ነገን ከዛሬ የተሻለ ለማድረግ ዘላቂ ሰላም እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

አዲስ አበባ:- ነገን ከዛሬ የተሻለ ለማደግና ለመለወጥ ዘላቂ ሰላም በእጅጉ ያስፈልጋል ሲሉ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ገለጹ።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማህበር ከመቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ጋር ያዘጋጁት የጸሎት መርሀ ግብር ትናንት ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንደገለጹት፤ ሰላም የመረዳዳት፣ የመግባባት፣ የመተማመን እና በነጻነት የመኖር መሠረት ነው።

ነገን ከዛሬ የተሻለ ለማድረግ፣ ለመለወጥ እና ለመበልጸግ ሰላም በእጅጉ አስፈላጊ ነው። ከዚህ አኳያ ሁላችንም በዘርና በሃይማኖት ሳንለያይ ስለሰላም መሥራትና መጸለይ ይጠበቅብናል ሲሉ አስታውቀዋል።

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ሰላምና መተማመን የቀነሰበት፣ ጥላቻ የገነነበት፣ መለያየት የሰፈነበት ከመተባበር ይልቅ መጠላለፍ በስፋት የሚታይበት መሆኑን ገልጸዋል።

እነዚህ አሉታዊ መስተጋብሮች በማህበረሰቡ ያለውን መተማመንና አብሮነት የሚያፈርሱ፣ የሀገሪቱን እድገት ወደኋላ የሚጎትቱ በመሆኑ፤ ከግጭት፣ ከጥላቻ፣ ከቂምና በቀል፣ ከመለያየት እና ከግጭት በመራቅ ሰላምን ማስፈን ከሁላችንም ይጠበቅብናል ብለዋል።

ከግጭት ወደ ውይይት፣ ከቂምና ጥላቻ ወደ ሰላምና ፍቅር በመመለስ የጋራ መኖሪያችን የሆነችውን ኢትዮጵያን በአንድነትና በመተባበር እንጠብቅ ሲሉ ተናግረዋል።

ከተባበርን የማንሻገረው ነገር የለም፤ ያቀድነውን እንተገብራለን፤ ያለምነውን እናሳካለን፤ ሰላማችን የበዛና የተትረፈረፈ ይሆናል ሲሉ ጨም ረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት አባቶች ለሀገር ሰላም፣ ለሕዝብ አንድነት ለመጸለይ አንድም ቀን እንደማይታክቱ አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል የተቸገሩትን መርዳት የአምላክን ትዕዛዝ መጠበቅ በመሆኑ በመቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል የሚገኙ ወገኖችን መርዳትና ከጎናቸው መቆም እንደሚገባ ተናግረዋል።

የመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማህበር ከመቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል መስራችና ሥራ አስኪያጅ ቢኒያም በለጠ በበኩላቸው፤የሃይማኖት አባቶች በቦታው ተገኝተው ላደረጉላቸው የጸሎትና ጉብኝት መርሀ ግብርን አመስግነዋል።

መቄዶንያ ከስምንት ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ድጋፍ እያደረገ ያለ ማዕከል መሆኑን ገልጸው፤ ሁሉም ሰዎች ለማዕከሉ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You