የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን መዲና ኪዬቭ የሚገኙ ውሳኔ ሰጪ ማዕከላት ላይ ኦሬሽኒክ በተሰኘው አዲሱ የሀገሪቱ የባለስቲክ ሚሳኤል እንደሚመቱ አስጠነቀቁ። ዩክሬን ከአሜሪካ የተለገሰችውን አታካምስ ሚሳኤል በመጠቀም ሩሲያ ላይ እየፈጸመችው ያለውን ተከታታይ ጥቃት ተከትሎ ፑቲን የተቀናጀ ነው ያሉትን አጸፋዊ ምላሽ መስጠት መጀመራቸውን ተናግረዋል።
ሩሲያ ከትናንት በስቲያ ሌሊት የዩክሬን የኃይል አቅርቦትን ከመታች በኋላ ነው ፕሬዚዳንት ፑቲን የሀገራቸውን አቋም የተናገሩት። የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ለማንኛውም የሩሲያ ጥቃት ከባድ ምላሽ እንደሚሰጥ አስጠንቅቀዋል። ባለፈው ሳምንት ዩክሬን ከአሜሪካው አታካምስ በተጨማሪ ከዩናይትድ ኪንግደም የተለገሳትን ሻዶው ሚሳኤልን የሩሲያ ግዛትን ዘልቃ እያስወነጨፈች ትገኛለች።
ምዕራባውያን አጋሮች የሩሲያን ምድር በእነዚህ ሚሳኤሎች እንድትመታ ፈቃድ መስጠታቸውን ተከትሎ ነው ዩክሬን እነዚህን ጥቃቶች እየፈጸመች ያለችው። ሩሲያ በአጸፋው በርካታ ሰዓታትን
የፈጀ የድሮን እና የሚሳኤል ጥቃቶችን ፈጽማለች። በእነዚህ ጥቃቶች ሞት ባይከሰትም ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዩክሬን ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ውጪ ሆነዋል። ዘለንስኪ የሰላማዊ ሰዎች እና የሃይል መሠረተ ልማቱን ለመምታት የክላስተር አረሮች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ተናግረዋል።
“ክላስተር አረር ተሸካሚ መሣሪያዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት የሚፈጸምባቸው በጣም አደገኛ የሩስያ የጦር መሣሪያ አይነት ነው” ብለዋል ዘለንስኪ።
ሩሲያ በፈጸመችው በዚህ ጥቃት ኦሬሽኒክን ጨምሮ 90 ሚሳኤሎች እና 100 ሰው አልባ አውሮፕላኖች መሳተፋቸውን
ፕሬዚዳንት ፑቲን ተናግረዋል። እንደ ፑቲን ከሆነ ኦሬሽኒክ የተሰኘው የሩሲያ አዲሱ ባለስቲክ ሚሳኤልን ማክሸፍ አይቻልም። የአሜሪካ ባለሥልጣት ሩሲያ ጥቂት ቁጥር ያላቸው የሙከራ ኦሬሽኒክ ባለስቲክ ሚሳኤሎች ሊኖራት እንደሚችል የሚያምኑ ሲሆን በበርካታ ቁጥር ለማምረት ጊዜ ያስፈልጋታል ይላሉ።
ዘለንስኪ ፕሬዚዳንት ፑቲን “ጦርነቱን የማቆም ፍላጎት የላቸውም እንዲሁም ሌሎች ይህንን ጦርነት እንዳያቆሙ መከላከል ይፈልጋል” ሲሉ ተናግረዋል።“ጦርነቱን ማባባሱ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የሩሲያን አቋም እንድትቀበል ጫና ለማድረግ የታለመ ነው” ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ፑቲን በበኩላቸው ዩክሬን የኒውክሌር መሣሪያዎችን እንድታገኝ ሀገራቸው እንደማትፈቅድ ገልጸዋል። መሣሪያዎቹን ካገኘች ሩሲያ ማንኛውንም መሣሪያዎች ትጠቀማለች ማለታቸውን የሩሲያው መንግሥታዊ ሚዲያ አርአይኤ ዘግቧል። ባለፈው ሳምንት ስማቸው ያልተጠቀሰ ምዕራባውያን ባለሥልጣናት ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከሥልጣን ከመልቀቃቸው ከጥር ወር በፊት ለዩክሬን የኒውክሌር መሣሪያ እንዲሰጡ ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል መባሉን ቢቢሲ የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ዘገባን ጠቅሶ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ህዳር 21/2017 ዓ.ም