አህጉራዊ ቅንጅት – ለአፍሪካ ቡና ተወዳዳሪነት

አፍሪካ የቡና መገኛና በስፋት የምታምርት እንደመሆኗ ከዘርፉ የሚገባትን ያህል ጥቅም እያገኘች አለመሆኗን የዘርፉ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ በርካታ ቡና አምራች ገበሬዎች ላሉባቸው እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት ቡና የኢኮኖሚያቸው የጀርባ አጥንት ተደርጎ እስከ መወሰድ ቢደርስም፣ ከብራዚል እና ከሌሎች የዓለም ሀገራት ጋር ሲነፃፃር ተጠቃሚነታቸው እምብዛም ስለመሆኑ ይገለጻል፡፡

ለዚህ ምክንያቶቹ ከእርሻ እስከ ገበያ ድረስ ያሉ ችግሮች መሆናቸው የሚጠቀስ ሲሆን፣ በዋናነት ደግሞ ሀገራቱ በቅንጅት አለመሥራታቸውን ተከትሎ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆነው አለመገኘታቸው ይነሳል፡፡

64ኛው የበይነ- አፍሪካ የቡና ድርጅት ከፍተኛ የፖሊሲ መድረክ ሰሞኑን በአዲስ አበባ በተካሄደበት ወቅት እንደገለጸውም፤ አህጉሪቱ በዓለም የቡና ገበያ ውድድር ዘልቃ እንድትገባም ሆነ ተወዳዳሪ እንድትሆን የሀገራቱ ትብብርና በቅንጅት መሥራት ወሳኝ ሚና አለው። በተለይም ቡና በጥሬው ከመላክ በዘለለ እሴት ጨምሮ በመላክ ተጠቃሚ እንድትሆን የሀገራቱ መንግሥታት ሊረባረቡ ይገባል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ እንዳስታወቁት፤ ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ብቻ ሳይሆን ምርታማነትና የምርት ጥራትን በመጨመር የዓለም የገበያ መሪ መሆንን ትሻለች፡፡፡ ለዚህም ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶችን የሚቋቋም የቡና ምርታማነትን ለማረጋገጥ እየሠራች ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር የአፍሪካ ቡና ምርት ተወዳዳሪ እንዲሆን የበኩሏን ሚና ትወጣለች። በተለይም የአፍሪካ የቡና ምርት ከማሳ እስከ ገበያ ተወዳዳሪና ለችግር የማይበገር ዘርፍ እንዲሆን እየሠራች ትገኛለች፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት የቡናን ምርታማነት ለማስቀጠልና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ባስቀመጠችው አቅጣጫና ባዘጋጀችው እቅድ መሠረት በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ የቡና ችግኞችን መትከሏን ዶክተር ግርማ ይናገራሉ፡፡ ቡናን በጥራትም ሆነ በብዛት በማምረት የወጪ ንግድ ገቢዋን መጨመር መቻሏንም ጠቅሰዋል፡፡

በተያዘው 2017 በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከሚላክ የቡና ገቢ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ማቀዷን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ በምርት ጥራት፣ በገበያ ተደራሽነትና ተጠቃሚነት ላይ አበክራ እየሠራች መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ በተለይም እሴት ያልተጨመረበት ቡና ለውጭ ገበያ ከማቅረብ ይልቅ እሴት በመጨመር ዘርፉ የሚያመነጨውን እድል ለመጠቀም መሥራቱን እንደተያያዘችው አስገንዝበዋል፡፡

የአፍሪካ የቡና ዘርፍ ለሚያጋጥሙት ችግሮች በዘላቂነት መፍትሔ ለማስቀመጥም ከሀገራት ጋር በትብብር እንደምትሰራ ያስታወቁት ዶክተር ግርማ፤ ከማሳ እስከ ዓለም አቀፍ ገበያ ባለው የቡና እሴት ሰንሰለት ከፖሊሲ ትግበራ ጀምሮ አስፈላጊውን ሥራ ማከናወን ወሳኝ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በዋናነትም በዓለም ገበያ የአፍሪካ ቡና ተወዳዳሪ እንዲሆን እና ለችግሮች የማይበገር ሆኖ እንዲቀጥል በትብብር መሥራት እንደሚያሻም ይናገራሉ፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ ከአምራቹ እስከ ቡና ላኪዎች ባሉት ሰንሰለቶች ሁሉ ተጠቃሚነትን ማጎልበት እና የገበያ መዳረሻዎችን ማስፋት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ ዘላቂ እና ጥራት ያለው የቡና ምርት በማምረት የአፍሪካን የቡና የወጪ ንግድ ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። በተለይ በቡና ምርት ላይ እሴት በመጨመር የዓለም አቀፍ ገበያ ዕድሎችን ማስፋት ያስፈልጋል፡፡ ለአፍሪካ ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ ተጨማሪ ዕድሎችን ለመፍጠር እሴት መጨመር ይገባል፡፡ በተለይም የየሀገራቱ መሪዎችና የዘርፉ ተዋናዮች በየእለቱ የአፍሪካ ቡና እሴት ሰንሰለት የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች በመለየት መፍታት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቡናን ምርታማነት፣ ጥራትና የገበያ ተደራሽነት ለማሻሻል የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ ትቀጥላለች፡፡

የአፍሪካ ቡና የአየር ንብረት ለውጥ፣ የዋጋ ተለዋዋጭነት እና የቁጥጥር ማሕቀፎችን ማጠናከር ያለመቻሉ አህጉሪቱ ከዘርፉ የሚገባትን ጥቅም እንዳታገኝ ያደረጋት መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም ኢትዮጵያ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በትብብር እንደምትሠራ ያመለክታሉ፡፡ ይህም በአዳዲስ ምርምሮች፣ በኢንቨስትመንቶች እና ስትራቴጂካዊ የፖሊሲ ጣልቃ ገብነቶች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ያስረዳሉ።

የበይነ- አፍሪካ የቡና ድርጅት ዋና ጸሐፊ ሶሎሞን ሳቢቲ በበኩላቸው እንዳስታወቁት፤ ድርጅቱ 25 የአፍሪካ ቡና አምራች ሀገራት አባል የሆኑበት ነው፤ የአፍሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የተሳተፉበት የፖሊሲ ፎረም በዋናነት በቡና ምርት ላይ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን መፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮችና ምቹ ሁኔታዎች ላይ መክሯል፡፡ የአፍሪካን ቡና ኢንዱስትሪ በምን መልኩ ትራንስፎርም ማድረግ እንደሚቻልና በተለይም የግሉን ዘርፍ በምን መልኩ መደገፍ እንደሚገባ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

‹‹በአፍሪካ ቡና ላይ እሴት በመጨመር ገቢ ከማሳደግ በዘለለ ለበርካታ ሥራ አጥ አፍሪካውያን የሥራ እድል ለመፍጠር ያግዛል›› የሚሉት ዋና ጸሐፊው፣ ለዚህም በዋናነት ሀገራቱ ምርታማነት ማሳደግ ላይ ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ፡፡ በተጓዳኝም በአህጉሪቱ ቡና ገበያ ላይ በሚስተዋለው የዋጋ መዋዠቅ እና የፋይናንስ እጥረት ላይ ያለውን ችግር ለመፍታት ሁሉም የበኩሉን ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቅበትም ያስገነዝባሉ፡፡

‹‹እንዲህ ዓይነቱ ጉባኤ ሲካሄድ ለ64ኛ ጊዜ ቢሆንም ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ የአፍሪካ ህብረት የቡናን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ስትራቴጂ ነድፎ እየሠራ ነው›› የሚሉት ዋና ጸሐፊው፤ ይህም እንደ ትልቅ እምርታ እንደሚታይ ይናገራሉ፡፡ በአፍሪካ ቡና ላይ እሴት የመጨመሩ ሥራ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አስገንዝበዋል፤ ይህም ለአፍሪካ ቡና ገቢ እድገት መሠረት እንደሚጥልና ለቡናው ዳግማ ትንሳኤ ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸው ያመላክታሉ፡፡

በመድረኩ የአውሮፓ የልማት ድርጅት ከፍተኛ ኃላፊዎች መገኘታቸውን አስታውሰው፤ ይህም የአፍሪካ ቡና እሴት ተጨምሮበት በዓለም ገበያ እንዲቀርብ ለሚደረገው አህጉራዊ ጥረት ድጋፍ ለማግኘት እንደሚያስችልም ይገልጻሉ፡፡

እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ ድርጅቱ የአፍሪካ ቡና በዓለም ገበያ ተዋዳዳሪ እንዲሆን ከማድረግ ባሻገር በሀገራቱ መካከል የእርስ በርስ የነፃ ግብይት ሥርዓት እንዲጠናከር እየሠራ ነው፡፡ አፍሪካ ከምታመርተው ቡና አብዛኛው ወደ አውሮፓ የሚላክ ሲሆን፣ ድርጅቱ ጥራት ያለው ቡና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሁም የገበያ ተደራሽነትን ለማስፋት በትኩረት ይሰራል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በሌሎች የአህጉሪቱ ሀገሮች የሀገር ውስጥ የቡና ተጠቃሚነት ባሕል እንዲጎለብት የማስተዋወቅ ሥራ ቡና አምራች የአፍሪካ ሀገራት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ያስገነዝባሉ፡፡ የእሴት ሰንሰለቱን በማጠናከር አህጉሪቱ ከዘርፉ የላቀ ተጠቃሚ እንድትሆንም ሁሉም የየራሱን ሚና መወጣት እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡

ለዚህም የአህጉሪቱ ከፍተኛ መሪዎች እና ባለሥልጣናት ድጋፍ ሊያደርጉ፤ ቁርጠኝነታቸውን በተጨባጭ ማሳየት እንዳለባቸው ያስረዳሉ፡፡ ‹‹በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የታደለች ናት ፤ ምክንያቱም የዓለም ገበያ ቢቀዛቀዝ ያመረተችው ቡና በሀገር ውስጥ ገበያ አያጣም፤ በመሆኑም ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የኢትዮጵያን ተሞክሮ ወስደው በሀገር ውስጥ ቡና የመጠቀም ባሕል እንዲጎለብት ማድረግ ይገባቸዋል›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ከአምስት ዓመታት ወዲህ በቡና የወጪ ንግድ ከፍተኛ እድገት እያስመዘገበች መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በዚህም በታሪኳ አይታ በማታውቀው ሁኔታ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቷን ጠቅሰዋል። ዘላቂ እና ጥራት ያለው ምርትን በማረጋገጥ የአፍሪካን የቡና የወጪ ንግድ ለማሳደግ የተቀናጀ እና ግልፅ ተግባራት አስፈላጊ መሆናቸውን ያስገነዝባሉ፡፡

ዶክተር አዱኛ እንዳሉት፤ የአፍሪካ የቡና ምርት አሁንም ከፍተኛ የወጪ ንግድ የገቢ ምንጭ ሆኖ በመሪነት የዘለቀ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ግብርና የሥራ ዕድል በመፍጠር እና የኤክስፖርት ገቢ በማስገኘት በአህጉሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡

በመሆኑም የዘርፉን ተጠቃሚነት ከፍ ለማድረግ በአፍሪካ ቡና ኢንዱስትሪ ውስጥ ኢንቨስት ማድረግ ይገባል። ለዚህም የአፍሪካ ሀገራት በጋራ መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት መሪዎችን ያሳተፉ መድረኮች ቡና አምራች ሀገራት በዘርፉ የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለመፍታትና ያሉትን ዕድሎች ለመጠቀም አቅም ይፈጥራሉ።

ኢትዮጵያ ዘላቂ የቡና አቅርቦት ሠንሠለትና የደን አያያዝን ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗንም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረው፤ ይህም የኤክስፖርት አቅምን እና የንግድ ዕድሎችን እንደሚጨምር ይጠቁማሉ። የአፍሪካ የቡና ኢንዱስትሪ የሚፈለገውን ዕድገት ለማሳካት የመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ ትብብር ማድረግን እንደሚጠይቅም አስገዝበዋል፡፡

በአፍሪካ ቡና አምራች የሆኑት 25ቱም ሀገራት በጋራ ተስብስበው የፈጠሩት ድርጅት በአህጉር አቀፍ ደረጃ በጋራ ሆነው ችግሮቻቸውን ለመፍታት እንዳስቻላቸው ዶክተር አዱኛ ያመለክታሉ፡፡ ከሁሉም በላይ በአሁኑ ወቅት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት እየተደረገ ላለው አህጉር አቀፍ ጥረት በጋራ መሥራታቸው በዓለም ላይ ተሰሚነት እንዲኖራቸው ወሳኝ ሚና እንዳለው ያስረዳሉ፡፡ በአፍሪካ ከሚመረተው የቡና ምርት 12 በመቶው ብቻ ለዓለም ገበያ እንደሚቀርብ ገልጸው፣ ተጠቃሚነቱን ሲታይ ከዓለም 13 በመቶ ደረጃ ላይ መሆኗን ገልጸዋል፡፡

