በሕዝብ ግፊትና በፓርቲ ሳቢነት የተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ በማለፍ ዛሬ አምስተኛ ዓመቱን እያከበረ ነው። በነዚህ ዓመታት ከፍ ያሉ ማህበራዊ፤ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትሩፋቶችን ለሀገር እና ለሕዝብ አስገኝቷል። ከነዚህም ውስጥ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ ሲጠየቁ ለነበሩ ጥያቄዎች ከቃል ያለፈ ተግባራዊ ምላሽ መስጠት ማስቻሉ ተጠቃሽ ነው።
ነባሮቹን ፖለቲካዊ እሤቶች በሚያጎለብትና የፖለቲካ ስብራቶቻችንን በሚጠግን መልኩ ፤ የዳርና የመሐል፤ ዋና እና አጋር፣ አርብቶ አደርና አርሶ አደር፤ ተራማጅና አድኃሪ፤ ጠላትና ወዳጅ፣ ወዘተ. የሚባሉትን ግንቦች በማፍረስ በሃሳብ ላይ ብቻ የተመሠረተ አዲስ ሀገራዊ የፖለቲካ አደረጃጀት እንዲፈጠር ረድቷል።
ተፎካካሪዎቹን በጠላትነት ከመፈረጅ የወጣ፤ የሃሳብ ልዩነቶችን እንደ ጌጥና እሴት አድርጎ የሚወስድ፤ በኢትዮጵያዊ እሴቶች ተመሥርቶ ፣ ከሌሎች ሃሳቦች በመማር፣ በገቢር ነበብ መንገድ የሚጓዝ፤ የርዕዮተ ዓለም እሥረኛ ያልሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ በማስተዋወቅ የኢትዮጵያን የፖለቲካ መልክአ ምድር ለውጧል።
ሲቪክ ተቋማት ላይ የነበረውን የተንሸዋረረ አመለካከት በማስተካከል፣ የታሠሩበትን ቀፍዳጅ ሕግ በማሻሻል ተቋማቱ ለራሳቸው ሆነ ለሀገር እንዲጠቅሙ በሚያስችል አዲስ ሕግና አደረጃጀት እንዲዋቀሩ አስችሏል። በዚህም ከለውጡ በፊት 1 ሺ900 የነበሩ የሲቪክ ማኅበራት ባለፉት አምስት ዓመታት 5 ሺ200 ደርሰዋል።
የዴሞክራሲ ተቋማት ነጻ፣ ገለልተኛና ተአማኒ ለማድረግ ረጅም ርቀት በመሄድ፤ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የሠብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የዕንባ ጠባቂ ተቋም እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን እንደገና እንዲደራጁ የሚያስችል የሕግና የአደረጃጀት ለውጦች እንዲያደርጉ አስችሏል።
መገናኛ ብዙኃን በሕግ ብቻ እንዲሠሩና እንዲተዳደሩ፣ የሁሉም ዓይነት ማኅበረሰብ የሃሳብ ገበታዎች እንዲሆኑ ለማድረግ ፤ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣንን ጨምሮ የመገናኛ ብዙኃን አሣሪ ሕጎች እንዲሻሻሉ አድርጓል። በዚህም ከለውጡ በፊት 122 የነበሩት መገናኛ ብዙኃን በአሁኑ 272 ደርሰዋል። የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ከ25 ወደ 78፤ የሬዲዮ ጣቢያዎች ደግሞ ከ52 ወደ 73 አድገዋል። የቋንቋ ተደራሽነታቸውም 39 ወደ 60 ቋንቋዎች ደርሷል።
በለውጡ ዘመን የነበረውን የኋላ ቀርነት ስብራት ቀርፎ ሀገሪቱን ለማዘመን ፤ በግብርና ዘርፍ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማስከበር በተሠራው ሥራ የባህልም የውጤትም ለውጥ እንዲመጣ አስቻይ ሁኔታዎችን ፈጥሯል።
ከዚህ በፊት የዝናብም ወቅት ብቻ ይጠብቅ የነበረው የግብርና ሥራ ባህል በመቀየር ዓመቱን ሙሉ የሚመረትበት ባህል እንዲመጣ አስችሏል። ስንዴን፣ ሩዝን፣ ገብስን፣ በቆሎንና የፍራፍሬ ምርቶችን ትኩረት አድርጎ በተሠራው ሥራ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚዋ የስንዴ አምራች ሀገር ሆናለች። ስንዴን ከውጭ ማስመጣትም አቁማለች። በአትክልትና በፍራፍሬ ዘርፍም የወጪ ምርት መጠናችን ጨምሯል።
በሌማት ትሩፋት በተሠራው ሥራ የወተት፣ የዶሮና የማር ምርቶች በየቤተሰቡ ሌማት ላይ እንዲገኙ የአስተሳሰብ መሠረት ፈጥሯል። በዚህም የዶሮ ሥጋን ምርት ከነበረበት 70 ሺህ ቶን ወደ 208 ሺ ቶን፤ የወተት ምርት ከነበረበት 7.2 ቢሊዮን ሊትር ወደ 10 ቢሊዮን ሊትር ደርሷል። የማር ምርት ደግሞ ከ129 ሺህ ቶን ምርት ወደ 272 ሺህ ቶን ለማሳደግ ተችሏል።
ኢትዮጵያ አረንጓዴ በማልበስ ሂደት ውስጥም ባለፉት ስድስት ዓመታት 40 ቢሊዮን የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ተተክለዋል። ከእነዚህ ውስጥ 50.4 በመቶ የደን ዛፍ ችግኞች፣ 48.6 በመቶ ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚሰጡ፣ የፍራፍሬ፣ የመኖና የማገዶ የእንጨት ዛፎች ናቸው። ይህም የለውጡ ትልቁ ትሩፋት ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
የኢንዱስትሪ ዘርፍ ምርታማነት ለማሳደግ በተሰሩ ሥራዎች ብዛት ያላቸው ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት አስችሏል። ከዚህ በፊት ከውጪ የሚገቡትን የቢራ ብቅል፣ የምግብ ዘይት፣ ፓስታና አልሚ ምግቦች፣ የተማሪዎች ዩኒፎርም፣ የጸጥታ አባላት የደንብ ልብስ፣ የኤሌክትሪክ ዕቃዎች (ፖል፣ገመድና ትራንስፎርመር) በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት ሥራ ውጤት እያሳየ ይገኛል።
በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በዲጂታል ኢትዮጵያ እና በሌሎች ቴክኖሎጂዎች ላይ የሚያደርገው ምርምር እና የሚያፈሰው ሙዓለ ንዋይ አሳድጓል። ለዚህም ቀደም ሲል የነበረው የዲጂታል አካውንት ከነበረበት 52.1 ሚሊዮን ዛሬ ወደ 205.4 ሚሊዮን ደርሷል። በዘመናዊ የክፍያ ዘዴ የተላለፈው የገንዘብ መጠንም 9.6 ትሪሊዮን ብር ዕድገት አሳይቷል።
ከተሞች ለዜጎች ምቹ፣ ጤናማና አካታች እንዲሆኑ ለማድረግ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ከአዲስ አበባ ተጀምሮ በአሁኑ ጊዜ ወደ ገጠሪቱ ኢትዮጵያ ደርሷል። በዚህ የዝመና ፕሮጀክት አማካኝነት መሠረተ ልማቶችን የማሟላት፣ ከተሞችን ጽዱና አረንጓዴ የማድረግ፣ በድህነት አኗኗር ውስጥ ላሉ ዜጎች ኢትዮጵያን የሚመጥን የመኖሪያ አካባቢዎችን የመስጠት፣ ሕጻናትና ወጣቶች ከሱስና ከአጉል ሕይወት እንዲርቁ የሚያስችሉ መዋያዎችን የማዘጋጀት፣ ማኅበረሰባዊ ትሥሥርን የሚፈጥሩ አደባባዮችንና መስኮችን የመፍጠር ሥራዎች እንዲሠሩ አቅም ሆኗል።
የጸጥታና የደህንነት ተቋማትን ለማዘመን በተሠራው ሥራ ሠብዓዊ፣ መዋቅራዊና ቴክኖሎጂያዊ ብቃት ያላቸው የጸጥታና የደህንነት ተቋማት እንዲፈጠሩ አስችሏል። እነዚህ ተቋማት ሕገ መንግሥቱን ብቻ መሠረት አድርገው ተልዕኳቸውን እንዲያከናውኑ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ሆነዋል። የሕግ፣ የአሠራርና የአደረጃጀት ሪፎርም በማድረግ ኢትዮጵያን የሚመጥኑ ተቋማት እንዲሆኑ አድርጓል።
በሀገሪቱ የነበረውን የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራት ለመጠገን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ በማድረግ ሁሉን አቀፍ ሥራ እንዲሠራ አስቻይ ሁኔታዎችን ፈጥሯል፤ በዚህም የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች ተተግብረዋል፤ ይህን ተከትሎም ከዓለም አቀፍ ተቋማት የሚገኘው ብድርና ድጋፍ ጨምሯል። የዕዳ ሽግሽግና ቅነሳ ውይይቶች ወደ ውጤት ተቃርበዋል። የሀገራችን የውጭ ምንዛሬ ክምችት አድጓል። የሀገር ውስጥ ገቢን የማሰባሰብ አቅምም ከፍ ብሏል።
ሀገሪቱ ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለመለየትና ለማስከበር ግልጽና ጉልሕ የሆነ መንገድን መከተል ጀምራለች። የባሕር በር የማጣት ስብራትን ለመጠገን በተሠራው ሥራም የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ተገቢና ትክክለኛ መሆኑን ዓለም በብዛት እንዲቀበለው ለማድረግ ተችሏል። በዓለም አቀፍ መድረኮችም ብሔራዊ ጥቅሞችን ሊያስከብሩ በሚችሉ የሁለትዮሽና ባለ ብዙ ዘር ትብብሮች በጉልሕ ትሳተፋለች። እንደ ብሪክስ ባሉ ማሕቀፎች ላይ ያደረጋቸው የአባላነት ተሳትፎም የለውጡ ትሩፋት ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ኅዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም