አዲስ አበባ፡– “እኛ ለዜጎቻችን የምናስበውን ያህል ለግብጾችም ለሱዳኖችም እናስባለን፤ ለሁሉም የሚሻለው ባልተገባ መንገድ ወዲህና ወዲያ ማለት ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ መነጋገር ነው” ሲሉ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) አስታወቁ። ከዓባይ ግድብ በኋላ ብዙ የዓባይ ግድቦችን መገንባት እንደሚጠበቅም አመለከቱ።
ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር)፣ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ ኢትዮጵያ ሁሌም የምትከተለው የፍትሃዊ ተጠቃሚነትን መርህ ነው። በምትከተለው መርህ መሠረት ለራሷ ዜጎች እንደምታስበው ሁሉ ለግብጾችም፣ ለሱዳኖችም ታስባለች፡፡
በአሁኑ ወቅትም ለግብጻውያን የሚሻለው ባልተገባ መንገድ ወዲህና ወዲያ ማለት ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ መነጋገር ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ጥሩው እና አዋጩ መንገድ የትብብር ማዕቀፉ ነው ብለዋል፡፡ ይህ ሕግ ሆኖ የጸደቀው ማሕቀፍ፤ ሁሉንም የተፋሰሱ ሀገሮች ማስጠለል የሚችል ትልቅ ጥላ ነው ሲሉም አስረድተዋል።
“ግብጾች የዓባይ ግድብ ግንባታ እንዳይሳካ ያላደረጉትና ያልሞከሩት ጥረት አልነበረም፡፡ ዛሬ ሲታይ ግን እነርሱ ያሉት ሳይሆን እኛ ያልነው ትክክል ሆኖ ተገኝቷል፡፡” ያሉት ሚኒስትሩ፤ ግድቡ ሙሉ በሙሉ እነርሱን የሚጎዳ አድርገው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሲናገሩ የነበረ ቢሆንም፤ መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን እንደንግግራቸው አለመሆኑ በግልጽ ሊታወቅ መቻሉን አመልክተዋል፡፡
እንደሚኒስትሩ ከሆነ፤ ግብጻውያኑ በዚህ ተረትተው የሚቆሙ እንዳልሆነ ከድርጊታቸው መረዳት ይቻላል። አይሳካላቸውም እንጂ በቀጣይም ሌላ ከመሞከር አይቦዝኑም። ቀደም ሲል የዓባይ ግድብ ግንባታ ፍጻሜ እንዳያገኝ በብዙ ደክመዋል፤ ግድቡ ኢትዮጵያን ብዙ ዋጋ ያስከፈላት ቢሆንም ግንባታውን ማሳካት ተችሏል። እውነትን ይዘን አሸናፊ መሆን ችለናል፡፡ አሁንም ማድረግ ያለብን ሥራችንን በአግባቡ መሥራት ነው፡፡
በአሁኑ ሰዓት በዓለም መድረክ ላይ ስለ ዓባይ ግድብ እምብዛም እያወሩ አይደለም፡፡ ያንን ትተው አሁን እያደረጉ ያለው ጎረቤት ሀገሮችን በኢትዮጵያ ላይ ማነሳሳት ነው፡፡ ይህ አካሔዳቸው አያዋጣቸውም ያሉት ሚኒስትሩ፣ ምናልባት ለሕዝባቸው “ኢትዮጵያን እንዲህና እንዲያ አድርገናታል” ለማለት ካልሆነ በስተቀር የሚያተርፉት ነገር አይኖርም፡፡ በዓባይ ግድብ ጉዳይ ሕዝባቸውን ሲዋሹ ነበር፤ በመጨረሻም እውነታው ሌላ ሆኖ በመገኘቱ ሕዝቡ ራሱ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ጥያቄ የሚያነሳባቸው ይሆናል፡፡” ብለዋል፡፡
ለኢትዮጵያውያን ትልቁ አዋጭ ጉዳይ በአንድነት ቆሞ የተጀመረውን ሥራ አጠናክሮ መቀጠል ነው፡፡ የዓባይ ግድብን ገንብተን አጠናቅቀናል፤ ይህም በጣም የተሳካ ሥራ ነው፡፡ ከሕዳሴ በኋላ በጣም ብዙ ሕዳሴዎች መገንባት አለባቸው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ዳቡስ፣ ዴደሳ፣ በሽሎ፣ አንገረብ፣ በለስ እነዚህ ትልልቅ የዓባይ ወንዝ ገባር ወንዞች ናቸው፡፡ እነዚህን ሀብቶቻችንን አስበንበት ለኢነርጂ፣ ለመስኖና ለሁሉም የልማት ሥራዎች ለማከናወን ቆርጠን መነሳት እንደሚያስፈልገን ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር) ጠቁመዋል፡፡
አሁን ላይ ያላሰብነውን ጭምር እንድናስብ እያደረጉን ነው፡፡ እንደሚታወቀውም የዓባይ ግድብን ስንጠቀምበት የነበረው ለኢነርጂ ብቻ ነበር፡፡ በአካባቢው በመስኖ ሊለማ የሚችል መሬት አለን፡፡ በጣም ገፍተው ከመጡ መሬቱም ውሃው የእኛ ነው፤ ሉዓላዊ ሀገር ነን፤ በአካባቢው ያለው ያንን ሰፊ መሬት መጠቀም እንችላለን ብለዋል፡፡
የናይል ተፋሰስ ሀገራት ማእቀፍ ከተፋሰሱ ሀገራት ከግማሽ በላይ በሆኑት ሕግ ሆኖ መጽደቁ የምንኮራበት ነው፤ አሳክተነዋልም፡፡ ምክንያቱም ወደ ስድስት የሚሆኑ ሀገራት ይህንን ፈርመው በሀገር ደረጃ ሕጋቸው አድርገውታል፡፡ በቀጣይ ሕጉን ተግባራዊ የምናደርግበት የ”ናይል ሪቨር ኮሚሽንን” ማቋቋም ነው ሲሉ አስረድተዋል።
ኮሚሽን ለማቋቋም እንቅስቃሴ ጀምረናል ያሉት ሚኒስትሩ፣ ከዚህ ጋር ተያይዞም በቅርቡ ዑጋንዳ ኢንቴቤ ላይ አንድ ስብሰባ እንደነበራቸውና በስብሰባው ላይ የተገኘው ልዑክ የውሃ ሚኒስትሮች ካውንስል የሚባለው እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ እርሳቸው እንደገለጹትም፤ በስብሰባቸው ወቅት ካቀረቡት ሃሳብ አንዱ የታችኞቹ ሀገሮች እና ሌሎቹ ያልፈረሙ ሀገሮች እንዲፈርሙ ማግባባት ላይ ነው፡፡ ለዚህ ሥራ ደግሞ ኮሚቴ ተዋቅሯል። በኢትዮጵያ እምነት የትኛውም የተፋሰሱ ሀገር ከዚህ ውጭ መሆን የለበትም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሀገራቱ ይጠቀሙበታል ተብሎ ስለሚታመን ነው።
ለእኛ ትልቁ ስኬት ከማዕቀፉ ሕጋዊ መሆን ጋር በተያያዘ ቀድሞ የነበሩ ሕጎች መሻራቸው ነው፡፡ ለምሳሌ የ1959ኙን ሕግ ሁለት ሀገሮች ብቻ ወስነው እንዳሻቸው የሚያደርጉትን አካሔድ ለውጦታል፤ ለእኛ ይህ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ በቀጣይ ደግሞ ኮሚሽኑ ከመጣ እሰየው ነው፡፡ መምጣትም አለበት፤ እኛም እንደግፈዋለን፡፡ ይህ ሕግ ግን ለእኛ ሰላም የሚሰጥ ነው፤ ለሁሉም የሚጠቅም ነው ብለዋል፡፡
አሁን ከኢትዮጵያ ውጪ ብዙ ሀገሮች ስለማሕቀፉ ሆነ ስለኮሚሽኑ ስለገባቸው ተፈጻሚነቱ እንዲፋጠን እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ እኛም የምንፈልገው ይህንኑ ነው። በአሁኑ ወቅት ፍትሃዊነት የሚለውን ቃል ዑጋንዳ እና ደቡብ ሱዳን በማቀንቀን ላይ ናቸው፡፡ ቀደም ሲል ስለፍትሃዊነት ስንጮህ የነበረው ብቻችንን ነበር፤ በአሁኑ ወቅት አጋዥ አግኝተናል፡፡ ስድስት ሀገሮች ስምምነቱን ፈርመው የሀገራቸው ሕግ አካል ስላደረጉት፤ ስለዓባይ በአግባቡ በዓለም መድረክ ላይ ማውራት ጀምረዋል፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡ የናይል ወንዝ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት ከጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ተፈጻሚነት መግባቱ የሚታወስ ነው፡፡
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ህዳር 26/2017 ዓ.ም