በመጪዎቹ አሥር ቀናት በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው የሆኑ አካባቢዎች ዝናብ ያገኛሉ

አዲስ አበባ፦ በሚቀጥሉት አሥር ቀናት በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ስለሚኖራቸው ለተዘሩ ሰብሎች አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ ለኢፕድ በላከው መግለጫ፤ በሚቀጥሉት አሥር ቀናት ዝናብ ሰጭ የአየር ሁኔታ ክስተቶች በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የደቡብ እና የደቡብ ምስራቅ፣ እንዲሁም በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተለይም በመጀመሪያዎቹ ቀናቶች ላይ የተሻለ ገጽታ ይኖራቸዋል ብሏል፡፡

በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የቦረናና ጉጂ ዞኖች፤ የሲዳማ ክልል ዞኖች፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች እና የሶማሌ ክልል ደቡባዊ ዞኖች ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ ነው ያለው፡፡

አልፎ አልፎ ባሉት ቀናት በተለይም በምዕራብ፤ በደቡብ ምዕራብ እና በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የሚጠበቀው እርጥበት ለተዘሩ ሰብሎች አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል ብሏል።

በተጨማሪም የእርጥበት ሁኔታው በአርብቶ አደርና በከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ለግጦሽ ሳርና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት በጎ ጎን ይኖረዋል ነው ያለው፡፡

አብዛኛውዎቹ የበጋ ወቅት እርጥበት ተጠቃሚ በሆኑት የታችኛው ገናሌ ዳዋ፣ ዋቤ ሸበሌ እንዲሁም ኦጋዴን መጠነኛ እርጥበት ያገኛሉ። በተጨማሪም አብዛኛው የባሮ አኮቦ፣ የመካከለኛው እና የታችኛው ኦሞ ጊቤ፣ ስምጥ ሸለቆ፣ ዓባይ፣ የታችኛው ተከዜ፣ ገናሌ ዳዋ፣ እና የላይኛው ዋቤ ሸበሌ ተፋሰሶች መካከለኛ መጠን ያለው እርጥበት ያገኛሉ፡፡

ይህ ሁኔታ የገፀምድር የውሃ ሀብትን በመጠኑ እንደሚያሻሽል ይጠበቃል። በተለይም አብዛኛዎቹ ግድቦች አሁናዊ የውሃ መጠናቸው ከመደበኛው የተቀራረበ እና በተወሰኑት ላይ ከፍ ያለ በመሆኑ በቀጣይ የሚጠበቀው እርጥበት ለሃይል ማመንጫም ሆነ ለበጋ መስኖ ውሃ አቅርቦት አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል።

በመሆኑም የሚመለከታችው አካላት በተለይም በእርጥበት አጠር አካባቢዎች የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች የውሃ ማሰባሰብ ሥራዎችን ማከናወን ያስፈልጋል ነው ያለው መረጃው።

በተጨማሪም በምዕራብ እና በደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ዝናቡ ቀጣይነት እንደሚኖረው ገልጿል። በሰሜን፣ በሰሜን ምዕራብ እና በመካከለኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው እርጥበት ይጠበቃልም ብሏል።

በመሆኑም አርሶ አደሮች ይህንኑ በመረዳት ሳይዘናጉ በማሳ ላይ የሚገኙና የደረሱ ሰብሎችን ባሉት ደረቅ ሰሞናት መሰብሰብ እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳስቧል።

በአብዛኛዎቹ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የሚኖረው ደረቅ የእርጥበት ሁኔታ የመኽር ሰብል ስብሰባና ድህረ ሰብል ስብሰባ ተግባራትን ለማከናወን አመቺ እንደሚሆን ገልጿል።

በአንጻሩ አብዛኛው አዋሽ፣ አፋር ደናክል የላይኛው እና የመካከለኛ ተከዜ ተፋሰሶች በደረቅ የእርጥበት ሁኔታ ስር ሆነው ይቆያሉ ሲል በመግለጫው ገልጿል፡፡

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ኅዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You