አዲስ አበባ፡- የሁለተኛውን ዙር የኮሪደር ልማት ሥራ በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባቸው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች የሁለተኛውን ዙር የኮሪደር ልማት ሥራ አፈጻጸም አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት፣ ከሥራ ተቋራጮች እና አማካሪ ድርጅቶች ጋር ትናንት ተወያይተዋል።
ይህን አስመልክተው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት እንደገለጹት፤ በመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት ሥራ በጥራትና በፍጥነት ስኬታማ ሆኖ ተጠናቋል። ከእዚህ የተገኙ ልምዶችን በመቀመር የተጀመረውን ሁለተኛ ዙር የኮሪደር ልማት ሥራ በተያዘለት ጊዜና ጥራት በማጠናቀቅ ለነዋሪዎች አገልግሎት ክፍት ማድረግ ይገባል።
የሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ሥራ ከመጀመሪያው ዙር አንጻር ሰፊና የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸው፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ዘላቂ ልማትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በትብብር፣ በተያዘለት ጊዜ፣ በጥራት ደረጃውን (ስታንዳርዱን) ጠብቀው እንዲያጠናቅቁ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን አመልክተዋል።
በትራፊክ መጨናነቅና አንዳንድ ምቾት በማይሰጡ ጊዜያዊ ሁኔታዎች ለተንገላታችሁ የከተማችን ነዋሪዎች ይቅርታ እጠይቃለሁ ያሉት ከንቲባዋ፣ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በውጤቱ እንደምንክሳችሁ ቃል ለመግባት እወዳለሁ ብለዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ረቡዕ ኅዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም