በመካከለኛው ምስራቅ የፈነጠቀው የሰላም አየር

አስራ አራት ወራት ለተጠጋ ጊዜ የተወረወሩ ድምበር ዘለል የጦር ፍላፃዎች በሺዎች ለሚቆጠሩ ንፁሃን ሞትና መፈናቀል ምክንያት ሆነዋል። ለከፉ ጥቃቶች፣ ለበርካታ ወታደሮችና ቁልፍ ወታደራዊ መሪዎች ሞት መንስዔ የሆኑ የጥይት አረሮች ካለፈው ማክሰኞ ምሽት ጀምሮ ወደ ሰገባቸው ተመልሰው ሰላም እንደ ውሃ ለጠማው ሕዝብ ለጊዜውም ቢሆን እፎይታ ሰጥተዋል። በእስራዔልና በሊባኖሱ ታጣቂ ሄዝቦላ ቡድን መካከል የአየርና የምድር ግጭቶች ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን በተኩስ አቁም ስም እንዲገቱ ስምምነት ላይ ተደርሷል። ይህ እለት ከእለት ነብሳቸውን በጨርቅ መጠቅለል ለቀራቸው ንፁሃን ትልቅ ብስራት ነው። የተኩስ አቁም ስምምነቱ በተለይም ለሰሜን እስራዔልና ደቡብ ሊባኖስ ዜጎች ትልቅ ትርጉም አለው ተብሏል።

ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ያቀረቡት ምከረ ሃሳብ በሁለቱም ወገኖች ተቀባይነት ማግኘቱ በብዙዎች ዘንድ እውን ለስልሳ ቀናት የታወጀው የተኩስ አቁም ስምምነት ወደ ዘላቂ ሰላም ለማምራት ያበቃ ይሆን? የሚል ጥያቄ አጭሯል። ፕሬዚዳንት ባይደን ማክሰኞ ምሽት ስለተኩስ አቁም ስምምነቱ በሰጡት መግለጫ፣ “በሊባኖስና በእስራዔል መካከል ሲካሄድ የቆየው ድምበር ዘለል ጦርነት ማብቂያው ይሆናል፣ ያቀረብነው የተኩስ አቁም ስምምነትም ለዘለቄታው ጦርነቱን ለማስቆም ከግምት ያስገባ ነው” ብለዋል።

በሁለቱም ወገኖች ያሉት ሲቪል ማህበረሰቦች በቅርቡ ወደ ህብረተሰባቸው በሰላም ተመልሰው መደበኛ ሕይወታቸውን ይመራሉ ሲሉም ባይደን ተናግረዋል። የሞት ሱናሚ ሲንጠው የቆየው የሊባኖስ ሰማይ የሰላም አየር ይነፍስበት ዘንድ በፕሬዚዳንት ባይደን የቀረበው ሃሳብ በሊባኖሱ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ኒካቲ በኩል ተቀባይነት ለማግኘት አፍታ አልፈጀበትም። ኒካቲ የተኩስ አቁም ስምምነቱን በደስታ እንደሚቀበሉ ለፕሬዚዳንት ባይደንም አሳውቀዋል።

ከጦር እስከ ረሃብን እንደ ጦር መሣሪያ የመጠቀም ወንጀል ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ ያወጣባቸው የእስራዔሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ፣ ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት መንግሥታቸው የተኩስ አቁም ስምምነቱን ማፅደቁንና ባይደንም እስራዔል ራሷን የመከላከል መብት እንዳላት መጥቀሳቸውን በማድነቅ ለስምምነቱ ተገዢ መሆናቸውን ገልፀዋል። ‹‹ሄዝቦላህ ስምምነቱን ጥሶ ራሱን ለማስታጠቅ የሚሞክር ከሆነ ግን ጥቃት እንፈፅማለን፣ በድንበር አካባቢ የሽብር መሠረተ ልማት የሚገነባ ከሆነም እናጠቃለን›› ያሉት ኔታኒያሁ፤ እስራዔል በሰሜናዊው ጎረቤቷ ከሚንቀሳቀሰው ሄዝቦላህ ጋር ስምምነት መፍጠሯ የእስራዔል ጦር ትኩረቱን ኢራን ላይ ብቻ ለማድረግ እንደሚያስችለውም ተናግረዋል።

አሜሪካ ባቀረበችው በዚህ የተኩስ አቁም ስምምነት ዝርዝር ነጥብ መሠረት እስራዔል በሚቀጥሉት ስልሳ ቀናት ጦሯን ከደቡብ ሊባኖስ በሂደት የምታስወጣ ሲሆን፣ በምትኩም የሊባኖስ ጦርና የመንግሥት የፀጥታ ሃይሎች ወደ ግዛቱ የሚሠማሩ ይሆናል። ባይደን ከፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑዔል ማክሮን ጋር ባወጡት መግለጫ ሁለቱ ሀገራት ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ መተግበሩንና ተፈፃሚ መሆኑን ለማረጋገጥ ከእስራዔልና ሊባኖስ ጋር እንደሚሠሩ በአፅኖት ገልፀዋል። በተጨማሪም አሜሪካና ፈረንሳይ የሊባኖስን መንግሥት የጦር ሃይል ለመገንባትና በመላው ሊባኖስ ውስጥ መረጋጋት ተፈጥሮ ሀገሪቱ ወደ ልማት ፊቷን እንድታዞር የሚደረጉ ዓለም አቀፍ ጥረቶችና ድጋፎችን ከፊት ሆነው ለመምራት ቃል ገ ብተዋል።

ሀማስ እስራዔል ላይ ከዓመት በፊት የፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ እስራዔል ከወሰደችው ምላሽ ማግስት ሄዜቦላ ከሀማስ ጎን በመቆም ነበር አዲስ የጦርነት ምዕራፍ የከፈተው። በዚህም ምክንያት በሄዝቦላና እስራዔል መካከል በርካታ የሚሳዔልና የሮኬት ጥቃቶች ሲፈፀሙ ቆይተዋል። ነገሩ እየተባባሰ ሲሄድ እስራዔል ከወር በፊት እግረኛ ወታደሮቿን በደቡብ ሊባኖስ አሰማርታ ርምጃ መውሰድ መጀመሯ ይታወቃል። ይህም ከሶስት ሺ በላይ ሊባኖሳውያን ሕይወታቸውን እንዲያጡ ከማድረጉ በተጨማሪ ከአስራ አምስት ሺህ በላይ የሚሆኑ መቁሰላቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ጦርነቱ በሊባኖስ ካስከተለው ሠብዓዊ ቀውስ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ኪሳራም ያደረሰ ነበር። እንደ ዓለም ባንክ መረጃ በዚህ ጦርነት ምክንያት የ8 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የኢኮኖሚ ኪሳራ ደርሷል። የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለማቋቋምም ረጅም ጊዜ የሚፈጅ ሲሆን፣ በማን ወጪ ይሸፈናል? የሚለው ጉዳይ ሌላ ጥያቄ የፈጠረ ሆኗል።

በሰላም ስምምነቱ መሠረት የእስራዔል ጦርና የሄዝቦላ ተዋጊዎች ከያዟቸውን የደቡባዊ ሊባኖስ ቦታዎች ከወጡ በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ የሊባኖስ ወታደሮች እንደሚሠማሩ ይጠበቃል። ይህ እንዴት ተፈፃሚ ይሆናል? የሚለው ጉዳይ ግን በግልፅ አልተቀመጠም። የሊባኖስ ወታደሮች የተሰጣቸውን ግዳጅ ለመወጣትም የሚያስችል ሀብት ወይም በቂ ገንዘብ፣ የሰው ኃይልና የመሣሪያ አቅም የላቸውም በማለት የሀገሪቱ መንግሥት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የድጋፍ ጥያቄ አቅርቧል። በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡ አንዳንድ ተንታኞች የገንዘብ ድጋፉ ከተለያዩ የሊባኖስ ዓለም አቀፍ አጋሮች ሊገኝ ይችላል የሚል ተስፋ አላቸው። መሣሪያና ተጨማሪ የሰው ሃይል ማሠልጠን የተፈለገው ግን በሊባኖስ መንግሥት በኩል ሂዝቦላን እስከወዲያኛው ለማዳከም ታስቦ ሊሆን ይችላል ይላሉ። ይህም በቀጣዮቹ ጊዜያት የሊባኖስ ጦር ከሂዝቦላ ጋር ወደ ሌላ የግጭት ምዕራፍ እንዳይገባ ስጋታቸውን ያጋራሉ።

የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከእስራዔል ጋር ያለውን ግጭት ወደ ፍፃሜ ሊያመጣ ይችላል የሚለው እምነት የበርካቶች ሆኗል።

በሥልጣናቸው የመጨረሻ ወራት ላይ እስራዔልና ሄዝቦላን ወደ ተኩስ አቁም ድርድር ማምጣት የተሳካላቸው ፕሬዚዳንት ባይደን በቀረቻቸው ጥቂት የሥልጣን እድሜ ከቱርክ፣ ግብፅ፣ ካታር፣ እስራዔልና ከሌሎችም ጋር ንግግር በማድረግ በጋዛ ተኩስ አቁም ተግባራዊ እንዲሆን ለማድረግ ቃል ገብተዋል። በተጨማሪም በጋዛ ጦርነት ምክንያት ወደ ኋላ የተመለሰውን ሳውዲ አረቢያን ጨምሮ በእስራዔልና በሌሎች የአረብ መንግሥታት መካከል ተጀምሮ የነበረውን በጎ የግንኙነት ምዕራፍ በማደስ አዳዲስ ስምምነቶችን ለማበጀት እንደሚሠሩም ቃል ገብተዋል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You