አዲስ አበባ፡– በትግራይ ክልል በበጋ መስኖ 70 ሺ ሄክታር መሬት ለማልማት እየተሠራ መሆኑን የክልሉ የግብርና ቢሮ የሆርቲካልቸር ጽህፈት ቤት አስታወቀ። በቂ የሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ማዳበሪያም እየቀረበ መሆኑን አመለከተ።
የጽህፈት ቤቱ ዳይሬክተር አቶ ሃይሌ ታደለ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት ፤ በ2017 ዓ.ም 70 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ለማልማት እቅድ ተይዟል፤ በዚህም ሁለት 228 ሺህ 905 ዜጎች ተጠቃሚ ይሆናሉ። እስካሁንም ከእቅዱ 27 ነጥብ አምስት በመቶ በዘር ለመሸፈን መቻሉን ያመለከቱት ኃላፊው ፤ በቀሪዎቹም ቦታዎች የመስኖ ልማትን ለማካሄድ የማሳ ዝግጅት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በክልሉ የመስኖ ልማት የክላስተር አመራረት በመጠቀም በተለይ በጎመን፤ በድንች፤ በበርበሬ፤ በቲማቲም እና በሽንኩርት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ያሉት አቶ ሃይሌ ፤ በዘንድሮ ዓመት አንድ ሺህ 400 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ ለማልማት እቅድ መያዙን ገልጸዋል። የበጋ ስዴ ልማቱም ባለፈው ዓመት በሶስት ወረዳዎች ተጀምሮ አበረታች ውጤት የተመዘገበበት እንደነበር አስታውሰዋል ።
የፌዴራል መንግሥት በሚያደርገው ድጋፍ ለበጋ መስኖ ልማት የሚሆን የማዳበሪያ እጥረት አልገጠመንም ያሉት አቶ ሃይሌ ፤ 150 ሺህ ኩንታል ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ለመጠቀም በእቅድ ተይዞ ነበር ፤ እስካሁን 68 ሺህ ኩንታል በየወረዳው እንዲሰራጭ ተደርጎ ጥቅም ላይ ውሏል ብለዋል። አርሶ አደሩ የሚያዘጋጀውን የተፈጥሮ ማዳበሪያም በስፋት እየተጠቀመ እንደሚገኝም አስታውቀዋል ።
14 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር እንደሚያስፈልግ ያመለከቱት ዳይሬክተሩ፤ እስካሁን አራት ሺህ ኩንታል ተጠቅመናል። በምርጥ ዘር ረገድ እጥረት አለብን ብለዋል።
የክልሉ መልክዓ-ምድር ተራራማ በመሆኑ እና ውሃ በዝቅተኛ ቦታ ላይ መገኘቱ የውሃ መሳቢያ ፓንፕ ለመስኖ ልማት ወሳኝ ግብዓት እንዲሆን አድርጎታል ያሉት ዳይሬክተሩ ፤ ባለፈው ዓመት 94 ዘንድሮ ደግሞ 72 የውሃ መሳቢያ ፓንፖችን ግብርና ሚኒስቴር ድጋፍ እንደተደረገላቸው አስታውቀዋል። ይህም አቅመ ደካማ ለሆኑ አርሶ አደሮችና ሥራ አጥ ለሆኑ ወጣቶች እንዲዳረስ ተደርጓል። አርሶ አደሮችም በራሳቸው ጊዜ እየተደራጁ የጥልቅ ውሃ ጉድጓድ እያስቆፈሩ እና ፓምፕ እየገዙ ወደ መስኖ ልማት መግባታቸውን ገልጸዋል።
ይህ ውጤት ሊገኝ የቻለው ከክልል እስከ ዞንና ወረዳ ድረስ በመምከር የንቅናቄ መድረክ ተፈጥሮ በመሠራቱ መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በውቅሮ ከተማ ለ505 ባለሙያዎች እና አመራሮች የአምስት ቀን የሙያ ሥልጠና መሰጠቱንም አመልክተዋል። በአጠቃላይ ለ228 ሺህ 905 የመስኖ ተጠቃሚዎች በየደረጃው ሥልጠና መሠጠቱን ገልጸዋል ።
አሁን ላይ የበጋ መስኖ ሥራው በጥሩ እንቅስቃሴ ላይ ነው የሚገኘው ያሉት ኃላፊው ፤ ያለውን አቅም ሙሉ ለሙሉ በመጠቀም ከፍተኛ ምርት ለማግኘት በከፍተኛ ትጋት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። በምርጥ ዘር ረገድ እጥረት እያጋጠማቸው ስለመሆኑም አመልክተዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ኅዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም