የከተማዋ ትልቁና የቱሪስቶቿ አይኖች ማረፊያ ሐይቋ ነው:: ስያሜዋን ያገኘችውም ከዚሁ ከሐይቋ ሲሆን፣ በሐይቁ ዳርቻዎች የሚገኙና የሚከናወኑ የተለያዩ ተግባሮችም ሌሎች መገለጫዎቿ ናቸው::
አዎን ሀዋሳ ከተማን አለ ሀዋሳ ሐይቅ ማንሳት አይቻልም፤ የዓሣ ገበያዋ፣ የጉዱማሌ ፓርክ፣ የፍቅር ሐይቅ፣ ታቦርና አላሙራ ተራሮች ሁሉም የከተማዋ ስም ሲነሳ አብረው የሚነሱ ናቸው:: አረንጓዴ ስፍራዎቿ፣ ሰፋፊ ውብ መንገዶቿ፣ ሞቃታማ አየሯ የሀዋሳ ከተማ ስም ሲነሳ አብረው ይነሳሉ::
ከተማዋ ለነዋሪዎቿ፣ ለጎብኚዎቿና እንግዶቿ ተመራጭ ስለመሆኗ ሁሉም የሚመሰክረው ሐቅ ነው:: ቱሪስቶች ለሁለት ለሦስት ቀናት መጥተውባት ሳምንት የሚቆዩባት ሲሉ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ባሕል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መቅደስ ሁሪሶ ተናግረዋል::
ከተማዋ በርካታ በቱሪስቶች ሊጎበኙ የሚችሉ የቱሪዝም ሀብቶች እንዳሏት መምሪያ ኃላፊዋም ጠቅሰው፣ ሐይቁ ብቻ ሳይሆን የሐይቁ ዳር የዓሣ ገበያ በቱሪስት የሚመረጥ ውብ መስሕብ መሆኑን አመልክተዋል፤ ስፍራው በሀገር ውስጥም በውጭ ቱሪስቶችም በእጅጉ እንደሚወደድ፣ ይህን ገበያ ሳይጎበኝ ወደመጣበት የሚመለስ ጎብኚ እንደሌለም ይገልጻሉ::
እሳቸው እንዳሉት፤ ሌላው የከተማዋ ውበት በዚሁ ገበያ አካባቢ የሚገኘው የጉዱማሌ ፓርክ ነው:: ይህ በሲዳማ ልማት ማኅበር የሚተዳደርና የሲዳማ ብሔረሰብ በየዓመቱ የሚያከብረው የዘመን መለወጫ የፍቼ ጨምበላላ በዓል የሚከበርበት ስፍራ፣ ቀድሞ አሞራ ገደል በመባል ይታወቅ ነበር፤ በማኅበሩ አማካይነት ከቀድሞው በተሻለ መልኩ አዳዲስ ነገሮች ተካተውበት እየተሠራ ይገኛል፤ በዚህም የቱሪስቶችን ቀልብ ይበልጥ እየሳበ ያለ ስፍራ መሆን እየቻለ ነው:: እነዚህ በሙሉ የሀዋሳ ስም ሲነሳ አብረው የሚነሱ የከተማዋ የቱሪስት መስሕቦች ናቸው::
የታቦር ተራራ ሌላው የከተማዋ ውበት ስለመሆኑ የማያውቅ የለም:: ተራራ መውጣት ለሚፈልጉ ቱሪስቶች ምቹ ስፍራ ነው የሚሉት ወይዘሮ መቅደስ ፤ይህም ተራራ በኢኮ ቱሪዝምነት እየለማ መሆኑን ጠቅሰው፣ የኢኮ ቱሪዝም ግንባታው ከተጀመረ ቆየት ያለና ሊጠናቀቅ ጥቂት ሥራዎች ብቻ የቀሩት መሆኑን ይገልጻሉ:: ግንባታው ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባ ወደ ከተማዋ የሚመጣውን የቱሪስት ፍሰት ይበልጥ እንደሚጨምረው ይጠበቃል ሲሉም ተናግረዋል::
አላሙራ ተራራም ሌላው የከተማዋ የቱሪስት መስሕብ ነው:: በዚህ ተራራ ላይ እስከ አሁን የተለየ ነገር ባይሠራም ወደፊት እንዲለማ በማድረግ ከታቦር ተራራ ጋር በድልድይ የማስተሳሰር ሀሳብ እንዳለም ወይዘሮ መቅደስ ጠቁመዋል::
የአፄ ኃይለሥላሴ የቀድሞ ቤተመንግሥት፣ ጣሊያን በአምስት ዓመቱ ቆይታው ሲጠቅመበት የነበረና ጥሎት የሄደው መድፍ ያለበት ስፍራ፣ ቡርቂቶ ፍል ውሃ፣ የሀዋሳ ሐይቅ መነሻ ተደርጎ የሚታየውና በተለይ በበጋ ወቅት የከብቶች መዋያ በመሆን የሚታወቀው ጨለለቃ ረግረጉ ስፍራ /ሆንሴ/ ሌላው የቱሪስት መስሕብ መሆኑንም ጠቁመዋል:: በዚህ ስፍራ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ከብቶቻቸውን እንደሚለቁ አስታውቀዋል::
‹‹የሀዋሳ ከተማ ሌላው ትልቁ መስሕብ ነው ብለን የምናስበው የከተማዋ ፀጥታና ደኅንነት ነው›› ሲሉ የሚገልጹት የመምሪያ ኃላፊዋ፣ የከተማዋ ሕዝብ ‹‹ከፖሊስ ይልቅ የከተማዋ ሠላምና ፀጥታ ጠባቂ፣ በእንግዳ ተቀባይነቱ በእጅጉ የሚታወቅ፣ ዳኤቡሹ ብሎ እንግዶቹን የሚቀበል›› ሲሉም ገልጸውታል::
ከተማዋ ከውጭም ይሁን ከሀገር ውስጥ ወደ ከተማዋ የሚመጡ ጎብኚዎችን የሚቀበሉ ትላልቅ ሆቴሎችና ሪዞርቶች በብዛት ያሉባት መሆኗን የማይመሰክር የለም:: ከባቡር ትራንስፖርት በስተቀር በሁሉም የትራንስፖርት አማራጮች ወደ ከተማ መምጣትም ሆነ ከከተማዋ መውጣትም ይቻላል:: ለአዲስ አበባና ለተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ያላት ቅርበት የቱሪስቶች ምርጫ ካደረጓት መካከል ይጠቀሳሉ::
ይህች ውብ ከተማ አሁን ደግሞ ለነዋሪዎቿ፣ ለቱሪስቶቿና ለእንግዶቿ ይበልጥ ምቹ በሚያደርጋት የኮሪደር ልማት ላይ ትገኛለች:: የኮሪደር ልማቱ ዘመኑን የምትመጥን ከተማ እንድትሆን የሚያስችሏትን ሌሎች ትሩፋቶችን ይዞላት እንደመጣም ወይዘሮ መቅደስ አስታውቀዋል::
በከተማዋ እየተካሄደ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ከተማዋን የበለጠ ውብ እንድትሆን የሚያደርግ ስለመሆኑ ገና ከአሁኑ በስፋት እንደሚታይ የመምሪያ ኃላፊዋ ጠቁመዋል:: በሀዋሳ ሐይቅ ላይ ቀደም ሲል የሚከናወኑ ሥራዎች እንዳሉ ሆነው በኮሪደር ልማቱ ሌሎች አዳዲስ ሰፋፊ ሀሳቦች ተይዘው ወደ ትግበራ ተገብቷል:: በዚህም ሐይቁ በራሱ የቱሪስት መስሕብ መሆኑ እንዳለ ሆኖ የበለጠ ቱሪስቶችን እንዲስብ ለማድረግ እየተሠራ ይገኛል ሲሉም አብራርተዋል::
በኮሪደር ልማቱ ከሚካሄዱት ግንባታዎች መካከል አንዱ መነሻውን ከአዲስ አበባ ሀዋሳ መግቢያ በር ወይም ሀዋሳ ጌት ከሚለው ጥቁር ውሃ አካባቢ አንስቶ ወደ መሐል ሀዋሳ የሚወስደውን ነባር መንገድ አድርጎ ፍቅር ሐይቅ አካባቢ ወይም ሻፌታ ታወር /ሀዋሳ ማዘጋጃ ቤት አደባባይ በሚል ይጠራ የነበረው አደባባይ/ የሚዘልቀው ነው:: ይህን በጣሊያን ጊዜ እንደተሠራ የሚነገርለትን ጠባብ መንገድ በኮሪደር ልማቱ የማስፋትና የማዘመን ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል::
ወይዘሮ መቅደስ እንዳብራሩት፤ ግንባታውን ለማከናወን የሚያስፈልገው የወሰን ማስከበር ሥራ በዚህ ሳምንት ተጠናቆ፣ ግንባታውን ከሚያካሂደው ተቋራጭ ጋር ሰሞኑን ውል ተፈርሞ ሥራው ተጀምሯል፤ ለግንባታው ሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር የተመደበለት ሲሆን፣ በአምስት ወራት ውስጥ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ታቅዷል::
በዚህ ግንባታም የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተካተውበታል:: በአንድ ጊዜ ስምንት መኪናዎችን የሚያስተላለፍ ተደርጎ የሚገነባ ሲሆን፣ በሁለቱም አቅጣጫዎች አምስት አምስት ሜትር ስፋት ያላቸው የእግር መንገዶች፣ በየመሐሉ የስፖርት ማዘወተሪያዎች፣ የሕጻናት መጫወቻ ስፍራዎች፣ አረንጓዴ ስፍራዎች፣ ወዘተ እንዲኖሩት ተደርጐ ይገነባል::
ሁለተኛው የኮሪደር ልማት የሚካሄድበት ስፍራ ፍቅር ሐይቅ አካባቢ መሆኑን የመምሪያ ኃላፊዋ ጠቅሰው፣ ለዚህም ሐይቁን በሚጠብቅ መልኩ ትልቅ ፕሮጀክት ተዘጋጅቷል፤ የሳይክል መንገድና ሌሎች ቱሪዝሙን ሊያሳድጉ የሚችሉ መሠረተ ልማቶች ለመገንባት ታስቧል ብለዋል::
ከሀዋሳ በር እስከ ፍቅር ሐይቅ ያለው ፕሮጀክት ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ሌሎች ግንባታዎች እንደሚገባ ጠቅሰው፣ አሁን የተያዘው አቅጣጫ ፕሮጀክት መጀመር ብቻ ሳይሆን ጨርሶ ማሳየት እንደመሆኑ የተያዘውን በማጠናቀቅ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ይገባል ሲሉ አብራርተዋል:: ሁሉም ግን እንዲያያዙ እንደሚደረግ ገልጸዋል::
ሌላው የኮሪደር ልማቱ ሲካሄድበት የቆየው አካባቢ ከሜምቦ አደባባይ እስከ ሪፈራል ሆስፒታል ያለው መንገድ ነው፤ የዚህ ግንባታ እየተጠናቀቀ መሆኑንና አካባቢውን ይበልጥ ውብ ማድረግ ማስቻሉን ገልጸዋል::
ወይዘሮ መቅደስ ወደፊት የኮሪደር ልማት የሚካሄድበትን የከተማዋን መሐል አካባቢም ጠቁመዋል:: ይህ ሚሊኒየም አደባባይ አካባቢ /ገብርኤል ቤተክርስቲያን አካባቢ/ የሚገኙ ነባር ግንባታዎችን በሙሉ በማንሳት የሚካሄድ ፕሮጀክት ሲሆን፣ ለከተማዋ ሕዝብ መተንፈሻ የሚሆኑ አረንጓዴ ስፍራዎች፣ ቤተመጽሐፍት፣ የሕጻናት መጫወቻዎች፣ የአረጋውያን ማረፊያዎች፣ ወተር ፓርኮች ለመገንባት መታሰቡን አመልክተዋል::
በኮሪደር ልማቱ የሚገነቡት መሠረተ ልማቶች ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ሀብታሙም ዝቅተኛ ገቢ ያለውም ሊገለገልባቸው በሚችል መልኩ የሚሠሩ ይሆናሉ:: በልማቱ በሚሠሩትና በተሠሩት የውሃ ፓርኮች፣ በሳይክል መንገዶች፣ በሕጻናት መጫወቻዎች ወዘተ ሁሉም የኅብረተሰብ ከፍል ያለምንም ክፍያ ሊዝናና እንደሚችልም ጠቁመዋል::
የከተማዋ የቱሪስት ፍሰት ከዓመት ዓመት እየጨመረ እንደሚገኝ ወይዘሮ መቅደስ ጠቅሰው፣ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 106 ሺ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች እንዲሁም 12 ሺ 250 የውጭ ቱሪስቶች ከተማዋን መጎብኘታቸውንም ተናግረዋል:: የሦስት ወሩ እቅድ የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች 102 ሺ እንደነበረ ጠቅሰው፣ አፈጻጸሙ ከእቅድ በላይ መሆኑን አመልክተዋል:: የውጭ ቱሪስቶች እቅድ 15ሺ እንደነበርም አስታውሰዋል:: እነዚህ የኮሪደር ሥራዎች ተጠናቀው የከተማዋ ውበት ሲጨምር ደግሞ የቱሪስት ፍሰቱ ከዚህ በእጥፍ ሊጨምር እንደሚችል እርግጠኛ ሆኜ እናገራለሁ ሲሉ ተናግረዋል::
የታቦር ተራራ ፕሮጀክት ከተጀመረ ስለመቆየቱና ስለመዘግየቱ፣ ሐይቅ ላይ ሊሠሩ ስለታሰቡ ነገሮች የተጠየቁት የመምሪያ ኃላፊዋ፣ ፕሮጀክቱ መዘግየቱን እሳቸውም አረጋግጠዋል:: ምክንያቱ ከኮንትራት እንዲሁም ከዲዛይን ችግር ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚህም ማስተካከያ ተደርጎ ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተያያዞ እየተሠራ መሆኑን ሊጠናቀቅ የቀረው ሥራ ጥቂት ሥራ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል:: ግንባታውን ፈጥኖ ለማጠናቀቅ እንደ ከተማ አስተዳደርም እንደ ክልልም ቁርጠኝነቱ እንዳለም አስታውቀዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ የሐይቅ ላይ የትራንስፖርቱ አገልግሎቱ በዘመናዊ ጀልባዎች ጭምር እየተካሄደ ነው፤ ከ100 ሰው በላይ የሚጭኑ ባለወለል ጀልባዎች አሉ:: ይህ አገልግሎት ብዙዎችን የሚያዝናና እና ሌላ ቦታ የሌለ የሚባል ነው:: ሐይቁ የካፌ አገልግሎት በተንሳፋፊ ቤቶች እየተሰጠበት የሚገኝም ነው::
በኮሪደር ልማቱ ደግሞ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ይሠራሉ ተብሎ ታስቧል:: ፕሮጀክቶቹ ወደፊት ይፋ የሚደረጉ ሲሆኑ የሳይክል መንገድ፣ የንባብ ቤቶች፣ ቢች በአሸዋ ላይ የሚሠራ ፕሮጀክትም ይኖራል፤ እንዲኖር ይደረጋል::
የሀዋሳ ከተማ ወደ ሐይቁ ማዶ እየተስፋፋ መሆኑንም ወይዘሮ መቅደስ ጠቅሰው፣ ሪዞርቶች፣ ሎጆችና ሆቴሎች ተገንብተው ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል:: እሳቸው እንደተናገሩት፤ ጎብኚዎች ሀዋሳ ማደር ካልፈለጉ 100 ብር ብቻ ከፍለው በጀልባ ወደ እነዚህ አካባቢዎች ተሻግረው ማደር ይችላሉ፤ በዚያው ልክም ማዶ ውለው ለአዳር ተመልሰው መምጣት ይችላሉ::
ከተማዋ ወደፊት የምታድገው በሐይቅ ማዶ አካባቢ እንደመሆኑ ለኢንቨስትመንት የሚያስፈልጉ ቦታዎች እየተሰጡ ናቸው:: ሁለቱን የከተማዋን አካባቢዎች ማገናኘት የግድ ነው፤ ይህን የሚያተሳስር የትራንስፖርት አገልግሎት ወደፊት ይኖራል ተብሎ ታስቧል፤ ፕሮጀክቱን ጊዜው ሲደርስ ብናነሳው ይሻላል ሲሉም ወይዘሮ መቅደስ ጠቁመዋል::
በሐይቁ አካባቢም እንዲሁ በቀጣይ የሚካሄዱና ጊዜው ሲደርስ ይፋ የሚደረጉ ፕሮጀክቶች እንዳሉ ጠቅሰው፣ በሐይቁ፣ ጉዱማሌ ፓርክ፣ የዓሣ ገበያ፣ ፍቅር ሐይቅ የቱሪስት አገልግሎቶች እየተሰጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል:: ዓሣውና ሾርባው፣ የጀልባው መዝናኛው ሀዋሳን ይበልጥ ያስተዋውቃታል፤ ሁሉንም ይበልጥ ለማዘመን በቀጣይ የሚሠራ ይሆናል ሲሉ አመልክተዋል::
ከሁለት ዓመት በፊት የሐይቁን አካባቢ ለመጠበቅ ሲባል ማናቸውም ግንባታዎችና ሥራዎች ከሐይቁ ከአንድ መቶ ሜትር ርቀት ላይ ብቻ መካሄድ እንዳለባቸው የተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ለቱሪስቶች አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ ማኅበራት ከአካባቢው እንዲነሱ ተደርጎ እንደነበር አስታውሰው፣ የሚፈለገው ፕሮጀክት ወደ ሥራ እስኪገባ ድረስ አገልግሎቶቹ እንዲቀጥሉ የሚል ውሳኔ መተላለፉንና ማኅበራት እንደገና ገብተው መሥራት እንዲጀምሩ መደረጉን አስታውቀዋል::
ከተማዋ በብስክሌት ትራንስፖርትና ስፖርት ትታወቃለች፤ ይህን መጠበቅ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የመምሪያ ኃላፊዋ ጠቁመዋል:: ሁሉም የኮሪደር ልማት ሥራዎች ሁሉም የከተማዋ መንገዶች ብስክሌትን ያካተቱ ተደርገው እንደሚገነቡ ጠቅሰው፣ የሜምቦ ሪፈራል እንዲሁም የሀዋሳ ጌት ሻፌታ ታወር የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ለብስክሌት መንገድ ትኩረት መስጠታቸውን አስታውቀዋል:: የኮሪደር ልማቱ የብስክሌት ስፖርቱ ከፍ እንዲል ያደርጋል ሲሉም ገልጸዋል::
በኮሪደር ልማቱ የተጀመሩ ሥራዎች በጣም አመርቂ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በሦስትና በአራት ወራት እያለቁ ናቸው፤ አራት ዓመት አምስት ዓመት የሚፈጁ ፕሮጀክቶች ነበሩ፣ ተጀምረው የማይጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ነበሩ፤ በአሁኑ ወቅት ግን በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅጣጫ መሠረት ሁሉም ክልሎችና ከተሞች ፕሮጀክቶችን እየጀመሩ እየጨረሱ ናቸው፤ የኛም ከተማ በሦስት ወር ውስጥ አንድ ፕሮጀክት ያስመርቃል፤ ቀጣዩ ደግሞ ተጀምሯል፤ ያ ሲጠናቀቅ ሌላው ይጀመራል ሲሉ አስታውቀዋል:: በዚህ አይነት ሁኔታ የከተማዋን የቱሪስት መስሕቦችና መዳረሻዎች እንዲያያዙ ለማድረግ ይሠራል ብለዋል::
በሀዋሳ መግቢያ በር ጥቁር ውሃ አካባቢ የከተማዋ የቱሪስት መረጃ ማዕከል መከፈቱን መምሪያ ኃላፊዋ ጠቁመው፣ በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምርም አስታውቀዋል:: በዚህም በዌብ ሳይትና በሌሎች ዘመኑን በዋጁ ቴክኖሎጂዎች መስሕቦቻችን እያስተዋወቅን ከሄድን የተሻለ የቱሪስት ፍሰት ይኖራል ብዬ አምናለሁ ሲሉም አስታውቀዋል::
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ኅዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም