በዓለም አቀፍ ደረጃ እያሽቆለቆለ ያለው ኤች አይቪ /ኤድስ በሽታ በአፍጋኒስታን፣ ግብፅ፣ በፊጂ፣ በፊሊፒንስ፣ በፓፕዋ ኒው ጊኒ እና በሳዑዲ አረቢያ በአውሮፓውያኑ 2010 እስከ 2023 ባለው ጊዜ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከ100 ፐርሰንት በላይ ጭማሪ እንዳሳየ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤች አይቪ/ኤድስ ፕሮግራም (ዩኤንኤድስ) ገልጿል ።
ከአጠቃላይ ሕዝባቸው ጋር ሲነጻጸር እንደ አፍጋኒስታን፣ ግብፅ እና ሳዑዲ አረቢያ ባሉ ሀገራት በኤች አይ የተያዙ ሰዎች በአንጻራዊነት ዝቅተኛ ነው። ግን አሁንም ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን አሳስቧል፡፡
የሀገራት መሪዎች በተቻለ መጠን የመከላከል አማራጮችን በማስፋት እና ሰዎች የጤና አገልግሎቶችን እንዳያገኙ የሚያደርጉ እንቅፋቶችን የማስወገድ ተግባራት ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ በኤች አይቪ የሚያዙ እንዲሁም እያስከተለ ያለው ሞት በከፍተኛ ደረጃ ቢቀንስም የሕዝብ ስጋትነቱን ለማስቆም ዓለም በመንገድ ላይ እንዳልሆነች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤች አይቪ/ኤድስ ፕሮግራም (ዩኤንኤድስ) አስጠነቀቀ።
ኢትዮጵያ በኤችአይቪ/ኤድስ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር በመቀነስ ረገድ ባለፉት አስራ አራት ዓመታት ጥሩ እመርታ ካሳዩ የአፍሪካ ሀገራት መካከል የተጠቀሰች ሲሆን፣ ይህም 60 በመቶ መሆኑ ተገልጿል።
እንደ ዩኤንኤድስ ከሆነ በዓለማችን ላይ 39 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሰዎች ኤድስ በደማቸው ያለባቸው ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ ግማሾቹ በደቡብ እና ምሥራቃዊ አፍሪካ ይገኛሉ።
በዓለማችን ላይ በኤችአይቪ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከአውሮፓውያኑ 2010 ጀምሮ በ39 በመቶ የቀነሰ ሲሆን፣ በኤድስ የሚሞቱትም እንዲሁ በግማሽ ቀንሷል።
ኬንያ፣ ማላዊ፣ ዚምባብዌ እና ኔፓል ኤችአይቪ/ኤድስን ከአውሮፓውያኑ 2010 ጀምሮ በተሳካ ሁኔታ በ75 በመቶ መቀነስ የቻሉ ሀገራት ናቸው።
እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት ኤድስን በመዋጋት ረገድ አፍሪካ እንደ አህጉር ቀዳሚውን ቦታ ይዛለች።
ሌሎች 18 ሀገራት ደግሞ ከአውሮፓውያኑ 2010 ጀምሮ በየዓመቱ በኤችአይቪ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር 60 በመቶ መቀነስ ችለዋል።
አብዛኞቹ ከሰሃራ በታች ያሉ ሀገራት ሲሆኑ፤ እነሱም ሌሶቶ፣ ኢስዋቲኒ፣ ቤኒን፣ ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ፣ ቦትስዋና፣ ኤርትራ፣ ላይቤሪያ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ቶጎ፣ ዛምቢያ፣ ቡሩንዲ፣ ጊኒ ቢሳው እንዲሁም ካዛኪስታን፣ ፖርቹጋል፣ ቤላሩስ እና ጣሊያን ናቸው።
ኤች አይቪ በደማቸው ውስጥ ካሉ የዓለማችን ሕዝቦች መካከል 77 በመቶ የፀረ- ኤችአይቪ መድኃኒቶችን ይወስዳሉ። ከሰሃራ በታች ወዳሉ ሀገራት ስንመጣ ደግሞ 82 በመቶ የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒቶች እንደሚወስዱ መረጃዎች ያሳያሉ።
የኤችአይቪ ቀውስን ለመግታት በተደረገው ትግል ምክንያት የሰው ልጅ አማካይ ዕድሜን ማሳደግ ተችሏል። በአውሮፓውያኑ 2010 የሰው ልጅ አማካይ እድሜ 56 የነበረ ሲሆን፤ በአውሮፓውያኑ 2013 ወደ 61 አድጓል።
“ዓለም ኤድስን እንደ የሕዝብ ጤና ስጋት የማስወገድ ጎዳና ላይ አይደለም ምክንያቱም በአገልግሎት ተደራሽነት ላይ በተለይም የተገለሉ ማኅበረሰቦችን በማካተት ደረጃ ሰፊ ክፍተቶች ይታያሉ። ኤች አይቪን በመከላከል ረገድ ያለው ቀውስ አሁንም ቀጥሏል” ብለዋል።
በአፍሪካ ያለው የህክምና መስፋፋት በኤች አይቪ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በደማቸው ያለው የቫይረስ ጫና መጠን እንዳይጨምር እንዲሁም የመተላለፍ አደጋን እንዲቀንስ ማስቻሉን ዩኤንኤድስ ገልጿል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ኅዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም