“ብሄራዊ ጥቅምን በሚያስከብሩ ጉዳዮቻችን ላይ የጋራ አቋም መያዝ አለብን” – ኡስታዝ ጀማል በሽር

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያውያን በውስጥ ግጭቶች እና ልዩነቶችን ከሚፈጥሩ አጀንዳዎች ይልቅ ብሄራዊ ጥቅምን በሚያስከብሩ አጀንዳዎች ላይ የጋራ አቋም መያዝ አለብን ሲሉ ኡስታዝ ጀማል በሽር ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያ የዓባይ ጉዳይን በተመለከተ ያላትን አቋም ለአረብ ሀገራት በአረብኛ ቋንቋ በስፋት በማድረስ የሚታወቁት ኡስታዝ ጀማል በሽር እንደ ሕዝብ ብሄራዊ የሆኑ አጀንዳዎቻችን ላይ አንድ ሆነን መቆም አለብን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ኡስታዝ ጀማል ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ግብጻውያን በመሀከላቸው መከፋፈል ቢኖርም በሀገር ጉዳይ ላይ ያላቸው አንድነት ጠንካራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ግብጻውያን በየትኛውም የሥራ ዘርፍ ላይ የሚገኙ ፤ ረጅም ዓመት ተፈርዶባቸው በእስር የሚገኙ ዜጎቻቸው ጭምር በሀገራቸው ጉዳይ ያላቸው አቋም አንድ ከመሆኑም በላይ ጠንካራ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የዓባይ ውሃ ባለቤት ብትሆንም በዜጎች ዘንድ የሚሰጠው ትኩረት ሊሠራበት የሚገባው መሆኑንም አንስተዋል፡፡ እንደሀገር በትምህርት ሥርዓታችን ውስጥ ተተኪ ለሆኑ ትውልዶች ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሀብትና የዓባይን ውሃ የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተሠጥቶ በመሥራት ላይ ያለን ተሞክሮ ደካማ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ጉዳይ ሊሻሻል የሚገባ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከዚህ ቀደም የነበሩ መሪዎች ዘንድ በእቅድ ላይ የነበረ መሆኑን ያስታወሱት ኡስታዝ፤ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የመሠረት ድንጋይ ተጥሎ ሥራ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ አሁን ላይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር ጠንካራ ሥራዎች መሠራታቸውን አንስተዋል፡፡

ኡስታዝ ጀማል ሀገርን ወክለው በዓባይ ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያ ያላትን አቋም በማሳወቅ በበርካታ የመገናኛ ብዙሃን ላይ በመቅረብ እና የራሳቸውንም ሚዲያ በማቋቋም በአረብኛ ቋንቋ በአረብ ሀገራት መገናኛ ብዙሃን ላይ በመሞገት ይታወቃሉ ፡፡

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ኅዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You