ጥራት ለአንድ ሃገር የወጪ ምርት ተወዳዳሪነት ለገቢ ምርት ደህንነትና ወሳኝ ሚና እንዳለው ይታመናል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ አይሶ ያሉ ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተቋማት ተቋ ቁመው ይሰራሉ፡፡ አንደ ሀገርም የጥራት አረጋጋጭ ተቋማት ተቋቁመው ይሰራሉ፡፡
የጥራት ማረጋገጫ ደረጃዎች ቴክኖሎጂና ሳይንስን በመጠቀም ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ያገናዘቡ እና ከሌሎች የዓለም ሃገራት አንፃር የተናበቡ መሆን ይኖርባቸዋል። የሀገር ውስጥ ምርትም ሆነ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ጥራታቸውን የጠበቁ እና ለማኅበረሰብ ደህንነት ቅድሚያ የሚሰጡ ከሆነ በአምራቹና ላኪው ብሎም በምርቱ ተጠቃሚ ዘንድ ተፈላጊ ይሆናሉ፡፡
ባለሀብቱም ላለመክሰር ሲል ጥራት ያለውን ምርት ለገበያ ማቅረብ ይፈልጋል። ማኅበረሰቡም ጥራታቸውን ያልጠበቁ ምርቶች በመጠቀም ከሚመጣበት የጤና እና የተለያዩ ችግሮች ለመዳን ጥራት ያለው ምርት ማግኘት ይመርጣል።
ሃገራት በየጊዜው የጥራት መስፈርቶቻቸውንና ደረጃዎች እያሻሻሉ ተግባራዊ ሲያደርጉ ይስተዋላል። ኢትዮጵያም በጥራት ላይ የሚሰሩ ተቋማትን አቋቁማ ስትሰራ ቆይታለች፡፡ በቅርቡ ደግሞ አዲስ የጥራት መንደር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ይፋ አድርጋለች፡፡
በዚሁ መድረክ ላይ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዶክተር ካሳሁን ጎፌ እንደገለጹት፤ የጥራት መንደሩ በሰባት ነጥብ 2 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፣ 20 ሕንፃዎችን ያካተተ ነው። አጠቃላይ ወደ ስምንት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እንደተናገሩት፤ የዚህ የጥራት መንደር ስያሜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብሔራዊ የጥራት መሰረተ ልማት የሚባል ሲሆን፣ መሰረተ ልማት ብቻ ሳይሆን የጥራት መሰረተ ልማት ነው። በዚህ የጥራት መንደር ውስጥ በሺ የሚቆጠሩ ወጣት ሙያተኞች ይሰራሉ። በተለይም ምግቦችን፣ አልባሳትን፣ ኮንስትራክሽንን ግብአቶች የሆኑትን ሲሚንቶ፣ ብረት፣ መስታወት፣ ቆርቆሮ፣ እንዲሁም ከጤና ጋር የሚያያዙ መሳሪያዎችን ጨምሮ ይጠግናሉ፤ ጥራታቸውም ይፈተሻሉ።
ቡናው፣ ሰሊጡ፣ ማሩ ሁሉንም ዓይነት ምግብ ነክ ነገር ወደ ውጭ የሚላክ በሙሉ በዚህ ተቋም ተመዝኖ ዓለም አቀፍ ደረጃ መሆኑ ይረጋገጣል። ከውጭ የሚገቡም እንዲሁ ወደ ሀገር ውስጥ ገበያ ከመውጣታቸው በፊት በጥራት መንደሩ ይፈተሻሉ። አልባሳት፣ ምግብ እና ጤና ለሰው ልጅ በጣም አስፈላጊ ጉዳዮች ናቸው። በትናንሽ ንክኪዎች፣ ኬሚካሎች ምክንያት የጤና መጓደል ሊያጋጥም ይችላል፤ እናም ፍተሻ ይደረግባቸዋል፡፡
ይህ መሰረተ ልማት በኢትዮጵያ ትልቅ ሲሳይ ሲሆን፣ በአፍሪካ ደረጃም እንዲህ አይነቱ መሰረተ ልማት ያላቸው ጥቂት ሃገራት ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የጥራት መሠረተ ልማት የሌላቸው ሀገራት ዘላቂ ዕድገት ማረጋገጥ እንደማይችሉም አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ የዕድገት መሠረቱ የኤክስፖርት አቅም ነው። ሀገራት ኤክስፖርት ለማድረግ እንደዚህ ዓይነት ተቋም በእጅጉ ያስፈልጓቸዋል። መከላከያን፣ ፖሊስን ወይም ሰፋፊ መንገዶችን ከመገንባት በላይ አስፈላጊ ተቋም ነው። ይህ ተቋም በተሟላ አቅም ሲሰራ ወጪ ንግዱ ያድጋል፤ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡትም በጥራት የተመረቱ ይሆናሉ። ሃገሪቱም በዓለም ገበያ የሚመረቱ ጥራት የጎደላቸው ምርቶች የሚጣሉባት አትሆንም ሲሉ ጠቅሰው፣ ተቋሙ ምርጥ ምርጡን የምትቀበል፣ በጥራት አምርታ የምትልክ ሀገር እንደሚያደርጋት አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳስረዱት፤ በመጀመሪያ ተሞክሮው የተወሰደው ከደቡብ አፍሪካ ሲሆን፣ ደቡብ አፍሪካ ሲ.ኤስ.አር ከሚባል የጥራት መሰረተ ልማት ተቋም አላት። ከዚሁ ከ30 ያላነሱ ዓመታት ተሞክሮ ካለው የደቡብ አፍሪካ ተቋም ልምድ በመቀመር ኢትዮጵያም መሰል ተቋም እንዲኖራት ብዙ የተደከመበት ሥራ ነው። አሁን ፍሬያማ ሆኖ መሳሪያዎቹ ገብተው፣ ሙያተኞቹ ሰልጥነው በተሟላ ሁኔታ የኢትዮጵያን የወጪ ገቢ ንግድ ተወዳዳሪ ማድረግ የሚችሉ አቅሞች የሚፈጥር ነው። የትኛዎቹም በውጭ አገር ያሉ መሰል ስራ የሚሰሩ ተቋማት ቢመጡ የእነዚህን ላቦራቶሪ ደረጃ ስለሚያውቁት በትክክል ለመገልገልም ፍቃደኛ ይሆናሉ።
ከሃገር ውስጥ በዚህ ቦታ የጥራት ሰርተፊኬት አግኝተው የወጡ ምርቶች በቀላሉ በዓለም አቀፍ ገበያ ተቀባይነት ይኖራቸዋል ሲሉም ጠቅሰው፣ እንደነዚህ ዓይነት ተቋማት መስከረም ተተክለው ጥቅምት የሚመረቁ ሳይሆን ሶስት እና አራት ዓመታትን ይጠይቃሉ፤ መዘጋጀትና ግብዓት ማግኘት ይፈልጋል ብለዋል።
በግቢው ከ20 በላይ ሕንፃዎች ያሉ ሲሆን፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ውጤት ከተገኘባቸው ተቋማት አንዱ ነው። ይህ ከገነባናቸው ሃገራዊ ተቋማት መካከል ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዝ በጣም ጠቃሚ ተቋም ነው ሲሉም አስታውቀዋል፡፡
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርሀተስፋ የምጣኔ ሀብት አማካሪ ናቸው፡፡ በተባበሩት መንግስታት ኒውዮርክ የፖሊሲ አማካሪ ሆነው ያገለገሉና አሁን በሰብአዊ ድርጅቶች አመራር ላይ በመምህርነት እያገለገሉ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባቸው የፋብሪካ ምርቶች በማኅበረሰቡ ላይ የጤናም ሆነ ሌሎች ችግሮችን ከማስከተላቸው በፊት ጥራታቸው በተገቢው መንገድ ተፈትሾ መግባት እንዳለባቸው ያመለክታሉ።
‹‹በመጀመሪያ ደረጃ አገራችን ከውጭ የምታስገባቸው ሁሉም እቃዎች፣ መድሃኒቶች፣ የኤሌክትሮኒክስ ቁሶች፣ ምግብ ነክ ነገሮች፣ አልባሳት ጭምር ጥራታቸው ታውቆና ተገምግሞ መግባት ይኖርባቸዋል›› ይላሉ። በመሆኑም የጥራት መንደር ምስረታው ለሃገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ይጠቅሳሉ፡፡
እርሳቸው እንደተናገሩት፤ በሃገሪቱ የጥራት ጥያቄዎች ምላሽ የሆነው የጥራት መንደር ምስረታው በየዘርፉ ከጥራት ጋር ተያይዞ የሚመጣውን የማኅበረሰብ ችግር ለመፍታት ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል። የጥራት መንደር ምስረታው መንግስት ሃገርና የሕዝቡን ደህንነት ከመጠበቅ ሌላ የቁጥጥር ስራ አንዱ ነው፡፡
የጥራት መጠበቂያ ቦታዎች መዘጋጀታቸው ለወጪ ንግዱም ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰቡ ለሚጠቀምባቸው ነገሮች ደረጃዎች እያወጡ እርማት በማድረግ ማኅበረሰቡንም ሊመርዙ የሚችሉ ነገሮች ወደ ገበያ እንዳይቀርቡ ቁጥጥር ማድረግ ያስችላል የሚል እምነት አላቸው።
ላቦራቶሪያቸውን ብቻ መያዝ ሳይሆን ከገበያ ናሙና እየወሰዱ ምርምር ሊያደርጉ የሚችሉበት ሁኔታም ይፈጠራል። ይህም ለመንግስት አቅም ግንባታ ትልቅ ጠቀሜታ አለው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ማንኛውም በፋብሪካዎች የተመረተ እቃ የ’ISO’ የዓለም አቀፍ ጥራት ማረጋገጫ ተሰጥቷቸው ወደ ውጭ የሚላኩበት ሁኔታን ይፈጥራል።
የአውሮፓም ሆነ የሌላ ሃገራት መንግስታት ወደ ውጭ የሚልኩ ኩባንያዎች፣ የሚጠይቋቸው መስፈርቶች መኖራቸውን አስታውሰው፤ መስፈርቶቹ ከአካባቢ፣ ከኬሚካል ይዘት እንዲሁም ከሕፃናት በሥራ መሳተፍ ጋር የተያያዙ መሆናቸውንም ያመለክታሉ። ‹‹ እኛ በአብዛኛው ከ70 በመቶ በላይ ወደ ውጭ የምንልካቸው እቃዎች በጥሬ ነው። ቡናም፣ በሰሊጥም ሌሎችም አዝዕርቶችን ጨምሮ እሴት ተጨምሮባቸው ወደውጭ ቢላኩ ኢኮኖሚውን በተሻለ የሚደግፍ ይሆናል›› ሲሉም አስታውቀዋል።
ሰሊጥ ወደ ዘይት ተቀይሮ ወደ ውጭ ቢላክ በብዙ እጥፍ ዋጋው እንደሚጨምር ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ይጠቅሳሉ፡፡ በተጨማሪም ከውጭ የሚመጣውንም ዘይት በማስቀረት የውጭ ምንዛሬን መታደግ እንደሚያስችል ያመለክታሉ፡፡ በመሆኑም የጥራት መንደር መመስረቱ ይህንን እውን ለማድረግ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን እሴት ተጨምሮባቸው ወደ ወጭ ሊወጡ የሚችሉ እቃዎችን ለማምረት የሚያስችሉ ናቸው። እነዚህ ኩባንያዎች በተለይ ነፃ ኢኮኖሚ ዞን በሚባሉት አካባቢዎች ሲሰሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ሰርተው ወደ ውጭ እንዲልኩ ነው። ከመንግስትም በርካታ እድሎች ይሰጣቸዋል። ፈቃድ ለማውጣት መጉላላት ጋር በተያያዘ ብዙ ጥቅም አላቸው። እነዚህ የኢኮኖሚክ ዞን የሚባሉትና እነ ቻይና፣ ዩናይትድ አረብ ኢምሬት፣ ሲንጋፖር የመሳሰሉት በከፍተኛ ደረጃ ያደጉባቸው ስለሆኑ በአንድ በኩል ተጀምሯል፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በሙሉ ወደዚያ ለመቀየር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ያብራራሉ።
እምሩ አያሌው ኢምፖርት ኤክስፖርት የተሰኘ የግል ኩባንያ መስራችና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ እምሩ አያሌው ጥራት የሁሉም ነገር ምንጭ ነው ይላሉ። አኩሪ አተር፣ ሰሊጥ፣ ኑገ የመሳሰሉትን ወደ ውጨ የሚልኩ ሲሆን፣ መኪና እና ማሽነሪዎችን ጎማዎችን፣ የኢንዱስትሪ ጥሬ እቃዎችን እንዲሁም ኬሚካሎችን ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባሉ።
የጥራት መንደር ምስረታው የአስመጪና ላኪውም ንግድ ስራ የተሻለ የተሳለጠ የሚያደርግ መሆኑን አቶ እምሩ ጠቅሰው፣ ጥራት የሌላቸው እቃዎች በሚላኩበት ጊዜ ደንበኛን ማጣት ይኖራል ሲሉ ይገልጻሉ። የሚወስደውም ሰው ሽያጩን ሙሉለሙሉ ሰርዞ ለአላስፈላጊ ወጪ ሊዳርግ እንደሚችል ተናግረው፣ ጥራትን ማዕከል አድርጎ የጥራት መንደሩ መሰራቱ ለአገርም ለነጋዴውም ወሳኝ ነው ሲሉ አስገንዝበዋል።
ቀደም ሲል ወደ ውጭ ለመላክ የምናቀርባቸው የጥራት ሰርተፊኬቶች ነበሩ፤ ወደ አገር ውስጥ ስናስገባም ጥራትን መሰረት ያደረጉ ግምገማዎች ይደረጋሉ ሲሉ አመልክተው፣ ያንን ያህል ጠንካራ እና ኣመኔታ ግን የነበራቸው አይደሉም ብለዋል። በግለሰብ ደረጃ የሚሰሩ ጥራትን እናረጋግጣለን የሚሉ ተቋማት እንደነበሩ አስታውሰው፣ እነዚህ ተቋማት በቀላል ነገር በመግባባት ሰርተፊኬቱን ሊሰሩ የሚችሉበት እድል የሰፋ መሆኑን ነው የገለጹት።
የዚህ የጥራት መንደር ምስረታ የቴክኖሎጂ ድጋፍ እንዳለው ጠቅሰው፣ በመንግስት ቁጥጥር ስር ስለሆነ ጥራት የሌለውን እቃ ጥራት እንዳለው አስመስሎ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የማቅረቡ ሁኔታ አይታሰብም ሲሉ ተናግረዋል።
የጥራት መንደሩ እውን መሆኑ ጥራት ያለው እቃ ወደ ውጭ እንዲወጣ፤ ጥራት ያለው እቃም ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ ምቹ እንደሚፈጥር አስታውቀው፣ የጥራት መንደሩ የተሻለ ቴክኖሎጂ መጠቀሙ በውጭ ደንበኞች ዘንድ የተሻለ እምነት እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።
እኛ ለምንልከው እቃ ይበልጥ አመኔታን ይፈጥራል። ደንበኞች ጥራቱን የጠበቀ እቃ እንደሚደርሳቸው እርግጠኛ በሆኑ ጊዜ የተሻለ ክፍያ ይሰጣሉ ሲሉም አስታውቀው፣ አንዳንዴም ተጨማሪ ክፍያ ማግኘት ያስችላል ብለዋል።
የሚሸጠው እቃ ጥራት ሳይኖረው ቀርቶ ተጨማሪ ከፍያም ተቀብሎ ከተገኘ በቀጣይ ጥቁር መዝገብ ውስጥ ሊያስገባ እንደሚችል አመልክተው፣ የጥራት መንደሩ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ የሚያደርግ እንዲሁም የተሻለ የሰው ሀብት ተመድቦ የሚመራው ከሆነ የጥራት ጉዳይ በእጅጉ እንደሚሻሻል ገልጸዋል፡፡ ቴክኖሎጂዎቹ አገርንም አስመጪውንና ላኪውንም እንደሚያገለግሉ ጠቅሰው.፣ ቴክኖሎጂውን የሚመራ ባለሙያ በቦታው ማስቀመጥ ተገቢ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ኅዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም