ዜና ትንታኔ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ቱሪዝምና ኪነጥበብ ቢሮ በመስተንግዶ እና ተመሳሳይ ጉዳዮች ዙሪያ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በሕግ ለመፍታት የሆቴል እና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች አለባበስ ደንብ ቁጥር 178/2016ን ተግባራዊ ማድረጉ ይታወሳል።
ደንቡ ፀድቆ ተግባር ላይ መዋሉን ተከትሎ ኢትዮጵያዊ ጨዋነትና እሴትን የጠበቀ የመስተንግዶ አገልግሎት ከማስፈንና የሀገሪቱን ገፅታ ከመገንባት አንፃር ምን ፋይዳ ይኖረዋል? ስንል የዘርፉን ምሁራን አነጋግረናል።
ወይዘሮ ቱሩፋት በላይነህ በሕግ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ጋዜጠኛ፣ ጠበቃና የሕግ አማካሪ ናቸው። እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ እስከ አሁን ያለው የሆቴልና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አለባበስ ሥርዓት የኢትዮጵያውያን ባህል፣ እሴት የሚመጥን አልነበረም።
በተለይ ሴት የመስተንግዶ ሠራተኞች ሰውነታቸውን የሚያጋልጥ አለባበስ እንዲከተሉ ይደረጋል፤ ወንዶችም ቢሆን በአንዳንድ የሰውነት ክፍሎቻቸው ደንበኞችን በማይመጥን አለባበስ ይታያሉ። ትርጉማቸው ምን እንደሆነ የማይታወቅ ንቅሳቶችንም እንዲሁ ያደርጋሉ።
የሕግ አማካሪዋ፤ ድርጊቱ የተጠቃሚዎችን መብት ከመጋፋት በላይ የሀገርን ገጽታ በብዙ መልኩ እንደሚያበላሽ፣ ኢትዮጵያዊነትንም እንደሚያሳንስ ያምናሉ። አለባበሳቸውም ሆነ የሚጠቀሟቸው ጌጣጌጦች በዚህ ድርጊት የማይታሙትንም ጭምር በሌሎች ባህል እንዲዋጡ ያደርጋል ይላሉ። ይህንን ድርጊት ለመከላከል የሚያስችል ሀገር አቀፍ ሕግ ባይኖርም ዓለም አቀፉን ደረጃ እንኳን ያሟላ አለባበስ ሥርዓት በስፋት እየተለመደ መሆኑን ያነሳሉ።
የአዲስ አበባ ከተማ የበርካታ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ስብሰባዎች የሚደረግባት እንደ መሆኗ መጠን ኢትዮጵያን ማየት የሚቻልበት እድል ሰፊ እንደሆነ የጠቆሙት የሕግ አማካሪዋ፤ የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ የከተማ አስተዳደር አስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር እንደገና ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 84/2016 አንቀፅ 95 መሠረት ይህንን ደንብ ማውጣቱ ፋይዳው ብዙ እንደሆነ ተናግረዋል።
ደንቡ ከላይ የተጠቀሱት ኢትዮጵያዊ እሴትን የሚፃረሩ የመስተንግዶ ሥርዓትን ያልተከተሉ ጥሰቶችን ከማስተካከሉም ባሻገር የሀገርን ገጽታ ከመገንባት አኳያ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነም ያብራራሉ። በተለይም ኢትዮጵያዊ ሥነ-ሥርዓትን፣ እሴቶችንና የአለባበስ ሥርዓትን ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ያነሳሉ።
የመስተንግዶ ሠራተኞችን አለባበስ የሚወስን ምንም ሕግ እንደሌለ የሚናገሩት ወይዘሮ ቱሩፋት፤ ይህ ደንብ ሕግ ሆኖ ለማገልገል ጭምር እንደሚረዳ ያስረዳሉ። ኢትዮጵያ የራሷ የሕግ ሥርዓት እንዲኖራት መሠረት የሚጥል መሆኑንም ይናገራሉ። የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገፅታ ለማሳየት እንደሚረዳ ባህልና እሴቶችን ለማወቅ የሚመጡ ጎብኚዎችን ቁጥር በማሳደግ በቱሪዝም ዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ከፍ ያደርጋል ይላሉ።
እንደ ሕግ አማካሪዋ ገለጻ፤ ደንቡ ሀገራችንን በብዙ መስኩ የሚያስተዋውቅ ነው። አንዱ ጥሩ ማሳያ የብሔር ብሔረሰቦች የአለባበስ ባህል ለቀሪው ዓለም ማስተዋወቅና ኢትዮጵያዊ ሥነሥርዓትን ማስረፅ ነው።
‹‹በመስተንግዶ ባለሙያዎች የሚለበሱና የማይለበሱ ነገሮችን ደንግጓል›› የሚሉት የሕግ አማካሪዋ፤ የደረት ክፍልን ያልሸፈነ ወይም ከአንገት በታች ያለውን የሰውነት ክፍል የሚሸፍን ሸሚዝ ያለበሰ፣ የሴቶች ጉርድ ቀሚስ ቁመቱና ቅዱ ከጉልበት በላይ ከሆነ፣ ከጋብቻ ቀለበት ውጪ ጌጣጌጦችን በሚታዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ ከተደረገ በደንቡ መሠረት የሚያስቀጣ መሆኑን አንስተዋል። በደንቡ የተቀመጡት ቅጣቶች የተለያዩ ሲሆኑ፤ ሕግ ተላልፎ የተገኘ አሠሪ (አካል) በድንጋጌው መሠረት ከአምስት ሺህ ብር ጀምሮ ተቋሙን እስከ ማሸግና የንግድ ፈቃዱን እስከመንጠቅ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወሰድበት ተጠቁሟል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች የማህበራዊና አካቶ ትግበራ ባለሙያ ወይዘሮ ምህረት መኩሪያ ደንቡ መውጣቱ አስፈላጊና ተገቢ መሆኑን የወይዘሮ ቱሩፋትን ሃሳብ ደግፈው ያብራራሉ። እርሳቸው እንዳሉት፤ የደንቡ መውጣት ባህላዊና ኢትዮጵያዊ ሥርዓትን የተላበሱ አልባሳት እንዲዘወተሩ ያግዛል፤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ለሚሠሩ ባለሙያዎችም የሙያ ክብር እንዲሰጣቸው ያደርጋል፤ ወጥ የሆነ የአለባበስ፣ የጌጣጌጥ እና የመዋቢያ አጠቃቀም ሥርዓት እንዲፈጠርም እድል ይሰጣል። ከሁሉም በላይ የሀገር ባህልና እሴት እንዲጠበቅ በማድረግ በዘርፉ ተሰማርተው የሚሠሩ ሙያተኞችን ከአካላዊ፤ ሥነ-ልቦናዊና ጾታዊ ጥቃት እንዲጠበቁ ያደርጋል።
ሁለቱም ባለሙያዎች በአዲስ አበባ ደረጃ ፀድቆ ሥራ ላይ የዋለው ደንብ በአግባቡ መተግበር ከቻለ በቀጣይ ወጥ የሆነ የአስተናጋጆች አለባበስ ይሰፍናል።
ባህላዊ እሴቶቻችንን ያስተዋውቃል፤ ቱሪዝሙን በማነቃቃት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ከፍ ያደርጋል። ከሁሉም በላይ ሙያው የተከበረ የሆቴልና የአገልግሎት ተቋማት ሠራተኞችን ይፈጥራል። ሕጋዊ አሠራሮችን ከመዘርጋት አኳያም የማይተካ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም