ቻድ ከፈረንሳይ ጋር ያላትን ወታደራዊ ስምምነት አቋረጠች። ፈረንሳይን ጨምሮ ከምዕራባዊያን ሀገራት ጋር ጥሩ ወዳጅነት የነበራት ቻድ ከፓሪስ ጋር የነበራትን ወታደራዊ ስምምነት አቋርጫለሁ ብላለች። የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው ማስታወቂያ ሉዓላዊነቴን በነጻነት ለማጣጣም ከፈረንሳይ ጋር የነበረውን ወታደራዊ ትብብሮች መቋረጣቸውን ገልጿል።
የቻድ አዲስ ውሳኔን ተከትሎ ፈረንሳይ በሀገሪቱ ያሰፈረቻቸውን ወታደሮች እንድታስወጣ ልትገደድ ትችላለች ተብሏል። ሌላኛዋ የፓሪስ ቁልፍ የአፍሪካ አጋር የሆነችው ሴኔጋል ፕሬዚዳንት ባሲሩ ፋዬ የፈረንሳይ ወታደሮች በሀገራቸው መስፈራቸው ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
ሀገሪቱ በሴኔጋል 350 ወታደሮችን ያሰፈረች ሲሆን ፕሬዚዳንት ባሲሩ ፋዬ ፈረንሳይ ወታደሮቿ በሀገራቸው መስፈራቸውን ከመተቸታቸው ባለፈ እንዲወጡ ፍላጎት ይኑራቸው አይኑራቸው አልተጠቀሰም። ፈረንሳይ ከቀድሞ ቅኝ ግዛቶቿ ጋር ያላት ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ ሲሆን ከኒጀር፣ ቡርኪናፋሶ እና ማሊ ተገዳ እንድትወጣ መደረጉ አይዘነጋም።
የፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን መንግሥት በቻድ ውሳኔ ዙሪያ እስካሁን ያሉት ነገር የለም። ፈረንሳይ በአፍሪካ ባሰፈረቻቸው ወታደሮች እና በቀጣይ ሊኖራት ስለሚችለው ግንኙነት ዙሪያ አዲስ እቅድ በማውጣት ላይ እንደሆነች ተዘግቧል። የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኖኤል ባሮት ከሰሞኑ የቻድ ጎረቤት በሆነችው ሱዳን ጉብኝት አድርገዋል።
ፈረንሳይ በቻድ፣ ጋቦን እና ኮትዲቯር በሚኖሯት ወታደሮች ዙሪያ አዲስ እቅድ ያወጣች ቢሆንም እስካሁን ዝርዝሩ ይፋ አልተደረገም ሲል አል ዐይን ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ህዳር 21/2017 ዓ.ም