ኤድስ ከሞት በላይ በሚፈራበት ዘመን ስሙ ሲጠራ በርካቶች በፍርሃት የሚሸበሩበትን ሁኔታ ለማስወገድ ከ36 ዓመታት በፊት ነው የዓለም የኤድስ ቀን መታሰብ የጀመረው። በወቅቱ አሜሪካዊው የሜዳ ቴኒስ ሻምፒዮና አርተር አሽ ተመርምሮ በሽታው እንዳለበት የተረዳበት ወቅት ነበር።
ከበሽታው ጋር ተያይዞ በነበረው አድልዎ እና መገለል በተለይም ኤድስ ከተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች ጋር በመያያዙ፤ አርተር ለዓመታት ያህል የጤናውን ሁኔታ ምሥጢራዊ አድርጎት ነበር። ስለበሽታው ከተናገረ በኋላ በፈር ቀዳጅነት ግንዛቤ ለመፍጠር የተለያየ ጥረቶችን አድርጎ ነበር።
ከ32 ዓመታት በፊት ሚያዝያ ወር ላይ አርተር የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በተገኙበት አዳራሽ ገባ።ሁሉም ካሜራቸውን ደግነው ነበር።በዚህች ወቅት በአሜሪካ ዴቪስ ካፕ ለተሰኘው ሽልማት የተመረጠ የመጀመሪያው ጥቁር መሆን ስለነበረው ሚና፣ ወይም በታላላቆቹ ዌምበልደን፣ ዩኤስ ኦፕን እና አውስትራሊያ ኦፕን የሜዳ ቴኒስ ውድድሮች ፈር ቀዳጅ ጥቁር አሸናፊ ስለመሆኑ አልነበረም።
በወንዶች የነጠላ ሻምፒዮና ውድድር የመጀመሪያ ጥቁር ሆኖ በታሪክ የተመዘገበው አርተር በልብ ህመም ምክንያት በርካታ ቀዶ ህክምናዎች አድርጎ ነበር።እነዚህን ቀዶ ህክምናዎች ተከትሎ በ36 ዓመቱ ነበር ከስፖርቱ ራሱን ያገለለው።ይህም በዚህ አዳራሽ ከመገኘቱ ከ12 ዓመታት በፊት ነው።
አርተር በግርማ ሞገሱ፣ በርቱዕ አንደበቱ፣ በጉብዝናው እና በስፖርታዊ ጨዋነቱ በውድድር ላይ ብቻ ሳይሆን ከሜዳ ውጪም ተወዳጅ ነበር።ኤድስ ገዳይ መሆኑ እና በበርካቶች ዘንድ እንደ ሞት መልዕክተኛ በሚታይበት በዚያ ወቅት ሚዲያው ስለአርተር ጤና ጭምጭምታዎችን ሰምቷል።
የአርተር የልጅነት ባልንጀራ እና የዩኤስኤ ቱደይ ጋዜጠኛ ዳግ ስሚዝ ስለሰማው ጭምጭምታ ፊት ለፊት አፋጠጠው።አርተር በማግስቱ ከአውሮፓውያኑ 1988 ጀምሮ እሱ እና የቅርብ ወዳጆቹ ብቻ የሚያውቁትን ምሥጢር በይፋ ተናገረው።“በኤድስ ተይዣለሁ አለ” የያዘው በአውሮፓውያኑ 1983 በቀዶ ህክምና ወቅት በተለገሰው በቫይረሱ በተበከለ ደም እንደሆነም ያለውን በስጋት ገለጸ።
አሜሪካ በልገሳ የሚሰጥ ደምን መመርመር የጀመረችው አርተር ከተያዘ ከሁለት ዓመት በኋላ፣ በአውሮፓውያኑ 1985 ነው።አርተር የተናገረው አስደንጋጭ ዜና ሀገሪቱን ሁሉ ከፍተኛ መሸበር ውስጥ የከተተ ነበር።ከህመሙ በተጨማሪ ሌላ አነጋጋሪ የሆነው ጉዳይ የግል መረጃን እና የሰዎችን መረጃ የማጋለጥ የፕሬስ ሥነ ምግባርን የተከተለ ነው የሚለው ነበር።
አርተር በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ “እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንድገባ መደረጌ በጣም የሚያበሳጭ ነው። የግል መረጃዬን ለመጠበቅ እንድዋሽ ልደረግ ነበር” ሲልም ተቸ። “የእኔን የጤና ሁኔታ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ አስገዳጅ የሆነ የህክምናም ሆነ አካላዊ ሁኔታ አልነበረም” ሲልም ተናገረ።
አርተር በኋላ ላይ ‘ደይስ ኦፍ ግሬስ’ በሚል ርዕስ ባሳተመው ማስታወሻ ‘ግላዊ መብቱ መከበር ነበረበት በሚል ከ700 በላይ ደብዳቤዎች ለዩኤስኤ ቱደይ መድረሱን አስፍሯል። በተጨማሪ 95 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ጋዜጣው የአርተርን ህመም ያጋለጠበትን አቋም አጥብቀው ተቃውመዋል።
አንዳንድ የኤድስ ተሟጋቾች አርተር ህመሙን መደበቁን ፤ እንደእሱ ያሉ ያገቡ ባለትዳሮች በኤችአይቪ ኤድስ ላይ ያለውን ግንዛቤ በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ እመርታ ማሳየት ይችሉ ነበር ሲሉ ተችተውታል።አርተር ስለበሽታው ይፋ ከማድረጉ ከአምስት ወራት በፊት የኤችአይቪ ቫይረስ በደሙ እንዳለ ያሳወቀው ታዋቂው አሜሪካዊው የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ማጂክ ጆንሰንን ከተነሳበት ጥያቄዎች መከላከል ይችል እንደነበር ያሰፈረ ደብዳቤ ለጋዜጣው ተልኳል።
በጋዜጣዊው መግለጫ ላይ በኤችአይቪ መያዙን በተረዳበት ወቅት ለምን በይፋ እንዳልተናገረ በተጠየቀበት ወቅት ስጋቱን ገልጾ ነበር።“መልሱ ቀላል ነው። በዚያ ጊዜ በኤችአይቪ መያዜን ይፋ ማድረግ በጣም ከባድ ነበር። ከባለቤቴ ጋር የቤተሰባችንን ግላዊ መብት በዘላቂነት ይጎዳዋል በሚል በምሥጢር ለመያዝ ወሰንን” ብሏል።
በዚሁ መግለጫ ስለበሽታው ለአምስት ዓመት ልጁ ካማራ እንባ ስለተናነቀው መናገር አልቻለም። ባለቤቱ ጂኒ እሱን ወክላ አነበበች።የዩኤስ ኤ ቱደይ የስፖርት አርታኢ ጄን ፖሊሲንሲኪ የአርተርን በኤችአይቪ መያዝ ይፋ ያደረገው ጽሁፍ እንዲታተም ያሳለፈው ውሳኔ የሚፀፀትበት ጉዳይ አይደለም።
“አርተር በ20ኛው ክፍለ ዘመን ከተከሰቱ ታላላቅ አትሌቶች አንዱ ነው። በዓለም ዘንድ ስመ ጥር ነው። በወቅቱ ለሞት በሚዳርግ ህመም መያዙ ታወቀ። ለ25 ዓመታት ጋዜጣን እንደ መምራቴ ይህ ዜና ነው” ሲል ለቢቢሲ በቅርቡ ተናግሯል።የፀፀት ስሜት ተሰምቶት እንደሆነ ሲጠየቅም “በጭራሽ አይሰማኝም። የፀፀት ስሜት ተሰማኝ ማለት በወቅቱ ውሳኔዬ የተሳሳተ ነበር ማለት ነው። ስህተት አልነበረም” ብሏል።
አርተር ኤድስ እንዳለበት ለዓለም ከገለጸ ከሶስት ወራት በኋላ በለንደን ተገኝቶ ነበር።በዚያን ወቅት ‘ፋይቲንግ ባክ’ ለተሰኘው የቢቢሲ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ቃለ መጠይቅ በተደረገለት ወቅት “የሆነ ወቅት ላይ ለሕዝብ ይፋ እንደማደርግ አውቅ ነበር። ቫይረሱ በተገኘብኝ ወቅት ጤናዬ ጥሩ ስለነበር በዚህ ሳልረበሽ ሥራዬን ለመቀጠል ወሰንኩ። በዚያን ጊዜ አደባባይ መውጣት ማለት የሚያስከትለው መዘዝ ቀላል አልነበረም” ሲል ምላሽ ሰጥቷል። አርተር የግላዊ መረጃን የመጠበቅ መብትን በተመለከተ በተደጋጋሚ ጋዜጠኞችን ሞግቷል።
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም