ኮርፖሬሽኑ ከ120 ሺህ በላይ ቤቶችን ለመገንባት ማቀዱን አስታወቀ

– ለ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች 336 ሊፍቶች ተገዝተዋል

አዲስ አበባ፡- በመንግሥት እና የግል አጋርነት ከ120 ሺ በላይ ቤቶችን ለመገንባት ማቀዱን የአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን አስታወቀ። ለ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች 336 ሊፍቶች ተገዝተው ሀገር ውስጥ መግባታቸውም ተጠቁሟል።

የኮርፖሬሽኑ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ፍቃዱ አለሙ ፤ ከአዲስ ዘመን ተጠየቅ አምድ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት ፤ ኮርፖሬሽኑ በመንግሥት እና የግል አጋርነት ከ120 ሺህ በላይ ቤቶችን ለመገንባት አቅዷል። ከዚህ ውስጥ 60ሺ ቤቶች የሚገነቡት በኦቪድ ሪል እስቴት ነው።

ለውጡ ሲጀመር ኮርፖሬሽኑ 54 ቢሊዮን ብር እዳ እንደነበረበት ፤ የተለያዩ አሠራሮችን በመተግበር እዳውን ወደ 32 ቢሊዮን ብር መቀነስ እንደቻለ የጠቀሱት ኢንጂነር ፍቃዱ፤ አሁን ላይ ለእዳው በቀን ስምንት ሚሊዮን ብር ወለድ እየተከፈለ እንደሆነ አስታውቀዋል። እዳውን ባለመክፈሉም ለግንባታ የሚሆን አዲስ በጀት ማግኘት እንዳልተቻለ አመልክተዋል።

ኮርፖሬሽኑ አዳዲስ ግንባታዎችን ለመጀመር በመቸገሩ በከተማ አስተዳደሩ በተጠና ጥናት ሌሎች አማራጮችን መጠቀም ጀምሯል ያሉት ኢንጅነሩ ፤ ከዚህ ውስጥ የመንግሥት እና የግል አጋርነት ስትራቴጂ አንደኛው ነው። በዚህም ከ22 አልሚዎች ጋር የመንግሥት እና የግል አጋርነት ውል ተፈራርመናል። ሰባቱ አልሚዎችም ወደ ሥራ ገብተው ግንባታ ጀምረዋል ብለዋል።

ከአሳንሰር (ሊፍት) ጋር በተያያዘም ለሚነሱ ቅሬታዎች፤ አሁን ላይ በጣም ብዙ ህንፃዎች አሳንሰር /ሊፍት/ ያስፈልጋቸዋል። ከዶላር ጭማሪው ጋር ተያይዞ አንድ ሊፍት ከዚህ ቀደም ከነበረው ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ጭማሪ ማሳየቱን አመልክተዋል።

የሊፍት ገጠማ ሥራው ከፍተኛ ገንዘብን ይጠይቃል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ፤ ይህም ሆኖ የነዋሪዎችን ችግር ለመቅረፍ አሁን ላይ የተወሰኑ ሊፍቶችን ለመግዛት ጨረታ አውጥተን በሂደት ላይ እንገኛለን ብለዋል።

ከእነዚህ ውስጥ ለ40/60 ፕሮጀክቶች የሚሆኑ 336 ሊፍቶች ግዥ ተፈጽሞ ሀገር ውስጥ ገብተዋል።70 የሚሆኑ ሊፍቶች የመገጣጠም ሥራ ተጀምሯል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ፤ ከሊፍት ከአቅራቢው ጋር የተወሰነ ችግር አጋጥሞ እንደነበር እና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በጋራ በመሆን ችግሩን መፍታት እንደተቻለም ጠቁመዋል።

ለ20/80 ፕሮጀክቶች ሊፍት ለማቅረብ አራት ድርጅቶች ጨረታ ማሸነፋቸውን ፤ ከእነዚህ መካከል አሁን ላይ ሥራቸውን በአግባቡ እየሠሩ ያሉት ሁለቱ መሆናቸውን አመልክተዋል። ከሁለቱ አንደኛው የሊፍት ገጠማ ሥራውን ማገባደዱን አስታውቀዋል። በጨረታ ካሸነፋቸው ህንፃዎች ሁለት ብቻ እንደቀሩትም ገልጸዋል።

የሊፍት ገጠማ ሥራው እየተከናወነ ያለው ለአሁኖቹ ግንባታዎች ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊት ለተገነቡ ህንጻዎች ጭምር ነው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ፤ አሁን ላይ በነባር ፕሮጀክቶች ላይ የነበረው የሊፍት ገጠማ ችግር በአብዛኛው እየቀረፈ እንደሆነ ገልጸዋል።

ሁለተኛው የሊፍት አቅራቢ ድርጅት ማቅረብ ከነበረበት 230 በላይ ሊፍቶች ግማሽ ያህሉን አቅርቧል። ከ120 በላይ ለሚሆኑ ህንጻዎች የገጠማ ሥራዎችን ሠርቷል። ቀሪ ሥራዎችን በፍጥነት እንዲያጠናቅቅ እየተነጋገርን ነው ብለዋል።

ጨረታ ያሸነፉ ሌሎች ሁለት ድርጅቶች በሥራ ላይ እንደሌሉ አመልክተው ፤ ለበሻሌ ሳይት አሳንሰር ለማቅረብ የተዋዋለው ድርጅት በውሉ መሠረት ሥራዎችን እያከናወነ ባለመሆኑ ውሉ ተቋርጧል። ይህን ተከትሎም በሻሌ ሳይት አዲስ ጨረታ ለማውጣት በሂደት ላይ እንደሆነ አስታውቀዋል።

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ኅዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You