ጋዜጠኝነት ክቡር ሞያ ነው:: ክቡርነቱም ክቡር ከሆነው ከሰው ልጅ ሕይወት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ በመሆኑ ነው:: ጋዜጠኝነት ክቡር ብቻ አይደለም ታላቅም ነው:: መነሻውም መድረሻውም የሰውነት ተፈጥሮ ነው! ዓላማው ሕዝብና የሕዝብ ጥቅምን ማስጠበቅ ነው::
ተልዕኮው ሰውን አስቀድሞ በሰዎች መካከል እኩልነት፣ ፍትህ፣ ሰላም፣ ዲሞክራሲ እንዲኖር፤ የሃገርና ሕዝብ ዕድገትና ብልጽግና እንዲረጋገጥ መንገድ ማቃናት ነው:: ከዚህ የሚበልጥ ትልቅ ዓላማም የለም:: ትልቅ ስም ብቻ ሳይሆን ትልቅ ኃላፊነትን የሚያሸክምም ነው:: በሌላ በኩል ጋዜጠኝነት ሕዝብን ያክል ነገር የመምራት ትልቅ ኃላፊነት የተጣለበት የመንግሥትነት ሚናም የተሰጠው ሞያ ነው::
ሚና ብቻ አይደለም፤ ጋዜጠኝነት በራሱ አራተኛ መንግሥት ነው:: መንግሥትነት ደግሞ ትልቅም ከባድም ነገር ነው:: መንግሥትነት ደግሞ ቀላል ነገር አይደለም፣ እንደ መንግሥትነት ከባድ ነገርም የለም:: “መንግሥትና እግዚአብሔር አንድ ናቸው” የሚለው የአገሬ ሰው አባባልም ዝም ብሎ የተባለ አይደለም:: ትልቅ ሚስጥርን ያዘለ ዕፁብ ድንቅ የሚያስብል አስተሳሰብን የተሸከመ ፍልስፍና ነው::
ለምን ቢባል በዚህ አባባል ውስጥ “አንድ ናቸው” የሚለው ተለዋጭ ዘይቤ የሁለት ታላላቅ አካላትን ማንነት ማሳየት ዋነኛ ዓላማው ነው – የመንግሥትንና የእግዚአብሔርን የግብር ተነጻጻሪነት! ታዲያ እዚህ ጋር “መንግሥትና እግዚአብሔር የሚመሳሰሉበት (አንድ የሚሆኑበት) ማለትም የግብር ተመሳስሎአቸው በምንድር ነው?” የሚለውን ጥያቄ ስንመልስ ነው የሚስጥሩ ሚስጥር የሚገለጽልን::
ታላቁ ሚስጥር “እግዚአብሔር የዓለሙን ፍጥረት ከፈጠረ በኋላ ዝም ብሎ ያለ ሕግ አልተወውም የሚል ነው”:: የፈጠረውን ፍጥረት ሁሉ፣ ሕይወት ያለውንም ሕይወት የሌለውንም፣ የሚታየውንም የማይታየውንም፣ ሰማይንም ምድርንም የሚያስተዳድርበት ሕግና ሥርዓት አበጅቶለታል:: ዳር ድንበር፣ ወሰንና መዳረሻ፣ ቅርጽና መጠን፣ ልኬት ሕልቆ መሳፍርት በሌለው አጽናፈ ዓለም ውስጥ ያለውን ፍጥረት ሁሉንም እንደየፍጥርጥሩ በሥርዓቱና በአግባቡ ይመራል፣ ያስተዳድራል::
ይህም ብቻ አይደለም እግዚአብሔር ለሚመራውና ለሚያስተዳድረው ፍጥረቱ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ሁሉ አንዳችም ሳያስቀር አሟልቶ ያቀርባል:: ቀንና ሌሊትን፣ ፀሃይና ጨረቃን፣ ክረምትና በጋን እያፈራረቀ ፍጡራኖቹን ይመግባል:: ይህንንም የሚያደርገው ሳይጠየቅ ነው:: ምክንያቱም ሰማይና ምድርን መምራትና ማስተዳደር ታላቅ ስልጣን ብቻ ሳይሆን ታላቅ ኃላፊነትም በመሆኑ ነው::
መንግሥትም እንደ እግዚአብሔር ሁሉ ከባዱንና ትልቁን “የመምራትና የማስተዳደር ስልጣን” የተሸከመ መሆኑ ነው ትልቅ ያስባለው:: ምክንያቱም ሁሉንም ከፊት ሆኖ በበላይነትና በአዛዥነት መምራትና ማስተዳደር ብቻ ሳይሆን ልክ እንደ እግዚአብሔር ሁሉ ያለ ማንም ጎትጓችነትና ጠያቂነት የሚመሩትን አካል ደህንነትና ጥቅም በአግባቡ አስጠብቆ መገኘትን ግድ ይላል::
በሌላ አባባል ከታላቁ ስልጣን ጀርባ ከባድ ተጠያቂነት መኖሩንም አውቆ ኃለፊነትን በአግባቡ መወጣትን ይጠይቃል:: ሕዝብን የመምራትና የማስተዳደር ስልጣንና ኃላፊነት ወይም የመንግሥት ተግባር ምን ያህል ከባድ መሆኑን ለመግለጽ “መንግሥትና እግዚአብሔር አንድ ናቸው” ከሚለው የእኛው ኢትዮጵያዊ አባባል በላይ የተሻለ ማሳያ ሊኖር እንደማይችል የሚያስረግጥ ነው:: ዓረፍተ ነገሩ ከአባባልነትም በላይ ግሩም ድንቅ የሆነ ሚስጥር በውስጡ አምቆ የያዘ ጥልቅ ፍልስፍና ነው የተባለበት ምክንያትም ይኸው ነው::
መንግሥትነት ይህን ያህል ትልቅና ከባድ ነገር ከሆነ መንግሥት ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ማለትም መንግሥት በስልጣኑ እንዳይባልግና ሕዝብን እንዳይበድል የመንግሥትን አሠራር የመቆጣጠር ኃላፊነት የተጣለበት ጋዜጠኝነት ደግሞ ከመንግሥትነትም በላይ ታላቅና ከባድም ነው!
ይሁን እንጂ ሃቁ ይኼ ሆኖ ሳለ የጋዜጠኝነት ሞያ የታላቅነቱን ያህል የሚያሸክመውን ታላቅ ኃላፊነት የራሱ አካላት ከጋዜጠኝነት መርህ ፍጹም በተቃራኒው ሲጓዙ በተለያዩ ጊዜያት በዓለማችን ላይ ተስተውለዋል:: ለሰውና ለሰው ደህንነት ከሚታገለው ከእውነተኛው የጋዜጠኝነት ሞያ የወጡት እነዚህ አካላትም ከዓላማው በተቃራኒ ሞያውን ለሰው ጥፋት ሲጠቀሙበትም ተስተውሏል::
ለሰው ልጆች ሕይወትና ደህንነት ዘብ የሚቆመው ታላቁ ሞያም ለታላቅ ጥፋት መሳሪያ ሆኖ ሲያገለግልም የሰው ልጅ በዓይኑ በብረቱ የተመለከተበት ታሪክም የዓለማችን የቅርብ ትውስታ ነው:: አሁን ላይ በእኛ ሃገር በተለይም ከለውጡ በኋላ ሃገራችን ውስጥ ባሉ አንዳንድ የሚዲያ ተቋማት የምናስተውለው ሁኔታም ይህንኑ ነው::
ሕዝብና የሕዝብን ጥቅም በማስቀደም፣ በሰዎችና በሕዝቦች መካከል እኩልነት፣ ፍትህ፣ ሰላም፣ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን፣ የሃገር ዕድገትና ብልጽግና እንዲመጣ በመስራት ፋንታ ጋዜጠኝነት ለብዙ ሺ ዘመናት አብሮ በኖረ ወንድማማች ሕዝብ መካከል በክፋት ፈላስፎች የተፈበረከ ሃሰተኛ የጥፋት ታሪክን ለማስተማር እያገለገለ ይገኛል::
በተለይም ድህረ ዘመናዊነትና ቁሳዊነት ከፈጠረው ልቅነትና ሞራላዊ ዝንፈት ጋር ተያይዞ ክቡሩ ሞያ ጋዜጠኝነት ጥላቻን የሚሰብኩ፣ ወንድም ወንድሙን እንዲያፈናቅል፣ እንዲገድል አመራር የሚሰጡ ከአውሬም ከሴጣንም የሚብስ የክፋት፣ የጭካኔና የጥፋት ስብዕና የተላበሱ ታህተ-ሰብዕ ሰዎች የሚሰሩት አሳፋሪ ሞያ ሆኗል::
ምክንያታዊ ልዩነቶች እንኳን በመቀራረብና በመነጋገር፣ በውይይታና በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበት ዲሞክራሲያዊ ባህል እንዲዳብር ሰው ሁሉ በእኩልነትና በሰላም አብሮ እንዲኖር የሚታገለው አፍቃሬ ሰብኡ ሞያ ጋዜጠኝነት የሰው ልጅ ወዶ ባልሆነው ተፈጥሯዊ ልዩነቱ ምክንያት እርስ በእርሱ እንዲጠፋፋ የሃሰት መረጃን የሚያሰራጭ ፀረ ሰው ሞያ ሆኖ ታይቷል::
ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በሀገራችን እየተከሰቱ ባሉ ግጭቶች እንደምንታዘበው ሁልጊዜ እውነትን መሰረት አድርጎ ለሰው ልጆች ሕይወትና ደህንነት ዘብ የሚቆመው ታላቁ ሞያ ጋዜጠኝነት በሃሰተኛ መረጃ ስርጭትና ቅስቀሳ ክቡር የሆነው የሰው ልጆች ሕይወት እንዲጠፋ ምክንያት ሲሆን ብሎም ግጭቶች ወደ አስከፊው የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲለወጡ ሁነቶችን በልዩ ትኩረት ሲያስተላልፍ ሰምተናል፣ ተመልክተናል::
ታዲያ ታላቁንና ክቡሩን ሞያ በዚህ መንገድ የሚተገብሩ ሰዎችን ስናይ “እነዚህ ሰዎች እንዲህ የሚያደርጉት እውነት የሞያውን ምንነት፣ ሥነ ምግባርና ለሰው ልጆች ሁለንተናዊ ሕይወት የሚያበረክተውን ታላቅ አስተዋጽኦ ያህል በአግባቡ ካልተገበሩት በዚያው ልክ የሚያስከትለውን ታላቅ ጥፋት የማያውቁት ሆነው ይሆን?” “ወይስ እያወቁትም ቢሆን እንዲያደርጉት የሚያስገድድ ክፉ አለቃ ኖሮባቸው ይሆን?” ብለን መጠየቃችን የማይቀር ነው::
እኔ ሁለተኛው ነው የሚል ጥርጣሬ አለኝ – እያወቁትም ቢሆን በግዴታ ከእውነታው የሚያጣላ፣ ሕሊናቸውን አውሮ፣ እጅና እግራቸውን አስሮ ለጥፋት የሚያሰማራ አደገኛ አለቃ ያለባቸው ይመስለኛል:: የአለቃው ስምም “አዛዥ ጥቅሙ” ይባላል (የኔ ግምት ነው እንግዲህ):: አለቃው በጠባብ የጥቅም ፖለቲካ ሕዝብን በተለያዬ መንገድ በመከፋፈልና በመነጣጠል ከዚያም እንደ ግል ቤቱ በብቸኝነት አጥሮ ይዞ፣ ሕዝብን በማስያዣነት አቅርቦ የስልጣንም ሆነ የገንዘብ ጥሙን ለማርካትና የፈለገውን ሁሉ ማግኜት ነው
ሕሊና የመልካምና ክፉ ነገሮች ሁሉ መመዘኛ፣ የእውነተኛው ዳኛ መቀመጫ መንበረ እግዚአብሔር ነውና ለጥቅም ብሎ አንድን ጥፋት ሆን ብሎ እያወቁ መፈጸም የኋላ ኋላ እረፍት አይሰጥም:: ጥፋቱ የሚፈጸመው በሰው ልጆች ሕይወትና በሕዝብ ላይ ሲሆን ደግሞ የበለጠ ያማል:: እናም “ሰው አየ፣ እግዚአብሔር አየ” ነውና፣ የሕሊና ሰላም ባለበት ደረቅ ቆሎ፤ በክህደት ከሚቆረጥ ጮማ ይበልጣልና በእንዲህ ዓይነት አጥፊ የጋዜጠኝነት ተግባር ላይ የተሰማራችሁ ወገኖች ለገንዘብ ወይንም ለቁሳዊ ጥቅም ከሆነ በዚህ የጥፋት ድርጊት ላይ የተሰማሩት ቢተውት መልካም ነው::
ሁለተኛ ነገር በሕዝብ ላይ የሚሰራ በደል ከበደል ሁሉ የከፋ ነው:: የተማሩ መሃይማን ሊያፈርሷት የሚታገሏትን አገር ሳይማር በጥበብ ገንብቶ ታላቅ አገር ለትውልድ ያወረሰ ታላቅ ሕዝብን በገንዘብ፣ በቁሳዊ ጥቅም አለያም በርካሽ ፖለቲካዊ ፍላጎትና ስልጣን ጥማት የደህንነት መንገድ የሆነውን መልካሙን ሞያ ተጠቅሞ ሕዝብ ላይ ለጥፋት መዝመት አንድ ቀን በራስ ላይ ጥፋት ያመጣል::
ሚዲያን ተጠቅመው የሩዋንዳን ሕዝብ ለጥፋት የዳረጉት የጥፋት አበጋዞች እነርሱም አልተረፉም፤ በደገሱት የጥፋት ማዕበል አብረው ጠፍተዋል:: ይህን የምለው እነዚህ የጥፋት ተዋንያን በምክር ይመለሳሉ ብየ አይደለም:: በሌላው መንገድ ሞክረውት፣ ሞክረውት አልሳካ ያላቸው እና ሚዲያንና ክቡር የሆነውን ሞያ በመጠቀም አሁን ላይ ሕዝብን በሕዝብ እያነሳሱ በሃገር ላይ ጥፋትን እየደገሱ የሚገኙት እንዲህ ዓይነቶቹ የጥፋት ልጆች አብዛኞቹ ፍቅርና ይቅርታ አያውቁም::
ይቅርታ ስታደርግላቸው የሚገድሉ፣ ስትስማቸው የሚነክሱ እነዚህ የጥፋት ልጆች ለየት ያሉ ፍጡራን በመሆናቸው እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ እነርሱ ጋር አይሰራም:: እናም ከተለመደው አካሄድ የተለየ ለእነርሱ ባህርይ የሚሆን ተገቢነት ያለው ተጨባጭ እውነታውን የሚዋጅ የመፍትሔ እርምጃ ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል:: ማለትም ለጥቅሙ ሲል ወድዶ ሕሊናውን ሽጦ በጥፋት ተግባር ላይ ለሚሰማራ ኃይል ለክቡሩ የሰው ልጅ ሕይወት ደህንነት ሲባል በሕግ ተገድዶ ከጥፋቱ እንዲመለስ ማድረግ ያስፈልጋል:: ክቡር ለሆነው የሰው ልጅ የሚያገለግለው ክቡሩ ሞያ ጋዜጠኝነት በክብር ይያዝ፤ ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ኅዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም