«ብልጽግና ከጠላትና ወዳጅ የፖለቲካ ሥርዓት ወደ ሃሳብ ልዕልና የተሻገረ ፓርቲ ነው»  ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፡- ብልጽግና ከጠላትና ወዳጅ የፖለቲካ ሥርዓት ወደ ሃሳብ ልዕልና እና ገንቢ የተፎካካሪ ፖለቲካ የተሻገረ ፓርቲ መሆኑን የብልጽግና ምክትል ፕሬዚዳንትና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ እንደገለጹት “የሃሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መልዕክት የብልጽግና ፓርቲ አምስተኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን አስመልክቶ የተዘጋጀውን የፎቶግራፍ አውደ ርዕይን ትናንት በሳይንስ ሙዚየም ሲከፍቱ እንዳሉት፤ ብልጽግና አካታችነትን፣ ሚዛን መጠበቅን፣ ስብራት መጠገንን እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን መሠረት በማድረግ የተመሠረተ ፓርቲ ነው። አካታችነትን ለመተግበርም ጥልና ልዩነት የሚፈጥሩ ግንቦችን ማፍረሱን፣ ከጠላትና ወዳጅ የፖለቲካ ሥርዓት ወደ ሃሳብ ልዕልና እና ገንቢ የተፎካካሪ ፖለቲካ መሻገሩን ገልጸዋል።

ፓርቲው ኢትዮጵያ እንዳይገቡ ታግደው የነበሩ የፖለቲካ ኃይሎች በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ የሚታገሉበትን መድረክ ማመቻቸቱን አመልክተው፤ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ለሀገር ግንባታ በጋራ መሥራት እንደሚቻል የተግባር ምሳሌ መሆን እንደተቻለም አስታውቀዋል።

ከዚህ ቀደም የነበረውን የሚዛን መዛነፎችን ብልጽግና በመደመር አዲስ ዕሳቤ ፍትሀዊነት እንዲሰፍን ማድረጉን አንስተው፤ ታሪካዊ ስብራቶች ለመጠገንና ለዘመናት ያልተግባባንባቸውን ጉዳዮች ለመፍታት የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን፣ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲና የተሀድሶ ኮሚሽን ተቋቁመው እየሠሩ ይገኛሉ ብለዋል።

የብልጽግና ፓርቲ አምስት ዓመታት ጉዞ የብርሃን ፍንጣቂ ጨረር በማሳየት በአጭር ጊዜ በርካታ የልማት ሥራዎች የተሠሩበት መሆኑን ጠቁመው፤ የአዲስ አበባ ከተማ በእነዚህ ጥቂት ዓመታት ያካሄደችው ሁለተናዊ ለውጥ አንዱ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል።

የልማት ሥራዎቹ ድህነትን ለማሸነፍ ፈርጀ ብዙ ፋይዳዎች ያላቸው ናቸው ያሉት አቶ ተመስገን፤ ግባችን ብልጽግና፤ መንገዳችን ደግሞ በመደመር ዕሳቤ ያሉንን ሀብቶች፣ ባሕሎች ፣ እሴቶችና አቅሞችን ደምረን ታላቅ ሀገራዊ አቅም እንፈጥራለን ብለዋል።

በሀገሪቱ የሰላምና የልማት ሥራዎችን በማጠናከር በዓለም የፖለቲካና የኢኮኖሚ መድረክ ኢትዮጵያ የሚገባትን የመሪነት ሚና መጫወት እንደሚኖርባት አመልክተው፤ ለዚህም ብልፅግና ፓርቲ ያለ ዕረፍት በመሥራት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ በበኩላቸው፤ ብልፅግና ፓርቲ ባለፋት አምስት ዓመታት ውስጥ በእያንዳንዱ የተለያዩ ዓለም አቀፍና ሀገራዊ ፈተናዎች እያለፈ እዚህ የደረሰ ጠንካራ ፓርቲ መሆኑን ገልጸዋል።

ያጋጠሙንን ሁሉንም ፈተናዎች በአሻጋሪ ሃሳብ፣ በአሰባሳቢነትና በብሄራዊ አንድነት ወደ ድል እየቀየርናቸው መጥተናል ብለዋል።

የፎቶ አውደ ርዕዩ የለውጡ ፍጥነት፣ ጥራትና ብዛት፣ የነበሩ ፈተናዎችን እንዲሁም የተመዘገቡ እመርታዎችን የሚያሳይና የሚያስታውስ መሆኑን አንስተው፤ በአራት ዋና ዋና ክፍሎች የቀረበ መሆኑን ገልፀዋል።

በተጨማሪም አውደ ርዕዩ የለውጥ ፍሬዎችና ዛሬ ላይ ሁነን ነገን የምናይበት የብልፅግና ማረጋገጫ ምእራፍን ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአውደ ርእዩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮችና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ማህሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ህዳር 20/2017 ዓ.ም

Recommended For You