ከቨርቹዋል ጓደኛዬ

ከአንድ ዓመት በፊት ይፋ በሆነው በእዚህ ጥናት ማህበራዊ ሚዲያን እየተጠቀሙ ያሉ ሰዎች ቁጥር ወደ አምስት ቢሊዮን ከፍ ማለቱን ይፋ አድርጓል።ይህ ቁጥር የዓለምን ሕዝብ 62.3 በመቶ ይሆናል። ጥናቱ ያወጡት የሞኒተሪንግ ኩባንያው ‘መልቲወተር’ እና ‘ዊአር ሶሺያል’ ሚዲያ ኤጀንሲ ሲሆኑ ባለፈው ዓመት የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ቁጥር 5.6 በመቶ አድጓል፤ ይህም የዓለም ሕዝብ ቁጥር ካደገበት 0.9 በመቶ ይበልጣል።

ኤኤፍፒ እንደዘገበው፤ የሜታው ፌስቡክ 2.19 ቢሊዮን ተከታዮች አንደኛ ደረጃ ይዟል። ሌላኛው በሜታ ስር የሚተዳደረው ኢንስታግራም ደግሞ 1.65 ቢሊዮን ተከታዮች በማፍራት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ባለቤትነቱ የቻይናው ባይቲዳንስ የሆነው የአጭር ቪዲዮ ማጋሪያ የሆነው ቲክቶክ በ1.56 ቢሊዮን ተከታዮች ሦስተኛነት ይከተላል። እዚህ ላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ እነ ዩቲውብ፣ ቴሌግራም፣ኋትስአፕ፣ኤክስ፣ሊንክዲን እና ሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች ባለ ሁለት ስለት ወይም አፍ ሰይፎች ናቸው።

አዎ ለሰናይ ተግባር ወይም ለጥፋት ልንጠቀምባቸው እንችላለን። የምናየውም የምንሰማውም ይሄንኑ ነው። ጥላቻን የሚቀፈቅፉም፣ ፍቅርን የሚሰብኩም፣ሀሰተኛ መረጃ የሚነዙም፣በሀቀኛ መረጃ ሀሰተኛ መረጃን የሚያጋልጡም፣የሰዎችን አካውንት ሰርስረው ገብተው ወይም አታለው የሚዘርፉትም፣ሆነ ለሰዎች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩትም፣ለተቸገሩ ሰዎቸ ገንዘብ ከተከታዮቻቸው አሰባስበው የሚረዱትም ሆነ ለእርዳታ የተሰበሰበን ገንዘብ ቅርጥፍ አድርገው የሚበሉት፣ ቅስምን የሚሰብሩም ሆነ የተሰበረን ቅስም ወጌሻ ሆነው የሚጠግኑምአሉ።

በማህበራዊ ሚዲያ ሱስና በሌላ ጠንቅ ብዙዎች ለድብርትና ለሞት ቢዳረጉም፤ይሄን ሚዲያ ተጠቅመው ሕይወታቸውን የቀየሩም ወዘተረፈ በእዚህ ማህበራዊ ሚዲያው አሉ። በተለይ በሕይወት ልምድ፣በሥራ፣በንባብ ያገኙትን ዕውቀት ያለ ምንም ስስት የሚያካፍሉ ቀልቤን ይገዙታል። ፌስቡክ ካስተዋወቀኝ ቨርቹዋል ወዳጆቼ ጥልቅ አንባቢ የሆነው የመጽሐፍ ብል ወይም ቡክወርም አሳፍ ሀይሉ ቀዳሚው ነው ያነበባቸውን መጽሐፍት እየገመገመ ለወዳጆቹ ያደርሳል።

ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ እኔም ለቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሕጻናት ጋዜጣ ቢጀመር እንዲሁም መጽሐፍት የሚገመገሙበት ቋሚ አምድ በአዲስ ዘመንና በሄራልድ እንዲኖር ሃሳብ አቅርቤ ነበር። አዲሱ አመራር የልጆችን መጽሔት “ብላቴናት”ብለው ሲያስጀምሩ በወቅቱ ግጥምጥሞሹ አስገርሞኝ ነበር።

የኢዜአው ሀብታሙ አክሊሉ ደግሞ ማህበራዊ ሚዲያ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት ከሚያስችሉ እሴቶች ውስጥ አንዱ የሆነውን ሃሳብን በነፃነት የማንሸራሸር ዕድልን ያመቻቻል። ባለን የማህበራዊ ሚዲያ አካውንት ካለንበት ቦታ ሆነን የትኛውንም ሃሳብ የመግለፅ ነጸነትን ያጎናፅፈናል። ማንኛውንም አይነት ይዘት ያላቸው መረጃዎችን ለበርካታ ተከታዮቻችን በተመጠነ ዋጋና በፈጠነ ለማስተላለፍም የማህበራዊ ሚዲያ ሚና የጎላ ነው። ለእዚህም ነው እንግዲህ ማህበራዊ ሚዲያ ሃሳብን በነፃነት በማንሸራሸር ለዲሞክራሲ ሥርዓት መገንባት ሰፊ ሚናን ይጫወታል የሚባለው።

ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ አላማ ከተጠቀምንበት ፈርጀ ብዙ ችግሮችን በመቅረፍ የማህበረሰብ ለማህበረሰብ ግንኙነቶችን ልናጠናክርበት እንችላለን። በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻችን ውስጥ የሚገጥሙንን ፈታኝ ሁኔታዎች ለመሻገር የሚያስችሉ መላዎችን ማህበራዊ ሚዲያ ሊጠቁመን ይችላል። ኅልቆ መሳፍርት የሌላቸውን ማህበራዊ ጉዳዮች በማህበራዊ ሚዲያ አማካይነት ለማከናወን እንችላለን። ማህበራዊ ሚዲያን ሃዘን የገጠማቸውን ለማፅናናት፤ በደስታ ውስጥ የሚገኙትን ደስታቸውን ለመጋራት፣ የታመሙትን ለማበርታት ብሎም ሌሎችን በማስተባበር ከሕመማቸው እንዲያገግሙ ለማድረግ፣ የተቸገሩትን ለመርዳት ወዘተ ጥቅም ላይ ልናውለው እንችላለን። አሁንም በርካቶች እያደረጉት የሚገኘው ይህንኑ ነው።

ሰዎች የማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ቢዝነሶቻቸውን ያሳድጉበታል፤ የተሻሉ የሥራ ዕድሎችን ያመቻቹበታል። ከተለያዩ ደንበኞቻቸው ጋር ይተዋወቁበታል፤ አልፎ ተርፎም በዕለታዊ የቢዝነስ እንቅስቃሴዎቻቸው ዙሪያ ይመክሩበታል፤ ይዘክሩበታል። በማህበራዊ ሚዲያ አማካይነት በሚፈጠሩ የቢዝነስ አማራጮች ማደግ ሳቢያም ዜጎች ዘርፈ ብዙ የሥራ ዕድሎች ይፈጠርላቸዋል። እግረ መንገዱንም መንግሥት የሥራ አጥ ቁጥሩን ከመቀነስ ባሻገር ምጣኔ ሀብቱንም በጠንካራ መሠረት ላይ ሊገነባ ይችላል።

እነዚህ ቀደም ብለን የጠቃቀስናቸው አብነቶች ወደ ተቋማት ሲመጡም ጠቀሜታቸው እምብዛም የተለየ አይደለም። በተለይ የመንግሥት ተቋማት የማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም አገልግሎት አሰጣጣቸውን በማሳለጥ በሕዝብ የሚቀርብባቸውን ቅሬታ ለመቀነስ ሊጠቀሙበት ይችላሉ። የመንግሥት ተቋማት ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የአገልግሎት አሰጣጣቸውን ሁኔታ የተመለከቱ መረጃዎችን በመሰብሰብ ግብረ መልስ ሊያጠናቅሩበት፣ የተገልጋያቸውን አመለካከት በአዎንታዊ መሠረት ላይ ለመገንባት የሚያስችል ግንዛቤን ለመፍጠር፣ ውስን በሆነ ሀብት በርካታ ተግባራትን ለማከናወን ሠራተኞቻቸውን ሲያነቃቁበት ታይቷል።

በአገልግሎት አሰጣጣቸው ዙሪያ የሚሰጡ አስተያየቶችን በመሰብሰብ ለመተንተን እንዲሁም አገልግሎት አሰጣጣቸውን የደንበኞቻቸውን ቅሬታ መሠረት አድርገው ይፈቱበታል። ተቋማት በቀውስ ጊዜ ላይ በሚገኙበት ወቅትም የተለያዩ ሃሳቦችን በማንሸራሸር ከቀውስ ውስጥ ለመውጣት ማህበራዊ ሚዲያ አይነተኛ ሚና አለው። ይህንኑ ጉዳይ ከግንዛቤ አስገብተው ይመስላል በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ የመንግሥት ተቋማት የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች እየሆኑ ነው፤ ምንም እንኳ ተቋማቱ ማህበራዊ ሚዲያን ውጤታማ በሆነ መልኩ ስለመጠቀማቸው ጥናት ማድረግን የሚጠይቅ ቢሆንም። ወደ ተነሳሁበት ስመለስ ለዛሬ “ጥቂት ቆይታ ከናሲም ኒኮላስ ታሌብ ጋ፤” የሚለውን የቨርቹዋል ወዳጄን አሳፍ ሀይሉ የመጽሐፍ ግምገማ ላጋራችሁ ወደድሁ።

ታሪክን የሚነዱትና፣ ታሪክ ብለን የምንጠራውን ነገር የሚፈጥሩት በአብዛኛው የታሰበባቸውና በዕቅድ የተከናወኑ ነገሮች ሳይሆኑ፣ የአጋጣሚ ነገሮች ናቸው ይለናል። ዛሬ የሆነ ታሪክ እየተከናወነ፣ ነገ በእርግጠኝነት እንዲህ ነው የሚሆነው ብሎ መናገር የሚችል ማንም የለም። ሁሉንም ታሪክ ተብሎ የሚነገረንን ነገር ምክንያትና ውጤት አበጅተው፣ ለጆሮ አጣፍጠው የሚነግሩን፣ ነገሩ ከሆነ በኋላ ወደኋላ ተመልሰው ለነገሩ ሰበብ ይሆናሉ የሚባሉ ነገሮችን የሰበሰቡ ተራኪዎች ናቸው። በወቅቱ ግን ምንም ሊናገሩ የማይችሉ ናቸው።

ታሪክ የአጋጣሚ ውሳኔዎችና ድርጊቶች፣ የተለያዩ ሰዎች ነሲባዊ ፍላጎቶችና ምኞቶች ውጤት እንጂ coherent የሆነ የሚመራበት principle የለውም! ስለሆነም ከታሪክ የምንማረው ምንም ነገር የለም ይላል። ይሄ በምጡቅ አስተሳሰቦቹ በዓለም አድናቆትን ያተረፈ፣ ትውልደ ሊባኖሳዊ በዜግነት አሜሪካዊ የማቲማቲክስና ስታቲስቲክስ ምሁር፣ እና የስቶክ (de­rivatives) ንግዶች ኤክስፐርትና ባለፀጋ ደራሲ ዶ/ር ናሲም ኒኮላስ ታሌብ ነው።

የመጽሐፉ ርዕስ የሆነው “Black Swan” ምንድነው? “ስዋን” የሚባሉት እነዚህ አንገተ ረዣዥሞቹ፣ ቅርፃቸው ትልልቅ ዳክዬና ፍላሚንጎ የመሠሉት፣ የምዕራቡ ዓለም ተወዳጅ ግዙፍ የወፍ ዝርዮች ናቸው። በምዕራቡ ዓለም ለመቶዎች ዓመታት ነጫጭ ስዋኖች (white swans) ብቻ ናቸው በምድር ላይ ያሉት ተብሎ ይታመን ነበር። በእነሱም ላይ ለመቶዎች ዓመታት ያልተደረገ ጥናት አልነበረም።

በመሐል ግን በ1900ዎቹ መባቻ ገደማ ካሉት ዓመቶች በአንዱ፣ በድንገት አውስትራሊያ ውስጥ አንድ Black Swan ተገኘ። ዓለም ጉድ አለ። እስከዛሬ የያዝነው ሳይንስና ቲዎሪ ሁሉ ፉርሽ ሆነ አለ። የአንድ ጥቁር ወፍ መገኘት፣ ለ300 ዓመት የተደረገውን የሰውልጅ ሳይንስና ታሪክ ሁሉ በዜሮ አባዝቶት ቁጭ አለ። ናሲም ታሌብ የሰው ልጅ ታሪክ ሁሉ ልክ እንደ Black Swan ነው ይለናል።

ይቺ ሀገር በታሪክ ሁሉ ያልተደፈረች ሀገር ነች ተብሎ መዓት ሺህ ታሪክ ይፃፋል። ፈረንሳዮች ስለገነቡት ማጊኖት ላይን ስለተባለ የድንበር መከለያ ግንብ ብዙ ይተነትናል። ያንን ግንብ ፈረንሳዮቹ የገነቡት በታሪክ ከጀርመኖች በተደጋጋሚ ጥቃት የመጣባቸውን አቅጣጫ አጥንተው ደርሰውበት፣ የወደፊት ወረራን ለዘለዓለሙ ለማምከን ነበር። ግንሳ?

ሒትለርንና ሙሉ በሙሉ ብረት ለበስ የሆነውን የእነ ሄንዝ ጉደሪያንን ታንከኛ ፓንዘር ዲቪዥኖች፣ Blitzkrieg (መብረቃዊ ጥቃት) ከነተባለው የጥቃት ስልት ጋር አዘዘባቸው። በፈረንሳዮቹ በማጊኖት ላይ ተማምነው ቁጭ ብለዋል። ዝግጅት አላደረጉም። ሒትለር በታሪክ ገጥሟቸው ከማያውቅ አቅጣጫ መጥቶ፣ ማጊኖታቸውን ደረማምሶ፣ ፓሪስ ገባ። ብዙዎቹ የሆነውን እያዩም፣ አምነው መቀበል አልቻሉም ነበር ይለናል። ከታሪክ የምንማረው ምንም ነገር የለም ይለናል። የሒትለር ጥቃት ለፈረንሳዮች እንደ Black Swan ነበር ይለናል። በቃ የሆነ ነገር ይመጣና፣ የያዝከውን ሁሉ ያስጥልሃል። የምታውቀው የመሰለህ ሁሉ አዲስ ሆኖ ይቀጥላል።

አውሮፓ ሠለጠነች፣ በሰው ልጅ የእድገት ታሪክ እርስ በርስ የሚበላሉት ያልሠለጠኑ ኋላቀር ሕዝቦች ናቸው እየተባለ በቴክስት ቡኮች ሁሉ ሰፍሮ ትውልዶች ተማሩበት። ኮሩበት። ስለ አውሮፓ ሥልጣኔ እየተጋነነ ተነዛ። በኋላስ ? በ20ኛው ክፍለ ዘመን በመሐል አውሮፓ ላይ፣ 5 ሚሊዮን አይሁዶችን ወይም ጂዊሾችን ሥጋቸውን በፋብሪካ እያነደደ፣ በሞራቸው ሳሙና የሚሠራበት የሰው ልጆች ጭራቅ ተከሰተ። የዓለም ጦርነት ተለኩሶ በሰው ልጆች አጠቃላይ ታሪክ ያልታየ የሚሊዮኖች ሞት ተመዘገበ። በዓለም ታሪክ ያልታየ የኒውክሌር ቦምብ ከተሞችን ከነመቶ ሺህዎች ነዋሪዎቻቸው እንደ ቅቤ አቀለጣቸው። እንዴ? አውሮፓ አልሠለጠነም ማለት ነው? የተማርነው ታሪክስ ? ምሁሮቻችን ያጠኑልን ሳይንስስ? በቃ black Swan መጣበታ። ፉርሽ ሆነ። በዜሮ ተባዛ።

ብዙው የሰው ልጅ ሥልጣኔ ቱሩፋት የምንለው ግኝትም በአጋጣሚ የተገኘ ነው ይለናል ናሲም ታሌብ። ፔኒሲሊን በአጋጣሚ የተወለደ ነው። መኪናና ሞተር በአጋጣሚ። አውሮፕላን በአጋጣሚ። ደማሚት ፈንጂ በአጋጣሚ። ሬዲዮና ስልክ በአጋጣሚ። ሁሉም ነገር በአጋጣሚ ይፈጠርና የነበረውን ነገር ሁሉ አጥፍቶ እንደ አዲስ ሌላ ታሪክ ያስጀምራል ይለናል። ለምሳሌ የሞባይል ስልክ ከመምጣቱ በፊት የእጅ ሰዓት ትልቅ ቢዝነስ ነበር፤ ትልልቅ የሰዓት ሠሪ ኢንዱስትሪዎችም ነበሩ። ከእዚያ ሞባይል ስልክ ላይ ሰዓት መጣልን። የሰዓት አምራቾች ሁሉ ለዘመናት ከቆዩበት የሰዓት ቢዝነስ ባንዴ ዘጭ ብለው ከሠሩ ብዙዎቹ ሥራ ቀየሩ። ይህን ማን አስቦት ነበር? ብሎ ይጠይቃል ናሲም። ከየትኛው ታሪክ ነው የምንማረው ይህንን? በቃ የሞባይል ቴክኖሎጂ እንደ Black Swan ሆኖ ከች አለ! እና የዓለምን ታሪክ ቀየረው።

ከታሪክ የምንማረው ከታሪክ አለመማራችንን ብቻ አይደለም ይላል ናሲም ኒኮላስ ታሌብ። ዓለምንና ሰዎቿን (ሁሉንም ፍጡራን) የሚገዛው አንድ እርግጠኛ የሆነ የተፈጥሮ ሕግ ካለ፣ እሱ the law of uncer­tainty ነው ይለናል። በአንድ ነገር ብቻ እርግጠኛ ሆነን መናገር እንችላለን ይላል። በእዚህች ምድር ላይ በምንም ነገር እርግጠኞች መሆን እንደማንችል ያትታል። ይሞግታል።

ከታሪክ የምንማረው ብቸኛ ነገር ካለ ይሄ ነው ይላል! እርግጠኛ ካለመሆን ታሪክ ደግሞ ምንም ትምህርት ሊወሰድበት አይችልም! ሁሉም ሳይንሶችና ሳይንቲስቶች ግን ይሄንን አይነግሩንም።ኒውተን ያገኘውን የፊዚክስ መሠረት የሆነ የሣይንስ ፎርሙላ፣ ከመቶዎች ዓመት በኋላ አልበርት አንስታይን መጣና በዜሮ አባዛው። የአልበርት አንስታይን ሪሌቲቪቲ ብላክ ስዋን ነው ለሣይንሱ። ሳይንቲስቶቹ ግን ይህን ከማመን ይልቅ የቀደመውን የሚቃረን አዲስ ነገር ሲመጣባቸው “ግኝት” (discovery) የሚል የዳቦ ስም ያወጡለትና ራሳቸውን ያታልላሉ ይለናል።

የናሲብ ታሌብ ሃሳቦች ብዙ ናቸው። እጅግ አነጋጋሪ፣ አከራካሪና አስገራሚም ናቸው። በእዚህ ዘመን እንደ እነ ኩንዴራና ዩቫል ሐረሪ ሁሉ፣ በምጡቅ ሃሳቦቹ የሚታወቀው ይህ ሰው፣ ብዙ የሚገራርሙ ሃሳቦች አሉት። ሙሉ በሙሉ ባትቀበለው እንኳ፣ የሆነ አሳማኝ ነጥብ ግን እንዳለው ትገነዘባለህ። አለመደመም አትችልም። ተነባቢ፣ ተደማጭና ተፅዕኖ አሳራፊም የሆነው በአዚሁ የተነሳ ይመስለኛል።

በእርግጥ ከታሪክ የምንማረው የተወሰነማ ነገር መኖር አለበት። የሰው ልጅ ያለፈበትን ሁሉ ስለሚደግመው አይደለም ታሪክ የምናጠናው። እንዳይደግመውም ጭምር ነው። ለምሳሌ ዩቫል ኖህ ሐረሪ የሰው ልጅ ከእርሱ በላይ የመጠቁ የሌላ ዓለም ፍጡራን መኖርና አለመኖር ለምን ያስጨንቀዋል? ለምንስ የማይታወቁ በራሪ አካላትን (UFOዎችን) ለማጥናት ቢሊዮንና ትሪሊዮን ዶላሮች ይከሰክሳሉ ኃያላኑ? ብሎ ይጠይቅና መልሱን ይሰጠናል። ምክንያቱም የሰው ልጅ በታሪኩ እርሱ ከሌሎች የምድሪቱ ፍጡራን የመጠቀ ጭንቅላት ስላለው በሌሎቹ ፍጡራን ላይ ያደረገውን ክፋት ስለሚያውቀው ነው ይላል። እና ከእርሱ የበለጠ ጭንቅላት ያለው ፍጡር ከመጣበት፣ በሌሎቹ ላይ ያደረገውን ነገር፣ ዩፎዎቹም በእኛ ላይ ይፈፅሙብናል ብሎ ስለሚፈራ ነው ይለናል። ከእኛ የበለጠ ጭንቅላት ያላቸው ፍጡራን ወደምድር ከመጡ፣ ለምሣሌ ዘራችንን እያረቡ አርደው ሊበሉን፣ በየሆቴሉ የሰው ሬሲፔ እያስቀመጡ በእኛ አካል ሊዝናኑብን ይችላሉ። ልክ እኛ ከብቶችንና ዶሮዎችን እንደምናደርገው። ወይ ደሞ ለሳይንሳዊ ላብራቶሪዎቻቸው መሞከሪያ ሊያደርጉን ይችላሉ።

ልክ እኛ አይጦችንና ዝንጀሮዎችን እንደምናደርገው ማለት ነው። ወይ ጠምደው ሊያርሱብን፣ ወይ በስፖርት እያወዳደሩ ሊደሰቱብን፣ ወይ ለመስዋዕታቸው ሊያርዱን፣ ወይ የአካል ክፍሎቻቸው አልሠራ ሲላቸው የእኛን ኩላሊትና ልብ እየነቀሉ እንደ ስፔር ፓርት ሊጠቀሙብን ይችላሉ። ልክ እኛ በአሳሞች ላይ እንደምናደርገው ማለት ነው። ወይ zoo ውስጥ ከትተውን ልጆቻቸውን ይዘው እየመጡ ሊጎበኙንና እኛን እየቀረፁ የሕጻናት ፊልም ሊሠሩብንም ይችላሉ። በአጠቃላይ የሰው ልጅ ከሌሎቹ እንስሳት የበለጠ ጭንቅላት ስላለው በሌሎቹ እንስሳት ላይ ያደረጋቸውን ነገሮች በሞላ፣ ዩፎዎቹም ከሰው የበለጠ ጭንቅላት ካላቸው፣ በእኛ ላይ ሊያደርጉብን ይችላሉ ብሎ መስጋቱ ነው ሌት ተቀን ዩፎዎችን በምድርና በማርስ ላይ የሚያፈላልገው ይለናል ኖህ ሐረሪ።

ስለሆነም የአሁን ሥራዎቻችንና የወደፊት ዕቅዶቻችን፣ቴክኖሎጂዎቻችን፣ የነገ አካሄዳችን ሁሉ ያሳለፍነውን ታሪክ ታሳቢ አድርጎ የሚራመድ ነው። እና ታሪክን ማጥናት፣ አሁን ያለውን ብቻ ሳይሆን የነገ መዳረሻችንንም ያሳየናል ባይ ነው የጥንት ታሪክ ምሁሩ ፕ/ር ዩቫል ኖህ ሐረሪ። ታዲያ እንዲህ የመሰለውን ጠንካራ ክርክር (argument) ከታሪክ እርግጠኛ ያለመሆንን ካልሆነ በቀር ምንም አንማርም የሚለው ናሲብ ታሌብ እንዴት ያየዋል?አላውቅም።

ልብ ብሎ ማየት ግን ይጠበቅበታል።ናሲብ ታሌብ አንድ ቦታ ምን ይላል? በዓለም ላይ ያለ ሳይንስ ሁሉ የየራሱን black swan የሚጠባበቅ በምሁራን የተደረተ ቁጩ ነው ይልና፣ ምናልባት ለእውነቱ የሚጠጋጋ አንድ ብቸኛ ምድራዊ ሳይንስ ጥቀስ ካልከኝ ስታቲስቲክስ ብቻ ነው ይላል።ስታቲስቲክስ የነገሮችን አካሄድና አዝማሚያ ብቻ ነው የሚያሳይህ። ብዙው ድርጊታችን በምን ዙሪያ እንዳተኮረ ይነግርሃል።

በእዚህ በኩል ከሌሎች ሳይንሶች ይሻላል። ግን እሱም ቢሆን ስላለፈው እንጂ ስለወደፊቱም ሆነ ስለዛሬው በእርግጠኝነት የሚነግርህ ምንም ነገር የለም ይላል። እና እሺ ታሪክን ካላመንን፣ ሳይንስን ካላመንን፣ የእግዜርንም የተስፋ ቃል ካላመንን… ምንን እመኑ ነው የሚለን ይሄ ሰውዬ? የሚል ጥያቄ ይመጣብሃል። መልሱ ቀላል ነው። እርግጠኛ አለመሆንን ብቻ እመነውና ከጭንቀቶችህ ሁሉ ነፃ ውጣ ባይ ነው።Anything can happen, everything is possible, and don’t bother yourself to know so much about any­thing. Just live your life and enjoy this life while you’re alive ! ዓይነት ነው ፍልስፍናው።

በምንም ነገር ላይ ከመጠን በላይ አትጨናነቅ። እኔ ሦስት ዓመት እሠራና አንድ ዓመት አርፋለሁ ይላል። ምክንያቱም በአንድ ዓመቷ ደግሞ ያመለጠኝን ማንበብ፣ መጻፍ ስለምፈልግ። አለበለዚያ ይሄን ምኞቴን ሳላሳካው በሥራ እንደተጠመድኩ እኮ በእዚያው በአንዱ ቀን ልምርሽ እችል ነበር። ይልሃል። ጓደኞቼ አሪፍ አሪፍ ቤት ሠርተዋል ይልሃል። ይመቻቸው። እኔ ደሞ አሪፍ አሪፍ ስቶሪዎቼን ኮምኩሜያለሁ ይላል። ይመቸኝ። የማናችን ነው ልክ? ከታሪክ የምንማረው ምንድነው? ይላል።

ሁላችንም ወደእዚያኛው ይዘን የምንሄደው ነገር የለም። ሁሉንም ጥለነው ነው የምንሄደው። መቼ እንደምንሄድም አናውቀውም።ከሆነ ታዲያ፣ ለምን አሁን እርግጠኛ በሆነው በተሰጠን ሰዓት ደስ ያለንን አድርገን፣ ሆነን፣ አስበን፣ ፅፈን፣ ተናግረንና እስክስታ ወርደን አንኖረውም ሕይወታችንን? የሚል አንድምታ አለው አባባሉ። ግን ደራሲው የሚያነሳቸውን ሺህ ሃሳቦቹን አጠቃልሎ በእዚህ ብቻ መደምደም፣ ፍርደ ገምድልነት ይመስለኛል። የሚናገረው ብዙ ነው። ብዙ አስደማሚ ቁምነገሮችም አሉት። ለዛሬው እዚሁ ላይ ብንሰነባበትስ፤

ሻሎም !

አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 10 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You