ዜና ትንታኔ
ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ አቅርባ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከምታገኝባቸው የግብርና ምርቶች አንዱ የሆነው የሰሊጥ ገቢ እያንሰራራ መሆኑን ተጠቁሟል። የኢትዮጵያ ሰሊጥ በዓለም ገበያ ተፈላጊ ቢሆንም፣ ባለፉት አምስት ዓመታት በተለያዩ ሀገራዊ ችግሮች ምክንያት በምርት መጠን ቀንሷል፤ ገበያውም የመቀዝቀዝ ሁኔታ ታይቶበታል።
በቅርቡ በተካሄደው የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ዓለም አቀፍ ጉባኤ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት የኢትዮጵያ ጥራጥሬና ቅባት እህል ላኪዎች ማህበር የቦርድ አባል ሙሉጌታ ኪ/ማርያም (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ከአምስት ዓመታት በፊት ከ300 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ሰሊጥ አምርታ ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት ትልክ ነበር። ባለፉት አምስት ዓመታት ግን ምርቱ እየቀነሰ በመምጣቱ የምትልከው ምርት ከ200 ሺ ሜትሪክ ቶን በታች ነው።
ይህ የምርት መቀነስ የተወሰነ መሻሻል አሳይቶ አምና ከነበረበት 125 ሺህ ሜትሪክ ቶን አሁን ወደ 163ሺህ ሜትሪክ ቶን ከፍ ብሏል። ለዓለም ገበያ አቅርባ በቶን የምታገኘው አንድ ሺህ 500 ዶላርም ወደ አንድ ሺህ 800 ዶላር አድጓል ይላሉ።
ለምርቱ መቀነስ በዋናነት የሚጠቀሰው ሰሊጥ በስፋት የሚመረትባቸው እንደ ሁመራ ባሉ አካባቢዎች የተካሄደው የሰሜኑ ጦርነትና ከእሱ ጋር የተያያዙ ግጭቶችና አለመረጋጋት መከሰቱ፤ የአየር ንብረት ለውጥና አርሶ አደሩ የበለጠ አዋጪነት ወደ አላቸው ሰብሎች ማምረት መግባቱ እንደሆነ ይገልጻሉ።
ሙሉጌታም (ዶ/ር) አርሶ አደሮች ሰሊጥ ከማምረት ወደ ሌሎች ሰብሎች ፊታቸውን ማዞራቸውን ይጠቅሳሉ። በአንዳንድ አካባቢዎች በተለይ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዞ ያልታረሰ መሬት መኖሩንም ያመለክታሉ።
ስልጡን ያልሆነው የሰሊጥ ንግድ ሥርዓት ሀገሪቱ ከቅባት እህሉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንዳሳጣትም ይናገራሉ። ‹‹ምርቱን ላኪዎች በተባለው ወቅት ያለመጫን፤ የሎጅስቲክስ ችግርና ኮንትራትን በአግባቡ አለመፈፀም የመሳሰሉት ጉድለቶች መኖራቸውም ሀገሪቱ ከምርቱ የተሻለ ተጠቃሚ እንዳትሆን አድርገዋታል›› ብለዋል።
በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የግብርና ኢኮኖሚክስ ምርምር ዳይሬክተር ታደለ ማሞ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ከአምስት ዓመታት በፊት በዓለም የሰሊጥ ገበያ ከምርጥ አስር ሀገራት አንዷ ነበረች። ከሁለት ዓመት በፊትም 11ኛ ደረጃ ላይ ነበረች፤ በተለይም ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዞ የምርት መቀነስ መከሰቱ ደረጃዋን ለማስጠበቅ አዳጋች ሆኖባታል። የሰሊጥ ምርታማነት ዝቅተኛ መሆኑም የጥራቱን ያህል በብዛት በማምረት ገበያውን መቆጣጠር አልተቻለም ይላሉ።
እንደ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ያሉ ሰሊጥ በስፋት የሚያመርቱ ሀገራት በሄክታር 48 ኩንታል እንደሚያመርቱ ታደለ (ዶ/ር) ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ እያመረተች ያለችው በአማካኝ ከስምነት ኩንታል እንደማይበልጥ ይናገራሉ።
በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት ዝርያዎችን ማሻሻልና ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ማድረግ ላይ ውስንነት እንደሚስተዋሉ ጠቅሰው፤ አሁንም የኢትዮጵያ ሰሊጥ በዓለም ገበያ ተፈላጊ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከኢትዮጵያ ሰሊጥ መዳረሻ ሀገራት መካከልም ቻይና፣ እስራኤል፣ ቬትናም፣ ቱርኪዬና ሳዑዲ አረቢያና ጃፓን ዋነኞቹ ናቸው። ይሁንና ከፍላጎቱ አንፃር በሚፈለገው ደረጃ ሰሊጥ እየተመረተ አይደለም ነው ያሉት።
ታደለ (ዶ/ር) አብነት አድርገው እንደሚጠቅሱት፤ ቻይና በየዓመቱ እስከ 382 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ ኢትዮጵያ ሰሊጥ የመግዛት ፍላጎት ቢኖራትም በአሁኑ ወቅት እየተሸጠ ያለው ከ70 ሚሊዮን ዶላር አይበልጥም። ይህም መላክ ከሚገባው አንድ አራተኛ ብቻ መሆኑን ያመላክታል።
ሙሉጌታ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የምትልከው ሰሊጥ እሴት ያልተጨመረበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ መሆኑም የምርቱ ባለቤት እሷ ሆና እያለች ሌሎች ሀገራት በምርቱ ላይ እሴት እየጨመሩ ለገበያ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል።
ይህም ሀገሪቱን የበይ ተመልካች አድርጓታል። በተለይ እንደ እስራኤል ያሉ ሀገራት ከኢትዮጵያ የገዙትን ሰሊጥ እሴት ጨምረው ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት በመላክ ከፍተኛ ዶላር ያገኛሉ ሲሉ ይገልጻሉ።
አሁንም የኢትዮጵያ ሰሊጥ በዓለም ገበያ ላይ የጥራትና የዋጋ መለኪያ መስፈርት ተደርጎ እንደሚወሰድ በመጥቀስም ታደለ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ ሰሊጥ አሁንም ተፈላጊ ነው ሲሉ የጠቀሱትን ሃሳብ የሚያጠናክር ሃሳብ አንስተዋል።
‹‹ኢትዮጵያ ሰሊጥ አንድ ሺህ 700 ዶላር ሲሸጥ የሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሰሊጥ አንድ ሺህ 600 ዶላር ይሸጣል። ሌሎች ሀገራት የሚወስዱት ከእኛ የተረፈውን ገበያ ነው›› ሲሉ ያብራራሉ።
ኢትዮጵያ የገበያ ችግር ሳይሆን በሚፈለገው መጠን ማቅረብ አለመቻሏ ነው ችግሯ ሲሉ ጠቅሰው፤ ከሁሉም በላይ ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ያስገነዝባሉ።
መንግሥት ለስንዴ የሰጠውን ትኩረት በሰሊጥም እንዲደግም ጠይቀው፤ ለሰሊጥ ተስማሚ በሆኑ አካባቢዎች በዓመት ሁለትና ከዚያ በላይ ማምረት የሚቻልበት ሁኔታ ሊፈጥር እንደሚገባም አመልክተዋል። ምርታማነትን ከማሳደጉ ጎን ለጎንም እሴት ጨምሮ ለዓለም ገበያ በማቅረብ የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን ሊሰራ ይገባል ሲሉም መክረዋል።
እንደ ታደለ (ዶ/ር) ማብራሪያም፤ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ አንዱና ወሳኙ ቁልፉ ነገር ምርታማነትን መጨመር ነው። ዘመኑን የዋጁ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችንና ምክረ-ሃሳቦችን ለአርሶ አደሩ ማቅረብ ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ሰሊጥ ያለውን ተቀባይነት ለማስቀጠል እንዲቻል ምርቱ ከማሳ እስከ ገበያ መዳረሻ ድረስ ጥራቱን ጠብቆ እንዲላክ ማድረግ ይገባል።
በተለይ ለአፍላቶክሲን እንዳይጋለጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት። ለዚህ ደግሞ የዘመነ የአመራረት ሂደትን መከተል የሚያስፈልግ ሲሆን፤ አጠቃላይ አሰራሩንም ዲጂታላይዝ ማድረግ ወሳኝ ነው ይላሉ።
ዋነኛ የገበያ መዳረሻ ሀገራትን የመግዛት አቅም ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መለየትም ይገባል። ፍላጎታቸውን ያማከለ ስራ መስራት በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ለመሆን ያስችላል። የተወዳዳሪ ሀገራትን የግብይት ስልትና ስትራቴጂ ማጥናት፣ አዳዲስ ስልቶችን መንደፍ ይጠቅማል።
በአቅም ደረጃ እንደ ህንድ ፣ ሱዳንና ናይጄሪያ ተወዳዳሪዎች ሲሆኑ፤ እነዚህ ሀገራት እንዴት ስኬታማ ሊሆኑ ቻሉ? የማምረት ስልታቸው ምንድን ነው? የጥራት መስፈርታቸውን እንዴት ነው የሚያሟሉት? የሚሉትን ጉዳዮች በጥልቀት ማወቅም ይገባል ነው ያሉት።
‹‹ከሁሉ በላይ ለምርት መቀነስ ዋነኛ ምክንያት የሆነውን የፀጥታ መደፍረስ ማስወገድ ይገባል›› ሲሉ ታደለ (ዶ/ር) አስገንዝበው፤ በተለይም ከፍተኛ አምራች በሆኑት እንደሁመራ ባሉ አካባቢዎች ለአምራቹ ምቹና ሰላማዊ ሁኔታ መፍጠር እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።
በቅርቡ የተመረቀው ብሔራዊ የጥራት መንደርም እንደ ሰሊጥ ያሉ የግብርና ምርቶችን ጥራት በማረጋገጥ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ምርት ለማቅረብ ትልቅ ዕገዛ የሚያደርግ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም