንደመሆኑ ለከተማዋ የሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም::
በመጨረሻም ሥራ ሳይመርጡ ዝቅ ብሎ መሥራትን ወጣቶች መለማመድ እንዳለባቸው የመከሩት አቶ ወላንሳ፤ አሁን አሁን ምንም ሳይሠሩ በአንድ ጊዜ ብዙ ገንዘብ ለማግኘት የሚያልሙና አቋራጭ መንገድ የሚፈልጉ በርካታ ወጣቶች እንዳስተዋሉ ጠቅሰዋል:: ይህ ተገቢነት የሌለው መሆኑን ገልጸው፣ ወጣቶች ለሥራ እራሳቸውን ዝግጁ ማድረግ እንዳለባቸው ይመክራሉ፤ ሰዎች ሥራ ሳይንቁ ያገኙትን ሥራ መስራት ከቻሉ በሀገሪቱ ብዙ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ይላሉ:: ለዚህም ከትንሽ ተነስተው ትልቅ ደረጃ የደረሱ በርካታ ሰዎችን በአብነት ማንሳት እንደሚቻል ነው ያስገነዘቡት::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ኅዳር 28 ቀን 2017 ዓ.ም