ሥርዓት አልበኝነትን በአሰራር ሥርዓት መግራት

ረጅም ታሪካዊ ዓመታትን አስቆጥራለች። ብዙዎች እንጀራ የበሉባት፤ ሕይወታቸውን የቀየሩባት፣ አሁንም ድረስ የብዙዎች የሥራ ቦታ የሆነች፤ ከትንሽ እስከ ትልቁ የንግድ እንቅስቃሴ የሚፈስባት የገበያ ስፍራ ናት፡፡ ከአፍሪካ አንደኛው ግዙፉ ” ኦፕን ማርኬት” ተብላ የምትጠራ፤ የተለያየ የምርት ዓይነት የሚገለባበጥባት የኢኮኖሚ መዘወሪያ ማዕከል ናት። ይች ስፍራ ማን ናት ለሚል የአዲስ አበባዋ መርካቶ ገበያ ናት፡፡ መርካቶ ውስጥ ገብቶ ተጠይቆ የሚታጣ ከቶ አንድም ነገር አይታሰብም። ሁልጊዜም ሙሉ ሁሌም ዝግጁ ሆና ደንበኞቿን ትጠብቃለች።

ሠርክ አዲስ ስትሆን በሯ ክፍት ነው። በአነስተኛ ዋጋ ብዙ ነገሮችን መሸመት ያሰበ፤ ሰፊ አማራጮችን ማየት የፈለገ ከመርካቶ ሌላ የተሻለ ገበያ አይመለከትም፤ አይጠራም። ከጅምላ አከፋፋይ እስከ ቸርቻሪ ግለሰብ ተጠቃሚ ሳይቀር የሚፈልገውን በገንዘቡ ገዝቶ፤ በዱቤም ተበድሮ ራሱን ለመለወጥ ሠርቶ ለመክበር ምርጫው የሚያደርገው ይችኑ መርካቶን ነው።

ነጋዴው እርስ በርሱ የሚተማመንበት፣ በዱቤ ተገበያይቶ ሠርቶ የሚከፍልበት፣ እቁብ ጥሎ ራሱን የሚለውጥበት፣ የብዙዎች ሕይወት የተለወጠባት አንቱ የተባሉ ነጋዴዎች ሀብት ያፈሩባት፣ ነጥረው የወጡባት፣ ለከተማውም ማዕከል የሆነች ሥፍራ በመሆኗ ሁሉንም እንደየአቅሙ ታስተናግዳለች።

መርካቶን ከዳር እሥከዳር የማያውቅ አውቆ ሥሟን የማያነሳ ይኖራል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። በየዕለቱ በሕዝብ ትርምስ ደምቃ ትውላለች። ከዜጋው እስከ ውጪ ሀገር ዜጎች ሳይጎበኟት አትውልም፤ ከዘመናዊ ሕንጻ እስከ ጎስቋላ ላስቲክ ለባሽ ጣራ ቤቶች የአይን ስበት ናቸው። በአጠቃላይ የቱሪዝም ገበያ ብትባል ያንስባት ይሆናል እንጂ አይበዛባትም።

ይህች የብዙዎች ዳቦና እንጀራ የሆነች ሥፍራ የሰው ነፍስ ሲቀር ለሽያጭ የማይቀርብበት ነገር እንደሌለም ይታወቃል። ሸማ ተራ፣ ጭድ ተራ፣ ምንአለሽ ተራ፣ ቦምብ ተራ፣ ቅቤ በረንዳ፣ እህል በረንዳ፣ በርበሬ በረንዳ፣ አሮጌ ተራ … የየቦታዎቹ መጠሪያ ስም የሚወጣው እንደየምግባሩ ነው። ተመሳስሎ የተሰሩ እቃዎች የሚገኝባት፣ ብዙዎች በአታላዮች ሀብታቸውን የተነጠቁበት፤ የደኸዩባት መጥፎ ትዝታዎችን በአእምሯቸው ያኑሩባት ቦታም ናት።

በመርካቶ የማይሰራ፣ የሌለ ነገር ቢኖር ” የለም ” የሚለው ቃል ነው። እያንዳንዱ ጥጋጥግ የወንዝዳርና የፍሳሽ መንገድ ሳይቀር የሚታየው አካባቢ ሁሉ የሥራ ቦታ ነው። ጥጋ ጥጉ ሁሉ መጠጋገኛና ማምረቻ የስራ ቦታ ነው። ብዙ ወንጀሎች፣ ንጥቂያ፣ ሕገ ወጥ ተግባራት፣ ማጭበርበር… በስፋት ይታያል ከተባለም በዋነኛነት መርካቶ ነው ብሎ ደፍሮ መናገር ይቻላል። ስንቱ አልቅሶ እርም መርካቶ የሚለው እንዳለ ሁሉ ማን እንደመርካቶ መርካቶን ሳይረግጡ መዋል መታመም ነው የሚሉም ብዙ ናቸው።

በመርካቶ በርካታ መልካም ነገሮች እንዳሉት ሁሉ ያንኑ ያህል ሕገወጥነት የተንሰራፋበት መሆኑም ይታወቃል። ሕጋዊ ስራና ሰራተኛ ፋራ ተደርጎ የሚታሰብበት፣ ደፋር እና ጉልበተኛ የሚነግስበት፣ ሕጋዊነት እንደ ሀጢያት የሚቆጠርበት፣ የተሰረቀ ንብረት በአደባባይ የሚቸበቸብበት ቦታም ነው።

የመንግሥት ሕጋዊ ገቢዎች ገቢ የማይሰበሰብበት፣ ምንም አይነት ደረሰኝ የማይገኝበት የገበያ ቦታ ነው። ይህ ማለት ግን አይን ያፈጠጠውን በአደባባይ የሚታየውን የገነነውን ችግር ለማሳየት እንጂ ሕጋዊ፣ ሀቀኛ፣ መብትና ግዴታቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁ ነጋዴዎች የሉም ለማለት አይደለም። በፊትም ነበሩ፤ አሁንም አሉ ለወደፊትም ይኖራሉ።

ትልቁ ጉዳይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ባለበት በዚህ ስፍራ የሚካሄደው ግብይት ሕግና ስርዓትን በተከተለ መልኩ ነወይ ? በደረሰኝ የሚደረግ ግብይት አለወይ ? የሚለው ነው። ይሄ ሲነሳ ምላሹ “አይደለም” የሚል ይሆናል። ምንም ያህል ገንዘብ የሚያወጣ እቃ (ሸቀጥ) የገዛ ማንኛውም ግለሰብ፣ ቸርቻሪ ወይም ጅምላ አከፋፋይ ከመርካቶ ነጋዴ የሚያገኘው ደረሰኝ እብምብዛም የለም።

ሲቀለድ እንኳን ” በመርካቶ የለም ደረሰኝ።” የሚል ነው። ወደ መርካቶ የሚገባም አብዛኛው ሸቀጥ ደረሰኝ የተቆረጠበት ሳይሆን በኮንትሮባንድ ነው። የፋብሪካ ምርት ውጤት የሆኑ ሸቀጦች፣ አልባሳት፣ የቤት እቃዎች፣ እህል፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ቡና፣ እጣን… እና ሌሎች ቁሳቁሶች በደረሰኝ ገቡ ከተባለም ከገባው ምርት ምናልባትም ተገዛ ተብሎ ደረሰኝ የተቆረጠለት ከግማሽ በታች ያለው ነው። አብዛኛው ሕገ ወጥ ስራ ሚሰራው በሕጋዊ መስመር ተሸፍኖ ነው። በመሆኑም ደረሰኝ ብርቅ ነው።

በሀገራችን በአብዛኛው ነጋዴ ዘንድ ታክስ አለመክፈል፣ ገቢን መሰወርና ግብር መቀነስ የመሳሰሉት እንደ ሕጋዊነት የሚቆጠሩ ልማድ ሆነው ቆይተዋል። ነጋዴ ታክስና ግብር የመሳሰሉ ግዴታውን እንዲወጣ ተወጥሮ ሲያዝ የመጀመሪያ ሥራው የገቢዎች ሰራተኞችን በጥቅም መደለል፣ የንግድ ቤቶችን በዐይን ምልከታ በማድረግና ለግምት በሚመጡበት ሰሞን ለሽያጭ የሚያቀርቡትን ማንኛውንም ሸቀጣ ሸቀጥ መደበቅ እና ናሙና በሚመስል መልኩ ብቻ መጠኑን አሳንሶ ማስቀመጥ ነው።

ክምችትን በተለያየ መጋዘን መደበቅ፣ የሸጡበትንና የገዙበትን ዋጋ ቀንሶ ማሳወቅ የመሳሰሉት ጎልተው የሚታዩ ችግሮች ናቸው። ይሄንን ሕገወጥነት ማቆምና ሕጋዊውን አሰራር ማስፋት አሁን በሀገራችን ለተጀመረው የኢኮኖሚ ሪፎርም ወሳኙና አንዱ መንገድ ሆኗል። ግብርን፣ ቫትን፣ ታክስ፣ እና ሌሎች የገቢ ምንጮችን ጥግ ድረስ አሟጦ በመጠቀም ገቢን የመሰብሰብ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ተደርሷል።

ሀገርን ለመለወጥ በሚሰራው እያንዳንዱ ስራ ላይ መሰረተ ልማት፣ የልማት ኮሪደር፣ ሌላውም ገንዘብ ይፈልጋል። በጀት ይጠይቃል። ይሄ ደግሞ ከሰማይ የሚወርድ አይደለም፤ ሁሉም በሀቀኝነት ሰርቶ ከሚከፍለው እና ከሌሎች ገቢዎችም ተሰብስቦ በሚገኝ ነው።

ሀገሪቱ ከነበረችበት ድህነትና ኋላ ቀርነት ለማውጣት በቆራጥነት መነሳሳት ተፈጥሯል። ያረጁና ያፈጁ ታሪኮችን በመቀየር ከተማዋን የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫነቷን የሚያስመሰክር ከተማ ለማድረግ ሥራዎች እየተሰሩ ነው። ለኑሮ ምቹ ጽዱና ጤናማ የሆነ አካባቢ እንዲፈጠር ጥረት እየተደረገ ነው። ይህንን እሳቤ ተግባራዊ ለማድረግ ከ130 ዓመት በላይ ያስቆጠረችውን አሮጌ ከተማ አፍርሶ መስራትን ይጠይቃል።

አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ ለማድረግ በርካታ ችግሮች አሉ። አንዱ እና ዋናው ችግር የሰዎችን አመለካከትና አስተሳሰብ ማረቅ እና የልማቱ አካል ማድረግ ነው። ሌላው ከተማዋን ውብ ለማድረግ የሚያስፈልገው የፋይናንስ አቅምን ማሳደግ ነው፤ ይሄ ደግሞ እስከ ዛሬ በነበረው የታክስ አሰባሰብ ሂደት ብቻ ገቢን ሰብስቦ በታሰበው ልክ ሀገርን ማልማትና ሌሎች ሥራዎችን መስራት አይቻልም። ገቢን የመሰብሰብና ገቢን የማሳደግ ሥራ መቼም በምንም ምክንያት እንደነበረው ችላ ተብሎ አይታለፍም።

ምክንያቱም ገቢ ዛሬ ለኢትዮጵያ የሕልውና ጉዳይ ነው። ስለዚህ አሁን በመርካቶ አካባቢ የተጀመረው ሕግና ስርዓት የማስያዝ ሕጋዊ አሰራርን የማስፈን ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት በመሰራት ላይ ነው፤ ሕጋዊ ስርዓትም መያዝ አለበት።

በአሁኑ ወቅትም በመርካቶ አካባቢ የሚታዩ ጉምጉምታዎች አሉ። የንግድ ቤቶችን መዝጋት፣ ሸቀጦችን መደበቅ፣ ለተፈጸመ ግብይት በአነስተኛ ዋጋ ደረሰኝ መቁረጥ፣ የግብይት እንቅስቃሴዎችን ከስራ ሰዓት ውጪ በጨለማና ሳይነጋ በሌሊት ማከናወን በአጠቃላይ የግብይት ሂደቱን ማስተጓጎልና የወሬ ውዥንብር መርጨት ጎልቶ ይታያል፤ ይሰማልም። ይሄ አካሄድ የትም አያደርስም የሚያመጣው ውጤትም አይኖርም። በሕገወጥ መንገድ እስካሁን ድረስ መሄድ ተችሎ ይሆናል። አሁንም በዚሁ መንገድ እቀጥላለሁ ብሎ ማሰብ አይቻልም። ስለዚህ ራስን ከሕጋዊ አሰራር ጋር ማላመድ ይገባል። ይሄንን መለማመድ ያስፈልጋል።

በአስፈጻሚ አካላት በኩልም ቀድመው መሰራት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ። በቅድሚያ የስነልቡና ዝግጅት እንዲያደርጉ ከተለመደው ሕገወጥነት ወደ ሕጋዊነት መሄድ እንደሚያስፈልግ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ የሚያጠፉትን ማስተማር ይገባል። የነበረውን ሕገወጥ አካሄድ ወደ ሕጋዊነት እንዴት ማምጣትና ቀጣዩን ትክክለኛውን መንገድ መከተል እንደሚችሉ ማሳወቅ ያስፈልጋል።

እስካዛሬ ከለመዱት አቋራጭ መንገድ ወደ ትክክለኛው መንገድ መጓዝ ሊጎረብጥ ስለሚችል ትምህርት፣ ክትትልና ድጋፍ ከዛ አለፍ ሲልም ሕግና ሥርዓት ማስከበርን ማለማመድ ይገባል። ልማቱ የሁሉም መሆኑን ማስረዳት ያስፈልጋል። ዛሬ መስዋዕትነት የምንከፍልለት የከተማ ልማት ለነገ ለልጆቻችን የምናስቀምጠው ታሪከ ጭምር መሆኑን ማሰብ ያስፈልጋል።

ለዚህም የልማቱ አጋር ለመሆን ዝግጁ መሆን ይገባል። ሁሉም ሰው ባለው አቅሙ በገንዘቡ፣ በእውቀቱና በሙያው የሚያደርገውን ድጋፍ ማስቀጠል አለበት። ሌላው ቢቀር እንቅፋት ባለመሆን መተባበርን ዛሬ የተጀመረው የልማት ኮሪደር ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ የፋይናንስ ምንጭ የሆነው የንግዱ ማሕበረሰብ የሚጠበቅበትን ግብር፣ ታክስ እና ቫት በወቅቱ በሀቀኝነት በመክፈል አርአያ ሊሆን ይገባል።

አዲስ አበባ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ የአፍሪካውያን ከተማ ናት፤ አሁንም ትላልቅ የሚባሉ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን እያካሄደች ትገኛለች። የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫነቷን በቀጣይም እያረጋገጠች መሄድ አለባት። ካላት ተፈጥሯዊ ሁኔታ ከታሪካዊነቷ ከአፍሪካ ሀገሮች የቱሪስት መዳረሻ ተመራጭ ከተማ መሆንም ይገባታል።

ይሄ ሁሉ የሚሆነው የታሰበውን ልማት ማምጣት ሲቻል ነው። በቂ የማረፊያ ቦታ፣ በቂ የመንቀሳቀሻ መንገዶች፣ በቂ የመዝናኛ የአይን ማረፊያ አካባቢዎች ሲፈጠሩ ነው። ለቱሪስት መስህብ የሆኑ ቅርሶችን ታሪካዊ ቦታዎች የመሳሰሉትን አቧራ አራግፎ አደባባይ ማውጣት ሲቻል ነው። ቱሪስቱ በከተማዋ ረዘም ያለ ቆይታ ካደረገ፣ አዲስ አበባን መተላለፊያው ካደረገ ለጎብኚው ሊሟሉለት የሚገቡ ነገሮች መኖር አለባቸው።

ዛሬ ያለንን አውጥተን ለምተን ነገ ደግሞ ከቱሪስቱ በምንሰበስበው ትልቅ ገቢ ተጠቃሚ መሆን ይኖርብናል። ይህም ቀሪውን ሀገር ለማልማትና ለማሳደግ ሥራ ይውላል። ሌሎች ከዘመኑ ጋር የሚያራምዱ ዕቅዶችንም ማሳካት ያስችላል። ዛሬ እንደ ኮሶ መድሀኒት የመረረን ነገ ጣፋጭ ፍሬውን ለማየት ያስችለናል። የሚጠበቅብንን ግብር፣ ታክስ፣ የገቢ ተመላሽ፣ ቫት… የመሳሰሉትን በአግባቡና በሰዓቱ በመክፈል የዜግነት ግዴታችንን እንወጣ። የንግዱ ማሕበረሰብ በዚህ በኩል ከጉትጉታና ከቅሬታ ወጥቶ አጋርነቱን ማረጋገጥ አለበት።

ሁሉም ሰው መብቱ እንዲከበርለት እንደሚፈልገው ሁሉ ግዴታውን በሕጋዊ መንገድ መወጣት አለበት። አንዱ ግዴታ ግብርንና ታክሰን መክፈል ነው። ይሄ ሲሆን ነው የሚፈለገውን ልማትና እድገት ማምጣት የሚቻለው። በከተማዋ እንደ ልብ ወጥቶ መግባት ሰርቶ መክበር፣ ወልዶ መዳር የሚቻለው የከተማው ጸጥታና ሰላም የተረጋጋ፣ የመልካም አስተዳደር ችግር የማይታይበት ሲሆን ነው።

ይሄ ደግሞ የራሱ በጀት ያስፈልገዋል። የከተማ አስተዳደሩ ገቢዎችን በሚፈልገው ልክ መሰብሰብ ካልቻለ የሚታሰበውን ልማት ማረጋገጥ አይቻልም። ፍትሀዊነትን ማረጋገጥ አይቻልም። እኩል ውድድርን ማስፈን አይታሰብም። ሕገወጥነትን መቆጣጠር አዳጋች ይሆናል።

የሀገሪቱ ዋነኛ የንግድ ማዕከል በሆነው መርካቶ በርካታ ሕገወጥ ተግባራት ይስተዋላሉ፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት እስከ 80 በመቶ የሚደርሱት በመርካቶ የሚካሄዱ ግብይቶች በሕገወጥ መንገድ የሚፈጸሙ ናቸው፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ጥቂት የሚባሉ ነጋዴዎች ሕጋዊውን የግብይት ሥርዓት የሚፈጽሙ ቢሆኑም አብዛኞቹ ነጋዴዎች የግብይት ሥርዓታቸውን የሚያካሂዱት በሕገወጥ መንገድ በመሆኑ መንግሥት መሰብሰብ የሚገባውን ከፍተኛ ግብር በማሳጣት ላይ ይገኛሉ፡፡

ግብር መክፈል ለሀገር ዕድገትና ለዜጎች ሁለንተናዊ መብቶች መረጋገጥ ካለው ፋይዳ አንጻር አስፈላጊ ከመሆኑም ባሻገር፤ በአንዲት ሉዓላዊ ሀገር ውስጥ ግብር መክፈል ግዴታም ጭምር ነው፡፡ ይህንን ተግባራዊ አለማድረግ ደግሞ የወንጀልና አስተዳደራዊ ቅጣቶችንም ያስከትላል፡፡

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ስለ ግብር አስፈላጊነትና ግዴታ ከተደነገገው በተጨማሪ በፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀጽ 116 እና በተመሳሳይ ድንጋጌዎች ግብርን አለመክፈል፣ ማጭበርበር፣ ግብር መሰወር፣ ተጨማሪ እሴት ታክስ ማጭበርበር እና በጠቅላላው ከታክስ ጋር ተያይዘው የሚፈጸሙ ወንጀሎች በእስር እና እንደየወንጀሉ ክብደት በብርም የሚያስቀጡ ናቸው፡፡

ማጭበርበር ለነጋዴውም የማይጠቅም፣ ሀገርን የሚጎዳ እና ትውልድ የሚገድል በመሆኑ መንግሥት ሕግን ለማስከበር እያደረገ ያለውን ርምጃ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዜጋም በመርካቶ ሕጋዊ የገበያ ሥርዓት እንዲሰፍን የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅበታል፡፡

ሀገር የሚጸናው በዜጎች ባለቤትነትና ተሳትፎ ነውና ስለሀገራቸው የሚቆረቆሩ ዜጎች ሕገወጥ ተግባራትን በማውገዝና በሕግ ማስከበሩ ተግባር አጋር በመሆን የዜግነት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል። ሥርዓት አልበኛውን ሥርዓት ማስያዝ የመንግስት ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ዜጋም ኃላፊነትና ግዴታ ጭምር ነው።

አዶኒስ (ከሲኤምሲ)

አዲስ ዘመን ኅዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You