ፋሽስቱ የወጣበት የመጨረሻው ውጊያ

ኢትዮጵያ ነፃነትን ለዓለም በማስተማር ደማቅ ታሪክ አላት:: ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አሸናፊ የሆኑት የዓለም ልዕለ ኃያል የተባሉት አራቱ ሀገራት (አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ሶቪየት ኅብረት) የጣሊያን ቅኝ ግዛት የነበሩት ሀገራት እንዴት ይሁኑ? በሚለው ጉዳይ ላይ ከ10 ዓመታት በላይ ተከራክረዋል:: በእነዚህ ክርክሮችና ውይይቶች ውስጥ፤ ቅኝ ያልተገዛችው ኢትዮጵያ ከኃያላኑ ሀገራት ጋር በአንድ አዳራሽ ተቀምጣ መክራለች:: ሙሉ ታሪኩን ‹‹የኤርትራ ጉዳይ›› ከሚለው የአምባሳደር ዘውዴ ረታ መጽሐፍ ላይ ማግኘት ይቻላል::

ኢትዮጵያ ለዚህ ክብር የበቃችበት ምክንያት ቅኝ ያልተገዛች ሀገር መሆኗ ነው:: ቅኝ የተገዙ ሀገራትን ልክ እንደ ሕጻን ልጅ ሞግዚት እናድርግላቸው ወይስ ራሳቸውን ችለው መኖር ይችሉ ይሆን? እየተባለ ሲመከር ኢትዮጵያ ግን የይገባኛል ጥያቄ ይዛ (ኤርትራንና ሱማሌን) ከኃያላኑ ጋር አብራ መካሪ ነበረች:: በጀግኖች ልጆቿ ሉዓላዊነቷን ባታስከብር ኖሮ በዚያ ውይይት ላይ መካሪ ሳይሆን ‹‹ማንን ሞግዚት እናድርግላት?›› እየተባለ የሚመከርባት ትሆን ነበር::

በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን 83 ዓመታት ወደኋላ መለስ ብለን በዚህ ሳምንት ኅዳር 19 ቀን 1934 ዓ.ም ወራሪው የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያ ውስጥ የመጨረሻውን ውጊያ አድርጎ የተሸነፈበትን እና የኢትዮጵያ ሙሉ ነፃነትና ሉዓላዊነት መከበሩ የተረጋገጠበትን የታሪክ ክስተቶች እናስታውሳለን:: ከዚያ በፊት እንደተለመደው ሌሎች የዚህ ሳምንት ክስተቶችን በአጭር በአጭሩ እናስታውሳለን::

ከ172 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 19 ቀን 1845 ዓ.ም ደጃዝማች ካሣ ኃይሉ ‹‹ዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› ተብለው ከመንገሣቸው በፊት ከግዛት ባላባቶች ጋር ካደረጓቸው ታላላቅ ጦርነቶች መካከል አንዱ የነበረውን የጉር አምባ ጦርነት ከደጃዝማች ጎሹ ዘውዴ ጋር አደረጉ:: ይህ ጦርነት ለአፄ ቴዎድሮስ ወደ ንጉሠ ነገሥትነት መምጣት እና ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ወሳኙ ጦርነት ነበር:: በዚህ ጦርነት ላይ የደጃች ጎሹ ጦር ለማሸነፍ ተቃርቦ ነበርና አንድ አዝማሪ ለደጃች ጎሹ አድሮ እንዲህ አለ::

ያንዣብባል እንጂ መች ይዋጋል ካሣ

ወርደህ ጥመድበት ከሽንብራው ማሳ

ወዲያውኑ የደጃች ካሣ (አፄ ቴዎድሮስ) ጦር አሸነፈ:: ያ አድርባይ አዝማሪ አቋሙን ቀይሮ እንዲህ አለ::

አወይ የአምላክ ቁጣ

አወይ የእግዜር ቁጣ

አፍ ወዳጁን ያማል የሚሠራው ሲያጣ

ዱላ ይገባዋል የአዝማሪ ቀልማጣ

ይህ አዝማሪ አፄ ቴዎድሮስን ለማስደሰት ብሎ አቋሙን ቀይሮ ንጉሡን ቢያወድስም፤ አፄ ቴዎድሮስ ግን ‹‹እንዲህ አይነት አድር ባይ ሰው አልወድም›› ብለው እንዳስገደሉት በታሪክ ተጽፏል::

ከ50 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 19 ቀን 1967 ዓ.ም ብርጋዴር ጄኔራል ተፈሪ ባንቲ የደርግ ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ::

ከ164 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 21 ቀን 1853 ዓ.ም የታሪክ ጸሐፊ፣ ተርጓሚ፣ ደራሲ፣ የቅኔ ሊቅ፣ የሃይማኖት መምህር የነበሩት እና በኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ስማቸው ጎላ ብሎ የሚጠቀሱት አለቃ ታዬ ገብረማርያም ተወለዱ::

ከ114 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 22 ቀን 1903 ዓ.ም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዘመናዊ መድኃኒት ቤት (ፋርማሲ) ተቋቋመ::

ከ30 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ልክ በዛሬዋ ቀን ኅዳር 22 ቀን 1987 ዓ.ም ደራሲ፣ የሥነ ጽሑፍ መምህር፣ ገጣሚ እና የተውኔት ጠቢብ የነበረው ዳኛቸው ወርቁ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ:: በተለይም ‹‹አደፍርስ›› በሚለው መጽሐፉ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀው ዳኛቸው ወርቁ፤ የመጽሐፉ የቋንቋ ረቂቅነት፣ የሀሳብ ጥልቀት እና የሥነ ጽሑፍ ቅርጽ የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎችን ሲያነጋግር ቆይቷል:: አደፍርስ በሥነ ጽሑፍ ቅርጽ የቃለ ትውኔት ቅርጽ እንዳለውም ይነገራል:: ደራሲ ዳኛቸው ወርቁን ‹‹የሥነ ጽሑፍ አብዮተኛው›› በሚል ርዕስ ከዚህ በፊት ሳምንቱን በታሪክ በዝርዝር መሥራታችን ይታወሳል::

በዝርዝር ወደምናየው ሳምንቱን በታሪክ እንሂድ::

ወራሪው የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያ ውስጥ የመጨረሻውን ውጊያ አድርጎ የተሸነፈውና ኢትዮጵያ ሙሉ ነፃነትና ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠችው ከ83 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 19 ቀን 1934 ዓ.ም ነበር:: ይህ ወቅት ጣሊያን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከጀርመን ጋር ተባብራ ባደረገችው ውጊያም የተሸነፈችበት ነበር::

ወደ ኢትዮጵያ ታሪክ ስንመጣ፤ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም አዲስ አበባ ገብተው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቢውለበለብና የፋሺስት ጦር መሸነፉ ይፋ ቢሆንም፤ ጦሩ ከአንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ጨርሶ አልወጣም ነበር:: በዚሁ ሳምንት ኅዳር 18 ቀን 1934 ዓ.ም የፋሺስቱ ጦር የመጨረሻ ይዞታው የነበረችውን ጎንደርን ለማስለቀቅ ኢትዮጵያውያን አርበኞች ከእንግሊዝ ጦር ጋር በጋራ በመሆን ውጊያ ከፈቱ:: በዕለቱ የአካባቢው የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር መሪ የነበረው ጀኔራል ናዚ የኢትዮጵያውያን አርበኞችና የእንግሊዝ ወታደሮች የጋራ ጥቃት ጥንካሬው ተስፋ ስላስቆረጠው ከአደባባይ ኢየሱስ ወደ መድኃኔዓለም ሄዶ ነጭ ጨርቅ አውለበለበ:: ምርኮ የመረከብ ሥራ ተጀምሮ ነበርና፤ አርበኛውም ሁሉ ጉራያ ማስጫ ከሚባለው ቦታ ከግንቡ ስር አደረ::

በምሥራቅ በኩል የተሰለፈው የኢትዮጵያ ጦር ግን ወደ ጎንደር ለመግባት ሲሞክር ተቀብሮ የነበረው የፋሺስት ጣሊያን ጦር ቦምብ ፈንድቶ ጉዳት አደረሰበት፤ እርምጃውንም አዘገየበት:: በማግስቱ ኅዳር 19 ቀን 1934 ዓ.ም ራስ ብሩ ወልደገብርኤል ከእንግሊዛዊው ሜጀር ጄኔራል ፎክስ ጋር ወደ ጎንደር ገቡ:: ‹‹ባለህበት እርጋ›› ተባለና ሁሉም ተረጋጋ:: ጄኔራል ናዚ ያለድርድር እጁን ሰጠ:: የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በፋሲለደስ ግንብ ላይ ተውለበለበ።

በማግሥቱ ኅዳር 20 ቀን 1934 ዓ.ም ልዑል አልጋወራሽ አስፋወሰን ኃይለሥላሴ ጎንደር ገቡ:: የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር በኢትዮጵያ የነበረው ቆይታም በዚሁ ተደመደመ:: በጎንደሩ ውጊያ የጣሊያን ሽንፈት የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር በአፍሪካ ምድር ያካሄደው የመጨረሻው ውጊያና የተከናነበው የመጨረሻው ሽንፈት ሆኖም ተመዘገበ::

አራት ኪሎ የሚገኘው የአርበኞች ድል መታሰቢያ (የድል ሐውልት) አፄ ኃይለሥላሴ ከእንግሊዝ ተመልሰው አዲስ አበባ የገቡበት ቀን ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ነው ተብሎ በታሪክ መዝገብ ላይ ቢሰፍርም፤ ኢትዮጵያ ከፋሺስቶች ሙሉ በሙሉ የተላቀቀችበት ቀን ኅዳር 19 ቀን 1934 ዓ.ም ነው፤ በዚሁ ዕለት ጄኔራል ናሲ የተባለው የፋሺስት ጦር መሪ ከነሠራዊቱ እጁን ሰጥቶ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በፋሲለደስ ግንብ ላይ ተውለበለበ። በነገራችን ላይ በደርግ ዘመነ መንግሥት ጊዜ የአርበኞች ቀን የሚከበረው ሚያዚያ 27 ቀን አልነበረም:: ደርግ የንጉሠ ነገሥቱን ታሪክ መቀየር እንደሚፈልግ ግልጽ ቢሆንም ሚያዝያ 27ም ቢሆን ግን ታሪካዊ ቀን ነው::

በወቅቱ ይታተም የነበረ ‹‹ባንዲራችን›› የተሰኘ ጋዜጣ በ1ኛ ዓመት ቁጥር 39 የካቲት 18 ቀን 1934 ዓ.ም ዕትሙ፤ ከፋሽስት ጣሊያን ጋር ለመጨረሻ ጊዜ ስለተደረገው የጎንደሩ ጦርነት የሚከተለውን መረጃ አትሟል::

ብዙ ሽንፈት የተከናነበው ሞሶሎኒ የጠቅላይ ጦር አዛዥነቱን ሥልጣን ለጀኔራል ናዚ ሰጠው። ናዚ የቀረውን አርባ ሺህ የሚሆነውን የጣሊያን ጦር አሰባስቦ የመጨረሻውን ፍልሚያ ለማድረግ ጎንደር ላይ መሽጎ መጭውን ጊዜ በጭንቀት ይጠባበቃል።

በደጃዝማች ሀብተሥላሴ በላይነህ የሚመራው አምስት ዓመት ሙሉ ጠላትን መግቢያ መውጫ ያሳጣው የሸዋ አርበኛ አምባላጌ ላይ ዱክ ዳውስታን ማርኮ በየቦታው የመሸገውን የጠላት ጦር እየደመሰሰ በተለይም ጠላት መቼም አይደፈሩም ብሎ የመሸገባቸውን ወልክፊት፣ ፍርቃ በር እና ቁልቋል በር የተባሉትን የጠላት ምሽጎች ሰባብሮ ጎንደር ደርሶ ለመጨረሻ ጊዜ ፋሽስቱን የጣሊያን ጦር ለመቅበር ዝግጅቱን ጨርሷል። በጀኔራል ፎክስ የሚታዘዘው የእንግሊዝ ጦርም በአየር፣ በመካናይዝድ እና በእግረኛ ጦር ተዘጋጅቶ የመጨረሻውን ትዕዛዝ ይጠባበቃል:: በመጨረሻም የጎንደር ከተማ በየአቅጣጫው ተከበበች::

የጎንደር ከተማ ከተከበበች በኋላ ኅዳር 18 ቀን 1934 ዓ.ም ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ጦርነቱ ተጀመረ:: የእንግሊዝ እና የጠላት መድፎች ሰማይና ምድሩን ያናውጡት ጀመር:: የእንግሊዝ የጦር አውሮፕላኖችም ከዳባት በመነሳት የናዚን የጦር ሰፈር በቦንብ ይቀጠቅጡት ጀመር።

በደጃዝማች ሀብተሥላሴ የሚመራው በደቡብ ጎንደር ሰፍሮ የነበረው አርበኛ ሌሊቱን ተጉዞ አድሮ ወደ ምሽጉ ተጠግቶ ስለነበር በፈንጂ ላይ እየተረማመደ የጣሊያኑን የጄኔራል ማርቲንን ሠራዊት ሰብሮ ቀድሞ ጎንደር ገብቶ የጠላትን ጦር ያርበደብደው ጀመር:: በጄኔራል ፎክስ የሚታዘዘው የእንግሊዝ መካናይዝድ ጦር የአዘዞን ግንባር ጥሶ ገባ:: በምሥራቅ በኩል የነበሩት አርበኞችና የእንግሊዝ ወገን የሆኑት የኬንያ ወታደሮች ደፈጫ የነበረውን የጠላት ጦር በጥንካሬ ወግተው አስለቅቀው ወደ ጎንደር ለመግባት ሲሞክሩ በተጠመደ ፈንጂ ከባድ ጉዳት ደረሰባቸው።

የእንግሊዝ ጦርም ከሰዓት በኋላ ወደ ስምንት ሰዓት ተኩል ሲሆን ወደ ፋሲል ግንብ ተጠጋ:: በዚህ ጊዜም ጀኔራል ናዚ በተጠባባቂነት ያስቀመጠውን የመጨረሻውን ጦር ቢልክም ውጤት ሳያመጣለት ቀረ። ከትንሽ ጊዜም በኋላ ጄኔራል ናዚ ከተደበቀበት ‹‹ካዲ ኢጣሊያ›› ከሚባለው ቤት አስተርጓሚ ሆነው ሲያገለግሉት ከነበሩት ከፊታውራሪ አስፍሓ ወልሚካኤል ጋር በመሆን እጁን ሰጠ።

ከዚህ በኋላ ሠራዊቱ እንዲረጋጋ የተማረኩና የተበተኑት የጠላት ወታደሮችም እንዲሰበሰቡ በተማረኩ የጠላት ወታድሮች ላይም አርበኞች ምንም ጉዳት እንዳያደርሱ የማረኳቸውን እንዲያስረክቡ የሚል ትዕዛዝ በመተላለፉ አርበኞች የማርኳቸውን የጠላት ወታደሮች እያመጡ ያስረክቡ ጀመር።

በዚህ ጦርነት አራት ሺህ የጣሊያን ወታደሮች ሲገደሉ፣ ስምንት ሺህ አራት መቶ የቆሰሉ ሲሆን፤ ሃያ ሰባት ሺህ ተማርከዋል:: ጄኔራል ናዚም የጦር ወንጀለኛ ሆኖ በእስር ወደ ኬንያ ተላከ።

በዚህ ጦርነት ከጠላት የተማረከውን ከባድና ቀላል የጦር መሣሪያ መድፍ፣ ታንክ፣ እና ከባድ የጦር ተሽከርካሪ አንድም ሳያስቀሩ እንግሊዞች በሱዳንና በኤርትራ በኩል አግዘው ወስደዋቸዋል።

ከድሉ በኋላ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የሚከተለውን የደስታ መግለጫ መልዕክት ጎንደር ለሚገኙት አርበኞች አስተላለፉ::

‹‹በዚህ በታላቅ ደስታ ምልክት በሚታይበት ቀን በሰንደቅ ዓላማችን ዙሪያ ተሰብስባችሁ በአየር ሲውለበለብ የምትመለከቱት አርበኞች ዓይኖቻችሁ ከኢትዮጵያ አየር ተለይቶ በማያውቀው ቀለም የተጌጠውን የነፃነት ምልክት ለማየት ሲወረወሩ ልባችሁ የሚሰማውን የደስታ ወለልታ መላ በጌምድር እንደሚሰማው ለኛም ይሰማናል። በዚህች ሰዓት በተወደደ ልጃችን አማካኝነት ስንናገራችሁ በመካከላችሁ እንዳለን ቁጠሩት። በአለፉት ዓመቶች የደረሰውን ፈተና ድል አድራጊ ለመሆንና በጎንደር ከተማ በዛሬው ቀን ይህን ለማየት ስትችሉ መሪር መንገድ አልፋችሁ ወደዚህ ቦታ ለመድረስ የበቃችሁ አርበኞቻችን በጦር ሜዳ የተመሰገኑ ጀግኖቻችንን እሬሳና አፅም ተራምዳችሁ ነው። ይህም ዛሬ የምታዩት ሰንደቅ ዓላማ በነዚያ ደምና በእናንተ ገበሬነት በለሰለሰ መሬት ላይ በቅሎና ለምልሞ ያደገ የነፃነት ሕይወት ዛፍ ነው። የአለፉት መታሰቢያና የኛና በሕይወት የተረፋችሁት ድካም አልጠፋምና እኛን ደስ እንዳለን እናንተም ደስ ይበላችሁ:: ይህ በወገኖቻችን ደም የበቀለው የሰንደቅ ዓላማ ዛፍ የዘለዓለም የሕይወት ዛፍ እንዲሆን ያለፉት በመስዋዕትነት የደከሙትን ያህል በሕይወት የቀረነው ወደፊትም የሚመጣው ትውልድ በአስፈለገ ጊዜ በመስዋዕት የሚሰጥበት የቃል ኪዳን ምልክት ነው››

ከዚህ በኋላ ልዑል አልጋ ወራሽ አስፋወሰን ጎንደር መጥተው ስለነበር፤ እርሳቸውን ተቀብለው ከእርሳቸው ጋር ሀገር ሲያረጋጉ ከቆዩ በኋላ ደጃዝማች ኃብተሥላሴ ከነሠራዊታቸው ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው የካቲት 16 ቀን 1934 ዓ.ም በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከፍተኛ የጦር ሰልፍና ሥነ ሥርዓት አቀባበል ተደርጎላቸዋል:: በጊዜው በቦታው ተገኝቶ የነበረው ‹‹ባንዲራችን›› የተባለው ጋዜጣ ሥነ ሥርዓቱን በምልከታ ሐተታ ዘግቦታል::

በአጠቃላይ፤ ኢትዮጵያ በዓድዋ ጦርነት ያሳየችውን የጀግንነት ድል በድጋሚ አስመስክራለች:: ከ40 ዓመታት ዝግጅት በኋላ ቂሙን ለመወጣት የመጣው የጣሊያን ወራሪ በድጋሚ ሽንፈት ተከናንቦ ተመልሷል:: ኢትዮጵያም ሉዓላዊነቷን በማስከበሯ በዓለም አቀፍ መድረኮችና ማኅበራት ላይ ከአድራጊ ፈጣሪዎች ጋር ተሳታፊ ለመሆን በቅታለች:: ክብር ለጀግኖች አርበኞቻችን!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ኅዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You