ብሄራዊ የስፖርት ማህበራት ሥራ አስፈጻሚዎች ምርጫን ተከትሎ ውዝግቦችና አግባብነት የሌላቸው አካሄዶችን መመልከት በኢትዮጵያ ስፖርት የተለመደ ነው:: ለአንድ ስፖርት በእውቀት፣ በጉልበትና በገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ለእድገቱ ከመሥራት ባለፈ የተለየ ጥቅማ ጥቅም ይገኝበት ይመስል የሚከወኑ ተግባራት የሚያስተዛዝቡ ሆነዋል:: በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ከሚሰጥ ውክልና አንስቶ እስከ ድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ያሉት መጠላለፎች ስፖርቱን ለማገዝ ሳይሆን ከጀርባው የተለየ ዓላማ እንዳለ ያስጠረጥራል::
ኢትዮጵያ ስሟን በበጎ የተከለችበት የአትሌቲክስ ስፖርትም የዚሁ ገፈት ቀማሽ ከሆነ ሰነባብቷል:: በዓለም አቀፍ ውድድሮች ከጊዜ ወደጊዜ እያሽቆለቆለ የሚገኘውን ውጤት ጨምሮ በርካታ አስተዳደራዊና የአሠራር ችግሮች በተደጋጋሚ እየተወቀሰ ያለው ፌዴሬሽኑ በሥራ አስፈጻሚ ምርጫ ወቅት ደግሞ ሌላ መልክ ይይዛል::
ዘንድሮም ፌዴሬሽኑ አዲስ ፕሬዚዳንትና ሥራ አስፈፃሚ አባላትን ለመምረጥ በተቃረበበት በዚህ ወቅት የሚታዩ ሽኩቻዎች መጪውን የአትሌቲክስ ጊዜም ይበልጥ አስፈሪ እንዳይሆን ያሰጋል::
ተመራጮች ለስፖርቱ እድገት፣ ኢትዮጵያ ከአቻዎቿ ጋር ለሚኖራት ተፎካካሪነት እንዲሁም ሀገርን ለሚያስጠሩ አትሌቶች ቅድሚያ ከመስጠት ይልቅ ለሚቀመጡባት አንዲት ወንበር የሚጨነቁ መሆን የለበትም::
በጀግናውና ታላቁ አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ የባዶ እግር ድል የተፈጠረው የኢትዮጵያና የአትሌቲክስ ስፖርት ዝምድና የተከበሩ ይድነቃቸው ተሰማ እና ንጉሤ ሮባን በመሳሰሉ የስፖርቱ ባለውለታዎች ተጠናክሮ ዛሬ መድረሱ ይታወቃል:: ይሁን እንጂ ዘመኑ ከደረሰበት ሥልጣኔና የሌላው ዓለም አሠራር አንጻር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ እየዳከረ የሚገኝበት አካሄድ ሽቅብ ሳይሆን ቁልቁል ይዞት እንዳይወርድ ያሰጋል:: ከምድሯ ምርጥ አትሌቶችን ማፍራት የቀጠለችው ሀገር ፌዴሬሽኑን ለመምራት በሚደረግ የእርስ በእርስ ሴራና ሽኩቻ ቦታው በማይመጥነው ሰው እንዳይያዝ መጠንቀቅ ያስፈልጋል::
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አሁን ላይ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ዓለም አቀፍ ውድድሮች በደል ደርሶባቸው ሲያነቡ የታዩ አትሌቶችና አለአግባብ የተገፉ አሠልጣኞችን ሮሮ ሰምቶ እንባቸውን የሚያብስ አመራር ነው የሚፈልገው::
በቅርቡ የሚካሄደውን የፌዴሬሽኑ 28ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔና እሱን ተከትሎ በሚከናወነው የሥራ አስፈጸሚ ኮሚቴ ምርጫ ተሳታፊ የሚሆኑ እጩዎች ከቀናት በፊት ታውቀዋል:: ይሁንና በትክክለኛው መንገድ ከመታወቃቸው አስቀድሞ ስሌታዊ በሆነ መንገድ እነማን በየትኛው ክልል አሊያም ከተማ አስተዳደር ሊወከሉ ይችላሉ የሚለው ይታወቅ ነበር:: ምክንያቱ ደግሞ አካሄዱ ትክክለኛውን መንገድ ሳይሆን ብልጣ ብልጥነት የተንሰራፋበትና ሥልጣንን ብቻ ዓላማ ያደረገ በመሆኑ ነው:: በተለያዩ ቡድኖች በመከፋፈልም አንዱ ሌላኛውን ለማዳከም መታተራቸውም ለስፖርት ቤተሰብ በገሃድ እየታየ ይገኛል::
ብሄራዊ ፌዴሬሽኑን ለመምራት የሚደረገው ሽኩቻ እዚያው የሚወሰን ሳይሆን እንደየደረጃው እየወረደ ያለና በጉባዔው ድምጽ የመስጠት መብት ባላቸው ማህበራትንም ያዳረሰ መሆኑ ደግሞ የጉዳዩን አሳሳቢነት ይበልጥ ያጎላዋል::
ከዚህ ቀደም ፌዴሬሽኑ ይመራበት የነበረው የሥራ አስፈጻሚ አወቃቀር ስፖርቱን በማያውቁ ሰዎች መሆኑ ተጽዕኖ አድርጎብናል ያሉ አትሌቶች ከፍተኛ ንቅናቄ በመፍጠራቸው አትሌቶችን ወደ አስተዳደሩ ቦታ እንዲመጡ ማድረጉ የሚታወስ ነው:: ይሁንና ባለፉት ሁለት የሥልጣን ዘመናት ከታዩ አንዳንድ መልካም ጅምሮች ባለፈ አስቀድሞ እንደተጠበቀው አዲስ ነገር ሊታይ አልቻለም:: ስፖርቱን የመሩ አንጋፋ አትሌቶችም መሬት ላይ ሊወርድ የቻለ ውጤታማ አሠራር ተግባራዊ አለማድረጋቸው አትሌቱን ሊያስደስትም ሆነ እንደ ሀገር ውጤታማ ሊያደርግ አልቻለም:: በመሆኑም ለመሪነት በስፖርቱ ውስጥ ማለፍ ብቻም ሳይሆን በእውቀት፣ በሥርዓት እና በእቅድ መሥራት የሚችል ሰው የግድ አስፈላጊ መሆኑ ሊሠመርበት ይገባል::
ስለስፖርቱ እድገት የሚቆረቆሩና አቅም ያላቸው ሙያተኞች ወደፊት ከመምጣት ይልቅ ምርጫው እየቀሩት በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የእጩዎች ማሳወቂያ ጊዜ አንስቶ በርካታ አነጋጋሪና ግራ አጋቢ ሁኔታዎች ሲከሰቱ ቆይተዋል:: ለእጩነት የሚቀርቡ አካላት ለአንድ ክልል ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አለማግኘትን ተከትሎ ሌሎች ክልሎችን እንደ አማራጭ መጠቀም ሁኔታ በግልጽ ታይቷል:: ሕጉ የሚፈቅድላቸው ቢሆንም ከዚህ ቀደም በፌዴሬሽኑ ውስጥ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ያገለገሉ ነገር ግን ስፖርቱን ማሳደግ ያልቻሉ አካላትን በድጋሚ ለተመራጭነት ማቅረብ ደግሞ በክልሎች በኩል የታየ ግዴለሽነትና የሚያስታዝብ ሁኔታ ነው::
አትሌቶችም ሆኑ ሌሎች ከፌዴሬሽኑ በሥራ አስፈጻሚነት ምርጫ የቀረቡ አካላት ሥልጣን ለማግኘት ከሚያደርጉት ርብርብ ይልቅ ለስፖርቱ ተስፋ ሰጪ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንደሚገባቸው ለስፖርቱ የሚቆረቆሩ አካላት አበክረው ይገልጻሉ:: በአትሌቶች ዘንድ በተደጋጋሚ የሚነሱ ጥያቄዎችና ቅሬታዎችን ለመመለስና በቀጣይም መሰል ሁኔታ እንዳይፈጠር የሚያስችል አሠራርን መዘርጋትም ተጠባቂ ጉዳይ ነው:: ፌዴሬሽኑ የሚሠራው ለስፖርቱ ሆኖ ሳለ የስፖርቱ ዋነኛ ተዋናዮች ግን አሁንም ድረስ ከለላ የሚሆናቸውንና በፍትሃዊነት የሚያስተናግዳቸው ባለማግኘታቸው ምክንያት ዓለም አቀፍ ውድድሮች በተካሄዱ ቁጥር እምባቸውንና ምሬታቸውን መመልከት የተለመደ ሆኗል:: ጥቂት የማይባሉትም በዚሁ የአሠራር ብልሽት ምክንያት ተሰደው ለማያውቁት ሀገር በዜግነት ተሰልፈው ኢትዮጵያን ለመርታት በመፎካከር ላይ ይገኛሉ:: በእርግጥ ይህ ሁኔታ ያማል ነገር ግን በትክክል ለአትሌቱ መቆምና መብቱን ማስከበር የቻለ አካል ማግኘት ለዓመታት ምኞት ብቻ ሆኖ ቀርቷል::
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ አባላት መካከል አንዱ የአትሌቶች ማህበሩ ቢሆንም የሚመሩትን አካላት ለመምረጥ የሚያስችለው የድምጽ መጠን ግን ግራ አጋቢ ነው:: በመሆኑም በጠቅላላ ጉባዔው ድምዳሜ ላይ የሚደረሱ ነገር ግን አትሌቱን ሊጎዱ የሚችሉ ውሳኔዎችን የማስቀየርም ሆነ እነሱን ያማከለ አሠራር ተግባራዊ እንዲሆን የሚያስችል አቅም ማዳበር አልቻለም:: ይህም አትሌቶችን በሚመለከት ጉዳይ ላይ ሁሌም መፍትሄ አልባ የሆኑ ቅሬታዎች ምንጭ ሊሆን ችሏል::
የአትሌቲክስ ስፖርት ኢትዮጵያን ከሌላው ዓለም በቁንጮነት ያስቀመጣት የሀገር ባለውለታ ስለመሆኑ በአያጠራጥርም:: ለስፖርቱ የተመቸ የአየር ሁኔታ እና መልከዓ ምድር፣ እጅግ በርካታ ውጤታማና በማደግ ላይ ያሉ አትሌቶችም አሏት:: በዚህም ምክንያት ታላላቅና ዓለም አቀፍ የሩጫ ውድድሮችን የማስተናገድ ሰፊ እድል አላት:: ይሁንና እንኳን ውድድሮችን ለማስተናገድ የሚያስችሉ ጥራታቸውን የጠበቁ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ ይቅርና አትሌቶች ዝግጅት ታዳጊዎችም ልምምድ የሚያደርጉበት ሥፍራ እንደልብ ለማግኘት ፈታኝ ነው:: ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ሀገር አቀፍ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር ውድድሮችን ለማስተናገድ መሰናክሎችን ማለፍ አስገዳጅ መሆኑን ነው:: በእርግጥ ፌዴሬሽኖች የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን የማስገንባት ኃላፊነትና አቅም የላቸውም:: ነገር ግን ከሕዝቡ የሚወከሉትና ዓላማውም በሃሳብ፣ በጉልበትና በገንዘብ ስፖርቱን ያግዛሉ በሚል የሚመረጡ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የተለያዩ ስትራቴጄዎችን በመቅረጽና የተለያዩ አካላትን በማስተባበር አንድ ርምጃ ማራመድ ይጠበቅባቸዋል::
ስለሆነም በዕጩነት የቀረቡ አካላት የታሪክ ተወቃሽ ከመሆን ለመዳን ያላቸውን ጊዜ ሊጠቀሙ ይገባል:: ሥልጣን ከመያዝ ባለፈ በመጪዎቹ አራት ዓመታት በምን መልኩ ስፖርቱን ተፎካካሪ እንደሆነ ለማቆየት ያስችላል፣ ከእነማን ጋር መሥራት ውጤታማ ያደርጋል እንዲሁም መከተል ስለሚገባቸው የረጅም ጊዜ ዕቅዶች ማሰላሰልና ከወዲሁ መዘጋጀት ይገባቸዋል:: ከሥልጣንና ጥቅማ ጥቅም ሀገር ትልቃለችና የኢትዮጵያን አትሌቲክስ አስቀድሙ!!
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ኅዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም