እንደ ሀገር እጅግ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ የሚፈስበት እግር ኳሳችን ከሚንቀሳቀሰው ገንዘብ በዘለለ ሌላ ትኩረትን የሚስብ አዎንታዊ ርዕሰ ዜና መፍጠር ከተሳነው ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይባስ ብሎም የእግር ኳሳችን ዓይነተኛ ነፀብራቅ የሆነው ብሔራዊ ቡድናችን በፉክክር ጨዋታዎች ለመጨረሻ ጊዜ ሰኔ 2/2014 ግብጽን ሁለት ለባዶ ከረታ በኋላ ዳግም ወደ ድል ለመመለስ 893 ቀናት ፈጅተውበታል።
ብሔራዊ ቡድናችን(ዋልያዎቹ) በቅርቡ በ2025 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የመጨረሻ ጨዋታ ዲሞክራቲክ ኮንጎን 2ለ1 እስከረታበት ፍልሚያ ድረስ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ 17 የነጥብ ጨዋታዎችን ቢያደርግም ማሸነፍ የቻለው ይህን የመጨረሻ ፍልሚያውን ብቻ ነው። በእነዚህ አስራ ሰባት ጨዋታዎች ቡድኑ ሰባት ግቦችን ሲያስቆጥር በተቃራኒ ሃያ ስድስት ግቦች ተቆጥረውበታል።
የሀገር ውስጥ እግር ኳስ ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሰራው ድረ-ገፅ ሶከር ኢትዮጵያ በቅርቡ ባደረገው እና በርካታ የእግር ኳስ ቤተሰቡ በተሳተፈበት የሕዝብ መጠይቅ ከወቅታዊ የብሔራዊ ቡድኑ የውጤት አልባ ጉዞ በስተጀርባ አለ ስለሚሉት ምክንያት ባቀረበው የሕዝብ መጠይቅ 68% የሚሆኑት ምላሽ ሰጪዎች አሁናዊው የብሔራዊ ቡድኑ ውጤት ማጣት የአጠቃላይ የሀገራችን እግር ኳስ ነፀብራቅ ስለመሆኑ ሃሳባቸውን ሲሰጡ፣ ከምላሽ ሰጪዎቹ 28% የሚሆኑት ደግሞ ለቡድኑ ውጤት ማጣት ምክንያት ነው ብለው ያነሱት ጉዳይ የተጫዋቾች ብቃት ማነስን ሲሆን 18% ደግሞ በሜዳችን ያለመጫወታችን ለውጤት ማጣቱ እንደ ምክንያትነት ይቀርባል በማለት ምላሽ ሰጥተዋል። የተቀሩት 6% የሚሆኑ ድምፅ ሰጪዎች ደግሞ ከውጤት መጥፋቱ በስተጀርባ ሌላ ምክንያት ስለመኖሩ ጠቁመዋል።
ርግጥ እግር ኳሳችን ፈርጀ ብዙ በሆነ የሜዳ እና የሜዳ ውጭ ጉዳዮች የታሰረ መሆኑ የአደባባይ ሀቅ ነው። የተሰበሰበው የሕዝብ መጠይቅም እነዚህ ስር የሰደዱ የእግር ኳሳችን ችግሮች ተፅዕኗቸው በሁለንተናዊ የእግር ኳሳችን መልክ ላይ ስለማረፉ ዓይነተኛ ማስረጃ ነው።
የአሉታዊ ተፅዕኖ ደረጃቸው የሚለያይ ቢሆንም ከላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች የብሔራዊ ቡድኑ ተግዳሮቶች መሆናቸው ነጋሪ አያስፈልገውም። ሆኖም አጠቃላይ የሀገራችን እግር ኳስ ሁኔታ ለውጤት መጥፋቱ ዋነኛ ምክንያት መሆኑ እሙን ነው። ችግሩ ከክለቦች ውጤት ተኮር፣ ራዕይ አልባ ጉዞ እና ደካማ አደረጃጀት እንዲሁም በአጠቃላይ በሀገሪቱ በተለያዩ ደረጃዎች የሚታየው የእግር ኳስ አስተዳደር መዋቅራዊ የተቋማት ችግር የመነጨ ነው። አንድ ሀገርን የሚወክል ብሔራዊ ቡድን የክለቦች ነፀብራቅ ነው። በክለቦች አደረጃጀት ላይ ስር ነቀል ለውጥ ማድረግም እግር ኳሱን የሚያድነው ቀዳሚ ተግባር ነው። ሆኖም የክለቦቹን አሁናዊ ሁኔታ ሂደቱ የተወሳሰበ ያደርገዋል፤ የክለቦቹ አካሄድ ከታመመ ሰንበትበት ቢልም በተለይም ቅጥ ያጣው የገንዘብ አወጣጥ መንገዳቸው ከመንገዳገድ አልፎ ጠልፎ እንዳይጥላቸው ያሰጋል። ለዚህም የከሸፈውን የቻይና የእግር ኳስ አብዮት መለስ ብሎ መመልከት ተገቢና ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡
ባለፉት ቅርብ ዓመታት በቻይና የተነሳው የእግር ኳስ አብዮት የዓለምን ትኩረት ስቦ ነበር። የሩቅ ምስራቋ ሀገር ቻይና ሱፐር ሊጓን የዓለም ከዋክብት ተጫዋቾች መገኛና የድንቅ የእግር ኳስ መናኸሪያ የመሆን ውጥን ይዛ ነበር የተነሳችው። ሀገሪቷ ይህን ውጥኗን እውን ለማድረግ ከስምንት መቶ ቢሊየን ዶላር በላይ ለስፖርቱ ኢንዱስትሪ አፍስሳለች፡፡
እግር ኳስን በእጅጉ እንደሚወዱ የሚነገርላቸው በሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ዢ ጂፒንግ ድጋፍ ፤ ቻይና የዓለማችን ታላላቅ ከዋክብትን በገንዘብ በማማለል ሊጓን የማጠናከር ሥራን “ሀ “ ብላ ጀመረች። የዓለማችን ስመጥር ከዋክብት በቻይና ክለቦች ከፍተኛ የገንዘብ ክፍያ ወደ ሱፐር ሊጓ መትመም ጀመሩ። ከነዚህም መካከል ብራዚላዊው ኦስካር ፣ አርጀንቲናዊው ካርሎስ ቴቬዝ እና ቤልጂዬማዊው አክስል ቪትዝል ይገኙበታል። የነዚህ ተጫዋቾች ሊጉን መቀላቀል ለሌሎች ታላላቅ ተጫዋቾች መምጣት ምክንያት ሲሆኑ ጊዜ አልወሰደም። በ2016 በቻይና የፈነዳው ይህ የእግር ኳስ አብዮት በአውሮፓ እግር ኳስ ላይም ትልቅ ስጋት እስከመደቀን ደርሶም ነበር።
የሱፐር ሊጉ እንቅስቃሴ ጠንካራ ወደሚባል ደረጃ መድረስ ቢችልም ፤ የእግር ኳስ አብዮቱ የታሰበውን ግብ መምታት እንደማይችል ምልክቶች መታየት ጀመሩ። አንዳንድ ክለቦች በዕዳ ውስጥ የመዘፈቃቸው ዜና ይሰማ ጀመር። እአአ በ2017 የቻይና ስፖርት ሚኒስቴር የሊጉን ወጪን በተመለከተ ጥያቄ ማንሳት ጀመረ። ወጪዎችን ለመግታት እና “ምክንያታዊ ያልሆነ ኢንቨስትመንት” ለመቆጣጠር እንቅስቃሴ ጀመረ። ክለቦች “ገንዘብ ያባክናሉ” እና ለውጭ ተጫዋቾች “ከልክ በላይ ደመወዝ” ይከፍላሉ ሲል ወደ መክሰስ ተሻገረ። በዚህ ፈታኝ መንገድ ውስጥም ቢሆን በ2019 ሱፐር ሊጉ በጣም ትልቅ ደረጃ ላይ ደረሰ።
ያም ሆኖ በብዙ የተጠበቀው የቻይና እግር ኳስ አብዮት አስር ዓመት ሳይሞላው ጉዞው በተቃራኒው አቅጣጫ ሆኖ ተስፋው መፈረካከስ ጀመረ። የቻይና ክለቦች ተጫዋቾችን ወደ ቻይና ሱፐር ሊግ ለመሳብ በሚል ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ቢከፍሉም ፤ ትርፋማ መሆን አልቻሉም። ቻይና የጀመረችው መንገድ የተሳሳተ መሆኑን የተረዳችው ግን ዘግይታ ነበር።
የእኛም ሀገር ክለቦች እጣ ፋንታ ከዚህ የተለየ እንደማይሆን ምልክቶች መታየት የጀመሩት ዛሬ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ፈር የሳተውን አካሄድ ለማስተካከል አሁንም እድሉ ዝግ አይደለም፡፡
የኢትዮጵያ ክለቦች ለተጫዋቾች የሚከፍሉት ደመወዝ በአፍሪካ ትልቅ ከሚባሉት ቀዳሚ ደረጃዎች ውስጥ ቢመደብም የተጫዋቾች ብቃት እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ በየእለቱ የምናየው ነው፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ ላይ የሚታየውም ችግር የዚሁ ነፀብራቅ ነው፡፡ በሶከር ኢትዮጵያ መጠይቅ ላይ ምላሽ ከሰጡ 28% የሚሆኑት ለብሔራዊ ቡድኑ ውጤት ማጣት ምክንያት ነው ብለው ያነሱት የተጫዋቾች ብቃት ማነስ ሌላው የብሔራዊ ቡድኑ ተግዳሮት የሆነውም ለዚህ ነው።
እዚህ ላይ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ በብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት መንበር በቆዩባቸው ጊዜያት በጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ ካነሷቸው አንኳር ሃሳቦች መካከል በየሳምንቱ የተለያየ የብቃት ደረጃ ላይ ስለሚገኙት ተጫዋቾቻችን የገለፁት እንደ ማሳያነት ማንሳት ይቻላል።
አሰልጣኙ ደጋግመው እንደተናገሩት ተጫዋቾቻችን “በትንሽ ጭብጨባ” ከመንገድ ይስታሉ። የተጫዋቾቻችን የብቃት እንዲሁም የወጥነት ችግር ለማጠናከር የሶከር ኢትዮጵያን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የጨዋታ ሳምንቱን ምርጥ ቡድን መመልከት ዓይነተኛ ምስልን ይፈጥራል። በቀናት ልዩነት በሚደረገው በዚህ ምርጫ በተከታታይ ሳምንታት በወጥነት የሚመረጡ ተጫዋቾችን ማግኘት እምብዛም የተለመደ አይደለም።
ታዲያ ይህ ጉዳይ የእግር ኳሳችን ሀቅ በሆነበት የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች በእዚህ የተጫዋቾች ብቃት የወጥነት ችግር እና መውጣት መውረድ ውስጥ ሆነው ተጫዋቾችን እንዴት ባለ ሁኔታ ይመርጣሉ የሚለው ጉዳይ ሌላው መፍትሔ የሚሻ ጉዳይ ነው።
ሌላኛው ምክንያት በሜዳችን ያለመጫወታችን ጉዳይ ነው፡፡ እግር ኳሳችን ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ የሚንቀሳቀስበት ቢሆንም ይህ የገንዘብ ፍሰት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ዛሬ ላይ ያተኮሩ ወይም ተቋም የማይገነቡ እና በእቅድ የማይመሩ ወጪዎች መሆናቸው የእግር ኳሳችን መሠረተ ልማት ቀድሞ ከነበረበት ደረጃ ፈቀቅ እንዳይል ምክንያት ሲሆን እየተመለከትን እንገኛለን። እግር ኳሳችን በቢሊዮኖች የሚገመት በጀት የሚንቀሳቀስበት ቢሆንም በዘርፉ ያለው ስር የሰደደ ሙስና እና የገንዘብ አጠቃቀም ችግር በመሠረተ ልማት ላይ በቂ የሆነ ኢንቨስትመንት እንዳይደረግ ምክንያት ሆኗል። በዋነኝነት በልማት እና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ግንባታ ላይ መዋል የነበረበት ገንዘብ በጊዜያዊ እና ራዕይ የሌለው የበጀት አጠቃቀም ድክመት ምክንያት ብሔራዊ ቡድኑ ለስደት ከመዳረጉ ባለፈ የፌዴሬሽኑን ካዝና አራቁቶታል። ለዚህም የፌዴሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሰሞኑን በአንድ የቴሌቪዥን የምርመራ ዘገባ ላይ የተናገሩትን ማስታወስ በቂ ማሳያ ነው። ብሔራዊ ቡድኑ በሜዳው ማድረግ የነበረበት ጨዋታዎች በሌሎች ሀገራት ባደረገባቸው ባለፉት አራት ዓመታት ፌዴሬሽኑ ማውጣት ያልነበረበትን ከ85 ሚሊየን ብር በላይ ለማውጣት እንደተገደደ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራም በቅርቡ በአንድ የሬዲዮ መሰናዶ ላይ ለአብነት ሲገልፁ እንደተደመጡት፣ ብሔራዊ ቡድን በቅርቡ ታንዛኒያ ዳሬ ሰላም ላይ ላደረገው ጨዋታ ለሜዳ ኪራይ 20,000 ዶላር እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ ላይ ላደረጉት ጨዋታም እንዲሁ 90,000 ራንድ ወጪ ማድረጋቸውን አንስተዋል።
ታዲያ አሁንም በስደተኝነቱ የቀጠለው ብሔራዊ ቡድናችን በሜዳው እና በደጋፊው ፊት ሲጫወት ያገኝ የነበረውን ተጠቃሚነት የማጣቱ ጉዳይ ምናልባት በቁጥራዊ መለኪያዎች መለካት ባይቻልም ተፅዕኖ ከፍተኛ እንደሆነ የብሔራዊ ቡድናችንን የቅርብ ዓመታት ውጤቶች መመልከት በቂ ነው።
በሌላ በኩል ለውጤት መጥፋቱ አሰልጣኞችን ተጠያቂ ማድረጉም ተገቢ ነው፡፡ በአንድ ሀገር የእግር ኳስ እድገት የአሰልጣኞች ሚና ትልቅ ነው። አንጋፋው ኔዘርላንዳዊው አሰልጣኝ ሪኑስ ሚሽየልስ በ1970ዎቹ የኔዘርላንድን እግር ኳስ ገፅታ የቀየሩበት አብዮታዊ ለውጥ እንዲሁም ስኬታማው አሰልጣኝ አሪጎ ሳኪ የጣሊያንን እግር ኳስ ባሕል፣ የጨዋታ መንገድ እና የሥልጠና ዘዴዎች የለወጡበት መንገድ በጥልቀት ላስተዋለ የአሰልጣኞች ሚና ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ ለመረዳት አያዳግተውም። ይህንን በመንተራስ በጥቅሉ ስናየው በሀገራችን እግር ኳስ ውድቀት የአሰልጣኞች ድርሻም ቀላል እንዳልሆነ መገንዘብ ይቻላል። አሰልጣኞች የደካማው የክለባችን አደረጃጀት ሰለባ መሆናቸው የማይታበል ሀቅ ቢሆንም ዘመኑን የዋጀ የሥልጠና እና የአጨዋወት መንገድ በማበጀት ረገድ ያላቸው ውስንነት በእግር ኳሱ እድገት አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል።
ይህ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ችግር በብሔራዊ ቡድኑ ውድቀትም የራሱ ድርሻ አለው። ከዚህ በተጨማሪ ብሔራዊ ቡድኑ በቅርብ ዓመታት በአንፃራዊነት የተሻለ ለኳስ ቁጥጥር ቅድሚያ ከሚሰጡ አሰልጣኞች ወደ ቀጥተኛ አጨዋወት የቀረበ የጨዋታ ዕቅድ ያላቸው አሰልጣኞች መሸጋገሩም ወጥነት ያለው እና የተቀናጀ አጨዋወት እንዳይኖረው እንዲሁም የውህደት ደረጃው እንዲዋዥቅ አድርጎታል።
እግር ኳሳችን በፈርጀ ብዙ ችግሮች የተተበተበ እንደመሆኑ ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት ሰፊ ጥናት እና ምርምር የሚጠይቅ የዓመታት ሥራ ቢሆንም የአብዛኛዎቹ ችግሮቹን መነሻ የሆነው እና የእግር ኳሱ ባለቤት የሆኑትን ክለቦች አደረጃጀት ላይ ስር ነቀል ለውጥ ማድረግ ግን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ወሳኝ ተግባር ነው። ክለቦቹ በጥቂት ግለሰብ ላይ ጥገኛ የሆነ እና ተቋማዊ ባልሆነ አደረጃጀት መመራታቸውም በሜዳም ይሁን ከሜዳ ውጭ ያለውን የእግር ኳሱ ሁኔታ ክፉኛ ደቁሶታል። የአንድ ሀገር ብሔራዊ ቡድን ውጤታማነት ከክለቦች እድገት ጋር ቀጥተኛ የሆነ ትስስር አለው። የክለቦቹ ኋላ ቀር አደረጃጀት ላይ ለውጥ ማድረግም የወጣት ተጫዋቾች እድገት ማሳለጥ፣ የምልመላ ሥርዓት ለማስተካከል፣ ለአሰልጣኞች ምቹ የሥራ ከባቢ መፍጠር እንዲሁም በክለቦቹ አሰራር የተጠያቂነት እና ፍትሐዊ የሥራ ክፍፍል እንዲኖር ያስችላልና ትኩረት ይሰጠው።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሀገራችንን እግር ኳስ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ የዝግጅት ሥራዎች ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጠውን የ6 ዓመት ስትራቴጅክ እቅድ በድጋሚ ለመከለስ ስላስፈለገ በስፖርቱ እና በስትራቴጂክ እቅድ ዙሪያ እውቀት እና ልምድ ያላቸው እንዲሁም በበጎ ፈቃድ ለማገልገል ፈቃደኛ የሆኑ ሁሉ ማመልከቻቸውን እና የሥራ ልምዳቸውን በማስገባት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አድርጓል፡፡ ይህ ባለሙያዎችንና እውቀቱ ያላቸውን ሰዎች ወደ ስፖርቱ ለማቅረብ የሚደረግ ጥረት የእግር ኳሱን ስንክሳሮች መልክ ለማስያዝ አበረታች ጅምር ነውና ሊበረታታ ይገባል፡፡
ልዑል ከካምቦሎጆ
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም