
አዲስ አበባ፡- የእንስሳት ልማትን ለማረጋገጥ የመኖ አቅርቦትና የእንስሳት ጤና ጥበቃ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስታወቀ። በተለያዩ ጊዜያት እየተከሰቱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳት እያደረሱ ያሉ የእንስሳት በሽታዎች መኖራቸውም ተመላክቷል።
በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ስሩር ለኢፕድ እንደገለጹት፤ የእንስሳት ልማትን ለማረጋገጥ የእንስሳት ጤናና መኖ ላይ በስፋት መሥራት ይገባል።
መኖና ጤና በሌለበት የእንስሳት ሀብትን ውጤታማ ማድረግ አይቻልም ያሉት የቢሮ ኃላፊው፤ የእንስሳትን ጤና ለመጠበቅና በቂ መኖ ለማቅረብ በክልሉ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። ግለሰቦች የሚያመርቱት መኖ ከእንስሳት ፍጆታ የተረፈ እንዲሆንና የተረፋቸውን መኖ ለገበያ አቅርበውት የገቢ ምንጭ እንዲሆናቸው ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን ጠቁመዋል።
በክልሉ በርካታ የአርሶአደር ኅብረት ሥራ ማህበራት የመኖ ማቀነባበሪያ እንዳላቸው የገለጹት አቶ ኡስማን፤ ኢንዱስትሪዎቹ አቅማቸውን እንዲያጠናክሩ እየተሠራ ነው። ኢንዱስትሪዎቹ መኖን ለዶሮ፣ ለወተት ላም አርቢዎችና የማድለብ ሥራ ለሚሰሩት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ እየተደረገም ነው ብለዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተመረቁ ወጣቶችን በማደራጀት የመኖ ማቀነባበሪያ አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ተዘጋጅቶላቸው እየሠሩ ነው። በዚህም ተስፋ የሚሰጥ ውጤት እየታየ ነው። በየአካባቢው ካሉ የኅብረት ሥራ ማህበራት የሚገኙ ምርቶችን በማቀናጀትና በኢንዱስትሪዎች መኖን ማምረት የሚቻል ቢሆንም የአፈጻጸም ችግር ስላለ አቅም ለማጎልበትና ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው።
በክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የእንስሳትና የአሳ ሀብት ዘርፍ ኃላፊ አቶ እያሱ ተረፈ በበኩላቸው፤ በክልሉ መከላከልን መሰረት ያደረገ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ሥራ በስፋት እየተሠራ ነው ብለዋል።
እንደክልል በተለያዩ ጊዜያት እየተከሰቱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳት እያደረሱ ያሉ የእንስሳት በሽታዎች መኖራቸውን ጠቁመው ፤ ሁሉንም እንስሳት ያማከለና የጊዜ ካሌንደርን መሰረት በማድረግ ክትባቶችን ተደራሽ ለማድረግ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
እንደ አቶ እያሱ ገለጻ፤ በበጀት ዓመቱ አራት ወራት አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን እንስሳት ይከተባሉ ተብሎ ታቅዶ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን እንስሳት ተከትበዋል። ክትባት ቢኖርም እንስሳት መታመማቸው ስለማይቀር የህክምና አገልግሎት እንደሚሰጥና በዚህም የታመሙ እንስሳትን ማከም የሚያስችል መሰረተ ልማት የማዘጋጀት ሥራ ተሠርቷል። የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በቢሮው የክሊኒክ አገልግሎት ክፍል መኖሩንና በዛም ሸኮና ቀንድና ሌሎች ነገሮችን የማስተካከልና መሰል ሥራዎች ሥራ ይሠራል።
በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰትና ምርታማነት ላይ ጉዳት የሚያደርስ የገንዲ በሽታ መኖሩን የሚገልጹት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ በሽታውን ለመከላከል 2ሺ 200 እንስሳትን ኬሚካል መቀባት መቻሉን ገልጸዋል። ያም ቢሆን በሽታውን ለመከላከል የሚያስችል የኬሚካል አቅርቦት እጥረት መኖሩንና ግዢ ለመፈጸምም በሀገር ውስጥ በቂ አቅርቦት አለመኖሩ ችግር እንደሆነባቸው ተናግረዋል።
በሌማት ትሩፋቱ የታቀዱ እቅዶችን ለማሳካት በሚያስችል መንገድ አርሶአደሩ እንስሳቱን በሞት እንዳያጣና በበሽታ ምክንያት ምርት እንዳይቀንስ አስፈላጊውን ግብዓት የማቅረብና የባለሙያ አቅም በስልጠናዎች ማሳደግ ጥኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም