በቡና ዘርፍ ከምርት እስከ ዓለም ገበያ ያሉትን ቁልፍ አካላት የያዘ ብሔራዊ የቡና ፕላት ፎርም ሰሞኑን ይፋ ሆኗል። ይህ ፕላት ፎርም በኢትዮጵያ የቡና ወጪ ንግድ ላይ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ተገልጿል። በዚህ ዓመት ከቡና ዘርፍ ብቻ ለማስገባት ከታቀደው ሁለት ቢሊዮን ዶላር እ.አ.አ በ2033 ወደ አራት ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ምቹ መደላድል እንደሚሆን የቡና እና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ በየዓመቱ ወደ ውጭ ትልክ የነበረውን ቡና አስመልክቶ የወጡ መረጃዎች እንደጠቆሙት፤ በ2010 በጀት ዓመት 238 ሺህ 465 ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 838 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል። በ2011 ዓ.ም በ2010 ዓ.ም ከተላከው ያነሰ 230 ሺህ 764 ቶን ቡና በመላክ 763 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ተገኝቷል። አንዴ እየቀነሰ ሌላ ጊዜ ደግሞ እየጨመረ የቀጠለው የቡና የወጪ ንግድ፤ የዘርፉን ችግር ከስሩ በመንቀል ዘላቂ ዕድገት ለማስመዝገብ ከማምረት እስከ ገበያ ድረስ የተሳሰረ የቅንጅት ሥራን የሚጠይቅ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ዘንድሮ ከቡና የወጪ ንግድ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ነው። በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት አራት ወራት 150 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጪ ተልኳል። ወደ 700 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል። ከስድስት ዓመት በፊት ይህ የዓመቱ ገቢ ነበር። ሆኖም ከዚህ በላይ ለማግኘት የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው ይላሉ።
እነ ብራዚል እና ኮሎምቢያን የመሳሰሉ ቡና ላኪ ሀገሮች ከሚያመርቱበት ሁኔታ የኢትዮጵያ አመራረት እጅግ የተለየ ነው። በኢትዮጵያ በአንድ ጊዜ በገፍ
የሚመረትበት ሁኔታ የለም። የኢትዮጵያ ቡና የሚመረተው በተበታተነ መልኩ ሲሆን፤ አንድ አርሶ አደር ከአንድ ሔክታር በታች ያለው በመሆኑ ወደ ውጪ የሚላከው በብዙ አርሶ አደሮች የተመረተ ቡና ተሰብስቦ ነው። ከዚህ አኳያም ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልከው የቡና ምርት ውስጥ 85 በመቶ የሚሆነው በተበታተነ መልኩ ተመርቶ የተሰባሰበ እንደሆነ ያብራራሉ።
እንደ አዱኛ (ዶ/ር) ገለፃ፤ በኢትዮጵያ እንደሌሎቹ ሀገሮች ከቡና ከፍተኛ ገቢ ማግኘት ብዙ ሥራን ይጠይቃል። የተበታተነውን የመሰብሰብ ችግር እንዳለ ሆኖ ጉዳቱን ለመቀነስ፤ ቡና ገዝተው የሚልኩ ቡና ላኪዎች ጥራት ያለው የቡና ምርት ለዓለም ገበያ በማቅረብ ተወዳዳሪ ሆነው ለመገኘት ከአርሶ አደሩ ጋር ይሠራሉ። ሆኖም አሁንም የኢትዮጵያ ቡና በጥራት ተወዳዳሪ እንዲሆን በርካታ ሥራዎች ሊሠሩ ይገባል።
አዱኛ (ዶ/ር) እንደሚያብራሩት፤ ቀደም ሲል ቡና የፖለቲካ ጉዳይ ነው በሚል በውጪ ፕሮጀክት አይደገፍም ነበር። አሁን ግን ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ ዘርፉን ነፃ በማድረግ ቡና ላይ ፕሮጀክቶች እንዲመጡ እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እንዲሳተፉ ሰፊ ዕድል ተፈጥሯል። ሆኖም በየዓመቱ ትልቅ ገቢ ለማግኘት አልተቻለም ነበር። የዚህ ምክንያት ፕሮጀክቶች ቢኖሩም እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል የሚንቀሳቀሰው በራሱ ነው።
ብሔራዊ የቡና ፕላት ፎርም መፈጠሩ ማንኛውንም ከቡና ጋር በተያያዘ የሚሠራ የፕሮጀክት ሥራ በተበታተነ መልኩ ከመሥራት ይልቅ፤ ሰብሰብ ተብሎ በጋራ ለመጓዝ ያግዛል። ማን ምን ይሠራል? ምን ያህል ገንዘብ አለው? የትኛው ወረዳ ላይ የትኛው ቦታ ላይ ይሠራል? የሚለውን በመለየት ድግግሞሽን ለመቀነስ ይረዳል ነው ያሉት።
ሰብሰብ ብሎ መሥራት ምርትና ምርታማነትን ከመጨመር፤ ጥራትን ከመጠበቅ፣ ገበያን ከማፈላለግ እንዲሁም ኢትዮጵያ 30 በመቶ የቡና ምርት ወደ አውሮፓ የምትልክበት ሁኔታ ላይ የተጋረጠውን አደጋ ማለትም አዲሱን የአውሮፓ ሕብረት የአካባቢ ጥበቃ ሕግ መስፈርትን ማሟላት እንዲቻል ከማገዝ አንፃር ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ነው የተናገሩት።
95 በመቶ የሚሆነው ቡና በማህበሩ በኩል ለውጭ ገበያ እንደሚላክ የሚናገሩት፤ ደግሞ የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ደሳለኝ ዜና ፤ ማህበሩ በ15 ዩኒየኖች አማካኝነት ከሶስት ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮችን ያቀፈ ሲሆን፤ በተለይ ከፍተኛ ቡና አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች በዋናነት በኦሮሚያ፣ በሲዳማ፣ በደቡብ ምዕራብ ክልሎች ያሉትን ሁሉ ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።
ምርቶቹ የሚመረቱት ራቅ ባሉ አካባቢዎች መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ መሆኑ ደግሞ ቡና ከሚመረትባቸው አካባቢዎች ወደ ማዕከል ለማምጣት በጣም አስቸጋሪ መሆኑን ተናግረዋል። ቡናን ሰብስቦ ወደ ማዕከልም ሆነ ወደ ጂቡቲ ለመላክ የተለያዩ ውጣ ውረዶች ያጋጥማሉ። በዋናነት የሎጅስቲክ ችግር እየፈተናቸው መሆኑን አስረድተዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም በኢትዮጵያ ባቡር ድርጅት በኩል ለመላክ፤ አዲስ አበባ ሆኖ በኮንቴነር ለማሸግ ኮንቴነር ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተፈለገው ጊዜ በባቡርም ሆነ በመርከብ በዓለም ገበያ ላይ ለማድረስ የቡና እና ሻይ ባለሥልጣን እና ሌሎቹም ጥረት በማድረጋቸው፤ ብዙ ችግሮችን ተቋቁመው ሥራዎች በመሠራታቸው አሁን የተገኘውን ውጤት ማግኘት ተችሏል ነው ያሉት።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልከው ውስጥ ከ30 በመቶ በላይ የሚሆነው ቡና የሚላከው ወደ አውሮፓ ነው። አሁን ደግሞ አውሮፓ ህብረት (ዩኒየን) ያወጣው የአካባቢ ጥበቃ ሕግ ለአርሶ አደሩም ሆነ ለቡና ላኪዎች ፈተና ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ይገልጻሉ።
ባለፈው ዓመት ከቡና ወጪ ንግድ አንድ ነጥብ 43 ቢሊዮን ዶላር የተገኘው በከፍተኛ ጥረት መሆኑን የሚናገሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማህበር ፕሬዚዳንት ሁሴን አምቦ (ዶ/ር)፤ ጥራት ያለው ቡና በማምረት፣ በማጓጓዝ እና የተገባውን ቃል በመፈፀም በአጠቃላይ መንግሥት እና የግል ዘርፉ ተዋናዮች ከፍተኛ ጥረት በማድረጋቸው ውጤት መገኘት መቻሉን ገልፀዋል።
የኤግዚቢሽን ደረጃዎችን በማሳደግ ጅማ፣ ሃዋሳ እና ድሬዳዋ ላይ የውጭ አገር ገዢ እና የሀገር ውስጥ አምራቾችን በማሳተፍ መሃል ላይ ያለውን ሰንሰለት በመቀነስ በተሠራው ሥራ መፍትሔዎች ተገኝተዋል ነው ያሉት።
እንደ ሁሴን (ዶ/ር) ገለፃ፤ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች በዓለም ባለልዩ ጣዓም ቡና ተወዳድረው አንድ ኪሎ ቡና 104 ሺህ ብር ተሸጧል። ጥራቱ እየጨመረ አርሶ አደሩ ለጥራቱ ተገቢውን ዋጋ እያገኘ ነው። ነገር ግን አምራቹ ገበሬ በቀጥታ ከውጭ ገዢው ጋር የማገናኘት ሥራ መሠራት እና ይህንን እንቅስቃሴም ማስቀጠል እንደሚገባ ይጠቁማሉ።
የኢትዮጵያ ቡናን ወደ ውጭ የመላክ ጉዞ በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ ያለፈ ቢሆንም፤ አሁን ላይ አርሶ አደሩ ለጥራት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠቱ፤ የዘርፉ ተዋናዮች ሥራ የተደራረበ እንዳይሆን እና ተናበውና ተቀናጅተው እንዲሠሩ ብሔራዊ ፕላትፎርም በመፈጠሩ፣ እንዲሁም ግልፅ ፍኖተ ካርታ በመዘጋጀቱ በቀጣይ በዓለም ተወዳዳሪ መሆን እንደሚቻል አመላክተዋል።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ኅዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም