ከኢትዮጵያ ታምርት-የኢትዮጵያ ትርፍ!

የአንድ ሀገር እድገት የሚለካው ኢንዱስትሪው ባለበት የእድገት ደረጃና ለኢንዱስትሪ ባለው ምቹ ሁኔታዎች ነው። ዛሬ ላይ ያደጉ ሀገራት ተብለው የተለዩት በኢንዱስትሪው ዘርፍ የበለጸጉት ናቸው። በተመሳሳይ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ተብለው የተቀመጡትም በኢንዱስትሪው መስክ እያስመዘገቡት ባለው ውጤት ነው።

ኢትዮጵያ ለኢንዱስትሪ ምቹ ሁኔታዎች ካሉባት ሀገር መካከል አንዷ ናት። የሀገሪቱ ግዙፍ የአምራች ኃይል አቅም፣ ተፈጥሯዊ ሀብት እንዲሁም አመቺ ሕጋዊ ማሕቀፎች ለዘርፉ እድገት አወንታዊ አስተዋጽኦ ከሚያበረክቱ መልካም አጋጣሚዎችና አስቻይ ሁኔታዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

ነገር ግን ኢትዮጵያ የተቸራትን የተፈጥሮ ሀብት ወደ ሥራ በመቀየር የዜጎቿን የኑሮ ሁኔታና የሀገሪቱን ክፍለ ኢኮኖሚ ማሳደግ ካልቻሉ ሀገራት መካከል አንዷ ሆና ትጠቀሳለች። ሀገሪቱ ለኢንዱስትሪ ያላትን ምቹ ሁኔታ በአግባቡ አልተጠቀመችም ፡፡ ለዚህም በምክንያትነት የሚጠቀሱ በዓይነትም ሆነ በብዛት በርካታ የሚባሉ የዘርፉ ችግሮች አሉ።

በዘርፉ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ተገቢውን ትኩረት አለመስጠቱ፣ የሥራ ባሕል ደካማነት እንዲሁም ዘርፉን ለማበረታታት የሚወጡ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች በአግባቡ አለመተግበር ዘርፉን ተብትበው ከያዙ ችግሮች መሀል ተጠቃሾች ናቸው። ለችግሮቹ ስትራቴጀክ መፍትሄ አስቀምጦ መንቀሳቀስ ከተቻለ ግን ችግሩ ዘላቂ እንደማይሆን ይታመናል።

አሁን ላይ ዘርፉን ለማነቃቃት የተለያዩ ሥትራቴጂክ የመፍትሄ ሀሳቦች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው፤ ከነዚህ መሀልም የ”ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ” ተጠቃሽ ነው። የንቅናቄው ዋና ዋና ዓላማዎች የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች በጋራ በመፍታት ለዘርፉ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር፤ ዘርፉ ለኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ ማስቻል፤ በዘርፉ ያለውን የሥራ ባሕል ማሻሻል እንዲሁም የኢንዱስትሪ ምርቶችን ጥራትና ተወዳዳሪነት በማሻሻል ገቢ ምርቶችን የመተካት ሽፋንን ማሳደግ ናቸው።

ንቅናቄው በ2014 ዓ.ም ሲጀመር ዓለም አቀፋዊ እና ሀገራዊ ተግዳሮቶቹ ቀላል የሚባሉ አልነበሩም። የኮቪድ 19 መከሰትን ጨምሮ የምርት ግብዓት ምንጭ በሆኑት ራሺያና ዩክሬን መካከል የተነሳው ጦርነት፤ ሀገር ውስጥ ከነበረው ግጭት ጋር ተዳምሮ ሁኔታውን ፈታኝ አድርጎት ነበር። በውጫዊና በውስጣዊ ፈተናዎች ታጅቦ የተጀመረው ንቅናቄ ግን በሦስት ዓመታት በርካታ ሥራዎችን ማከናወን ችሏል። በዚህም ታላላቅ የሚባሉ ውጤቶች መመዝገብ ተችሏል።

የመጀመሪያውና እንደ ትልቅ ውጤት የሚነሳው አደረጃጀቱ ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እስከ ክልል ከተማ መስተዳደር ያሉ አደረጃጀቶች ተናባቢ እንዲሆኑ ሲሠራ ቆይቷል። ከፌዴራሉ አደረጃጀት ጋርም ተመሳሳይ እንዲሆኑ ተደርጓል።

ሌላው የድጋፍ ፤ የክትትልና በተለይ የኢንዱስትሪ ማኅበረሰቡ ግንዛቤ እንዲፈጥር ከማድረግ ጋር ተያይዞ የተገኘው ውጤት ነው። በንቅናቄው ከፌደራል እስከ ክልል ሰፋፊ ውይይቶች ተካሂደዋል። በዚህም ከውሳኔ ሰጪው ጨምሮ እስከ ዘርፍ ተዋናይ ባለሀብቶች ደጋፊ የሆኑ ተቋማት፤ ድረስ ሰፊ የሚባል ግንዛቤ እንዲፈጠር ተደርጓል።

ይህም በአጭር ጊዜ ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪ ላይ ውሳኔ የሚሰጥበት ሁኔታ እንዲኖር አስችሏል። ቀደም ሲል ይጓተት የነበረው የመሠረተ ልማት አቅርቦት፤ ከመብራት ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዲቀረፉ ከማድረግ አኳያ የንቅናቄው መጀመር አዎንታዊ አስተዋፅዖ አበርክቷል። በተለይ በዘርፉ ሰፊ ክፍተት የነበረበት የመሬት አቅርቦት ችግር እንዲፈታ ለማድረግ አስችሏል።

ለምሳሌ ቀደም ሲል የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች የማምረቻና መሸጫ ቦታ የማቅረብ፤ ለከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች መሬት የማቅረብ ችግሮች እንደነበሩ ተደጋግሞ ሲነሳ ቆይቷል። ንቅናቄው ከተጀመረ ወዲህ ግን 60 ሺ የሚጠጋ ሄክታር መሬት ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዲቀርብ መደረጉን የቅርብ ጊዜ መረጃዎች ያሳያሉ።

በተለያዩ ምክንያቶች ተዘግተው የነበሩ 837 ኢንዱስትሪዎች፣ እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል። ንቅናቄው ከተጀመረ ወዲህ 325 ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ማምረት እንዲጀምሩ ሆኗል። የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተግባራዊነትን ተከትሎ የተደረጉት ማሻሻያዎች የኢንዱስትሪ ዘርፉን የማምረት አቅም አጠቃቀም በማሻሻል፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በማሳደግ፣ ገቢ ምርትን በመተካት ትልቅ አቅም ፈጥሯል፤ እየፈጠረም ይገኛል።

ይህም የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች ‹‹በኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ በመፍታት፤ የኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት በማሻሻል ከፍተኛ ለውጦች እንዲመዘገቡ አስችሏል፡፡ በአሁኑ ግዜም ኢንዱስትሪዎች ገበያ እንዲያገኙ ከማድረግ አኳያ ትልቅ ውጤት መታየት ተችሏል። ‹‹የኢትዮጵያ ታምርት.›› ንቅናቄ መጀመር የሀገር ውስጥ ምርትን ማስፋትና የመጠቀም ባሕልን በማሳደግ ረገድ የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ትልቁን ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

ኤክስፖው በሀገር አቀፍ ደረጃ በዓመት አንድ ጊዜ፤ በክልሎችና እስከ ዞንና ወረዳ ድረስ ይካሄዳል። ይህም ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ልዩ የገበያ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል። በዘንድሮ በጀት ዓመት ‹‹የኢትዮጵያ ታምርት›› ኤክስፖ በክልሎች፣ በዞኖችና በወረዳዎች 94 የንግድ ትርኢቶች ተካሂደዋል። በነዚህ የንግድ ትርኢቶቹ 400 ሚሊዮን ብር የሚገመት ግብይት መፈፀሙንም ከሚኒስቴር መሥሪያቤቱ የተገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ።

በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ታምርት 2017 ኤክስፖ በርካታ አምራቾች ምርቶቻችን ያቀረቡበትና ከ120 ሺህ በላይ ጎብኝዎች የተሳተፉበት ነበር። ኤክስፖው የገበያ ትስስር ከመፍጠር ባሻገር፤ ሕብረተሰቡ በሀገር ውስጥ የተመረቱ ምርቶችን እንዲገዛና እንዲጠቀም እያደረገ ይገኛል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚሉት የሀገር ውስጥ ምርትን የመጠቀም ልምድ እየዳበረ ሲሄድ አምራች ኢንዱስትሪዎች ይበረታታሉ:: በዚህ ረገድ ‹‹የኢትዮጵያ ታምርት ›› ኤክስፖ የሀገር ውስጥ ምርትን የመጠቀም ባሕልን ከማሳደግ አንጻር በጎ ተጽእኖ መፍጠር ችሏል ።

በንቅናቄው ተኪ ምርቶች በሀገር ውስጥ ማምረት ከተጀመረ ወዲህ ሀገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘው ገቢ እያደገ መምጣቱ እንደ ስኬት የሚጠቀስ ጉዳይ ነው። ከዚህ አኳያ በ2015 ዓ.ም የነበረው 543 ሚሊዮን ዶላር ነበር፤ ነገር ግን ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት ከጀመረበት ከ2014 ጀምሮ 2 ነጥብ 98 ቢሊዮን ዶላር ማስቀረት ተችሏል፡፡ 2016 ዓ.ም ላይ 2 ነጥብ 844 ቢሊዮን ዶላር ሀገር ውስጥ እንዲቀር ተደርጓል።

በዘንድሮው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት 3 ቢሊዮን ዶላር ተኪ ምርቶች በሀገር ውስጥ መመረታቸው ይሄንኑ ሐቅ ያረጋግጣል። ሀገራዊ ንቅናቄው ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶችን ማምረት ከማስቻሉም በላይ የኢትዮጵያን የገበያ መዳረሻ በማስፋት ላይ ጭምር ነው። የአምራች ኢንዱስትሪውን የማምረት አቅም በማሳደግ የሥራ እድል በመፍጠር፤ ነገ የተሻለ ለማምረት መሠረትም እየጣለ ይገኛል።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) 3ኛውን ‹‹የኢትዮጵያ ታምርት.›› ኤክስፖ መርቀው ሲከፍቱ እንዳሉት፣ አምራች ኢንዱስትሪዎች የልማት ትስስር ማዕከል በመሆን የኢትዮጵያን የለውጥ ጉዞ እያፋጠኑ ይገኛል። የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄው ከተጀመረ ወዲህ ባሉ ጊዜያት የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከነበረበት 46 በመቶ ወደ 61 በመቶ ማሳደግ ተችሏል፡፡ በንቅናቄው አማካኝነት በሌሎች ዘርፎችም ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ተመዝግበዋል ሲሉም የሀገራዊ ንቅናቄውን ፍሬያማነት ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ አክለው እንዳሉት ; – በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተሰሩት የለውጥ ሥራዎች በአጭር ጊዜ በሀገሪቱ የማምረት አቅም ላይ የታየው ውጤት ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ እንዳላት አመላካች ናቸው። በተለይ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተገኘው ስኬት ፈተናዎችን በመቋቋም ጭምር የተመዘገበ መሆኑን፤ ሥራውም በምን ያህል ቁርጠኝነት እየተሠራ እንደሚገኝ ይጠቁመናል ።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተሠሩ ሥራዎች የአምራች ኢንዱስትሪውን የማምረት አቅም በማሳደግ፣ የሥራ እድል በመፍጠር፤ ነገ የተሻለ ለማምረት መሠረት በመጣል ትልልቅ ውጤቶችን ማግኘት ተችሏል። ይህም ኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ሀገር የማድረግ ሀገራዊ ሕልምን እውን ማድረግ የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ ስለመሆኑ አመላካች ነው ።

ለዚሁ ሃሳብ ማጠናከሪያ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በአንድ መድረክ ላይ የተናገሩትን እናስታውስ። አቶ መላኩ፣ “ ኢትዮጵያ ከማሸለብ ዘመን ወጥታ በዕድገት ጎዳና እንድትጓዝ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እስከ አሁን የተመዘገበው ውጤት ኢትዮጵያን በአምራች ኢንዱስትሪ የበለጸገች ሀገር የማድረግ ሕልማችንን የምናሳካበትን ጊዜ ሩቅ አያደርገውም “ ሲሉ ተናግረዋል። ይህ ሀገራዊውን ሕልም እውን እንዲሆን ፤ በ’ኢትዮጵያ ታምርት’ ንቅናቄ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ የተጀመሩት ሥራዎችብ አጠናክሮ መቀጠል ይገባል።

በንቅናቄው የታየው የተስፋ ብርሃን የበለጠ እንዲፈነጥቅ፤ ሁሉም ባለድርሻ አካል የበኩሉን መወጣት ይኖርበታል። በመንግሥት በኩል የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ለመጨመር የሀይል አቅርቦት፣ የመሬት፣ የሥልጠና፣ የብድር አቅርቦትና ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታት የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ መቀጠል አለበት። መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት በዘርፉ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ቢሮክራሲያዊ አሠራሮችን ማስተካከል ይኖርበታል።

በዘርፉ የተሰማሩ ባለቤቶች ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተፈጠሩላቸውን መልካም አጋጣሚዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ውጤታማ ለመሆን መትጋት ይኖርባቸዋል። ምርቶችንም በጥራትና በብዛት በማምረት በሀገርና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ በመሆን ሀገሪቱ የምትጠብቀውን ዓላማ የማሳካት ድርሻቸውን በአግባቡ መወጣት ይኖርባቸዋል።

ማኅበረሰቡም ኢትዮጵያ ስታመርትና የውጤታ ማነት ጉዟዋን ስትጀምር ‹‹የኢትዮጵያ ምርት በኢትዮጵያዊያን›› በሚል እሳቤ ሲሸመትና በሀገሬው ምርት ሲጠቀምና ሲኮራ ከውጭ ለሚመጣው ዓይኑን ከማማተር በሀገሩ የውስጥ ምርት ላይ ሲያተኩር ያኔ ‹‹የኢትዮጵያ ታምርት›› ንቀናቄ ተልዕኮውን ያሳካል። በዚህ ረገድ የራሳቸውን ምርት በመጠቀም ለውጥ ያመጡ ሀገራት እንደ ቻይና፣ ሕንድና ሲንጋፖር በማደግ ላይ ላለን ለኛ እንደምሳሌ የሚጠቀሱ ሀገራት ናቸው፡፡ ለዚህም ዜጋው የራሱን ምርት በመጠቀም ምን ያህል ለሀገሩ ዕድገት እንደሚቆረቆር ማየት ይቻላል፡፡

በጥቅሉ ኢትዮጵያ በአምራች ዘርፉ የጀመረችው የለውጥ ጉዞ እንዲሳካ በላቡ የሚተጋ ኢንቨስተር፣ ነጋዴ እና ባለ ኢንዱስትሪ ያስፈልጋል። ሆኖም በኢኮኖሚ አሻጥር፣ የሰላም ጠንቅ በመሆን፣ በሙስና፣ በኮንትሮባንድ ሀገርን የሚበድሉ እንዳሉ ይታወቃል። በመሆኑም ኢትዮጵያ እንድታመርት የሚተጉ ባለጸጎችን በእጅጉ ማብዛት እና የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ለማሳካት በሕገወጥ መንገድ የተሠማሩትን ማረም፣ ማስተካከል ይገባል።

በዚህ መልኩ ሁሉም በየዘርፉ ኃላፊነቱን መወጣት ከቻለ፤ የአምራች አንዱስትሪ ዘርፉ ምርትና ምርታማነት ወደሚፈለግበት ደረጃ ያድጋል። የሀገርን ምርት ለራስ ብቻ ከመጠቀም ተሻግሮም ምርትን ወደ ዓለም ገበያ በማስገባት የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት የማረጋገጥ ሕልማችንን እውን ማድረግ ይቻላል።

ዳንኤል ዘነበ

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You