«የእኛም ጥያቄ ነው» ግን ደግሞ… !

ብዙ ሕሙማን በሆስፒታል ውስጥ ተኝተዋል፤ ብዙዎች ደግሞ በተመላላሽ ሕክምና የሆስፒታሎችን ደጅ ይጠናሉ። ከፈጣሪ በታች አዳኝ ብለው የሚያምኑት እንዲሁም የሆኑት የጤና ባለሙያዎቻችንና ሀኪሞቻችን ናቸውና፤ ይሄ እምነት የሁሉም ሰው ነው። አልጋ ይዞ በኦክስጅን ላይ ያለው፤ በቀዶ ሕክምና ከበሽታው ሊላቀቅ ቀጠሮ ይዞ ሕይወቱን ለማዳን የሚጠብቅ ተስፈኛ ታካሚ … ሌላውም ሁሉ ተስፋው በጤና ባለሙያዎች ላይ ነው።

ወላጅ እናቱን፣ አባቱን፣ እህት ወንድሙን፣ ልጁን አሳክሞ ለማዳን፤ የእነሱን ከሕመማቸው መፈወስ የሚናፍቅ ከሕሙማኑ ጋር የሚንገላታው አስታማሚ ቤተሰብ የሀኪሙን በሰዓቱ መምጣት አለመምጣት ይናፍቃል። ደጅ ደጁን ይመለከታል። ሆኖም ሰሞኑን በጤና ባለሙያዎች አካባቢ የተሰሙ ወሬዎች አስደንግጠውታል፤ አደናግረውታል።

ሕመምተኛውንም ሆነ ሌላው ሕብረተሰብ ከጤና ባለሙያዎች ጋር ተያይዞ የተሰሙት የመብት ጥያቄዎች «ትክክል ይሆንም ስህተት» ከመብት ጥያቄው ጎን ለጎን ለመውሰድ የታሰቡት ቀጣይ ርምጃዎች የተባሉት ግን አስደንግጠውታል። እውነቱን ለመናገር እኔም ደንግጫለሁ፤ ተገርሜያለሁ። አሁንም ቢሆን የጤና ባለሙያው በቂ ደመወዝ እየተከፈለው ነው ብዬ አላምንም፤ ክፍያው ዝቅተኛ ነው፤ ክፍያው እንደ ሀገራችን የመክፈል አቅም ነው። ሆኖም ግን ክፍያው ያንሳል የሚለውን እወስዳለሁ፤ ጥያቄያቸው ምላሽ ማግኘት አለበት በሚለውም ሀሳብ እስማማበታለሁ።

ይህንን ስንል ግን አንድ ነገር ደግሞ ከሙያው ጋር አስተሳስሮ ማሰብ ጥሩ ነው። ሁሉም ሰው የሆነ ነገር መሆን ሲመኝ፤ ተምሮ በሆነ ሙያ ላይ ሲሰማራ እርካታው ደመወዝ እንደሚሆን አስቦ ብቻ አይደለም። ውስጣዊ ስሜቱን ለማርካት ጭምር ነው። ሰዎችን ለማገዝና ለማዳን ጭምር ነው። የእነዚህ ሰዎች ደመወዛቸው የአገልገሎት ተቀባዩ እርካታ ነው፤ ከዛ የሚገኘው ምስጋና እና ምርቃት ነው።

የጤና ባለሙያነትን ሙያ የመረጠና የተማረ ባለሙያም ደመወዙን ብቻ አስቦ እንደማይሆን እገነዘባለሁ። ሰውን ማዳን፣ በሞትና በሕይወት መካከል ያለችን ሕይወት መቀጠል፤ የተጨነቁ ሕሙማንና ቤተሰብን ከጭንቀታቸው መገላለገል ነው ትልቁ እርካታ። እስካሁንም የጤና ባለሙያዎቻችን «ደመወዛችን እርካታ ነው» ሲሉ ነው የምሰማው። ያ እርካታ አሁን የት ገባ?፤ የገቡት ሕዝብን የማገልገል ቃል ኪዳን ለምን ተረሳ?፣ ምን አዲስ ነገር መጣ ብዬ ራሴን ለመጠየቅ ተገድጃለሁ።

የደመወዝ ማነሱ የኢኮኖሚ ጫናው ቀደም ብሎም ነበር፤ አሁንም አለ። መብትና ጥቅማጥቅሞቻችን ይከበሩልን የሚለው ጥያቄም ተደጋግሞ ተነስቷል። ይሄንን ማንም አይክድም፤ ለምን ተነሳ ብሎ ቡራ ከረዩ የሚልም አካልም አይኖርም። ነገር ግን ጥያቄው የቀረበበት መንገድ የተሄደበት ርቀት ግን ለጥያቄው ጥያቄ ያነሳል። የጤና ባለሙያውንም ትዝብት ላይ ይጥላል።

የጤና ባለሙያው ለምን የመብት ጥያቄ አነሳ ብሎ ቅሬታ ያሰማና ያቀረበም የለም። ጥያቄው ተገቢ ነው፤ ቀደም ሲልም የጤና ባለሙያው የደመወዝ ፣ የመኖሪያ ቤት፣ የጤና መድህን፣ የዲውቲ (በትርፍ ሰዓት) ክፍያን አስመልክቶ ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል። አንዳንዱ ነገር ዘግይቶም ይሁን በወቅቱ በትክክል ጊዜውን ባላስታውሰውም ምላሽ አግኝቷል።

ለምሳሌ ያህል ሀኪሞች ያላቸው ገቢ አነስተኛ በመሆኑ፣ በመንግሥት ተቋማት ተረጋግተው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በሚል በሆስፒታሉ ውስጥ ከሥራ ሰዓት ውጪ በግል የሕክምና ክንፍ በሚል በተሻለ ክፍያ በመንግሥት ሆስፒታሎች፣ አልጋና የሕክምና መሳሪያዎች ሕክምና መስጠት እንዲችሉ ተደርጓል። ይሄ ይብዛም ይነስም የጤና ባለሙያውን ኢኮኖሚ ለመደገፍ ነው። ይሄ ግን በቂ ላይሆን ይችላል። ሁሉንም የጤና ባለሙያዎች በተጠቃሚነት ላያካትት ይችላል፤ ሆኖም ግን ጅምሮች አሉ የሚለውን መያዝ ይገባል።

የጤና ባለሙያው አሁንም ገቢው በቂ አይደለም፤ ጥያቄያችን አልተመለሰም ብሎ ጥያቄ ማቅረባቸው ተገቢ ነው። ግን ደግሞ ዶክተር ወይም ሀኪም ሲባል ለሙያው የተሰጠው ክብር አለ። በእያንዳንዱ ሰው አእምሮ ውስጥ የተሰጠው ቦታ ትልቅ ነው። በሕብረተሰቡ ዘንድ ሙያው እና የሙያው ባለቤት የሆነው ሰው ይከበራል።

እንዳውም እኮ የጤና ባለሙያዎች ሕሙማን ከፍለው መታከም ሲያቅታቸው ወይም መድሃኒት መግዣ ሲቸግራቸው አዋጥተው ሲረዱ ነው የሚታወቁት። በደም መፍሰስ ሕይወቷን ልታጣ ጫፍ የደረሰችን እናት ደም ለግሰው ነው የሚያተርፋት፤ በዓላት በመጡ ቁጥር ከሕሙማን ጋር በጋራ እናሳልፍ በጋራ እናክብር ብለው ምግብ ሻይ ቡና ሁሉ አዘጋጅተው አብረው በዓል ሲያሳልፉ ነው የሚታወቁት።

ይሄ በአካል በነበርኩበት ሆስፒታል የአዲስ ዓመት በዓል አብሬ አሳልፌ ያየሁት ነው። ይሄ ብቻ አይደለም፤ ሕሙማኖቻቸው ሲያልፉ ጭምር ሲያዝኑና ከቤተሰቦቻቸው ጋር አብረው የሚያለቅሱ አዛኞች ጭምር ናቸው። ይሄ ካለባቸው ሙያ በተጨማሪ ሰብአዊነት ያስገደዳቸው ነው። ይሄ ማንነታቸው የት ሄዶ ወዴት እርቆ ነው ታዲያ ሕሙማኖቻቸውን በየአልጋው በየወረፋ መጠበቂያው አስቀምጠው የሥራ ማቆም አድማ የሚያስቡት። ይሄ ከአንድ የጤና ባለሙያ የሚጠበቅ አይደለም፤ ከሞራልና ከሕግም አንጻር ተጠያቂነትም አለው።

አሁን ባለው የኑሮ ውድነት፣ የቤት ኪራይ፣ ትራንስፖርት… የጤና ባለሙያዎች የሚከፈላቸው ደመወዝ በቂ ነው ማለት አይቻልም። በቂ አይደለም። ግን ደግሞ ሌሎች የጤና ባለሙያዎችን ጭምር የሚያፈሩ መምህራን፣ የሀገርን ሰላምና ደህንነት የሚጠብቁት ፖሊስ፣ መከላከያ ሰራዊት… የሚከፈላቸው ክፍያ ዝቅተኛ መሆኑ ጭምር መታወቅ አለበት። በአጠቃላይ የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች የሚከፈለው ክፍያ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ስለዚህ ሁሉም የመንግሥት ሠራተኛ ጥያቄ አለው ማለት ይቻላል።

ጥያቄውን ሌላውም አካል ቢያነሳ የሚገርም አይሆንም ምክንያቱም ያስገደደው አሁን ያለው የኑሮ ውድነቱ በመሆኑ። ይሄንን መንግሥትም ሆነ ሌላው በደንብ ይረዳዋል። ነገር ግን እንዲህ አይነት ጥያቄዎች መቅረብ ያለባቸው እንዴት ነው? የሚለው አሁንም መታየት አለበት። እርምት ሊወሰድበት ይገባል። የተነሳው የመብት ጥያቄ ቢሆንም ጥያቄው የቀረበበት መንገድ ስህተት መሆኑን በድፍረት መናገር ያስፈልጋል።

የታሰበው የአድመኝነት መንገድ ብቻም ሳይሆን በወቅቱ የጤና ባለሙያ ይዞት የወጣው ጽሁፍም እንዲሁ ለራሱ ለጤና ባለሙያው ክብር የሚመጥን መስሎ አይሰማኝም። በታካሚው ዘንድም ክብሩን ዝቅ የሚያወርደው ይመስለኛል፤ ምክንያቱም ለሀኪሞቻችን ያለን ክብር ከፍ ያለ በመሆኑ። ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ የመብት ጥያቄ ትክክለኛ ጥያቄ ቢሆንም የሚቀርብበት መንገድ የሚያስወግዘው ትክክል እንዳይሆን የሚያደርገው ይሆንና ከጥያቄ በላይ ሌላው አጀንዳ ጎልቶ ይወጣል።

አሁንም በየማኅበራዊ ሚዲያው የታየው ይሄው ነው። አንዳንድ የተረሱ፣ ቦታና ሁኔታ ያጡ ፖለቲከኞች እና አክቲቪስቶች ሁሉ አስታውሱን አይነት አጀንዳ ጠለፋ ውስጥ ገብተዋል። ብዙዎች ሼርና ላይክ ማስቆጠሪያ ሲያደርጉት አስተውለን ታዝበናል። እያንዳንዱ የመንግሥት ሠራተኛ በቂ ደመወዝ እየተከፈለው እንዳልሆነ ይታመናል። ይሄ ለምን ሆነ ብለን ስናነሳ ደግሞ የሀገሪቱ ኢኮኖሚና የመክፈል አቅም ግምት ውስጥ ማስገባት ተገቢ ይሆናል። የጎረቤት ሀገሮች፣ የአፍሪካ ሀገራት፣ አውሮፓና አሜሪካ ያሉ የጤና ባለሙያዎች ወይም ሀኪሞች ደመወዝ አስልተን ወደ ማዶ ባንጋጠጥን ቁጥር የምንሄደው ትክክለኛ ወዳልሆነው መንገድ ይሆናል። ጥሩ ክፍያ አላቸው በሚባሉ ሀገራት ያሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሠራተኞች፣ መምህራን፣ ጽዳት ሠራተኞች… ሌላውም እያልን ከጠቀስን እነዛም የሚከፈላቸው በሀገራችን ካሉ ተመሳሳይ የሥራ መስክ ባለሙያዎችን ጋር ተመሳሳይ አይደለም። ስለዚህ የምናነጻጽረው ከሌላው ሀገር ጋር ሳይሆን ከሀገራችን ኢኮኖሚ ከሀገራችን የመክፈል አቅም ጋር መሆን አለበት። በሁሉም ዘርፍ ሙያተኞች ተመሳሳይ ጥያቄዎች አሉዋቸውና። እነዚህ ጥያቄዎች መፈታት አለባቸው፤ እንዳሰብነው ባሰብነው ልክ ግን ይሆናል ብሎ መጠበቅ ‹‹ላም ባልዋለበት ኩበት…›› እንደማለት ይሆናል። ሊከፈል የሚችለው በሀገሪቱ አቅምና ደረጃ ብቻ ነው።

ሀገራችን ለረጅም ዘመናት ደሀ ስትባል ቆይታለች። ድህነት ልክ እንደ ጀብደኝነት የኢትዮጵያ መገለጫ ነው። አሁን ይሄንን የትርክት ምዕራፍ አጥፈን ወደ ቀጣዩ የብልጽግና ምዕራፍ ለመግባት ጎንበስ ቀናውን ሁላችንም እናስተውላለን። በዐይናችን የምናየው በአንደበታችን የምንመሰክረው ሀቅ ነው። በአንድ ጊዜ ያሰብነው ብልጽግና ላይ ባንደርስም ወደ ብልጽግናው ሊያደርሱን የሚችሉ የጥርጊያ መንገዶችን ማስተካከል ደግሞ አሁን ካለው መንግሥት የሚጠበቅ ነው። አሁን እየታየ ያለው አካሄድም ይሄው ነው፤። ትናንት ከነበርንበት ድህነት መውጣት የምንችለው እንደነ ቻይና፣ ኮሪያ፣ ሲንጋፖር የመሳሰሉት ሀገራት የተለወጡበትን ዳገት መውጣት ፈተናውን በቆራጥነት ማለፍ ስንችል ብቻ ነው።

ለውጥ መራራ ነው፤ ብዙ መስዋዕትነትን መክፈልን ይጠይቃል። ይንን መስዋዕትነት ካልከፈልን የምንፈልገውን የተሻለ ደመወዝ ማግኘት አንችልም። አሁን ብዙ ሥራዎቻችን ገቢ የሚያመነጩ ናቸው፤ የሀገራችን ገቢ ባደገና ኢኮኖሚው በተንሰራራ ቁጥር የእያንዳንዳችን መብቶችና ጥቅሞች ይከበራሉ። ደመወዛችን ያድጋል ኑራችን ይለወጣል። እዛ ለመድረስ የሚኬደው መንገድ ግን እንደመድሀኒት መራራና ጎምዛዛ ነው። ጎምዛዛውን መድሀኒት በትክክል የወሰደ ሕመምተኛ በመድሀኒቱ እንደሚፈወሰው ሁሉ እኛም ጎምዛዛውን የመስዋዕትነት መንገድ አልፈን ተጠቃሚ እንሆናለን። እኛ ያሳለፍነውን መራራ ሕይወት መጪው ትውልድ እንዳይጠብቀው መስዋዕትነት እንከፍላለን። ይህን ስናደርግ ለመጪው ትውልድም የተሻለች ሀገር ጥሩ ክፍያ ያላቸውን ባለሙያዎች ማፍራት እንችላለን።

አሁን ሀገር ብዙም በኢኮኖሚው ባልተረጋጋችበት ሁኔታ ሰፊ ነገር ማሰብ፣ ያንን ለማሳካት አድማ መምታት በማንም በምንም መልኩ ተቀባይነት አይኖረውም፤ በፍፁም። የጤና ተቋማትና የሕዝብ ትራንስፖርት ፣….. በሀገሪቱ ሕግ መሰረትም አድማ ከማይመታባቸው ዘርፎች መካከል ተጠቃሾች ናቸው።

አንዳንድ ነገሮች ሲሰሙ ያስደነግጣሉ። አንዳንዶቹ ግራ ያጋባሉ እውነት ይሄ ወቅቱና ጊዜው ነው ብሎ ለመጠየቅ ያስገድዳሉ። እናም ይሄ ተገቢ ጥያቄ ቢሆንም ጊዜው ግን አይደለም። ቀደም ሲልም በመንግሥት በተነገረው መሰረት አንዳንድ ማስተካከያዎች ለማድረግ የሚያግዙ የሪፎርም ሥራዎች ተጀምረዋል። ወቅትና የሀገር አቅምን ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ምላሽ ይሰጣል የሚል ሀሳብ ነው ያለው። እኛም የዚህም ምላሽ ተግባራዊ መሆን በጉጉት እንጠብቃለን። ምክንያቱም ጥያቄው የእኛም ጥያቄ በመሆኑ። ስለዚህ ከመንግሥት ጋር መወያየት ይገባል፤ የፖለቲከኞች መጠቀሚያ ከመሆን መጠንቀቅም ያስፈልጋል።

ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

በአዶኒስ ( ከሲኤምሲ )

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You