ዜና ሐተታ
በኢትዮጵያ ከባህላዊ የአጥንት ህክምና/ወጌሻ /ጋር ተያይዞ የጎንዮሽ ጤና ጉዳቶች እየጨመሩ መምጣቸውን /Bone Setting Associated Disability/ የተሰኘው ሀገር አቀፍ የጥናት ቡድን በቅርቡ ያካሄደው ጥናት አመላክቷል። ለመጨመሩ ምክንያቱ ምንድን ነው፣ መፍትሄውና ጉዳቱስ ምን ይመስላል ስንል ምሁራንን አነጋግረናል፡፡
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር መንግስቱ ገብረዮሐንስ በሙያቸው የአጥንትና መገጣጠሚያ ስፔሺያሊስትና የጀርባ አከርካሪ ሰብ ስፔሺያሊስት ሀኪም ናቸው። ሀገር አቀፍ የጥናት ቡድኑን ከመሰረቱት ውስጥም አንዱ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ የኢትዮጵያ አጥንትና መገጣጠሚያ ሀኪሞች ማህበር ፀሀፊም ሆነው እየሰሩ ነው፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፤ በጥናቱ ከሶስት ሺህ በላይ የሚሆኑ ከጤና ተቋማት የመጡ፣ በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉና በባህላዊ መንገድ ታክመው የአጥንትና መገጣጠሚያ ጉዳት የደረሰባቸው አካላት ተካተው መረጃ ተሰብስቧል፡፡ ለጥናቱ በተሰበሰበው መረጃ መሠረት በተለይ ወደ ጤና ተቋማት ከመጡ ሰዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ ዘርፈ ብዙ የጤና ችግሮች እንደታየባቸው ተረጋግጧል፡፡
ወደ ጤና ተቋም ከመጡት ውስጥ 77 ከመቶ ያህሉ እንዲሁም በማህረሰብ ውስጥ ያሉ 68 ከመቶ ያህሉ የጎንዮሽ ጤና ጉዳት እንዳላቸው ያብራራሉ፡፡
በጥናቱ መሰረት በባህላዊ የአጥንት ህክምና / ወጌሻ/ ምክንያት በሰዎች ላይ የሚከሰቱ የጎንዮሽ ጤና ጉዳቶች ዋነኛ መንስኤዎች ሁለት መሆናቸውን ዶክተር መንግስቱ ይጠቅሳሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንደኛው መንስኤ አላስፈላጊና ተደጋጋሚ ማሸት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ አንድ ሰው መገጣጠሚያውም ሆነ ጡንቻው ከተጎዳ በኋላ በተደጋጋሚ በሚታሽበት ጊዜ የመዳን ሂደቱን እንደሚያዘገየው ያስረዳሉ፡፡ ይኸው አላስፈላጊና በድግግሞሽ ማሸት ታማሚዎች ቋሚ ህመም እንዲኖራቸው፣ ከህመማቸው ቶሎ እንዳያገግሙ፣ እንዲያብጥ፣ መንቀሳቀስ እንዳይችሉ፣ እጃቸውንና እግራቸውን መጠቀም እንዳይችሉ እንደሚያደርጋቸውም ነው ዶክተር መንግስቱ የሚናገሩት፡፡
ሁለተኛው የጎንዮሽ ጤና ጉዳት መንስኤ አጥብቆ ማሰር መሆኑ በጥናቱ እንደተመላከተ ዶክተር መንግስቱ ይጠቁማሉ፡፡ በተለይ የጎንዮሽ ጉዳቶቹ ጊዜያዊና ቋሚ የሆነ የአካል ጉዳት፣ ጋንግሪን ፈጥሮ እግርና እጅን ማጣት ብሎም ሞት የሚያስከትል ከሆነ በአብዛኛው መንስኤው አጥብቆ ከማሰር ጋር የሚገናኝ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡
እጅና እግር ለረጅም ጊዜ ጠብቆ ሲታሰር የደም ዝውውር የማያገኝ ከሆነ እጅ ወይም እግር በስብሶ ለጋንግሪን በሽታ እንደሚያጋልጥ ይገልፃሉ። የሰውነት መበስበስ ከመጣ ደግሞ ህይወትን ለአደጋ ስለሚጥል የበሰበሰውን አካል በቀዶ ህክምና ማስወገድ የመጨረሻው አማራጭ እንደሚሆንም ነው ዶክተር መንግስቱ የሚያስረዱት፡፡
ይህ ሀገር አቀፍ ጥናት ከመካሄዱ በፊት በሁሉም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች የተጠኑ ጥናቶች ከባህላዊ የአጥንት ህክምና /ወጌሻ/ ጋር በተገናኘ በርካታ የጎንዮሽ ጤና ጉዳቶች እንደነበሩ ማሳየታቸውን ዶክተር መንግስቱ ያስታውሳሉ፡፡ ከእነዚህ የጎንዮሽ ጤና ጉዳቶች መካከል እግርና እጅን ማንቀሳቀስ አለመቻል፣ የጡንቻ መሟሸሽና ከጥቅም ውጪ መሆን፣ የስብራት አለመዳንና፣ ኢንፌክሽንና ጋንግሪን መፈጠር ብሎም ለሞት የሚዳርግ መሆኑ እንደሚገኙበት ያብራራሉ፡፡
ከዚህ በፊት በባህላዊ አጥንት ህክምና /ወጌሻ/ ምክንያት ሲከሰቱ የነበሩ የጎንዮሽ የጤና ጉዳቶች መኖራቸው ሀገር አቀፍ ጥናቱን ለማካሄድ መነሻ እንደሆነም የጠቆሙት ዶክተር መንግስቱ፤በባህላዊ የአጥንት ህክምና /ወጌሻ/ መንስኤ የሚከሰቱ የጎንዮሽ ጤና ጉዳቶችን ለመቅረፍ ጥናቱ የተለያዩ መፍትሔዎችን ማመላከቱን ያነሳሉ፡፡
በጥናቱ መሰረት በአብዛኛው ለዚህ የጎንዮሽ ጉዳት ተጋላጭ ሕፃናት በመሆናቸው በተለይ ትምህርት ቤት አካባቢ የሚኖሩ ማህበረሰቦች ማለትም ልጆች፣ ወላጆች፣ መምህራንና ሌሎች አካላት የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን አማራጮችን በመጠቀም ስለጉዳዩ ግንዛቤ እንዲያገኙ ማድረግ፣ ማህበረሰቡን ማንቃትና መከላከል ላይ መስራት አንዱና ዋነኛው በጥናቱ የተመላከተ መፍትሄ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
በሌላ በኩል አደጋ ሲያጋጥም ከሚያሹና አጥብቀው ከሚያስሩ አካላት በተለይም ከባህላዊ የአጥንት ሀኪሞች /ወጌሻዎች/ ጋር ምክክር ማድረግና ስልጠና መስጠት፣ አሰራራቸውን እንዲያዘምኑ ማድረግ የጎንዮሽ ጤና ጉዳቱን ለመቀነስ በጥናቱ እንደመፍትሄ ከተቀመጡ ነጥቦች ውስጥ ሁለተኛው መሆኑን ዶክተር መንግስቱ ይናገራሉ፡፡
ሰዎች የአጥንትና መገጣጠሚያ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ጤና ተቋማት እንደሚመጡ የሚናገሩት ዶክተር መንግስቱ፤ ችግራቸው በትክክል ባለመታወቁ ከአራቱ አንዱ መጀመሪያ ወደ ጤና ተቋም መጥተው ከዚያም ወደ ባህላዊ የአጥንት ህክምና/ዊጌሻ/ እንደሄዱ ጥናቱ ማሳየቱን ያመለክታሉ፡፡ ይህም በጤና ተቋማት በኩል ችግሮች መኖራቸውን ጥናቱ እንደጠቆመና ጤና ተቋማትን፣ የተለያዩ የጤና ባለሙያዎችን፣ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞችን ማብቃትና ማሰልጠን ለዚህ ችግር መፍትሄ መሆኑን እንዳመላከተ ይጠቁማሉ፡፡
በባህላዊ የአጥንት ህክምና /ወጌሻ/ መንስኤ ለሚከሰቱ የጎንዮሽ ጤና ጉዳቶች አብዛኛዎቹ ሰለባዎች ሕፃናት መሆናቸውን ዶክተር መንግስቱ አንስተው፤ እነዚህ የጤና ጉዳቶች በዚሁ ከቀጠሉና መፍትሄ ካልተበጀላቸው የጤና ጉዳቱ ቀላል እንዳልሆነ ይገልፃሉ፡፡ በተለይ ቋሚ የአካል ጉዳት የሚያስተናግዱ ሕፃናት እንደሚበዙ ያመላክታሉ፡፡ ይህንኑ ተከትሎ በቤተሰብም ሆነ በሀገር ደረጃ የኢኮኖሚ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ህዳር 27/2017 ዓ.ም