የመከላከያ ሠራዊታችን የሰላም ተልዕኮ ስኬታማነት ከሕዝባዊነቱ ይመነጫል!

ሀገራችን ስለ ሰላም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጨባጭ ዋጋ ከሚከፍሉ ጥቂት ሀገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀስ ነች። እ.አ.አ ከ1950ዎቹ ጀምሮ እስከ ዛሬ በተለያዩ የሰላም ማስከበር ተልእኮዎች በመሳተፍ እና ውጤታማ ሥራዎችን በመሥራት ዓለም አቀፍ እውቅና አግኝታለች ።

በዓለማችን ሰላም እንዲሰፍን ከሊግ ኦፍ ኔሽን ጀምሮ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ውስጥ በመሳተፍ ብቸኛ አፍሪካዊት ሀገር ነች። በዚህም በብዙ የሰላም እጦት ውስጥ ለነበሩ የዓለም ሕዝቦች የሰላም ግንባታ አቅም ሆናለች። ዘላቂነት ላለው መረጋጋት ብዙ ዋጋ ከፍላለች።

ከኮሪያ ልሣነ ምድር የሚጀምረው የሀገሪቱ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ፣ በአፍሪካ በኮንጎ፣ በላይቤሪያ፣ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን፣ በኮትዲቯር፣ በብሩንዲ፣ በሩዋንዳና ከሶማሊያ ቀጥሎ አሁን ላይ ደርሷል። በዚህም በግጭት ውስጥ ለነበሩ እና ላሉ የአፍሪካ ሀገራት የእፎይታ ምንጭ ሆናለች።

የሀገሪቱ ሠራዊት በተሰማራበት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ከፍ ባለ ወታደራዊ ዲሲፕሊን የተሰጠውን ግዳጅ በስኬት በማጠናቀቅ የሚታወቅ ፣በሰላም እጦት የዕለት ተዕለት ሕይወታቸው የተዘበራረቀባቸውን በግዳጅ አካባቢ የሚኖሩ ሕዝቦችን ህይወት በማረጋጋትም ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው ነው ። ይህ ሕዝባዊ ባህሪው በሄደበት ሁሉ ስኬታማ እና ተመራጭ አድርጎታል።

በተለይም በአፍሪካ የሰላም ማስከበር ተልእኮዎች፣ የአፍሪካውያን ወንድሞቹን የሰላም ዕጦት ፣የሰላም እጦቱ የፈጠረውን ችግር በአግባቡ በመረዳት የተሰጠውን ተልዕኮ በአፍሪካዊ ወንድማዊነት መንፈስ በመከወን በብዙዎች ሕሊና ውስጥ ሊፋቅ የማይችል ወገናዊነት መፍጠር ችሏል፤ የግጭት ቀጣናዎችን በአጭር ጊዜ በማረጋጋትም ተጠቃሽ ሆኗል።

ሠራዊቱ ከፍ ያለ ጀግንነት እና የሕይወት መስዋእትነት በሚጠይቁ የሰላም ማስከበር ተልእኮዎች ፣ ግዳጆችን በልበ ሙሉነት በመፈጸም ዓለም አቀፍ እውቅና የተቸረው ነው። ለገዛ ህይወቱ ሳይሰስት ለተልእኮው ያለውን ታማኝነት በተጨባጭ የሕይወት መስዋእትነት በመሆን ችሏል።

በተለይም በጎረቤት ሶማሊያ አልሸባብ እና ሌሎች ጽንፈኛ ኃይሎች ከቁጥጥር ውጪ ሆነው ለአካባቢው ፤ከዚያም አልፎ ለዓለም ስጋት በሆኑበት ወቅት ፤ወንድም የሆነውን የሶማሊያ ሕዝብ ከእነዚህ ኃይሎች ለመታደግ ከፍ ባለ ወታደራዊ ብቃት እና ጀግንነት በመንቀሳቀስ አኩሪ ታሪክ ፈጽመዋል። በዚህም ከሶማሊያ ሕዝብ ለዘላለም የሚታወስ ከፍተኛ ከበሬታ አትርፎለታል።

አስቸጋሪ የሰላም ማስከበር ተልእኮዎችን በስኬት የመፈጸም ብቃቱ ሕዝባዊ ከሆነው ባህሪው ጋር ተዳምሮ የሶማሊያ ሕዝብ የሰላም አየር እንዲተነፍስ ፣ የእለት ተእለት ህይወቱን አንጻራዊ በሆነ ሰላም ውስጥ እንዲመራ ትልቅ አቅም ሆኖት ቆይቷል። የክፉ ቀን ወዳጅ በመባልም በሕዝቡ ዘንድ እውቅና አግኝቷል። ዛሬ አንዳንድ የሶማሊያ ባለስልጣኖች የኢትዮጵያን ውለታ ለማንኳሰስ ቢሞከርም የሶማሊያ ሕዝብ አስተዋይ ነውና ያተረፈላቸው ትዝብት ብቻ ሆኗል።

በቀጣይ በሶማሊያ ሊከናወን በታቀደው የሰላም ማስከበር ተልእኮዎች ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መሳተፍ ወሳኝ ስለመሆኑ፤ያለ ኢትዮጵያ ተሳትፎ ተልዕኮው ውጤታማ መሆን እንደማይችል የአብዛኞቹ እምነት የሆነውም ከዚህ ከሠራዊቱ ተልዕኮ የመፈጸም ብቃት እና ሕዝባዊነት የመነጨ ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ።

ሰሞኑን የመከላከያ ሠራዊቱ በደቡብ ሱዳን የሰላም ማስከበር ተልእኮ ግዳጁን በላቀ ብቃት እየተወጣ ስለመሆኑ በተባበሩት መንግሥታት በኩል እውቅና ማግኘቱም፤ ከዚሁ ወታደራዊ ብቃቱ እና ሕዝባዊነቱ የመነጨ ነው። እውቅናው ከዚህም ባለፈ ለአፍሪካውያን ወንድሞቹ ዘላቂ ሰላም መስፈን ያለውን ቁርጠኝነት በተጨባጭ ያመላከተ ነው።

ይህ የሠራዊቱ የጀግንነት እና ሕዝባዊ ባህሪ በአጋጣሚ የተፈጠረ ሳይሆን፤በኮሪያ ልሳነ ምድር የሰላም ማስከበር ተልእኮ ተጀምሮ እስከዛሬ የዘለቀ፣በተለያዩ ሀገራት በተሳተፉባቸው የሰላም ማስከበር ተልእኮዎች በተጨባጭ የታየ ፣ በሀገራቱ ሕዝቦች ምስክርነት የተረጋገጠ የአደባባይ ምስጢር ነው!

አዲስ ዘመን ኅዳር 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You