በአንድ ጊዜ “ቻርጅ” ለአንድ ዓመት የሚያገለግለው ጀኔሬተር

ዜና ሐተታ

ወጣት ፈዴሳ ሹማ ይባላል። ትውልድና እድገቱ ቄለም ወለጋ ደምቢ ዶሎ ከተማ ነው። በፌደራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ሠልጣኝ ነው። ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ ቴክኒክና ሙያ ዘርፍ አጫጭር ሥልጠናዎች መውሰድ ችሏል።

ከአካባቢው የማኅበረሰብ ችግር በመነሳት በአንድ ጊዜ “ቻርጅ” ለአንድ ዓመት አገልግሎት የሚሰጥ ስማርት ኤሲ ጄኔሬተር ፈጠራ ባለቤት ሲሆን ድምፅና ጭስ አልባ መሆኑን ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረገው ቆይታ ተናግሯል። ኤሲ ጄኔሬተሩ ከ24 ሰዓት ጀምሮ እስከ አንድ ዓመት በአንድ ጊዜ ቻርጅ መሥራት የሚችልም ነው።

ጀኔሬተሩ በፀሐይና በኤሌክትሪክ ኃይል ተሞልቶ (ቻርጅ) ተደርጎ የሚሠራ ነው የሚለው ወጣት ፈዴሳ፤ በፈጠራ ሥራውም ከ15 የፌዴራልና የክልል ተቋማት እውቅና ማግኘቱን ይገልጻል።

እንደ ወጣት ፈዴሳ ገለጻ፤ ኤሲ ጄኔሬተሩ ከቤት መጠቀሚያነት አንስቶ እስከ ኩባንያ ትላልቅ ማሽኖች እንዲሁም የተለያዩ ተሽከርካሪዎች የማንቀሳቀስ አቅም አለው። አሁን የተመረተው ሁለት ሺህ 500 ዋት ሲሆን ከአምፖል ጀምሮ ቲቪ፣ ኮምፒዩተር ማስነሳት እንዲሁም ለተለያዩ የቤት ውስጥ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አቅም ያለው ነው።

ጄኔተሩ እንደየተጠቃሚው ፍላጎት የሚሠራ ነው ያለው ወጣት ፈዴሳ፤ አንድ ጊዜ ተሞልቶ (ቻርጅ ተደርጎ) ለ24 ሰዓት ከሚያገለግል እስከ አንድ ዓመት ድረስ የሚያገለግለው ማምረት እንደሚልችል ይናገራል።

እስካሁን በገበያ ያለው ጀኔተር የድምፅና የአየር ብክለት ከማስከተል፣ ከዋጋ ውድነት፣ በተጨማሪ ከፍተኛ ነዳጅ የሚጠቀም በመሆኑ ይሄኛው ፈጠራ ልዩ እንደሚያደርገውም ነው የሚጠቁመው።

ወጣት ፈዴሳ፤ በተጨማሪም ምርቱ ቢበላሽ የመለዋወጫ እቃዎቹ ከ80 በመቶ በላይ ከሀገር ውስጥ የሚገኙ መሆኑን ጠቅሶ፤ የተቀረው 20 በመቶ የሚሆነው የማምረቻ ግብዓት በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የተለያዩ ሙከራዎች እየተደረገ ነው ይላል።

ምርቱ በተለይ ኤሌክትሪክ ያልደረሰባቸው አካባቢዎች ችግር ከመፍታትና ኤሌክትሪክ ሲቆራረጥ የሚፈጠረው እንግልት መቀነስ ጎን ለጎን ሀገሪቱ የጀመረችው ግሪን ኢኮኖሚ እውን ሊያደርግ የሚችል መሆኑን ያስረዳል።

ከኤሌክትሪክና ሶላር ኃይል በተጨማሪ ከዚህ በፊት ከነበረው ጀኔሬተር ቻርጅ ማድረግ የሚችል ነው ያለ ሲሆን ቴክኖሎጂው በተገቢው ጊዜ ወደ ሥራ ከገባና ሥራ ላይ መዋል ከቻለ ሀገሪቱ ለነዳጅ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ በመቀነስ አወንታዊ ሚና መጫወት የሚችል መሆኑን ያብራራል።

በፈጠራው ባትሪ በራስ አቅም ማምረት ተችሏል ያለው ወጣት ፈዴሳ፤ የቦታና የፋይናንስ ችግር ከተቀረፈ በቀን እስከ አምስት መቶ የማምረት አቅም እንዳለ ያመላክታል።

ምርቱ በየአቅሙ ተመርቶ የመሸጫ ዋጋውም ከ20 ሺህ ብር ጀምሮ እስከ ሦስት ሚሊዮን ብር ድረስ ለገበያ መቅረቡን ይገልጻል።

ስታርት አፕ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግርና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ያለው ሚና በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ኢትዮጵያም ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ወደ ትግበራ ከገባች ሰንበትበት ብላለች። ለተግባራዊነቱም ይረዳ ዘንድ የተለያዩ የፖሊሲ ማሻሻያዎች፣ ምቹ ሁኔታዎች የሚፈጥሩ የአሠራር ሥርዓቶች እንዲሁም ወጣቱ ወደ ፈጠራ እንዲገባ የሚያነቃቁ መድረኮችን እያዘጋጀች ትገኛለች።

በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አብዛኛው ዜጎቻቸው ወጣት በሆኑባቸው ሀገራት ስታርት አፕ ለኢኮኖሚው ግንባታ የማይተካ ሚና አለው። የትኛውም ዓይነት ሀብት ምንጊዜም ውስን በመሆኑ በተለያዩ ፈጠራዎች ኢኮኖሚያቸውን የገነቡ ሀገራት እድገታቸው ዘላቂ ማድረግ ችለዋል የሚለው የገሀዱ ዓለም እውነታ ነው።

በቅርቡ በሀገራችን የተጀመረው አምስት ሚሊዮን ኮደርስ ሥልጠና ለዚሁ ዓላማ ግብዓትነት መዋል የሚችል ነው። ይሁን እንጂ የስታርት አፕ ዘርፉ ውጤታማ ለማድረግ ካፒታል ገበያ መጠናከር፣ አዕምሯዊ ንብረት ምዝገባ ማሳደግና የባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት ካልተቻለ ከወረቀት የዘለለ እንዳይሆን እንደ ወጣት ፈዴሳ ሹማ የፈጠራ ባለቤቶችን መደገፍ ይገባል ይላሉ ባለሙያዎቹ።

ልጅዓለም ፍቅሬ

 

አዲስ ዘመን ህዳር 18/2017 ዓ.ም

Recommended For You