ይህም አፍሪካ በቡና ራሷን መመገብ እንደምትችል እንደሚያመለክት ጠቅሰው፣ አህጉሪቱ ብዙ ጫና ያለባት ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የሚገባትን ያህል ተጠቃሚ እንዳልሆነች ያስገነዝባሉ፡፡ ለዚህም አብነት አድርገው ‹‹ አዳዲስ ሕጎች በሚወጡበት እንዲሁም የዓለም አቀፍ የቡና ዋጋ በሚወርድበት ጊዜ አፍሪካ እንደ አህጉር ተጠቃሚ አይደለችም›› በማለት ይጠቅሳሉ፡፡ ሀገራቱ ተባብረው መሥራታቸው የጋራ ችግሮቻቸውን ለመፍታት እንደሚያስችላቸው ተናግረው በተለይ የአፍሪካ ነፃ ገበያ ቀጣና የፈጠረውን እድል በመጠቀም የእርስ በርስ ግብይቱን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡

ቡና የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ እንዲሆን መደረጉን አመልክተው፤ ‹‹በአሁኑ ወቅት ድምፃችንን በጋራ ማሰማት የምንችልበት እድል ስላለ ምርታማነትን ከመጨመር አኳያ፤ በተለይም አርሶ አደሮችን ከማገዝ አንፃር በጋራ መሥራታችን ተጠቃሚ ያደርገናል›› በማለት አብራርተዋል፡፡

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የህብረቱ መሪ ሀገር በሆነችበት ወቅት በርካታ ሥራዎችን ስታከናውን መቆየቷን አስታውሰው፤ በተለይም ቡና አፍሪካ ህብረት የ2063 አጀንዳ ሆኖ እንዲፀድቅ ከፍተኛ ጥረት በማድረጓ በየመድረኩ በሚያጋጥሙ ችግሮች ላይ ለመነጋገርና የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ማገዙን ያስረዳሉ፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ከምታመርተው ቡና 50 በመቶ የሚሆነውን በሀገር ውስጥ እንደምትጠቀም ዶክተር አዱኛ ጠቁመው፤ ‹‹ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ግን ቡና ያመርታሉ እንጂ አይጠቀሙም፤ ለምሳሌ እንደ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ዩጋንዳ ያሉ ሀገራት 99 በመቶ የሚሆነውን ምርታቸውን ወደ ውጭ ነው የሚልኩት፤ ይህ በመሆኑ የዓለም የቡና ዋጋ ሲወርድ ለኪሳራ የሚዳረጉበት ሁኔታ አለ›› ይላሉ፡፡ እነዚህ ሀገሮች በሀገር ውስጥ ቡና መጠቀም የሚችሉበትን እድል ለማስፋት ብዙ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህን ተከትሎም ለውጦች እየታዩ መሆኑን ያመላክታሉ። ኢትዮጵያም ይህንን እድል በመጠቀም የምታመርተውን ቡና ወደ ተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ለማቅረብ እየሠራች ነው ሲሉ ተናግረዋል ፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ ከድርጅቱ አባል ሀገራት በተጨማሪ ቡና ተጠቃሚ የሆኑ ሀገራትም የድርጅቱ አባል እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል፤ ይህም የንግድ ልውውጡን ለማጠናከርም ሆነ ቡናን በተሻለ ዋጋ ለማቅረብ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ በሌላ ሀገራት ጫና ስር የመውደቁንም አጋጣሚ ያጠባል፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በቡና የወጪ ንግድ እያስመዘገበች ላለችው እምርታ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው፡፡

‹‹በተለይም ከዚህ ቀደም የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ከባድ በመሆኑ ነጋዴዎች ቡና የሚልኩት የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ነበር፤ አሁን ግን ማሻሻያው የነበረውን ችግር ፈትቶታል፤ አሁን ላይ በነፃነት የውጭ ምንዛሬ የሚያገኙ በመሆናቸው ነጋዴዎች ግብይት ውስጥ ገብተው የሚረብሹበት ሁኔታን ያስቀራል›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በሀገር ውስጥ የቡና ዋጋ እንዲንር ይደረግ የነበረበትን ሁኔታ በመፍታት በሀገር ውስጥ የቡና ገበያ እንዲረጋጋ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡ ይህም ሀገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ ከፍ ለማድረግና በጥራት ለማምረት እድል ይሰጣታል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You