የሠላም ጉዳይ የቱን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለን የቀደሙ ሥልጣኔዎቻችንን እና አሁን ላይ ያለንበትን ሀገራዊ እውነታ ማጤን በራሱ በቂ እና ከበቂ በላይ ነው። ችግሩ ከአንድ ትልቅ ሀገራዊ ከፍታ አውርዶን አሁን ላይ ላለንበት ድህነት እና ኋላ ቀርነት ዳርጎናል። በቀጣይ ዕጣ ፈንታችን ላይ ሊያሳድር የሚችለውም ተፅዕኖ ቀላል አይሆንም ።
በዘመናት ውስጥ ልዩነቶችን/ችግሮችን በሰከነ መንፈስ ሀገር እና ሕዝብን ተጠቃሚ በሚያደርግ ውይይት እና ድርድር መፍታት የሚያስችል ባሕል መፍጠር አለመቻላችን፤ ከዚህ ይልቅ በግትርነት እና በኃይል ለነገሮች መፍትሔ ለመስጠት የሄድንባቸው መንገዶች በግጭት አዙሪት ውስጥ እንድንዳክር አድርገውን ቆይተዋል ።
ይህም ሕዝባችን ለዘመናት የሚናፍቀውን ልማት እውን አድርጎ፤ ለቀደሙት የገናናነት ትርክቶቹ ትንሳኤ ለመስጠት በየዘመኑ ያደረጋቸውን ጥረቶች አምክኖታል፤ መነቃቃቱንም አደብዝዞታል። በዚህም ትውልዶች ሕልማቸውን መኖር የሚችሉበት ሀገራዊ የፖለቲካ ምሕዳር አጥተው ሕልማቸውን ከሽፎ ለማለፍ ተገድደዋል ።
አሁን ያለውም ትውልድ ቢሆን በአዲስ የተሐድሶ መንፈስ፤ ከፍ ባለ መነቃቃት የሀገሩን ዕጣ ፈንታ ለመቀየር በቁጭት የጀመረው የለውጥ ጎዳና በተመሳሳይ ተግዳሮቶች ውስጥ ለማለፍ የተገደደበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በተለመደው የፖለቲካ ባሕላችን ተፈትኖ በብዙ መጎረባበጦች ውስጥ አልፏል ።
በአንድ በኩል የፖለቲካ ልዩነቶችን በኃይል የመፍታት አስተሳሰብ ስብራት ውስጥ ያለ፤ በዚህም አተርፋለሁ ብሎ የሚያምን ኃይል፤ በሌላ በኩል ይህ አይነቱ እሳቤ ለሀገርም ለሕዝብም ከዚያም ባለፈ ሀሳቡን ለሚያራምደውም ቡድን አትራፊ ሊሆን አይችልም በሚል ኃይል መካከል የተፈጠረው የአስተሳሰብ ተቃርኖ ሀገርን ዳግም ወደ ግጭት ወስዷታል።
ግጭቶቹ ሺዎችን ለሞት እና አካል ጉዳት ዳርጓል፤ ሚሊዮኖችን ከሞቀ ቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል፤ በትሪሊዮን የሚገመት የሀገር ሀብት አውድሟል። ከግጭቶቹ ጋር በተያያዘ በዜጎችን ላይ ከፍ ያለ፤ እስካሁን ያላገገመ የሥነ ልቦና ስብራት ተፈጥሯል። ግጭቶቹ የፈጠሩት ሀገራዊ የኢኮኖሚ መንገጫገጭም መላውን ሕዝባችንን ዛሬ ድረስ ዋጋ እያስከፈለ ነው።
ቀደም ብሎ እንደተገመተውም በእነዚህ ግጭቶች ሀገር እና ሕዝብ ላልተገባ ችግር ተዳረጉ እንጂ ማንም ተጠቃሚ አልሆነም ። ለሕዝባችን አዲስ የለውጥ ጉዞ ፈተና ሆነ እንጂ የትኛውንም ቡድን አሸናፊ አላደረገም። ይዘነው የመጣነው ፖለቲካ ባሕል የቱን ያህል አጥፊ እንደሆነ ለትውልዱ ተጨባጭ ማሳያ ሆነ እንጂ ማንንም አላተረፈም።
ልዩነቶችን በኃይል ለመፍታት የሚደረጉ የትኛውም አይነት ጥረቶች፤ ከትናንት እስከ ዛሬ ካስከፈሉን እና እያስከፈሉን ካለው ያልተገባ ዋጋ አንጻር እውነታውን በኃላፊነት መንፈስ ቆም ብለን ልናስብ ይገባል። ይህ የአስተሳሰብ ስብራት በዘመናት መካከል ለሕዝባችን ተስፋ ጥላ ሆነ የቆመ እርግማን መሆኑን በአግባቡ ልናስተውል ይገባል።
በተለይም ሀገር ተረካቢው፤ የነገይቱ ኢትዮጵያ ተስፋ የምታደርገው ወጣቱ ትውልድ፤ ይህ የአስተሳሰብ ስብራት በቀደሙት ዘመናት የነበሩ ወጣቶችን ተስፋ የነጠቀ፤ ሕልማቸውን ኖረው እንዳያልፉ ዋነኛ ተግዳሮት እንደነበረ ሊረዳ እና የዚህ ስብራት ሰለባ እንዳይሆን በጥንቃቄ መጓዝ ይገባዋል ።
የትኛውም አይነት የኃይል አማራጭ በብዙ የተስፋ ዲስኩሮች ቢታጀብ፤ የትውልዱን ዛሬ እና ነገዎች ከመብላት ባለፈ፤ የተስፋው ባለቤት ሊያደርገው አይችልም፤ ለዚህ ደግሞ ባለፉት ዘመናት የመጣንባቸው የግጭት/የኃይል መንገዶች ተጨባጭ ማሳያዎች ናቸው። የነበረውን ከማሳጣት፤ ተስፋ ያደረገውን ከመናጠቅ ያለፈ ፋይዳ አልነበራቸውም።
በነዚህ ግጭቶች ውስጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተሳታፊ የነበሩ ታጣቂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ትጥቅ የማስፈታትና ወደ ተሐድሶ ማዕከላት የማስገባት ሥራም ይህንን በዘመናት ብዙ ዋጋ ሲያስከፍለን የነበረውን የአስተሳሰብ ስብራት የማከም፤ ለሀገራዊ ተስፋችን ጥላ ከሆነው የግጭት አዙሪት ለመውጣት የሚያስችለን የመታረም መንገድ ነው!
አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 13 ቀን 2017 ዓ.ም