አውደ ርዕዩ የዜጎችን ሕይወት መለወጥ የሚችል የፈጠራ አቅም እንዳለ የሚያሳይ ነው

አዲስ አበባ፡- አውደ ርዕዩ በኢትዮጵያ የዜጎችን ሕይወት መለወጥ የሚችል ውስጣዊ የፈጠራ አቅም እንዳለ የሚያሳይ ነው ሲል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) የቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ በሳይንስ ሙዚየም ትናንት የመክፈቻ መርሃ ግብር ሲካሄድ እንዳሉት፤ አውደ ርዕዩ በኢትዮጵያ የዜጎችን ሕይወት መለወጥ የሚችል ውስጣዊ የፈጠራ አቅም እንዳለ የሚያሳይ ነው፡፡ አውደ ርዕዩ በሀገራችን አውዶች፣ ባህሎችና ማህበረሰቦች ላይ የተመሠረተ ፈጠራን የሚያሳይ ነው፤ ሀገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን የመለወጥ ኃይል አጉልቶ ያሳየም ነው ብለዋል፡፡

የፈጠራ ሥራዎች ከተለያዩ አካባቢዎች እውቀት፣ ወጎችና የሕይወት ተሞክሮዎች የሚመነጩ ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በመንግሥት በኩል በቤት ውስጥ ያደጉ የፈጠራ ሃሳቦች አብበው ኢኮኖሚያዊ እድገትን እንዲያመጡ የሚያበረታታ ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ተሠርተው በአውደ ርዕዩ ላይ የቀረቡ ቴክኖሎጂዎች ከውጭ የሚመጡ ሃሳቦችን ያላመዱ ብቻ ሳይሆኑ ከችግራችን የሚመነጩና ማህበረሰቡን ዘላቂነት ባለው መንገድ ለመጥቀም የተነደፉ ናቸው ሲሉ አብራርተዋል።

የፈጠራ ሥራዎቹ፤ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን፤ መፍትሄዎችንና ችግሮችን የመቋቋም ብልሃትና ቁርጠኝነት የሚያሳዩ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አውደ ርዕዩ በቤት ውስጥ ያደጉ የፈጠራ ሃሳቦች አብበው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እደገትን እንዲያመጡ የሚያበረታታ ነው ያሉት በለጠ (ዶ/ር)፤ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በቤት ውስጥ ያደጉ የፈጠራ ሃሳቦች አብበው ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲያመጡ የማበረታታት ሥራ ሠርቷል፤ እየሠራንም ነው ሲሉ ገልጸዋል።

አውደ ርዕዩ በሀገራችን ባህሎችና አውዶች የተመሠረቱ የፈጠራ ሥራዎች ተሠርተው የቀረቡበት ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ዓላማውም ሀገር በቀል ቴክኖሎጂዎች ጎልተው እንዲወጡ የሚያደርግ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በቤት ውስጥ ያደጉ ሃሳቦች የሚያብቡበትን ምቹ ሁኔታን በመፍጠር በኩል ዘርፈ ብዙ ሥራ ተሠርቷል፤ ከደቡብ የትብብር ድርጅት ያለውን አጋርነት በይበልጥ በማጠናከር የማህበረሰቡን ፍላጎት የሚያሟሉ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎችን የመደገፍና ወደ ተግባር እንዲገቡ ይሠራል ብለዋል፡፡

ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራ ለሁለተናዊ እደገት ለማስመዝገብ ያለው ሚና ትልቅ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ የፈጠራ ሃሳቦች አብበው እንዲያፈሩ እያደረግን ያለውን ሥራ አጠናክረን እናስቀጥላለን ሲሉ ጠቁመዋል።

የደቡብ ትብብር ድርጅት ዋና ጸሃፊ መንሱር ቢን ሙሳላም በበኩላቸው፤ ቴክኖሎጂ ለሀገራት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ቁልፍ መሣሪያ ነው። ሀገር በቀል ቴክኖሎጂን ማመንጨትና የማላመድ ሥራ መሥራት የሚገጥሙ ችግሮችን ለመፍታትም ሆነ ለማደግ ጠቃሚ ነው ብለዋል።

በቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለመሆን ፈጠራን መጠቀምና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ማምረት አስፈላጊ መሆኑን አመልክተው፤ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የፈጠራ ቴክኖሎጂ እንዲያስፋፋ ለቴክኖሎጂ ተቋማት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ ጠቁመዋል።

በአውደ ርዕዩ ከአስራ አራት ሀገራት የተውጣጡ የፈጠራ ባለቤቶች የተሳተፉበትና ስድስት ጭብጥ ጉዳዮችን ያካተቱ 41 ፈር ቀዳጅ የፈጠራ ጅምሮች የታዩበት ነው፤ ይህም ለወደፊት ሕይወት አዲስ ነገር መፍጠር እንደሚቻል ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ታደሠ ብናልፈው

አዲስ ዘመን ኅዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You